Tuesday, September 30, 2014

ምን ዓይነት ጸሎት በየትኛው ሰዓት ልጸልይ?

የኢንተርኔት አገልግሎት ፈጣን ባልሆነበት ቦታ በአማራጭነት ይህንን በጽሑፍ መልክ ያንብቡ:: ረጅም ትምሕርት ሲሆን በተቻለ መጠን በቂ መልክቱን በጽሑፍ አቅርበናል:: የቃላት ግድፈት ካለ እያረሙ እንዲያነቡ እንጋብዛለን::
የጸሎት ቦታ እንዴት ላዘጋጅ?

ክፉንና ደጉን ለመለየት አምልኮ ያስፈልጋል:: አምልኮ የሌለበት ህይወት አለም ላይ የወደቀ ነው ስለዚህም የአምልኮት ራእይ አንድ ክርስቲያን ሊኖረው ይገባል:: ማምለክ ማለት እግዚያብሔርን ከልብ መውደድ: ቃሉን በልቦና ማኖር: እና መጠበቅ: እርሱን ተስፋ ጉልበታችንን ማድረግ ነው:: በተግባር ደግሞ ኑሮን ጠባይን ለእግዚያብሔር መስጠት: ውስጣዊ ህይወታችንን ለክብሩ የተዘጋጀ ማድረግ :: ስለ ሐጢአታችን ንሰሐ ገብተን ሥጋውና ደሙን መውሰድ: እለት እለት ስለበደላችን ስለሐጢአታችን ለእግዚያብሔር መንገር:: እለት እለት እግዚያብሔርን የምናመሰግንበትን ግዜ ካገኘን የአምልኮት ሕይወት ገበና አለን ማለት ነው:: ሰብአ ሰገል ክርስቶስን በፍቅር ፈልገው እንደመጡ አንድ ክርስቲያንም ክርስቶስን ፈልጎ መምጣት አለበት:: በአምልኮት ባሕርይ ሔሮድስን ማለፍ ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር ነው:: ሔሮድስ ማለት የዚህ አለም ነገሮች ናቸው እነዚህም :የአለምን ሰዎች እውቀት: ሳይንስ እግዚያብርሔን የሚከለክል : የድንግል ማርያም ልጅ ክርስቶስን የሚከለክል ነው:: ሔሮድስ ማለት ሐብት : ስልጣን: ማዕረግ የመሳሰሉት እነዚህ ሁሉ የሔሮድስ መንገድ ጠቋሚ ናቸው:: ሰዎች የጥፋት ሞት ውስጥ የሚገቡት የአምልኮት ሕይወት በማጣት ነው:: እግዚያብሔርን የሚፈልጉ ሰዎች ሔሮድስ ጋር መቅረት የለባቸውም:: ኮከቡን ማየት አለባቸው ኮከቡም ያለው በሰማይ ነው::

ብዙ ክርቲያኖች ወደ እግዚያብሔር ቤት አይሔዱም ወይም ወደ ሰማይ ቀና አይሉም:: በዚህም ወደ ልባቸው የሚሔድባቸው መጣባቸው:: ሰይጣን ወደ ቤታቸው ወደ ኑሮአቸው ወደ ሕይወታቸው መጣ:: በዚህ ዓለም ገለልተኛ ሆኖ መኖር አይቻልም:: በዚህ አለም ሁለት ነገር ነው ያለው:: ጽድቅና ኩነኔ: ጨለማና ብርሃን: ሓጢአትና ጽድቅ: ሰላምና ጦርነት::ከፈለክ ወደ ብርሃን ካልፈለክ ወደ ጨላማ: ከፈለክ  እውነት ካልፈለክ ሐሰት: እንዲህ በጥንድ የተያያዘ ነው:: የእግዚያብሔርን በቅድምያ ከሰማን የእግዚያብሔር ጽድቅ ይገለጥልናል: የሰዎችን ከሰማን ሁል ግዜ እንደተደናገግርን ተስፋችንን በአልሆነ አቅጣጫ እየጠበቅን እንኖራለን:: ሔሮድስ ክፉ መሆኑን የምናውቀው ስናመልክ ነው::

የጸሎት ቦታ
የጸሎት አቅጣጫ ምስራቅን የተመለከተ መሆን አለበት:: በመንበርከክ በግንባር ልክ የእመቤታችን የቅዱስ ሚካኤል የቅዱስ እና የቅዱስ ገብርኤል በግራና ቀኝ : በመቆም ልክ የስላሴ የመድኃኔአለም ስእል ይደረጋል:: ከስእሉ ራቅ የሚባለው ክፍተቱ የመጽሐፍ መግለጫ ያህል ነው:: ስእሎቹ ተጸልዮባቸው ቅባ ቅዱስ ይቀባሉ ቢቻል ቤተ ክርስቶያን ተባርካው በቅዳሴ ግዜ ቅባ ቅዱስ ተቀብተው መሆን አለበት:: ስእሎቹ በጥሩ ፍሬም የተሰሩ ስእሎች መሆን አለባቸው:: ከስራቸው የጸሎት ወሃ : እጣን: እምነት:የወይራ ዘይት: የመጽሀፍ ማስቀመጫ: የምንጠቀምባቸው እንደ ሽቶ ዎች ካሉ አጠገብ መሆን አለባቸው:: ሽቶ የሚወዱ ዛሮች አሉ:: ተጸልዮበት ሽቶ ብንጠቀም ሽቶ የሚወዱ ዛሮችን መከላከል ይቻላል : የመንበርከኪያ ቦታ ደረቅ ያለ የጥጥ ፍራሽ ቢሆን ይመረጣል:: ግልበት በሚሰግድበት ግዜ መመቻቸት አለበት ነገር ግን በጣም የሚመች ሥፕንጅ መሆን የለበትም: ስንፍና እንዳይሰማው: የሚሞቅ ነገር መሆን የለበትም መቀዝቀዝም የለበትም:: በሚሰግድበት ግዜ በስእሎቹ ፊትለፊት  መስገድ ሲጀምር የሚከተሉትን ምልክቶች ያያል:- መዛል:መድከም መልፈስፈስ :: በሚጸልይበት ግዜ ከስእሎቹ የሚወጣ መንፈሳዊ እሳት አለ:: በሰውነቱ ላይ ከስእሎቹ ተጠግቶ ሲጸልይ መውረር መቅበጥበጥ:ማቃጠል የሚታይበት ይሆናል:: አንዳንዱም መንፈሱ ወዲያው መገለጥ ጠባይ አለው:: መንፈሱ ጸሎት በከፍተኛ ሁኔታ ጸሎት እየከለክለው የሚያጠቃው ከሆነ የቅዱስ ሚካኤልን ስእል በፍሬም በጥሩ ሁኔታ ሰርቶ  መሬቱ ላይ አድርጎ እጁ ላይ እና ሰይፉ ላይ በሚሰግድበት ግዜ መንፈሱ ሊጥለው ይችላል:: በዚህ ግዜ መቁጠርያ ያስፈልጋል::ጸጥ በል በጌታየ በየሱስ ክርስቶስ ስም ብሎ ሲመታው ቅዱስ ሚካኤል ሆይ እሰርልኝ ሲለው  በስእሉ ፊት ያለው ሐይል እየተገለጠ ቅዱስ ሚካኤል ሊያስርለት ይችላል:: ሰውየው እየሰማም እያወቀም መንፈሱን ሊያስርለት ይችላል:: በዚህ ግዜ ፕሮግራም ይዞ ወድ  እኔ ደውሎ አንዳንድ መረጃ እንለዋወጣለን:: የሚደክም ከሆነ ይደክማል የሚሸኝም ከሆነ ይሸኛል:: ሆኖም ግን  እነዚህን ልምምዶች በቀላሉ የሚመጡ  አደሉም:: ሰውየው በጥሩ የበረከት መንፈሳዊ ህይወት ለማለፍ እራሱን ማዘጋጀት አለበት:: ጸሎትን እንደ ደስታ አምላክን እንደማማረርያ ጎዳና ሳይሆን "ሁል ግዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ:ደግሜ እላለሁ ደስ ይበላችሁ::ገርነታችሁ ለሰው ሁሉ ይታወቅ::" እንዲል ገራገር መሆን አለበት:: "ጌታ ቅርብ ነው::በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ::" ፊልጵስዮስ 4:4-6

ራእይን ምሪቱን ለማግኘት ደግሞ የጸሎት ቦታችን ላይ ለባልና ሚስት የመኝታ ያህል መኖር አለበት: ቤተሰብ ካለው ከሌለው
መኝታውን እዚያ ያደርጋል: ልብሶቹ አንሶላዎቹ እዚያው መሆን አለባቸው:: የሚለብሰው ልብስ ላይ መስገድ አለበት ምክኒያቱም ብርድ ልብሱን ከሌላ መኝታ ቤት ሲያመጣ መንፈሱ ከብርድልብሱ ጋር ይመጣና ተንኮለኛው መንፈስ ራእዩን ይከለክለዋል:: እዚያው ከጸለየበት ከሰገደበት ግን መንፈሱን ያጠቃዋል:: የእግዚያብሔር የምስጋናው የጸሎቱ እሳት መንፈሱን ያቃጥለዋል:: ሊቋቋመው ስለማይችል ራእዩን አያጨልምበትም: ክፉና ደጉን የሚያውቅበት  ያገኛል:: የራእይን ተግባራዊነት ለመረዳት በመጽሐፍ ቅዱስ ኦሪት ዘፍጥረት  49 የሮቤልን ነገድ ታሪክ ያንብቡ:: ራእይን ለማግኘት በአምልኮት ስግደት ውስጥ ይቅርታን እንለምናለን : ምስጋና ለአብ ምስጋና ለወልድ ምስጋና ለመንፈስ ቅዱስ የምንልበትን ህይወት ስንጀምር ምስጋና ለአለም: ለመጠጥ: ለመድሐኒት:ሃይል ለሚሰጥ መድኃኒት.....ማለቱን እናቋርጣለን:: ለእግዚያብሔር መለኮታዎ ስልጣን መገዛት ስንጀምር እርሱም ይወደናል:: መውደዱን ያውቅበታል "እናንተ ደካሞች" ያለኮ ጌታ ነው:: ድካማችንን ሁሉ ያውቃል::" እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ" ማቴ 11:28 ያለ አምላክ ገር ነው:: የገርነት ድምጾቹን በስጋ ተገልጦ አሳይቶናል መክሮናል ገስጾናል ወደ ቅዱሳን ሕይወት እንድመጣ ረድቷል:: በረከቱን በሁሉም ጎን ለመስጠት ሕይወታችንን ጎብኝቷል:: የራእዩ አይነት ይለያያል: የተባረከ ልጅ ማግኘት የሚፈልግ ከዚያ ጽሎት ቤት ውስጥ ለምኖ ያገኛል:: በቤት ውስጥ መጸልይ ከቤተ ክርስቲያን በተጨማሪ ብዙ ጥቅም አለው:: "ኢያሱም ሕዝቡን፦ ነገ እግዚአብሔር በመካከላችሁ ድንቅ ነገር ያደርጋልና ተቀደሱ አለ። " መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 3:5 ቤተ ክርስቲያን መቀደሻ ናት: ቤት ደግሞ መባረኪያ እና ማምለኪያ ነው:: ይህ መገናኘት አለበት:: እቤትህ ሳታመልከው ቤተ ክርስቲያን አመልካለሁ ማለት እና እቤት አለመጸለይ ክርስቲያናዊ ህይወትን ጎዶሎ ማድረግ ነው:: እቤታችን ሰርቀን ነው የተኛነው:: የጸሎት ቦታ ከሌለ ሰውየውም ሌባ እንጀራውን ቤቱም ሌባ ከሆነ በዛ መኝታ የተጸነሰው ትውልድ ተስፋ የሌለው ጤናው የተጓደለ አገር አጥፊ ተስፋው የተቋረጠ...ቢሆን ምን የሚያሳዝን ነገር አለ?  አምልኮ ሕይወት የሌለበት ቤትና ሕይወት ግዜና ገንዘብ ምን ዋጋ አለው?  አንዳንዶች የሚኖሩበት ቦታ በልክፍት መንፈስ የተለከፉ ልጆች እንዲወለዱ አድርጓል:: ጉዳዩ ከተቀመጡበት ቦታ ያለው የመናፍስት ጥቃት ነው:: ለዚህ ነው የጸሎት ቤት መኖር ያለበት:: ሰዎች ብቻ አደሉም በሽተኞች ቦታውም ጭምር መሆኑ ሊገባን ይገባል:: ልጆችም ከዚያ ተወልደው አባታቸው ሲሰግድ ካዩ እነርሱም ሲያድጉ ሲጎለምሱ እና ለሌላው በረከት የመሆን ራእይ አላቸው:: እኛ እንግዲህ ከባዶ ቤት ተወልደናል ባዶነታችንን ልናምንበት ይገባል:: ስለዚህ የጽሎት ቦታ ያለው ቤት ከፍተኛ ትርጉም ያለው ነው:: የጸሎት ቦታ ያስፈልገናል::ከቤቱ አንዱ ክፍል የምስጋና ቦታ መሆን አለበት:: ለቴሌቭዥን ለሶፋ...አልፎም ለጫት ቦታ አለን ለአምላክ ግን ቦታ የለንም:: የእግዚያብሔር ምሕረት በየት በኩል መጥቶ ነው የሚባረከው? የእግዚያብሔር ራእይ በየት መጥቶ ነው ክፉና ደጉን የሚለየው? በቤት ክራይ እንኳን የመጣው ቀላል አደለም:: ተከራዮች ቤት ሲቀይሩ ጸልየው: እጣን አጢሰው: የምስጋና ጸሎት ጸልየው: እግዚያብሔር እለት እለት ያንን ቦታ እንዲባርክ ለምነው: ዲያብሎስን አባረው መሆን አለበት::ከዚያ የሚወለዱ ልጆች የተባረኩ:ለምስጋና የተዘጋጁ: ለሰላማቸው ምክኒያት የሆኑ ልጆች ይወለዳሉ:: የአምልኮ ሕይወት የገባ ትውልድ መሰረታዊ ምልክቶች እነዚህ ናቸው:: እዛው ቦታ ላይ ሰግደው ጸልየው እዛው ሲተኙ እራይ ያገኛሉ:: ራእይ ስናገኝ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን:: ራእዩ ያንተ ነው ወይ? ሲባል ሁለተኛ መልክት ይመጣል:: ከርሱም መሆኑ ተኝተን እንኳ ውስጣዊ ሰላም ይመጣል:: ሲነጋም  በረከቱ ይታያል: ሰላም እና ጸጥታው: ይመጣል:: ይህ ከጸሎት የሚመጣ በራእዩ እግዚያብሄር የሚሰጠው የመንፈስ ቅዱስ ክብር ነው:: ከጸሎት የሚመጣ ጸጋ:ክብር ነው:: እግዚያብሔር ለያንዳንዱ ክርስቲያናዊ ህይወት ላይ መልስ አለው::

ጸሎት ስናደርግ የመንፈሱ ባሕርያት

መሥገድ እና መጸለይ ሲጀምር በቤቱ ወይም በሕይወቱ ያለው መንፈሱ ይታገለዋል:: ለግዜው እንዲጨነቅ ያደርጋዋል:: በመቁጠርያ እየገረፈ  ጭንቀትህን አቁም ይላል የእግዚያብሄርን እርዳታ ይጠይቃል:: አምልኮቱን እየሰጠ ይቀጥላል:: ሐጢአትን እና ክፉ ሐሳቦችን ይቃወማል:: የሚሰራው እና በአለም ያለ የሚያየው ነገር የተባረከ እንዲሆን ጸልዮ ይወጣል:: እግዚያብሔር ካላበረታኝ እያሉ ማሳበብ መኖር የለበትም:: መንፈሱ መኖሩ ምልክቱ ለግዜው ራእይ ይከለክላል: መደንገጥ: ቅዥት የበዛበት ይሆናል: በሚተኛበት ቦታ ላይ መሯሯጥ:ቶሎ ቶሎ መባነን: ከእጅም ከእግርም አካባቢ መደንገጥ:: በጸሎት ቦታ በሚተኛበት ግዜ መንፈሱ ከሰው ጋር ተዋህዶ ስለሆነ አዲስ ነገር እየመጣበት ስለሆነ መንቀጥቀጥ: አውሬ ማየት :እንደ አይጥ መስሎ ሽርር ማለት በሰውነት አካባቢ ወይም በሚተኛበት ቦታ መራራጥ ናቸው::  በዚህ ግዜ መገሰጫ መንገዱ ሲነጋ ጸሎት ቦታ ላይ በሚቀመጥ በመቁጠርያ እንዲህ አይነት ራእይ አቁም አውቄአለሁ:: በክርስቶስ ስም አስሬሃለሁ:: የአንተን የጥፋትና የሞት ራእይ አልፈልግም! በድንግል ማርያም ስም አዝዤሃለሁ ብሎ ማታ ቀጥቅጦት ከተኛ ይህን አይነት ራእዩ ቀጥ ይላል:: እንዲህ አድርጎ ሲመታው ራእዩን መከልከል አይችልም:: "ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤" ዩሐ. 1:12 ነው የሚለው የግድ ቄስ ጳጳስ መሆን የለበትም:: ክርስቶስን በስጋና ደሙ ለተቀበሉት: በሰማያ አምባ ተስፋ አድርገው በቅድስና እንጀራ ለተባረኩት በስሙ ለሚያምኑት ስልጣንን ሰጣቸው:: በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም በተባረኩበት ስም አቁም ማለት አለበት:: ደዌም ወይም ከፍተኛ የራስ ምታትም/ማይግሬን/ ከሆነ በመቁጠርያ ሲመታው 5ት ምልክቶችን ያሳያል እነርሱም:- መውረር: መብላት: ማቃጠል: በሰውነት ውስጥ መሄድ እና በሚመታበት ግዜ እንደ ድንጋይ መሰማት የመንፈሱ መኖር ምልክት ነው:: እግዚኦ ማረነ ክርስቶስ: በእነተ ማርያም ማረነ ክርስቶስ : ኪርያላይሶን ክርስቶስ : በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም; በድንግል ማርያም ስም: ሰይጣንን በሰበረው በቅዱስ ሚካኤል ስም: በቅዱስ ገብሬል ስም: ውስጤ የተደበክ ጠላቴ ነርቭ የሆንከው: በሽታ የሆንከው: ቅዥት የሆንከው ተስፋ መቁረጥ የሆንከው መንፈስ እገስጽሃለሁ ብሎ ሲመታው ያልኳቸው ምልክቶች ይታያሉ:: ከዚያም በድንግል ማርያም ስም ወደ ግንባር ውጣ ሲለው ከሰውነቴ እንደሚንቀሳቀስ ነገር ወደ ግንባር ይወጣል:: ግንባር ላይ መታሰሩ በሌሎች ሰውነት ክፍሎች ላይ በአእምሮ በልብ ላይ ገዢ እንዳይሆንና :እየሰገደ ስለሚያዳክመው ነው: ሰግዶ የማያውቅ መንፈስ እየሰገደ ሲያሳየው በቀላሉ ይሸናፋል:: በሚሰግድ ግዜ ግንባሩን የሚያሳርፍበት የመስገጃ ስዕል ያስፈልገዋል:: ይህም የጌታችን : የስላሴ ስዕል ወይም የድንግል ማርያም ወይም መጽሐፍ ቅዱስ ወይም ድርሳናት ግንባሩን የሚያሳርፍበት መኖር አለበት:: ግንባሩን ማሳረፍ ልዩ መልክት አለው:: አምላኬ አንተን እወዳለሁ እገዛለሁ ፈጣርየ ነህ ማለት ነው:: "የሚያከብሩኝን አከብራለሁ" እንዲል:: 
ሌላው ደግሞ በኑሮየ በስልጣኔ በእድሌ ላይ አዛዥ አትሆንም ይህ ስልጣንህ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተሽሯል እያለ ሊነግረው ይገባል:: ክርስቲያን ከሆንክ ክርስትናህን ለማስተው ሰይጣን መታገል አለበት:: ከዘር የሚመጣ መንፈስ ነጻ አትሆንም:: ሰይጣን የራሱን ልጆች አሳድጓል: የእግዚያብሔር ልጆች ለመሆን የአምልኮት ሕይወት ሊኖረን ይገባል::  ጠላታችን በውስጡ መኖሩን እያንዳንዱ ማመን መቻል አለበት:: ባልና ሚስት ሁለቱም አብረው መጸለይ አለባቸው:: አንዱ አንዱን በልቶ:ልጆቻቸውን በልተው ስለሚሆን: የጸሎት ቦታ ሲኖር ልባቸው ሲሰበር አንድ የሚሆኑበትን መንፈስ ሲያገኙ ወደ እኔ ይደውላሉ: ራእያቸውን ይገልጹልኛል: ወደ በረከት እና ሰላም ይመጣሉ::

ምን ዓይነት ጸሎት በየትኛው ሰዓት ልጸልይ?


ሙሉ ትምሕርቱን ከ
Radio Abisinia Interview archive

* ያልሰገደ ትውልድ ራዕይ የለውም! ለሚሰግዱ ሠዎች፥ እግዚአብሔር መንገድ አለው።
የጸሎት ሥነ-ሥርዓት፦
፩ኛ፤ በመንፈቀ ሌሊት
፪ኛ፤ በነግህ ጊዜ ፲፩ ሠዓት (5:00 AM በፈረንጆች) ዌዳሴ ማርያም፣ ሰይፈ መለኮት፣ ሠይፈ ሥላሴ ወይም ከቅዱሳን አንዱ፤
፫ኛ፤ በ፫ ሠዓት (9:00 AM በፈረንጆች) አርጋኖን፣ መልክአ ገብርኤል፤
፬ኛ፤ በ፮ ሠዓት (12:00 PM በፈረንጆች) መልክአ ስላሴ፣ መልክአ ሚካኤል፤
፭ኛ፤ በ፱ ሠዓት (3:00 PM በፈረንጆች) መልክአ መድኃኒዓለም፣ መልከአ ኡራኤል፤
፮ኛ፤ በ፲፩ ሠዓት
፯ኛ፤ ማታ ከመኝታ በፊት በ፫ ሠዓት (9:00 PM በፈረንጆች) መልክአ ሩፋኤል፣ አርጋኖን፤
በተጨማሪ፦ በነዚህም በሰባቱ የጸሎት ጊዜያት፥ እግዚኦታ ፲፪ ጊዜ፣ በእንተ ማርያም ፲፪ ጊዜ፣ ኦ አምላክ ፲፪ ጊዜ፣ ኦ ክርስቶስ ፲፪ ጊዜ፣ ያድኅነነ እመዓቱ ፲፪ ጊዜ፣ ተዘከረነ እግዚኦ በውስተ መንግሥትከን ፲፪ ጊዜ፤ ማድረስና ከቀዳሚትና ከእሑድ እንዲሁም ከታላላቅ በዓላቶችና ሥጋ ወደሙ ከተቀበሉበት ዕለት በስተቀር ሰባት ሰባት ጊዜ መስገድ ይገባል።
ልዩ ማሳሰቢያ፦ ሥራና ጸሎት ጐን ለጐን የሚጓዙ (በሥራ መስክም እያሉ ጸሎትን አብሮ ማዋሕድ ስለሚችሉ) ስለሆነ፤ የሥራን ሠዓት ሳይሻሙ እግዚአብሔርን በአጭር ጸሎት አነጋግሮ (ጸልዮ) ወደ ሥራ መሰማራት ይቻላል።
በ፮ ሠዓት ጸሎት (12:00 PM በፈረንጆች) መልከአ ሚካኤል ማንበብ፦
* ቅዱስ ሚካኤል ሆይ እርዳኝ፣ የአጋንንትን ኃይል ገስፅልኝ፣ ርኩሳን መናፍስትን አስወግድልኝ፣ ታላቅ የኾነውን ቅዱስ የኾነው ሰይፍህን በክፉ መናፍስት ላይ ጣለው፣ ቆራርጠው፣ የበረከትህን ተስፋና ኃይል ለእኔም ስጠኝ፣ ከጎኔ ተሰለፍ፣ ኃይሌን አጠናክር፣ ውስጣዊ ሕይወቴን በመንፈስህና በፀጋህ አስበኝ፣ በምስጋና ስፍራ ኹሉ፤ በጸሎትህ እርዳኝ። አባታችን ሆይ ........
የዘወትር የአምልኮ ስግደት፦ (መቅረት የሌለበት)
* ለአብ እሰግዳለሁ፣ ለወልድ እሰግዳለሁ፣ ለመንፈስ ቅዱስ እሰግዳለሁ፣ ምስጋና ይሁን ለአብ፣ ምስጋና ይሁን ለወልድ፣ ምስጋና ይሁን ለመንፈስ ቅዱስ፣ በረከቱን ለሰጠን፣ ኃይሉን ላበዛልን፣ በዚህ ሠዓት ላቆመን፣ በቸርነቱ መንገድ ለመራን፣ በዚህ ሠዓት በፀጋ ለጠበቀን፣ በብርሃኑ ኃይል ለመራኸን፣ ላንተ፥ ክብር ምስጋና ይግባኽ፤ ሃሌ ሉያ ለአብ፣ ሃሌ ሉያ ለወልድ፣ ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ፤ ቅዱስ እግዚአብሔር፣ ቅዱስ ኃያል፣ ቅዱስ ሕያው፣ ቅዱስ ኤልሻዳይ፣ ቅዱስ አዶናይ፣ ቅዱስ ያህዌ፣ ቅዱስ ጸባኦት፣ ቅዱስ ኢየሱስ፣ ቅዱስ ክርስቶስ፣ ቅዱስ አማኑኤል፣ የድንግል ማርያም ልጅ፤ ክብር ምስጋና ይግባው!።
የንስሐ ስግደት፦
* ኪርያ ላይሶን ኢየሱስ፣ ኪርያ ላይሶን ክርስቶስ፣ ኪርያ ላይሶን አማኑኤል፣ አቤቱ ክርስቶስ ሆይ ማረን፣ አቤቱ አምላክ ሆይ ማረን፣ አቤቱ መድኃኒዓለም ሆይ ማረን፣ አቤቱ የድንግል ማርያም ልጅ ሆይ ማረን!።
ክብረ በዓል ከሆነ፦
* ስብሐት ለአብ፣ ስብሐት ለወልድ፣ ስብአት ለመንፈስ ቅዱስ፣ ቅዱስ እግዚአብሔር፣ ቅዱስ ኃያል፣ ቅዱስ ሕያው፤ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ።
የክብር ስግደት፦
* ለቅዱስ ሚካኤል እሰግዳለሁ፣ በቅዱስ ሚካኤል እሰግዳለሁ።
የፀጋ ስግደት፦
* ለድንግል ማርያምም እሰግዳለሁ፣ ክብር ምስጋና ይገባሻል።





1 comment: