Thursday, December 24, 2015

አንዲት እህት ከሆዷ ውስጥ ጥቁር ወፍ ወጣላት

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በደብረ ወልደ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስ እና በመካነ ጎለጎታ ቅድስት ማርያም ጠበል ሰሞኑን ከአንዲት እኅት ከሆዷ ጥቁር ወፍ ወጣላት፡፡ በክርስትና ስሟ መንበረ ማርያም ተብላ የምትጠራው እኅት ለ20 ዓመታት ያህል በሆድ ሕመማት ስትሰቃይ መቆየቷን የምትናገረው መንበረ ማርያም፤ ስቃይዋን በዘመናዊው ሕክምና ለማስታገስ ያልሔደችበት ቦታና ያልወሰደችው መድኃኒት የለም፡፡ ይሁንና የምትወስደው ሕክምና ለጊዜው ስቃይዋን ከማስታገስ በስተቀር ከሕመሟ ልትድን ባለመቻሏ ከዚህ በኋላ ይግደለኝ እንጂ ሕክም ናም ሆነ መድኃኒት መጠቀም የለብኝም፤ ብላ ጠበል ለመጠመቅ እንደ ወሰነች ትናገራለች፡፡ በውሳኔዋም መሠ ረት ወደ ወልደ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስ ቤተክርስቲያን ጠበል በመሄድ ስትጠመቅ በላይዋ ላይ የሰፈሩ 681 አጋንንት እንዳሉ በላይዋ ላይ ያደሩት የሰይጣን ሠራዊት ለፍልፎ በጥቁር ወፍ አምሳል ከሆዷ ውስጥ ሊወጣላት ችሏል፡፡ ምእመናን በዕለቱ ከሆዷ ውስጥ በትውከትነት እንደ ጥይት ተወርውሮ የወጣውን ጥቁር ወፍ ከነሕይወቱ በማየት በቪዲዮ በመቅረጽ የእግዚአብሔርን ድንቅ ተአምር እንደ መሰከሩ ተገልጿል፡፡


የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ ሰምቶ ይህንኑ ወፍ የወጣላትን መን በረ ማርያምንና ያጠመቋትን አባት ሊቀ ትጉኃን ስሙር አሐዱን በማነጋገር ድርጊቱ እንዴትና ምን ይመስል እንደነበር በሰፊው ዘግቧል፡፡

እግዚአብሔር ሥራው ድንቅ ነው፤ ተዓምሩ ዕፁብ ነው፤ ተነግሮ አያልቅም፤ ይህን ሥራውን መመስከር ደግሞ የእኛ ተግባር ነው፡፡ ለረጅም ዓመታት በሕመም ስትሰቃይ የነበረች በስመ ጥምቀቷ መንበረ ማርያም የተባለች ወጣት የእግዚአብሔርን የድንቅ ሥራው መገለጫ ሆናለች፡፡

ለዚህች እህት እግዚአብሔር ያደረገላት ገቢረ ተአምር ሲሰሙት ለጆሮ የሚከብድ፤ እንዲሁም በወቅቱ ድር ጊቱ ሲፈጸም የተመለከቱ ምእመናንን ሁሉ ያስደመመ ነበር፡፡ «ማን ያርዳ የቀበረ፤ ማን ይናገር የነበረ» ነውና ሥረ መሠረቱ ምን፣ እንዴትና መቼ ሆነ? የሚለውን ጉዳይ እሷው ባለታሪኳ እንዲህ ትተርክልናለች፡፡

«ያመኝ የነበረው ገና የአራት ዓመት ልጅ እያለሁ እሰቃይ ነበር፡፡ ለምሳሌ የራስ ምታት፣ ነስር፣ የሆድ ቁርጠት፣ የአንጀት ኢንፌክሽን ወዘተ እየተባለ በመታመም ሁልጊዜ ሐኪም ቤት እመላለስ ነበር፡፡ እናቴ እንደ ነገረችኝ የሕመሙ መነሻ ወተት ነው፡፡ «ወተት ጠጥተሽ የአንጀት ኢንፌክሽን ያዘሽ» ያለችኝ እናቴ በየክሊኒኩ እየወሰደችኝ ስታስመረምረኝ መድኃኒት እንደሚያዙልኝ አጫውታኛለች፡፡ ራሴን ማወቅ ስጀምር ትምህርት ቤት ገብቼ ስማር ሆዴን ያመኛል፡፡ በተለይ በበጋ ወራት ተምሬ ሁለት ወር ክረምት በሚሆንበት ወቅት ክፉኛ ያመኛል» ስትል ተናግራለች፡፡

መንበረ ማርያም በሕመሟ መጥናት ብዙ ጊዜ ሐኪም ቤትና ክሊኒክ ተመላልሳ እንደታከመች ገልጻል ናለች፡፡ ነገር ግን ጠበልስ አልሞከረች ይሆን? የሚለው ጥያቄ አጫረብንና ጠየቅናት፤ እርሷም ስትመልስ «በዚያን ወቅት ቤተሰቦቼ የሚያስቡት ሐኪም ቤት የሚባለውን እንጂ ጠበልን አልነበረም፡፡ እኔም ቢሆን በወ ቅቱ ጠበልን አላሰብኩትም፤ ብቻ ሐኪም ቤት ሔጄ የተለያየ መድኃኒት ይታዘዝልኛል እወስዳለሁ፡፡ ለጊዜው ያስታግሥልኛል፤ ጨርሶ ግን ሊያድነኝ አልቻለም፡፡ ይባስ ብሎ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ወስጄ ጥሩ ውጤት በማምጣት አራት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ገብቼ የመጀመሪያ ዓመት መማር ስጀምር በሽታው ክፉኛ አሰቃየኝ፡፡ ያስጨንቀኛል፣ ከፍተኛ የራስ ምታት ሕመም ይሰማኛል፤ ማጥናት አልችልም ነበር፡፡ የሴሚስተር ፈተና ደርሶ ሁለት ሳምንት ሲቀረው አንደኛው ዐይኔ ውስጡ ሲቆስል ሌላኛው ዕንባ ማፍሰስ ጀመረ፡፡ ዕንባው ያለምንም ማቋረጥ ለ24 ሰዓታት ይወርዳል፡፡ ቤተሰቦቼ ሁኔታው አላምር ቢላቸው ወደ አንዲት ታዋቂ የዐይን ሐኪም ወሰዱኝ፡፡ እሷም 'በሕይወቴ እንዲህ ዐይነት ነገር ዐይቼ አላውቅም፤ ዐይኗ ውስጥ ቁስል አለና የመታት ነገር አለ ወይ?' ብላ ጠየቀች፡፡ ይሁንና ቤተሰቦቼም ሆኑ እኔ ምንም ነገር የመታኝ ነገር እንደሌለ ለዶክተሯ ነገርናት፡፡ በየሰዓቱ የሚደረግ ጠብታ አዛልኝ ለጊዜው ተሻለኝ፡፡ የከፍተኛ ትምህርቴን ግን ሳልማር ለሁለት ዓመት ያህል አቋረጥኩ» ትላለች የሕመሙን አስከፊነት የምትናገረው መንበረ ማርያም፡፡

መንበረ ማርያም እንደገለጸችልን በጤና መታወክ ሳቢያ ለጊዜው ትምህርቷን ብታቋርጥም ለትምህርቷ ያላት ቁጭት ከፍተኛ ስለነበር በሽታው መጣ ሔድ እያለ ቢያስቸግራትም ከዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በመግባት ትምህርቷን በሥራ አመራር የትምህ ርት ዘርፍ ለአራት ዓመታት ያህል ተከታትላ በ1996 ዓ.ም በዲግሪ ተመርቃለች፡፡

ይሁንና ሌላ ያላሰበችው ችግር ገጠማት፤ ይህስ ምን ይሆን? ለዚህም መንበረ ማርያም ስትናገር «የወር አበባዬ ከመጣበት ጊዜ አንሥቶ አሁን እስከዳንኩበት ጊዜ ድረስ በየወሩ በጣም እያመመኝ ክፉኛ ያሰቃየኛል፡፡ ስቃዩን ለማስታገሻ እያልኩ ፓ¬ራሲታሞል ክኒን በየአራት ሰዓት ልዩነት ሁለት ሁለት ፍሬ በመዋጥ በቀን 10 ፍሬ እወስድ ነበር፡፡ ሐኪም ቤትም ብሔድ የሚሰጡኝ መርፌ ነው፡፡ አልሻል አለኝ፡፡ የሕክምና ባለሙያዎቹ 'አግብታ ትውለድ፤ ሴቶች እንዲህ ዐይነት ሕመም ሲሰማቸው ይሻላቸዋልና መውለድ አለብሽ' ብለው አስተያየት ይሰጡኛል» ትላለች፡፡

እንደ መንበረ ማርያም አገላለጽ ብዙ ጊዜ መድኃኒትም መዋጥ ሌላ ችግር /Side-effect/ ስላለው መድኃ ኒት መውሰዱን ታቋርጣለች፤ «ከድጡ ወደ ማጡ» እንዲሉ ይባስ ብሎ በየወሩ ያማት የነበረው እንደ አዲስ የማያቋርጥ የማኅፀን ሕመም ይሰማት ጀመር፡፡ በዚህን ጊዜም በታወቁ የማኅፀን ሐኪም በመታየት በወር አበባ ሳቢያ የተነሣ በማኅፀኗ ውስጥ ትናንሽ ዕጢዎች እንዳሉ ይነገራትና የወር አበባዋ ከመምጣቱ በፊት ለአንድ ሳምንትና ከመጣም በኋላ ለአንድ ሳምንት የሚወሰድ ከባድና በጣም ውድ የሆነ መድኃኒት ይታዘዝላ ታል፡፡ ይህ የሆነው ከሁለት ዓመት በፊት ነው፡፡

«በዚህን ጊዜ የመጨረሻ ቁርጥ ውሳኔ ወሰንኩ» ትላለች መንበረ ማርያም፡፡ «መሞቴ ለማይቀር ነገር ለምን እሰቃያለሁ? በመድኃኒትስ ለምን እቃጠላለሁ?» በማለት ወደ ጠበል ቦታ ለመሔድ ወሰነች፡፡ ጠበሉን እንድትሞክር ያነሣሣትና ምክንያት የሆነቻት ደግሞ ጓደኛዋ እንደሆነች ተናግራለች፡፡ «አንድ ጓደኛዬ እንደ እኔ ዓይነት ሕመም ይሰማት ስለነበር ጻድቃኔ ማርያም ሔዳ ጠበል ጠጥታ እንደዳነች ነገረችኝ፡፡ እኔም ጠበል መጠጣትና መጠመቅ እንዳለብኝ መከረችኝ፡፡ መድኃኒቱን አቋርጬ ጠበል መጠመቅ ጀመርኩ፡፡ እየጾምኩ በተከታታይ ጠበሉን ስጠጣና ስጠመቅ በየወሩ የወር አበባዬ ሲመጣ ያመኝ የነበረውን ተወኝ፡፡ በመቀጠል ከማኅፀኔ ሥጋ ነገር ተቆርጦ ወጣ፡፡ በዚህ ጊዜ ቤተሰቦቼ «እጢው ወጣልሽ» በማለት ተአምር አሉ፡፡ ሥጋ መሰል ባዕድ አካል ከወጣልኝ በኋላ ምንም ዓይነት ስሜት ሳይሰማኝ ጤነኛ ሆንኩ፤ ጠበሉንም አቋረጥኩት» በማለት ገልጻለች፡፡

በዚህ መልኩ ለውጥ ያገኘችበትን ጠበል ስታቋርጥ ዳግም ሕመሙ ጀመራት፡፡ መንበረ ማርያም ትናገራ ለች፡፡ «ጠበሉን ለአንድ ዓመት እንዳቋረጥኩ በሽታው በባሰና በሚያስፈራ መልኩ ተመልሶ መጣ፡፡ እንደገና ጠበሉን መጠጣት ጀመርኩ፤ በዚህን ጊዜም ደጋግሞ የሆነ ነገር በሕልሜ ያሳየኛል፤ በሆነ መንገድ ላይ በጣም ጥቁርና ትልቅ ሰውዬ ዝም ብሎ ቆሞ ዐያለሁ፣ ቀጥሎ እኔ ሕፃን ልጅ ታቅፌ ሳመልጥ እሱ ትልቅ ድንጋይ ይዞ እየተከተለ በማስፈራራት ሲያሯሩጠኝ ዐያለሁ፡፡ ይህን ያየሁት በድሮው ቤታችን መገናኛ አካባቢ ነው፡፡

የመንበረ ማርያም ዋናው ታሪክ የሚጀምርው በግንቦት ወር 2001 ዓ.ም ነው፡፡ በዕለተ ሰንበት እሑድ ቀን ቅዳሴ አስቀድሳ ስትመለስ እንደተለመደው የወር አበባ ይታያትና በቃላት ሊገለጽ በማይችል ሁኔታ በጽኑ ትታመማለች፡፡ መንበረ ማርያም እንደገለጸችው «መጽሐፈ አርጋኖን ይዛ ከአንዱ ክፍል ወደ አንዱ ክፍል እየተንቆራጠጠች 'ወይኔ! እመቤቴ ኧረ አድኚኝ' እያለች መኝታ ክፍሏ ሆና ስታጣጥር በድንገት በግድግዳ ላይ የተሰቀለውን የቅዱስ ሚካኤል ሥዕል ታያለች፡፡ እያጣጣርኩ በክፍሌ ውስጥ ቁጭ ብዬ ድንገት የተሰቀለውን የቅዱስ ሚካኤል ሥዕል ቀና ብዬ ማየት ስጀምር የፌዝ ሳቅ መሳቅ ጀመርኩ፡፡ በዚህን ጊዜ ራሴን እየለወጠኝ ነው፤ አልፎ አልፎ እንጂ ምን እንደምሠራም አላውቅም፤ መጣሁልህ ይላል፡፡ እንደዛር ማጓራት ጀመርኩ፤ አባቴ ሲሰማ ደነገጠ፡፡ እሱ እንደነገረኝ ሁለት እጄን ይዞ የቅዱስ ገብርኤል ጠበል እየረጨ 'አንተ ማነህ?' ሲለው 'እባክህ አንተ አታውቀኝም! ዝም ብለህ ነው፤ ተቃጠልኩ ጊዜዬ ሲደርስ የምለቅበት ቀን አለ፡፡ እሷን የያዝኩት ከማኅፀን ጀምሮ ያሳደግኳት እኔ ነኝ' በማለት ለፈለፈ፡፡ በመቀጠል 'እናቷንም የገደልኩ እኔነኝ' ሲል ራሱን ገለጠ» በማለት መንበረ ማርያም አስረድታለች፡፡ እናቷ በካንሰር ሕመም ምክንያት በ1995 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውንም ገልጣልናለች፡፡

በቅዱስ ሚካኤል ሥዕል ሳቢያ ማንነቱን የገለጠው ሰይጣን እንደያዛት ስታውቅ፣ የትመጠመቅ እንዳ ለባት ታስባለች፡፡ በመጨረሻም በደብረ ወልደ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን ሔዳ ጠበል መጠመቅና መጠጣት ትጀምራለች፡፡ በአምስተኛው ቀን ያደረባት ርኩስ መንፈስ መለፍለፍ ይጀምራል፡፡ በተለይ ሰኔ 10 ቀን 2001 ዓ.ም በዕለተ ረቡዕ ስትጠመቅ 681 አጋንንት እንደ ሠፈረባት ይለፈልፋል፡፡ ብዙ ሰው እንደጨረሰና አሁንም ብዙዎችን እንደያዘ ገልጾ እርሷ ላይ ሲደርስ ግን እንደተጋለጠ ተናግሯል፡፡ «ምእመናን እንደነገሩኝ ከሆነ «አንቺ ስትጮኺ እንደ አንበሳ ነው፤ የሚያስፈራና ከአንቺ የሚወጣ ድምፅ አይመስልም ብለውኛል፡፡ እኔ ግን በመሐሉ «መድኃኔዓለም መጣ» የሚል ድምፅ ሰማሁ እንጂ ራሴን አላውቅም፡፡ 

መጨረሻ ላይ ራሴን ሳውቅ ከእኔ የወጣውን ጥቁር ወፍ ይዘው አሳዩኝ፡፡ አላመንኩም፡፡ ሰው እልል እያለ 'አይዞሽ ተነሽ እመቤታችን ከነልጇ የሠራችልሽ ተአምር በጣም ድንቅ ነው፡፡ ተነሥተሽ ድንቅ ተአምሯን ትመሰክሪያለሽ' አሉ፡፡ ልብሴን ለብሼ ስወጣ ብዙ ምእመናን ቆሞ በሞባይልና በቪዲዮ የወጣውን ጥቁር ወፍ ይቀርጻል፡፡ ከሆዴ የወጣው ትልቅ አፍ ያለው ወፍ ደም ጎርሶ በሕይወት ለተወሰነ ደቂቃ ልቡ ይመታል፡፡ እኔ ራሴን አላመንኩም፤ ደስታ አይሉት ሐዘን ተደበላለቀብኝ፣ ሰውነቴ ከላይ እስከታች ይርዳል» ስትል የእግዚአብሔርን ድንቅ ተአምር መስክራለች፡፡

ሰኔ 10 ቀን ከ681 አጋንንት ውስጥ ሰማንያው ጥቁር ወፍ ሆኖ ሲወጣ ሰኔ 12 ቀን ሌሎች ቀሪዎቹ በጉንዳን መልክ ወጥተናል ብለው በመለፍለፍ ለቀቁ፡፡ በወቅቱም የጠበሉ ቦታ በጉንዳን ተወሮ እንደነበር መንበረ ማርያም ገልጻለች፡፡ ያ በሕልሟ ሲያባርራት ያየችው ጥቁር ሰው እርኩስ መንፈስ እንደሆነና ሕፃኑ ደግሞ መድኃኔዓለም ሆኖ እንዳዳናት አምና ተርጉማዋለች፡፡
መንበረ ማርያም ስለተደረገላት ድንቅ ተአምር ሰኔ 10 እና 21 ቀን 2001 ዓ.ም የእመቤታችን ክብረ በዓል ዕለት በቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ ቤተክርስቲያን በመድረክ ላይ ወጥታ ለሕዝበ ክርስቲያኑ መስክራለች፡፡

በመጨረሻ ያነሣንላት ጥያቄ «የተደረገልሽን ተአምር እንዴት ትገልጭዋለሽ?» ነበር፡፡ እሷም «እግዚአብሔር ያደረገልኝን ድንቅ ተአምር በቃላት ልገልጸው አልችልም፡፡ ኃያሉ እግዚአብሔር እኔን አድኖኛል ምስጋና ይድረሰው፡፡ እኔ ግን የማተኩረው ስለተደረገልኝ ተአምር መመስከር ብቻ ሳይሆን ስለማስተላለፈው ነገር ነው፡፡ ይኽም እግዚአብሔር እንዲህ ማዳን እየቻለ ሰይጣን ሊሰለጥንብን አይገባም፡፡ በሥራ፣ በትምህርት ቤትና በዕለት ተዕለት ሥራችን ላይ ውጤታማ እንዳንሆን መሰናከል እየሆነ ነው፡፡ ሕይወታችንን እያበላሸ መሆኑን አልተረዳንም፡፡ ስለዚህ ስመ ክርስትና ብቻ ይዘን መቀመጥ ሳይሆን በጾም በጸሎት እግዚአብሔርን ማገልገል ይኖርብናል፡፡ ከንስሓ አባት ጀምሮ የሃይማኖት አባቶችም ማስተማር አለባቸው፡፡ እያንዳንዱ ሰው ራሱን ይመርምር፤ ክፉ መንፈስን መዋጋት አለበት» ብላለች፡፡

«ማየት ማመን ነው» እንደተባለው በወቅቱ በደብረ ወልደ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስና በመካነ ጎለጎታ ቅድስት ማርያም የጠበል ቦታ ሲያጠምቋት የነበሩትና ድርጊቱን የተመለከቱት ሊቀ ትጉኃን ስሙር አሐዱ ስለሁኔታው እንዲነግሩን ጠይቀናቸው እሳቸውም ታሪኩን እንዲህ አወጉን፡፡ «ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም፤ ነገሩ ተአምር ነው፡፡ ከዚህ በፊት በእርኩስ መንፈስ የታሰሩ፣ የተተበተቡ ሰዎችን በእግዚአብሔር ኃያልነትና መስቀል በመታገዝ በላያቸው ያለውን አጋንንት አስለቅቄያለሁ፡፡ ይህ ግን ልዩና በሕይወቴም ገጥሞኝ የማያውቅ ነው፡፡ በዕለቱ እኅታችን መንበረ ማርያም ወደምትጠመቅበት ክፍል ስትገባ ጀምሮ በጣም ትጮሃለች፡፡ በመስቀል እያጠመቅሁ ምንድን ነህ? ስለው አጋንንት ነን አሉ፡፡ ቀጥሎ ስንትናችሁ? አልኩት 600 አጋንንት ነን አሉና እውነቱን አውጣ ብዬ አጥብቄ ስይዘው 680 ብሎ ለፈለፈ፡፡ መጨረሻ ላይ 681ኛ ተልከስካሽ የዛር መንፈስ እንዳለ ገልጾ ከሰኔ 10 ቀን 2001 ዓ.ም ጀምሮ በተከታታይ በአራት ቀናት ውስጥ ተከፋፍሎ ወጣ» ብለዋል፡፡

እንደ እሳቸው አባባል ሰኔ 10 ቀን 2001 ዓ.ም 80ው ጥቁር ወፍ ሆኖ ሲወጣ፤ በነጋታው «593ቱ ጉን ዳን ሆኜ እወጣለሁ» ብሎ ጮኸ፤ ሲለቅ ወዲያውኑ ከየት መጣ ሳይባል አካባቢውን ጉንዳን ወረረው፡፡ በሦስተኛው ቀን ደግሞ ሰባት ሲወጣ ከሰባቱ አንዷ ብቻ ሴት ሆና ተገኘች፡፡ እሷም «ከውጭ ሀገር ነው የመጣነው፤ ሥራችን ተመሳሳይ ፆታዎችን ማጋባት ሲሆን በውጭው ዓለም አጥለቅልቀነው ወደ አፍሪካና ኢትዮጵያ በብዛት እየገባን ነው» ብላ ተናግራለች፡፡

«በመጀመሪያ ዋናውና አለቃው ' አጋንንት ጥቁር ወፍ ሆኖ ሲወጣ 600ው ሠራዊት ነኝ ብሎ ወጣ፡፡ አለ ቃውን አጋንንት» እንዴት ብለህ ነው የምትወጣው» ስለው እንደ አንበሳ አጓርቼ እወጣለሁ አለ፡፡ ልጅቷ እንደ አንበሳ እያጓራች ሳለ ጥቁር ወፍ በደም ተለውሶ ከሆዷ ውስጥ በአፏ ወጣ፤ ሲወጣም ልክ እንደ አየር ሞገድ ተወርውሮ ገንዳ ነገር ላይ አረፈ፡፡ ይህ እርኩስ መንፈስ ወፍ ሆኖ ሲወጣም ግፊት ስለነበረው እኔን ሁሉ ገፍትሮኛል፡፡ የወጣው ጥቁር ወፍ ከነሕይወቱ በመሆኑ ለተወሰነ ደቂቃ የማስካካት ድምፅ አሰምቷል፡፡ ለግማሽ ሰዓት ያህልም በሕይወት ቆይቶ ምእመናን ዐይተውታል፡፡ ድርጊቱ የሁሉንም መንገደኛ ቀልብ የሳበ ስለነበር መናፍቆች ሳይቀሩ ተመልክተው በእመቤታችን ድንቅ ተአምር ተገርመ ዋል፡፡ በተለይ አንድ ከነቀምት የመጣ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ በተአምሩ ተደንቆ ሲያለቅስ ዐይቻለሁ» በማለት ሊቀ ትጉኃን ስሙር አስረድተዋል፡፡

«አጋንንቱ መንበረ ማርያምን እንዴት እንደያዛት ስጠይቀው በተለያየ ምክንያት በይበልጥ በዛር ውላጅ ሲወርድ ሲዋረድ በዘር ሐረግ የመጣ እንደሆነ ለፍልፏል፡፡ ለ20 ዓመታት ያህል በሆዷና በማሕፀኗ ላይ ከፍተኛ ጫና በማድረስ ያሰቃያት እንደነበር ዘርዝሯል፡፡ በወር አበባዋ ጊዜ ምጥ እያበዛ ያሰቃያት እንደነበር ተናግሯል፡፡ እመቤቴ፣ እመቤቴ እያለች የእመቤታችን ማርያምን ስም እየጠራች አስቸገረችኝ እንጂ ሆዷን ኦፕራሲዮን አስደርጌ በሰበብ ልገድላት ነበር» ሲልም ተናግሯል ይላሉ፡፡

«ድርጊቱ በጣም የሚከብድ እና በእኔ ላይ የደረሰ ያህል ተሰማኝ፤ እኔም በሁኔታው በጣም ያዘንኩበትና ያለቀስኩበት ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ ድርጊት በእኔ ላይ ተከስቶ ቢሆን ኖሮ ምን ልሆን እንደምችል ትንሽ ቆም ብዬ ማሰብ ጀመርኩ፡፡ እሷ ግን እጅግ በጣም ጠንካራ፣ በእምነቷ ጽኑ ነች፡፡ በእምነቷ ጽናት እግዚአብሔር ድንቅ ሥራውን ሠራላት፡፡ አሁን ሙሉ ለሙሉ ጤነኛ ነች ብለዋል፡፡ እርኩስ መንፈሱ አባቷን ሳይቀር ሌሎች ሰዎችንም ይዣለሁ ብሎ በመለፍለፍ ልጅቷ ቤት ድረስ በመሔድ መጥተው እንዲጠመቁ ተናግሬያለሁ» በማለት ሊቀ ትጉኃን ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም «የማስተላልፈው መልእክት አለ፡፡ እግዚአብሔር ብዙ ሥራ ይሠራል፤ እግዚአብሔር እኛ እንድንድን የማያደርግልን ነገር የለም፡፡ ከዚች እኅት ትልቅ ትምህርት አግኝተንበታል፤ የክርስቶስ ስልጣን ይህን ዐይነት የሚሠራ ከሆነ እኛ የት ነን? ብለን ማሰብ አለብን፡፡ ትንሽም ብትሆን እምነት ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ወደ እግዚአብሔር በመቅረብ ጠበሉን፣ እምነቱን ልንጠጣ ይገባል፤ ሥጋና ደሙን ልንቀበል ያስፈልጋል፡፡ ይህ ከሆነ መዳን እንዳለ ማመን ይገባል» ሲሉ ሊቀ ትጉኃን ስሙር አሐዱ አስረድተዋል፡፡
በርግጥም መንበረ ማርያምና አጥማቂዋ ሊቀ ትጉኃን እንደገለጡት በየጠበሉ ቦታ ሲታይ በርኩስ መንፈስ በመተት፣ በዛር፣ በአጋንንትና በመሳሰሉት የተያዙ ሰዎች በእግዚአብሔር ኃይል ሲፈወሱ ማየት ጉድ ያሰኛል፡፡ ሰይጣን የምንፈራው ሳይሆን ታግለን የምናሸንፈው መሆኑን ማንም ሰው ሊያውቀውና ሊረዳው ይገባል፡፡ አውቆም በጾም በጸሎት እርምጃ ሊወሰድ ይገባል፡፡ የበለጠ ደግሞ መምህራን ሓላፊነት ወስደው ማስተማር ይኖርባቸዋል፡፡

ከእጇ ዘይት የሚፈልቅ የቅድስት ኤልሳቤጥ አስገራሚ ታሪክ

 


Tuesday, December 22, 2015

ድንቅ ተአምር - ሰሜን አሜሪካ ሚኒሶታ


ትላንት እሁድ ታህሳስ 10/2008 ዓ.ም በጾመ ነቢያትን ግዜ በደብረ ሰላም መድኃኔዓለም የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የተነገረ ተዓምር ላካፍላችሁ።

ቦታው ሰሜን አሜሪካ ሚኒያፖሊስ ሚኒሶታ ውስጥ ነው። እህታችን ዘጠኝ ወር በማሕጸኗ የተሸከመችውን ጽንስ በሰላም ተገላግላ እንደ እናት ወግ ልጇን አቅፋ ስማ ተንከባክባ ለማሳደግ ጊዜዋ ደርሶ ነበርና መያዝ የሚገባትን ነገር ሁሉ አዘጋጅታ ጨርሳ ወደ ሆስፒታል ታመራለች። በዚህ በጭንቅ ሰዓት ታድያ ካዘጋጀችው እቃዎቿ አንዱ የእናታችን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ስዕለ አድኅኖ ነበር። እህታችን ከመግባቷ በፊትም " እመቤቴ በሰላም ተገላግዬ ከቤተሰቦቼ በደስታ እንድገናኝ በሰላምም ወደቤቴ እንድገባ ከልጅሽ ከመድኅኔዓለም አማልጂኝ ጭንቁን አቅልይልኝ" ብላ ጸሎት አደረገች። ከጥቂት ጊዜም በኋላ ሴት ልጅን በሰላም ተገላገለች ሁሉም ነገር ደስታ ሆነ። ነገር ግን ይሄ ደስታ ምንም ያህል ሊቆይ አልቻለም ነበር። ባለቤቷ መታጠቢያ ክፍል ደርሶ እስኪመለስ ድረስ ነገሩ ሁሉ የተገላቢጦሽ ሆነ ያ ሁሉ ደስታ በደቂቃዎች ወደሃዘን ተለወጠ። እህታችን የወለደቻትን ልጅ እያጠባች ባለችበት ሰዓት በድንገት ራሷን ትስታለች። ወዲያው ሃኪሞች ተጠሩ ከፍተኛ እርዳታ ተደረገላት ነገር ግን መንቃት አለቻለችም። በዚህም ምክንያት በከተማዋ አሉ የተባሉ ስፔሻሊስት ዶክተሮች እና ሊሎችም ከፍተኛ የሕክምና ባለሞያዎች ቢሯሯጡም መልሱ ከነሱ አልነበረምና ምንም ሊረዷት አልቻሉም። በዚህ ጊዜ መላው ቤተሰብ በሃዘን ተዋጠ። 

በከተማው ካሉት አቢያተ ክርስቲያናት አንዱ ወደሆነው ታላቁ ደብር ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን በመምጣት ዘወትር በማሕሌት በኪዳን እንዲሁም በቅዳሴ ሰዓት በካሕናት አባቶች ጸሎት እንዲያዝላት ሽና ስሟ እየተጠራ እንዲጸለይላት
ይጠይቃሉ።ካሕናቱም በፍጹም ታዛዥነት ጽሎቱን ይጀምራሉ። እህታችን በዚሁ ሁኔታ ላይ እንዳለች ሳምንታት አለፉ። ካሕናቱም ጽሎቱን ቀጠሉ ነገር ግን አንድ ያልተጠበቀና አስደንጋጭ ነገር ተፈጠረ።የተፈጠረው ነገር ያልተጠበቀና እጅግ ተስፋ አስቆራጭ ነበር ሙሉ የሰውነት ክፍሏ ስራ አቆመ።የልብ ምቷም ቆመ። ሃኪሞቹ ተጠርተው ቢመጡም ከዚህ በላይ ምንም ማድረግ አይችሉም ነበር። ይሄን ጊዜ በሰው እጅ ያለው ተስፋ ሲሟጠጥ ሸክም ሲከብድ ቢዘገይ እንኳን የሚቀድመው የሌለው አምላክ ስራውን የጀመረው። እህታችን በእናቱ ፊት ለምልጃ ያቀረበችው ጸሎት ከዶክተሮቹ እጅ ተቀብሎ ስራውን መስራት ጀመረ። የተገጣጠሙላት መሳርያዎች ሳይነቀሉ ለስድስት ደቂቃዎች ቆሞ የነበረው የልብ ምቷ በድንግል አማላጅነት በመድኃኔዓለም ሐኪምነት ስራውን ጀመረ። ሃኪሞቹ በጣም ደነገጡ ምንም ያደረጉት ነገር ሳይኖር ለስድስት ደቂቃዎች ስራ አቁሞ የነበረው ልብ አሁን ደግሞ መስራት ጀመረ። ይሄ ከሰው ልጅ አእምሮ በላይ ነው። እስከዛሬም ሆኖ የማያውቅ ይሆናል ተብሎም የማይጠበቅ በጣም አስገራሚ ነገር ነው የተደረገው የሚል ብቻ ነበር የነሱ መልስ። ከዚህም በኋላ እህታችን ሙሉ በሙሉ ከበሽታዋ ድና እንደጓጓችለት በእመቤታችንን ምልጃ በመድኃኔዓለምን ምህረት ለዚህች ቀን ደርሳ ልጇን ታቅፋ አምጥታ ክርስትና ለማስነሳት በቃች ልጅቷም ወለተ ኪዳን ተብላ ተሰይማለች። ይህንን በሰው ሃሳብ ሲመዘን እጅግ ከባድና ከአስተሳሰባችን በላይ የሆነን ነገር ሌላ ሰው ቢናገረው እንዴት ይታመናል? በሳይንስ እይታ የልብ ምት አይደለም ለስድስት ደቂቃ ቀርቶ ለጥቂት የደቂቃዎች ሽርፍራፊ እንኳን ስራ ቢያቆም ያ ሰው ሞቷል ማለት ነበር። በሰው የተዘጋውን በር ሳይሆን በእግዚአብሔር እጅ ያለውን ቁልፍ ተመልከት እንዳሉ አቡነ ሺኖዳ ሳልሳዊ እሱ ታሪክን ቀያሪ ነውና የአራት ቀን እሬሳን ያስነሳ አምላክ ሃዘኑን በደስታ ለወጠ። የካሕናቱና የቤተሰቡ ያልተቋረጠ ጸሎት መንበረ ጸባዖት ደረሰ። አዎ በትክክልም ተደርጓል እህታችንም በአውደ ምህራት ቆማ በጸሎት ሲያስቧት የሰነበቱትን ካሕናት እና ምዕመናን አመስግና የጭንቅ ጊዜ ደራሿን ድንግልን ከምንም በላይ ደግሞ እርሱ ሐኪም እርሱ ስፔሻሊስት ሆኖ ለዚህ ያበቃትን ጌታ መድኃኔዓለምን በአንደበቷ አመሰገነች።
"ወመኑ መሐሪ ዘከማከ"
"አቤቱ እንዳንተ ያለ መሐሪ ማነው?" አይደል ያለው ሊቁ!
እህታችንን ያማለደች እመቤታችን ምልጃዋ ጸጋ ረድኤት በረከቷ አይለየን። መሐሪው አምላካችን የያንዳንዳችንን የልቡና መሻት ይፈጽምልን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!

Friday, December 11, 2015

በወረብ አብሮ የሚሳተፈው የቅዱስ መርቆርዮስ ስዕል

በጣርማበር የቅዱስ መርቆርዮስ ምስል እንዴት እንደሚንቀሳቀስ ተአምሩን ተመልከት ነጮቹ መናፍቃን ተአምሩን አይተው ደንግጠው በአድናቆት እጃቸውን በአፋቸው ይዘዋል የቅዱስ መርቆርዮስ በረከቱ ይደርብን አሜን::


 
ተአምር በ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ከርስቲያን
አባ ሳህለ ማርያም

Wednesday, December 9, 2015

የደብረ ዓሣው አባ ዮሐኒ

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን
ኅዳር 5- የደብረ ዓሣው አባ ዮሐኒ የተሰወሩበት ዕለት ነው፡፡ አባታቸው አባ አሞኒም በዚህች ዕለት ነው ያረፉት፡፡ ዳግመኛም ዛሬ የቅዱስ ሌንጊኖስ ራስ የታየችበትና ተአምር ያረገችበት ዕለት ነው፡፡ 

የቅዱስ ለንጊኖስ ራስ የታየችበት ተአምር ያረገችበት ዕለት፡- ይኸውም ቅዱስ ለንጊኖስ በመጀመሪያ ጌታችንን ጎኑን በጦር የወጋው ነው፡፡ የመድኃኔዓለም የፍቅሩ መጠን ልክ የለውምና ይህንንም ጎኑን በጦር የወጋውን ሰው በወቅቱ ዕውር የነበረችውን አንድ ዐይኑን አበራለት በኋላም በስሙ አምኖ ወንጌልን ሰብኮ በሰማዕትነት እንዲያርፍ መረጠው፡፡ በሙሉ ልቡ አምኖ እስከሞት ድረስ ለመታመን ተዘጋጅቶ በክፉዎች አይሁድ ፊት ስለ ጌታችን አምላክነት መመስከር ጀመረ፡፡ አይሁድና ሮማውያንም በምስክርነቱ እጅግ ተቆጥተው ያሳድዱት ጀመር፡፡ ወደ ታናሹዋ እስያ ወደ ቀጵዶቅያ ሄዶ በዚያ ወንጌልን እንደ ሐዋርያት በመስበክ ብዙዎችን ወደ ቀናች እምነት መልሷቸዋል፡፡ አይሁድም በክፋት ተነሥተው የሐሰት ምስክር አቁመው በመኳንንት ዘንድ በሐሰት ወንጅለው በቀጵዶቅያ አገር ሐምሌ 23 ቀን አንገቱን በሰይፍ አስቆረጡት፡፡ ራሱንም ብቻዋን ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዷት፡፡ በምስክርነቱ የቀኑና የተናደዱ በዚያ የሚኖሩ አይሁድም ራሱ ተቆርጣ ባዩአት ጊዜ እጅግ ተደስተው ከከተማ ውጭ በአንድ ኮረብታ ላይ ቀበሯት፡፡
ከብዙ ቀንም በኋላ በቅዱስ ለንጊኖስ ስብከት ያመነች አንዲት ሴት በቀጵዶቅያ አገር ራሱን ከቆረጡበት ጊዜ ጀምራ በተቆረጠበት ቦታ በመቆም ስለእርሱ ታለቅስ ነበር፡፡ ከጊዜም በኋላ ዐይኖቿ ታወሩ፡፡ የጌታችንን መቃብር ለመሳለም ተነሥታ ከነልጇ ወደ ኢየሩሳልም መጣች፡፡ ኢየሩሳልም በደረሰችም ጊዜ ልጇ ሞተ፡፡ በሀዘንም ሆና ሳለ ወደ ሀገሯ መርቶ የሚወስዳት ስላጣች መሪር ልቅሶን አልቅሳ ደክሟት ተኛች፡፡ ተኝታም ሳለ ቅዱስ ለንጊኖስን ከሞተ ልጇ ጋር በራእይ አየችው፡፡ ራሱ ተቀብራ ያለችበትንም ቦታ ነገራትና ሄዳ እንድታወጣ አዘዛት፡፡ ቅዱስ ለንጊኖስ ወዳመለከታት ወደ ቦታው ሄዳ ስታስቆፍረው መዓዛው እጅግ ጣፋጭ የሆነ የሽቱ መዓዛ ወጣ፡፡ አማኟም ሴት የቅዱስ ለንጊኖስ ራሱ ያለችበት ቦታ ስትደርስ ታላቅ ብርሃን ተገለጠላትና ዐይኖቿ በሩላት፡፡ የቅዱስ ለንጊኖስን ራስና የልጇን ሥጋ ይዛ ወደ ሀገሯ ወስዳ ባማረ ቦታ አኖረቻት፡፡ ይኸም ተአምር ኅዳር 5 ቀን የተፈጸመ ነው፡፡
/////////////////////////
አቡነ አሞኒና ልጃቸው አቡነ ዮሐኒ፡- መጽሐፍ አባታቸውን ዘስዩመ ተንቤን እሁሁ ይላቸዋል፡፡ እናታቸው ደግሞ ዓመተ መንፈስ ቅዱስ የሚባሉ ደገኛ ምግብራቸው ያማሩ ሀገር ወዳድ ናቸው፡፡ አቡነ አሞኒ የካቲት 5 ቀን አክሱም ውስጥ ሲወለዱ ሰይጣናት የወላጆቻቸውን ቤት ከበው በማየታቸው እንደተወለዱ በእጃቸው ቢያመለክቱ በአንድ ጊዜ 60 ሰይጣናት ተሸንፈው እንደጢስ በነው ጠፍተዋል፡፡ አሞኒ ማለት አሸናፊ ማለት ነው፡፡

አባ አሞኒ የራስ ፀጉራቸው ልብስ መጎናጸፊያ ሆኖላቸው የኖሩ ታላቅና ቀደምት አባት ናቸው፡፡ በደመና ተጭነው ደብረ ዘይት ድረስ በመሄድ ከአባ እብሎይ ጋር ተገናኝተው ብዙ ምሥጢርን አውርተዋል፡፡ አባ ዮሐኒን ያሳደጉት አስተምረው ያሳደጓቸው አባ አሞኒ ናቸው፡፡ የእናቱን ጡት ፈጽሞ ጠብቶ የማያውቀውን የመንፈስ ቅዱስ ልጃቸውን አባ ዮሐኒን እሳቸው እያጫወቱት የታዘዘ አሞራ በክንፎቹ እያለበሰው ቶራ (ሰሳ) እያጠባችው ነው ያደገው፡፡ መነሻ ታሪኩም እንዲህ ነው፡-

የተንቤን አውራጃ ገዥ የነበረው ሰው በዘመኑ ዐፄ ካሌብ የነበሩበት ዘመን ነበርና አብሯቸው ወደ ምድረ ኖባ ሄደው ሰባት ዓመታትን የፈጀ የጦር ዘመቻ ክርስያኖችን በሚያሠቃዩ ነገሥታት ላይ አዳሄዱ፡፡ የተንቤኑ አውራጃ ገዥም ወደ ዘመቻው ከሄደ ቆይቶ ነበርና ታናሽ ወንድሙ የገዥውን ሚስት ‹‹ወንድሜ የቀረው ሞቶ ነው እንደ ኦሪቱ ሕግ እኔው ላግበሽና ልጆቹን ላሳድግ›› አላት፡፡ እርሷም ‹‹ባሌ ቢሞት ይነገረኝ ነበረዘመቻ የሄደው ሁሉ አልተመሰም›› ብላ እምቢ ብትለው በግድ ተገናኛት፡፡ በዚህም ጊዜ አባ ዮሐኒ ተፀነሱ፡፡ በሚያዝያ 5 ቀንም ተወለዱ፡፡
ከዘጠኝ ወር በኋላ ማሏ ከዘመቻ መጣና ወደ ቤቱ ተመለሰ፡፡ የአካባቢውም ሰው ወጥቶ በክብር ሲቀበለው ሚስቱ ግን ምጥ ተይዛ ታማ ስለነበር ወጥታ አልተቀበለችውም፡፡ ‹‹የት ሄደች? ምንስ ሆነች?›› ብሎ ሲጠይቅ ልጅ አይደብቅምና አንድ ሕፃን ‹‹አርግዛ ልትወልድ በምጥ ላይ ትገኛለች›› አለው፡፡ የአውራጃውም ገዥ ያለችበት ድረስ ሄዶ ቢያያት ያማረ ወንድ ልጅ ታቅፋ አገኛት፡፡ ከዚህም በኋላ ከቤቱ ምሰሶ ጋር ጥፍንግ አድርግ አስሮ እየገረፋትና እያስጨነቃት ከማን እንዳረገዘች ጠየቃት፡፡ እርሷም የወንድሙን ምሥጢር ለመጠበቅና ወንድማማቾቹን ላለማጣላት ሥቃዩን ታግሳ ዝም አለች፡፡ በዚህ ቅጽበት የራማው ልዑል ቅዱስ ገብርኤል 40 ዓመት ሙሉ ዘግተው በበረሃ ለሚኖሩት ለአባ አሞኒ ተገለጠላቸው እንደ አውሎ ነፋስ አምዘግዝጎ ወስዶ አውራጃ አገረ ገዥው ቤት አደረሳቸው፡፡
እንደደረሱ ዓመተ ማርያም በጽኑ ድብደባና ግርፋት እየተሠቃየች እያለ አባ አሞኒ የጸጉራቸውን አጽፍ ለብሰው ራቁታቸውን ደጇ ላይ ቆመው አየቻቸው፡፡ በዚህም ጊዜ ለባሏ ‹‹ያውና ከዚህ መነኩሴ ነው የወለድኩት›› አለቸው፡፡ አተንቤቱ አውራጃ አገረ ገዥውም አባ አሞኒን ይዞ ጽኑውን ግርፋት በወታደሮቹ አስገረፋቸው፡፡ በመቀጠልም ገና የእናቱን ወተት እንኳን ያልቀመሰውን ጨቅላ ሕፃን አንሥቶ ‹‹እንካ ልጅህን ይዘህ ጥፋ ከዚህ›› ብሎ ሰጣቸው፡፡ አባ አሞኒም በዚህ ጊዜ ‹‹ዮ ሀበኒ ዮ ሀበኒ›› አሉ፡፡ በትግርኛ እሽ ስጠኝ ማለት ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት ነው ሕፃኑ በኋላ ላይ ‹‹አባ ዮሐኒ›› የተባሉት፡፡ አባ አሞኒም ሕፃኑን ተረክበው ወደ ደብረ ዓሣ ተራራ ሥር ሄደው ልጁን ከወይራ ዛፍ ሥር አስተኝተው ‹‹አምላኬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! ኃጢአቴን ተመራምረህ ይህንን ሕፃን የሰጠኸኝ አላጠባው ጡት የለኝ አላበላው እህል የለኝ›› ብለው የጨቅላው ሕፃን ነገር እጅግ ቢያስጨንቃቸው ምርር ብለው አለቀሱ፡፡ ጸሎታቸውንም እንደጨረሱ ተራራውን በመስቀል ምልክት ቢባርኩት በተራራው መሐል ላይ እንደመደብ ያለ አልጋ በተአምራት ተሠርቶ አገኙት፡፡ ሕፃኑንም ከዚያ አስተኝተው ድጋሚ ጸሎት ሲጀምሩ ቶራ (ሰሳ) መጥታ እግርና እግሯን አንፈራጣ ሕፃኑን አጠባችውና ሄደች፡፡
አባ አሞኒም በዚህ ደስ ተሰኝተው ሕፃኑን ‹‹የምግብህ ነገር ከተያዘ ግዴለም›› ብለው ሌሊቱን ሙሉ ሲጸልዩ አድረው መለስ ቢሉ ዳግመኛም ሕፃኑን የታዘዘ ንስር አሞራ በክንፎቹ ጋርዶ አልብሶትና አቅፎት እንዳደረ ተመለከቱ፡፡ አባታችንም እጅግ ደስ ተኝተው እግዚአብሔርን አመሰገኑት፡፡ እንደዚሁ ሁሉ ቀን ቀን ቶራዋ እያጠባችው ሌሊት ሌሊት ንስር አሞራው አልብሶት እያደረ ሕፃኑ ሦስት ዓመት ሆነው፡፡ አባ አሞኒም ከሰባት ዓመቱ ጀምረው እስከ 12 ዓመቱ ድረስ ፊደል፣ ንባብ ከነትርጓሜው፣ ብሉይንና ሐዲስን፣ ምግባር ሃይማኖትን ሥርዓተ ቤተ ክርስያንን ሁሉ አስተማሩት፡፡
አባ አሞኒ ልጃቸው አድጎ 12 ሲሆነው ከዚህም በኋላ ዲቁና ሊያሾሙትና አክሱም ጽዮን ወስደው ሊያስባርኩት ቤተ ካህናት ከተባለው ቦታ ይዘውት ሲሄዱ ልዩ ስሙ ሲሂታ ከሚባለው ቦታ ሲደርሱ ከወገባቸው በላይ እራታቸውን የሆኑ እንስራ የተሸከሙ ዓሥር ሴቶች አገኙ፡፡ አባ ዮሐኒም አባታቸውን ‹‹አባቴ እነዚህ ደረታቸው ላይ ቀንድ ያላቸው ጽጉራቸው የረዘመ ምንድናቸው? እንደእኛ የሆኑ መስህታን የሚባሉት እነዚህ ናቸውን?›› አሏቸው፡፡ አባ አሞኒም ‹‹አይደሉም ልጄ ዝም ብለህ ሂድ›› አሏቸው፡፡ በኋላ ግን ትዝ ሲላቸው ‹‹በዱር እንስሳት ያሳደኩት ልጄ ወንድና ሴት ለይቶ ሲያውቅ በዚያው ሊሳሳት አይደልምን?›› ብለው በማሰብ ዲቁናና ክህነቱ ይቅርበት ብለው ተመልሰው ወደ በዓታቸው ይዘውት ገቡ፡፡
ከዚህም በኋላ አባ አበይዶ ወደ አባ አሞኒ መጣና እሳቸውን ከአባ ዮሐኒ ጋር እያገለገሏቸው ተቀመጡ፡፡ ዮሐኒ እየጻፈ አበይዶ የሚጻፍበትን ቆዳ እያዘጋጁ ሦስቱም በአንድነት በተጋድሎ መቀመጥ ጀመሩ፡፡
አባ ዮሐኒ 20 ዓመት አባ አሞኒ ደግሞ 40 በሆናቸው ጊዜ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ለአባ አሞኒ ተገለጠላቸውና ‹‹አሞኒ ሆይ ከእንግዲህስ እግዚአብሔር ወደኔ ና ብሎሃል›› አላቸው፡፡ እሳቸውም ልጆቻቸውን አባ ዮሐኒንና አባ አበይዶን ጠርተው ‹‹በሉ እንግዲህ እኔ ወደ እግዚአብሔር መሄዴ ነውና ጸልዩልኝ›› አሏቸው፡፡ ከማረፋቸውም በፊት አባ ዮሐኒን ለብቻቸው ጠርተው ‹‹አንተ አባ ዮሐኒ ካሁን በፊት ሲሂታ ላይ ያየሃቸው ሴቶች ናቸው፣ አዳምንም ከገነት ያስወጡ ናቸው፡፡ ወደፊትም እንደ እነርሱ ያለ የደረሰብህ እንደሆነ ካለህበት ገደል ተወርውረህ ውደቅመ በባሕር ውስጥ ጥለቅ›› ብለው ነግረዋቸው በዛሬዋ ዕለት ኅዳር 5 ቀን በ160 ዓመታቸው በሰላም ዐረፉና ወደ ጠራቸው እግዚአብሔር ሄዱ፡፡
አባ አሞኒ ካረፉ ከ12 ዓመት በኋላ የአባ ዮሐኒ ወላጅ እናታቸው የልጇን ነገር ስታጠና ኖራ ነበርና አሁን ባሏም ስለሞተ አባ አሞኒም ስላረፉ ልጇን ልታይ ከ32 ዓመት በኋላ መጣች፡፡ ቀሚስ ለብሳ ፀጉሯን ተሠርታ በሴትነቷ ልጇ ካለበት ቦታ በመሄድ ማነጋገር እንደማትችል ስላወቀች ፀጉሯን ተላጭታ የወንድ ልብስ ቁምጣ ለብሳ በሁለመናዋ ወንድ መስላ ወደ ደብረ ዓሣ ተራራ አመራች፡፡ እዚያም እንደደረሰች በቅዱሳን ሥርዓት መሥረት ሦስት ጊዜ ‹‹አውሎ ግሶን፣ አውሎ ግሶን፣ አውሎ ግሶን›› አለች፡፡ ሰይጣን ይህን ስም ሲሰማ 40 ክንድ ይርቃል፡፡ የደብረ ዳሞ መነኮሳት እንደ ሰላምታ መለዋወጫ ይጠቀሙበታል፡፡ አባ ዮሐኒም ይህን ድምጽ ከውጭ በሰሙ ጊዜ ‹‹አንተ ማነህ?›› አሉ፡፡ እርሷም ‹‹ዓመተ መንፈስ ቅዱስ ነኝ›› አለቻቸው፡፡ አባታችንም አንድም ድምፁዋ ወትሮ ከሚያውቁት ድምፅ ስተለየባቸው ደግሞም ትዝ ሲላቸው እነዚያ እንስራ አዝለው ደረታቸው ላይ ቀንድ ያላቸው ሆነው ውኃ ቀድተው ሲሄዱ በመነገድ ያዩአቸው ሴቶች ድምፅ ሆነባቸው፡፡ ደግሞም ‹‹ወልደ እከሌ፣ ክንፈ እከሌ›› ሲባል እንጂ ‹‹ዓመተ፣ ወለተ›› ሲባል ሰምተው አያውቁም ነበርና አባታቸው አባ አሞኒ የነገሯቸው ትዝ አላቸው፡፡ በዚያውም ቅጽበት የሚጽፉባትን ብዕር ጆሮአቸው ላይ እንደሰኩ 500 ሜትር ርዝመት ካለው ትልቅ ተራራ ላይ ራሳቸውን ቁልቁል ወረወሩ፡፡ ነገር ግን መሬት ሳይደርሱ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በአየር ላይ እንዳሉ ተቀበላቸው፡፡ ብዕራቸው ግን መሬት ላይ ወድቃ ሸምበቆ ሆነች፡፡ ወዲያውም አባ ዮሐኒ ክንፍ አውጥተው ከቅዱስ ገብርኤል ጋር ጎን ለጎን ሆነው በዛሬው ዕለት ኅዳር 5 ቀን ወደ ብሔረ ሕያዋን ይዟቸው ገባ፡፡
ብሔረ ሕያዋን ያሉ እነ ሄኖክና ኤልያስም ‹‹ሰው ከሚሞትበት ሀገር ሞት ወደሌለበት አገር ማን አመጣው/›› አሉ፡፡ መልአኩም በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ባዘዘኝ ጊዜ እኔ ገብርኤል ነኝ ያመጣሁት›› አላቸው፡፡ ቀጥሎም መልአኩ ‹‹አንተ ሄኖክ ምንም ንጹሕ ብትሆን በሥርዓተ ሥጋ ተወልደህ በሥርዓተ ሥጋ አድገህ ሚስት አግብተህ ወልደሃል፣ እግዚአብሔርም እዚህ ያደረሰህ በንፅህናህ ነው፤ አንተም ኤልያስ ምንም ድንግል ብትሆን በሥርዓተ ሥጋ ተወልደህ በሥርዓተ ሥጋ አድገህ ከዚህ ደርሰሃል፤ ይህ አባ ዮሐኒ ግን ከተወለደ ጀምሮ የእናቱን ጡት አልቀመሰም፣ ቀን ቀን ሰሳ እያጠባችው ሌሊት ሌሊት ንስር አሞራ በክንፎቹ እያለበሰው አድጓል እንጂ›› ብሎ ነገራቸው፡፡ ቀጥሎም መልአኩ የአባ ዮሐኒን ገድል ዘርዝሮ ከነገራቸው በኋላ ሊሞት ያለበትንም የአሟሟቱን ነገር ከነገራቸው በኋላ ‹‹ታዲያስ እንዲህ ያለውን አምጥቼ ከብሔር ሕያዋን ባስገባው ፍርዴ እውነት አይደለምን?›› አላቸው፡፡ ሄኖክና ኤልያስም ይህን ጊዜ ‹‹ይገባዋል›› ብለው አባ ዮሐኒን በምስጋና ተቀበሉት፡፡
ከዚህም በኋላ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ወደ ደብረ ዓሣ ተመልሶ መጥቶ ለአባ አበይዶ ተገለጠላቸውና አባ ዮሐኒን ብሔረ ሕያዋን እንዳስገባው ነገራቸው፡፡ በመጀመሪያ ሄኖክና ኤልያስ አላስገባ ብለው እንደነበርና በኋላም መልአኩ ራሱ የአባ ዮሐኒን ገድላቸውን ከነገራቸው በኋላ በምስጋና እንደተቀበሉት ለአባ አበይዶ ነገራቸው፡፡ ቀጥሎም መልአኩ የአባ ዮሐኒን ገድላቸውን እንዲጽፉትና እንዲያስተምሩበት ለአባ አበይዶ አዘዛቸውና ዐረገ፡፡ አባ አበይዶም አባ ዮሐኒ ከገደሉ ተወርውረው ሲወደቁ አንድ ደስ የሚል ወንድ ሲቀበለው አይተው ነበርና አሁን መልአኩ ሲነግራቸው እጅግ ደስ አላቸው፡፡ አባ አበይዶም በታዘዙት መሠረት የአባ ዮሐኒን ገድል ጻፉት፡፡ እርሳቸውም ትናንት ኅዳር 4 ቀን በሰላም ዐረፉ፡፡
በፎቶው ላይ እንደምታዩት ተንቤን የሚገኘው የአባ ዮሐኒ ቤተ ክርስቲያን አቀማመጡ እጅግ አስደናቂ ነው፡፡ ተራራው መሀል ላይ ወደሚገኘው ቤተ ክርስቲያኑ ለመውጣት 150 ሜትር ተራራውን መውጣት ይጠይቃል፡፡ ሽቅብ ከተወጣ በኋላ አፈ ጽዮንን ትገኛለች፡፡ ከአፈ ጽዮን በኋላ ከድንጋይ የተፈለፈለ 12 መድረክ ያለው የውስጥ ለውስጥ የጨለማ መንገድ አለ፡፡ በመጨረሻ ብርሃን ወዳለብ ስፍራ ሲወጣ በስተግራ በኩል 12 ሜትር ርቀት ላይ ቤተ መቅዱሱ ይገኛል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ 13 ጉልላቶች አሉት፡፡ ገዳሙ ጥንት 58 ዓምደ ወርቅ ነበረው፡፡ በአንድ ወቅት በመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት 22ቱ ሲሰባበሩ አሁን ያሉት 36ቱ ብቻ ናቸው፡፡ ገዳሙ ውስጥ ሦስት ቤተ መቅደሶች ያሉ ሲሆን አንዱን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ይቀድሱበት የነበረው ነው፡፡ ገዳሙ ደብረ ዓሣ እየተባለ ይጠራል፡፡ ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያኑ በመሬት መንቀጥቀጥ ከመፍረሱ በፊት ጣራው የዓሣ አንበሪ ቅርጽ ነበረው፡፡ ዐፄ ገብረ መስቀልም በወቅቱ በዚህ ዓሣ ምስል ያሠሩት ቅዱስ መስቀል በገዳሙ ውስጥ ይገኛል፡፡ አንድም ደግሞ በመጀመሪያ ዐፄ ገብረ መስቀል እና ሌሎቹም ቅዱሳን አበው በገዳሙ ውስጥ ሱባኤ ገብተው ሳለ ቅዱሳን በዓሣ ተመስለው ሲወጡና ሲገቡ በማየታቸው ነው ገዳሙ ‹‹ደብረ ዓሣ አባ ዮሐኑ›› የተባለው፡፡
ሌላው በተፈጥሮአዊ አቀማመጡ እጅግ ድንቅ በሆነው በዚህ ገዳም ውስጥ አስገራሚ የመቃብር ጉድጓዶች አሉት፡፡ መቃብሮቹ የጠፈለፈሉ ዋሻዎች ናቸው፡፡ አንዱ ዋሻ በአንድ ጊዜ ከ6 ሰዎችን ጎን ለጎን አስተኝቶ መያዝ አይችልም ነገር ግን በጣም የሚገርመው የመቃብር ጉድጓዶቹ እስከዛሬም ድረስ አልሞሉም፡፡ አንድ ሰው ከተቀበረ ከዓመት በኋላ አስክሬኑ ይጠፋል፣ አጥንቱም አይገኝም፡፡ ሰሌኑ ግን እስከ ሁለት ዓመት ይቀመጣል፡፡
ለአባ ዮሐኒ ለዚህ ገደማቸው ዕጣን ጧፍ ዘቢብ የሰጠ ሰው ቢኖር ስጦታውን እንደ አቤል መሥዋዕት አድርጎ ጌታችን እንደሚቀበልለት ለጻድቁ ቃልኪዳን ገብቶላቸዋል፡፡
እግዚአብሔር ቢፈቅድ በዘንድሮው በ2008ቱ ለ16 ቀን ያህል በሚደረገው የኅዳሩ የአክሱም ጽዮን ጉዞአችን ላይ ከምንሳለማቸው ከ110 በላይ ገዳማትና አድባራት ውስጥ አንዱ ይህን እጅግ ድንቅ የሆነው የአቡነ ዮሐኒ ገዳም ነው፡፡

ለልዑል እግዚአብሔር ምስጋና ይሁን! እኛንም በአማላጅነታቸው የምንታመን የተዋሕዶ ልጆች የሆንን ሁላችንን ዛሬ ኅዳር 1 ቀን በዓመታዊ በዓላቸው አስበናቸው የምንውለውን የአባ አሞኒን፣ የአባ ዮሐኒንና የአባ አበይዶንና የቅዱስ ሌንጊኖስን ረድኤት በረከታቸውን ያሳድርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን፡፡
(ከአባ ዮሐኒ ደብረ ዓሣ ገዳም የተገኙ ጽሑፎች፣ የጥቅምትና የሐምሌ ወር ስንክሳር፣ ቤተ ክርስቲያንህን ዕወቅ-ማኅበረ ቅዱሳን፣ ሐመር 13ኛ ዓመት ቁ.2 1997 ዓ.ም)

Tuesday, December 8, 2015

የቅዱስ ሚካኤል ተዓምር

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
"ቅዱስ ሚካኤል በእለተ ቀኑ ያደረገው ተአምር ።"




ምስክርነቱን ስታዳምጡ የህጻናቱ እድሜ የ 6 ዓመትና የ3 ዓመት በሚለው ይስተካከል።


የቅድስት ኤልሳቤጥ አስገራሚ ታሪክ 

ባሕታዊ አባ ገብረጊዮርጊሥ በአምስተርዳም

Monday, December 7, 2015

ድንቅ ተዓምር በወይን አምባ ቅዱስ ገብርኤል - የ ተሃድሶ መንፈስ


በወይን አምባ ቅዱስ ገብርኤል በዓለ ንግስ ላይ በታቦቱ ፊት በቅዱስ ገብርኤል ከክፉ መናፍስት የተፈወሰው ወንድም:: ሰይጣን የውሸት አባት ቢሆንም "የተሃድሶ መንፈስ" ይኖር ይሆንን? በርግጥ በተለያየ ግዜ ከ መምሕር ግርማ ወንድሙ እንደተማርነው የ 666 መንፈስ እና የመናፍቅ መንፈስ የሚባል እንዳለ እርግጥ ነው:: ተሃድሶ እና የመናፍቅ መንፈስ አንድ አይነት ናቸው:: 

Testimony of a protestant pastor from east Hararge
ተአምር በ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ከርስቲያን

Memehir Girma wondimu Nequ Part 1

 

Sunday, November 22, 2015

ፀበሉ ፈዋሽ ዘብር ቅድስ ገብርኤል


በሰሜን ሸዋ ሀገር በመንዝ ላሎ ምድር (ዘብር ደብረ ምህረት ቅድስ ገብርኤል) አጭር ታሪክ ተአምረኛው ዘብር ቅድስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን የተመሰረተው በ4ተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በውል ባይታወቅም ከቀድሞ አባቶች ሲነገር እንደቆየና እንደሚነገረው በንግስት አድሃና ዘመነ መንግስት ነው ተብሎ ይገመታል።ምክንያቱም የኦሪት ሊቀ ካህናት የእንበረም ልጅ የሕዝበ ባርክ የልጅ ልጅ አጽቀ ሌዊ በንግስት አድሐና ዘመነ መንግስት መንዝን አጥምቆ አብያተ ክርስትያናትን እንዳቀና ታሪክ ያስረዳል።

በቀደምትነት ከቀኑት፣ከተመሰረቱት እጅግ ጥቂት አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንድ ተአምረኛው ና ፀበሉ ፈዋሽ ዘብር ቅድስ ገብርኤል አንድ ነው። ደብረ ምህረት ተብሎ ስያሜ የወጣለት ይህ ቤተክርስቲያን በአሁኑ ሰአት ለ60አመት ያስተዳደሩት ሊቀ ሊቃውንት አባ አክሊሉ ከ100 አመት በላይ የሆናቸው የዕድሜ ባለፀጋ መንፈሳዊ አባት ሲሆኑ በመንዝና በሰሜን ሸዋ የአብነት ት/ቤት እንዲስፋፋ ያደረጉ ከ50,000 ሽይ በላይ የሚቆጠሩ የቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት፣አስተዳዳሪዎች፣ካህናት፣ዲያቆናት፣መዘምራኖች ሊቃውንቶች በአቋቋም በቅኔ በድጓ ያፈሩ ለጵጵስና ተመርጠው ፣የተወለድበትን ሀገር በንጽህና በቅድስና በእውነት በማገልገል የቦታውን ቃል ኪዳን ለመጪው ትውልድ እንዲተላለፍ ያደረጉ የቤተክርስቲያን አባት በአሁኑ ወቅት አሉ። ፎቷቸው ከታች ይገኛል፣ የቦታው ቃልኪዳን የመላአኩ ቅድስ ገብርኤል ታሪኩም ሆነ ቃልኪዳኑ በድርሳኑ በተአምሩ እንዲሁም በመጽሐፍ ቅድስ ላይ ያለው እንዳለ ሆኖ ዳን•3÷24—30 ዳን•8÷15—18 ሉቃስ 1÷8—20 ለቦታው የተሰጠው ክብርና ቃልኪዳን አንድ ባህታዊ አባት መጥተው ከእየሩስሌም ብዙ ቅድሳን መላዕክትም ሳይቀሩ በቦታው ላይ በአፀዱ ላይ እንደ ንብ ስፍርውበታል ብለው ተናግረዋል፣ከዚህም በተጨማሪ በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደና የከበረ የቅድሳን አበው መናህሪያ ማረፊያ የቃልኪዳን ቦታ በመሆኑ የበዓለ ወልድና የአብነ ሃብተማርያም ገዳም ውስጥ የቅድሳን አበው አጽማቸው በመገኘቱ ነው ታሪኩ እንዲህ ነው ። አባ አክሊሉ ተማሪ ሞቶባቸው መቃብር ሲቆፍሩ አፈሩ አልቆ አንድ ወጥ ድንጋይ

 አግኘተው ሲያነሱት አንድ አባት መልካቸው የሚያምር፣ስጋቸው ያልፈረሰ ፣ፂማቸው የሚያምር መስቀላቸው ይዘው ያልቆሸሸ ንጽህ ከነመግነዛቸው ምንም አፈር ሳይነካቸው በመገኘቱ ሲሆን መቃብራቸውም ተመልሶ ተግጥሟል፣ከዚህም ሌላው የሴት መሎክሴ አጽምም ምንም ሳይሆን ተገኝቷል።12ነገ 13÷20—21 በዚህ ቦታ የሚነኘው ድህነት ይህ ተብሎ አይወሰንም በተለይ አባቶች (መስቀል፣መቋሚያ)ይዘው ፀሉት ሲያደርሱ ችግር የደረሰበት ምዕመኑ (መገበሪያ—ይዞ የተቻለውን ያህል ስንዴ፣ጧፍ፣ጣኑን፣ዘቢብን)ይዞ ቀርቦ የደብሩ ካህናት ጸሎት አድርገው ኃይል አጋንንትን ይጣልላችሁ ብለው (መስቀልና መቋሚያ ዘቅዝቀው ፀሎት ያደርጋሉ ንስሀ ገብቶ ፀሎት የተደረገለት ሁሉ ድህነት ያገኛል)። መተቱም፣አጋንቱም ይታሰራል ፣የተበደለውም ፣የተቀማውም፣የተዘረፈው፣በተለያየ አጋንት ተይዞ ሃብት ንብረቱ አእምሮው እውቀቱ የተበተነበት፣ትዳር ሰላም የሌለው፣ ከቤተሰብ ጋር የሚጋጭ፣ስራ ወይም ትዳር እንቢ ያለው የተለያየ ችግር ያለበት በቅዱስ ገብርኤል ቃልኪዳን ድህነትን ያገኛል።

የቅዱስ ገብርኤል ጽላት በአንድ አባት ራእይ ተገኘ


Tuesday, November 10, 2015

የ ኪዳነ ምሕረት ተአምር

የሚገርም የእመቤታችን ማርያም ተአምር ታሪክ ፦በራያ አልማጣ በጥሙጋ ከተማ ኪዳነ ምሕረት በተባለች ቤተክርስቲያን ለበተክርስቲያኑ ግንባታ የሚሆን ድንጋይ በመኪና ተጭኖ ከመጡት ብዙ ድንጋይ መካከል አንደኛው ድንጋይ ሲጠረብ አልጠረብም ይላል አሁንም ግንበኞቹ በተደጋጋሚ ሞከሩ ሊጠረብ አልቻለም ከዛ ሳይጠረብ ለግንባታ ሊጠቀሙበት ወደ ላይ ለመስቀል አንደኛው ግንበኛ በሁለት እጁ ተሸክሞ ወደ ላይ በሚወጣበት ጊዜ የተሸክመው ሰው እዛው ባለበት ቦታ ልክ እንደ ኤሌክትሪክ ይነዝረዋል ከዛም ከላይ ወደታች ሲወድቅበት ያ ተአምረኛ ድንጋይ ከ ሁለት ይከፈላል በጣም በሚገርም ሁኔታ ከአንደኛው ድንጋይ የምትመለከቱት የእመቤታችን ሥዕል ታየ በጣም የሚገርመው ለ 3 ዓመት መራመድ ያቃታት ሴት የድንጋዩ ፍንጣሪ እግሯን ሲመታትፈውስ አገኘች ማየት ማመን ነው ጥሙጋ እየመጣቹህ መመልከት ትችላላቹህ የእመቤታችን አማላጅነት አይለየን አሜን

Saturday, October 17, 2015

አንዳሳ ቅዱስ ጊዬርጊስ ፀበል

በደብረ መንክራት አንዳሳ ቅዱስ ጊዬርጊስ ለበርካታ አመታት ስትሰቃይ የነበረች እህታችን የቅዱስ ጊዬርጊስን ፀበል በመጠጣት እና በመጠመቅ ከሆዷ ውስጥ ሶስት መርፌ እና አንድ ምላጭ ወጦላታል። ይሂን ታምር በአይኔ በማየቴ እግዚአብሄርን አመሰግናለሁ። ፀበሉ በርካታ ታምራትን እያደረገ ሲሆን በተለያዩ ደዌዎች፣በርኩሳን መናፍስት የተጠቁ ወዘተ እየተፈወሱ ይገኛሉ። ክብር ለቅዱስ
ጊዬርጊስ አምላክ ለእየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ጋር ይሁን

Thursday, October 1, 2015

ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ

ግንቦት 14- ሙሽራው ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ ከጫጉላ ቤቱ ወጥቶ የመነነበት ዕለት ስለሆነ በሀዘን የሚያስለቅሰውን ቅዱስ ገድሉን እንመለከታለን፡፡ በተጨማሪም ዛሬ የታላቁ አባት የአባ ጳኩሚስ በዓለ ዕረፍት ነው፣ ድንጋዩን እንደ ጀልባ ተጠቅመው ጣናን የተሻገሩት የአቡነ ያሳይ ዘመንደባም ዕረፍታቸው ነው፡፡
መልካም የበረከት ንባብ!!!
ሙሽራው ገብረ ክርስቶስ፡- ሙሽራው ገብረ ክርስቶስ ወላጅ አባቱ የቍስጥንጥንያው ንጉሥ ቴዎዶስዮስና እናቱ ንግሥት መርኬዛ በስለት ያገኙት ብቸኛ ልጃቸው ስለሆነ ሃይማኖትን እያስተማሩት በምግባር በእጅጉ ተንከባክበው አሳድገውታል፡፡
የአባቱን ንግሥና በመውረስ ቍስጥንጥንያን እንዲገዛላቸው በመፈለግ ወላጆቹ ለአካለ መጠን ሲደርስ የሮሙን ንጉሥ ሴት ልጅ አጋቡት፡፡ እርሱ ግን ዓለምን ፍጹም በመናቅ የክርስቶስን መስቀል ለመሸከም የተዘጋጀ ነበርና የሠርጉ ዕለት ሌሊት የእርሱንም ሆነ የሙሽይቱን ድንግልና እንደጠበቀ ከጫጉላ ቤት ወጥቶ በመርከብ ተሳፍሮ ሩቅ ሀገር በመሄድ በቤተክርስቲያን ተቀምጦ ከነዳያን ጋር ተደባልቆ በመለመን ለምኖ ያገኘውንም ለሌሎች እየመጸወተ በጾም በጸሎት ተጠምዶ 15 ዓመት ኖረ፡፡
እመቤታችን ተገልጻ ለአንድ የቤተክርስቲያኑ አገልጋይ የገብረ ክርስቶስን ጽድቅ ብትነግረው ምሥጢሩን ለሀገሩ ሁሉ አዳረሰበት፡፡ ሙሽራው ገብረ ክርስቶስም ‹‹ግብሬ ታወቀ፣ ከዚህ ውዳሴ ከንቱ ልሽሽ›› በማለት ወደሌላ ሀገር በመርከብ ሲጓዝ ፈቃደ እግዚአብሔር መርከቢቱን ያለ አቅጣጫዋ ወስዶ አባቱ ደጅ አደረሰው፡፡ ማንነቱን እንደደበቀና ዓለምን ምን ያህል እንደናቃት ይረዳ ዘንድ በአባቱና በንጉሡ ደጅ የኔ ቢጤ ለማኝ ሆኖ ለአባቱ ውሾች የሚሰጠውን ፍርፋሪ እየተመገበ አሁንም 15 ዓመት ሙሉ በትዕግስት ተቀመጠ፡፡
የአባቱ አሽከሮች እንኳን እጣቢና ቆሻሻውን ሁሉ እየደፉበት ሲያሠቃዩት የአባቱ ውሾች ግን የእግሩን ቁስል ይልሱለት ነበር፡፡ በአጠቃላይ ገብረ ክርስቶስ እጅግ የተከበረ የታላቅ ንጉሥ ልጅ ሲሆን ነገር ግን ዓለምን ፍጹም በመናቅ ስለ ጽድቅ ተሰዶ እየለመነ ያገኘውን እየመጸወተ በጾም በጸሎት እየተጋደለ 30 ዓመት ሙሉ ተቀመጠ፡፡ በመጨረሻም ጌታችን እመቤታችንን፣ ቅዱሳን መላእክትን ሁሉ፣ ከገብረ ክርስቶስ በፊት የነበሩ ነቢያትን ሁሉ፣ ሐዋርያትን፣ ጻድቃንን፣ ሰማዕታትን ሁሉ አስከትሎ መጥቶ ቃልኪዳን ከገባለት በኋላ ከጌታችን ጋር አብረውት የመጡት ሁሉ በታላቅ ክብርና ምስጋና እያመሰገኑት ጌታችን ክብርት ነፍሱን በእቅፉ ተቀብሎ አሳርጓታል፡፡
የቁስጥንጥንያው ሊቀ ጳጳሳት አባ ቴዎፍሎስ በቅዳሴ ላይ ሳሉ ከንጉሡ ቤት ሄደው የገብረ ክርስቶስን ሥጋ እንዲያመጡ የእግዚአብሔር ድምፅ ከሰማይ በትእዛዝ መጣላቸውና ሄደው ቢያዩ የገብረ ክርስቶስን ሥጋ በንጉሥ አባቱ ደጅ ወድቆ አገኙት፡፡ በገብረ ክርስቶስም እጅ ላይ በጥቅል ወረቀት የተጻፈ ደብዳቤ ነበርና ወስደው ሊያነቡት ሲሞክሩ ወረቀቱ አልላቀቅ ብሎ ፈጽሞ እምቢ አላቸው፡፡ ብዙ ምሕላና ጸሎት ከተደረገ በኋላ ወረቀቱ ከእጁ ላይ ተላቀቀና ሲነበብ ገብረ ክርስቶስ ስለ አምላኩ ፍቅር ብሎ ለ30 ዓመታት ያሳለፈውን እጅግ አሠቃቂ መከራ በተለይም በአባቱ ደጅ ማንም ሳያውቀው ያሳለፈውን እጅግ አሳዛኝ መከራና በኀዘን የሚያስለቅሰውን ታሪኩን በራሱ እጅ በዝርዝር ጽፎት ተገኝቷል፡፡ ንጉሡ አባቱና ንግሥት እናቱም ይህንን ልጃቸው የጻፈውን መልእክት ባነበቡ ጊዜ የሚሆኑት ጠፋቸው፡፡
በጣም የሚገርመው ደግሞ ወላጆቹ ሚስት አድርገው ያመጡለት የሮሙ ንጉሥ ሴት ልጅ ለባሏ ታማኝ ሆና 30 ዓመት ሙሉ በእናት አባቱ ቤት በትዕግስት ስትጠብቀው መኖሯ ነው፡፡ እርሷም ታሪኩ ሲነበብ ብትሰማ እንደ ዕብድ ሆነች፡፡ የቅዱስ ገብረ ክርስቶስን ሥጋውን ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲወስዱ እጅግ አስገራሚ ተአምራት በድውያን ሕመምተኞች ላይ ተፈጽሟል፡፡ ከተአምራቱ የተነሣ መንገዱ በሕዝብ ተጨናንቆ አላሳልፍ ቢላቸው ንጉሡ በመንገድ ዳር ወርቅ እየበተነ ሰው ወርቁን ለማንሳት ሲሄድ በፍጥነት ወደ ቤተ ክርስቲያን አድርሰውታል፡፡ ዕረፍቱም ጥቅምት 14 ቀን ሲሆን ዛሬ ከጫጉላ ቤቱ መንኖ የወጣበት ዕለት ነው፡፡
አቡነ ያሳይ ዘማንዳባ፡- የደብረ በንኰል ገዳም አበምኔት አቡነ መድኃኒነ እግዚእም በአንድ ቀን ለሰባት አባቶች የምንኵስናን ልብስ አልብሰዋቸል፤ አስኬማ ዘመላእክትን አስታጥቀዋል፡፡ እነዚህም ሰባት ታላላቅ አባቶች "ሰባቱ ከዋክብት" በመባል የሚታወቁት ናቸው፡፡ እነዚህም አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ፣ አቡነ ሳሙኤል ዘቆየፃ፣ አቡነ ሳሙኤል ዘጣሬጣ፣ አቡነ ያሳይ ዘማንዳባ፣ አቡነ ዮሐንስ ዘጉራንቋ፣ አቡነ ታዴዎስ ዘባልተዋር እና አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ ዘጉጉቤን ናቸው፡፡ እነዚህም 7ቱ ከዋክብት ከተሰዓቱ (ከዘጠኙ) ቅዱሳን በኀላ መላዋን ኢትዮጵያ በወንጌል ያዳረሱ ታላላቅ ቅዱሳን ናቸው፡፡ አቡነ ያሳይ ዘማንዳባም አንዱ ናቸው፡፡
ጻድቁ ድንጋዩን እንደ ጀልባ ይጠቀሙበት ነበር፡፡ የማንዳባው አቡነ ያሳይ የመድኃኔዓለምን ታቦት ይዘው ወደ ደሴቲቱ የገቡት ትልቁን ድንጋይ እንደ ጀልባ ተጠቅመው በድንጋዩ ላይ ተቀምጠው የጣናን ሐይቅ እየቀዘፉ ነበር፡፡ ትልቁ ጠፍጣፋ ድንገይ ዛሬም ድረስ በገዳማቸው ውስጥ በክብር ተቀምጦ ይገኛል፡፡
ጻድቁ በይበልጥ የሚታወቁት በ"አትማረኝ ዋሻ" ታሪክ ነው፡፡ በገድላቸው ተጽፎ እንደሚገኘው ዋሻው በጣና ሐይቅ ደሴቶች መካከል ከሚገኙ ገዳማት መካከል ከማን እንደ አቡነ ያሳይ መድኀኔዓለም አንድነት ገዳም በስተ ምእራብ አቅጣጫ የጣና ሐይቅን ጉዞ ከገታው አንድ ተራራ ሥር የሚገኝ ነው፡፡
ጻድቁ ከእግዚአብሔር በተሰጣቸውም ጸጋ በጣና ሐይቅ ላይ እንደ ጀልባ በሚጓዙበት አንድ ጠፍጣፋ ድንጋይ ተቀምጠው በጣና ደሴት ላይ ለአገልግሎት በመፋጠን ላይ እያሉ ዛሬ አትማረኝ ዋሻ ተብሎ ወደሚጠራው አካባቢ ሲደርሱ አንድ አባት ዋሻው ውስጥ “አትማረኝ፣ አትማረኝ፣ አትማረኝ” እያሉ ሲጸልዩ ያገኟቸዋል፡፡ አቡነ ያሳይ በሰውዬው ጸሎት በመገረም ቀርበዋቸው “አባቴ ምን ዓይነት ጸሎት ነው የሚጸልዩት? ይበሉ ከዛሬ ጀምረው “ማረኝ” እያሉ ይጸልዩ" በማለት አቡነ ዘበሰማያትን አሰተምረዋቸው ይሄዳሉ፡፡ አትማረኝ እያሉ ይጸልዩ የነበሩት አባትም “ማረኝ” እያሉ መጸለያቸውን ቢቀጥሉም ብዙ መግፋት ሳይችሉ ጸሎቱ ይጠፋባቸዋል፡፡ ጸሎቱን ያስጠኗቸው አባት አቡነ ያሳይ በድንጋዩ ላይ ተቀምጠው ጣናን አቋርጠው ርቀው ሳይሄዱባቸው ከኀላ በውኃ ላይ በባዶ እግራቸው እየተራመዱ በመከተል ይደርሱባቸዋል፡፡ “አባታችን ያስጠኑኝ ጸሎት ጠፋብኝ፡፡ እባክዎ እንደገና ያስተምሩኝ” ይሏቸዋል፡፡ አቡነ ያሳይ የእኚህ አባት መብቃት (በባሕር ላይ በባዶ እግራቸው መራመዳቸውን) ተመልከተው “አባቴ እግዚአብሔር የልብ ነውና የሚመለከተው እንዳስለመዱት ይጸልዩ የእርስዎ ይበልጣል” ብለዋቸው ይሔዳሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ቦታው አትማረኝ ዋሻ ተብሎ ተጠርቷል፡፡
አቡነ ያሳይ እጅግ አስገራሚ ተአምራትን በማድረግ ወንጌልን በሀገራችን ያስፋፉ ሲሆን ተጋድሎአቸውን ፈጽመው ከጌታችን ታላቅ ቃልኪዳን ተቀብለው በዛሬዋ ዕለት ዐርፈዋል፡፡ በረከታቸው ይደርብን!
ኃያል መነኮስ አባ ጳኩሚስ፡- በሥርዓተ ምንኵስና ታሪክ ሌላውን ታላቅ ሥፍራ የያዘው ደግሞ የአባ እንጦንስ ደቀ መዝሙር የነበረው አባ ጳኩሚስ ነው (23ዐ-346 ዓ.ም)፡፡ አባ ጳኩሚስ ግብፅ ውስጥ ኤስና በምትባል መንደር ከአረማውያን ቤተሰቦች በ29ዐ ዓ.ም ተወለደ፡፡
በቆስጠንጢኖስ ዘመነ መንግሥት ለውትድርናም ተመልምሎ አገልግሎት ሰጥቷል፡፡ በውትድርናው ዘመን የክርስቲያኖችን ቆራጥነት፣ ደግነትና ርኀራኄ በማየቱ ልቡ ስለተነካ ግዳጁን ፈጽሞ ሲመለስ በ313 ዓ.ም የክርስትናን እምነት ጠንቅቆ በመማር አምኖ ተጠመቀ፡፡ የአባ ጳኩሚስ ልቡና የቅዱስ እንጦንስ ደቀ መዝሙር በነበረው በአባ ጴላጦንስ ኑሮ ስለተማረከ ወደ በረሃ ወርዶ የብሕትውናን ኑሮና ሥርዓት ሲማር ከቆየ በኋላ በ32ዐ ዓ.ም በዓባይ ወንዝ አጠገብ ታቤኒስ ከተባለው ቦታ የራሱን ገዳም መሠረተ፡፡
እዚህ ጋር የመነኮሳትን ትውልድ መመልከቱ ተገቢ ይሆናል፡፡ ርዕሰ መነኮሳት የሆኑት አቡነ እንጦንስ በእግዚአብሔር ፈቃድና ትእዛዝ ምንኩስናን ከሊቀ መልአኩ ከቅዱስ ሚካኤል እጅ ተቀበሉ፡፡ እንጦንስም ታላቁ መቃርስን አመነኮሷቸው፤ ታላቁ መቃርስም ጳኩሚስን አመነኮሷቸው፤ እንዲህ እንዲህ እያለ የአባቶቻችን የምንኩስና ትውልድ እስከ ጻድቁ አባታችን ተክለ ሃይማኖት የደረሰ ሲሆን እሳቸውም ያመነኮሷቸው እጅግ ብዙዎች ናቸው፡፡



ጳኩሚስም ቴዎድሮስን፣ ቴዎድሮስ ደግሞ አቡነ አረጋዊን(ዘሚካኤልን)፣ አረጋዊ ክርስቶስ ቤዛነን፣ ክርስቶስ ቤዛነ መስቀል ሞዐን፣ መስቀል ሞዐ ዮሐኒን፣ ዮሐኒ ኢየሱስ ሞዐንና ተክለ ሃይማኖትን(በቆብና በአስኬማ)፣ ኢየሱስ ሞዐ
ተክለ ሃይማኖትን(በቅናትና በቀሚስ)፣ ተክለ ሃይማኖት ኢየሱስ ሞዐን (በቆብና በአስኬማ) ወልደዋል፡፡
ዻኩሚስ መጀመሪያ ወደ ምንኩስናው ዓለም የመጣው በታላቁ አባ ዸላሞን አማካኝነት ነው፡፡ ለተወሰነ ጊዜም መንፈሳዊ አባቱን እየረዳ ሕይወተ መነኮሳትን አጥንቷል፡፡ በመንፈሳዊ ሕይወቱና በተጋድሎ እየበረታና እየደረጀ ሲሔድ ከአባ ዸላሞን ተለይቶ ማሕበር መስርቶ ለመኖር አምላኩን ጠይቆ ፈቃድ በማግኘቱ በሕግ የሚመራ የመጀመሪያውን ገዳም መሥርቷል፡፡
ቅዱስ ዻኩሚስ ጸሎቱ አጋንንትን ከአካባቢው አያስቀርባቸውም ነበር፡፡ አካሉ አልቆ በአጥንቶቹ እስኪቆም ድረስ ጾሟል፡፡ ዓርብ ዓርብ የጌታችንን ሕማማት እያሰበ ከእንባ ጋር ይሰግዳል፡፡ እንባውና ላበቱ ከፊቱ እየወረደ አካባቢው ጭቃ ይሆን ነበር፡፡ ጌታችንም መስቀል ተሸክሞ ይታየው ነበር፡፡ አባ ጳኩሚስ ሲሰግድ ወዙ ወርዶ መሬቱን ጭቃ አደረገው፣ ወዲያው ጌታችን ተገለጸለትና ጳኩሚስ "አንተን አገኝ ብዬ እንዲህ እደክማለሁ" አለው ጌታችንም "እኔም እንጂ ላንተ ብዬ እንዲህ ሆኜ ተሰቅያለሁ" ብሎ በዕለተ ዓርብ እንደተሰቀለ ሆኖ ጐኑን እንደተወጋ ደሙ እንደፈሰሰ ሆኖ ታይቶታል፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን በበረሃ ሳለ መልአክ መጥቶ በነሐስ የተጻፈ ሕግ ሰጠው እርሱም በዚሀ የመጀመሪያውን ሥርአተ መነኮሳትን አዘጋጅቷዋል። ከዚህም ባለፈ በርካታ ሥራዎችን ሠርቷል፡፡ ቅዱስ ዻኩሚስ ጫማ ሳይጫማ እሾህን ሳይሰቀቅ ይረግጥም ነበር፡፡
አባታችን ቅዱስ ዻኩሚስ ከርሕራሔው የተነሣ አጋንንት ያደሩባቸውን ሰዎች ሲያገኝ በቀጥታ ከመፈወስ ይልቅ ደዌውን ርኩሳን መናፍስቱንም ወደ እርሱ እንዲገለበጡ ያደርግ ነበር:: ከዚያም በጾም በጸሎትና በስግደት መድረሻ ያሳጣቸዋል፡፡ ያንጊዜ በግዳቸው እየጮሁ ሲወጡ ደጉ አባት "ምነው ትንሽ ቆዩ እንጂ" እያለ ይቀጣጠብባቸዋል፡፡ አንድ ዕለት ቅዱስ ጳኩሚስ አንዲት ሴት ብዙ አጋንንት ሰፍረውባት ስትሰቃይ አየና "አቤቱ ጌታዬ ሆይ ይህን ሁሉ እንዴት ትችለዋለች?" ብሎ በእርሷ ላይ ያለውን የአጋንንት መንጋ ወደ እርሱ እንዲገለበጥ ፈጣሪውን ለመነ፡፡ በዚህ ጊዜ በአንድ ቀፎ ውስጥ ያሉ ንቦች ወደ ሌላ ቀፎ እንደሚገለበጡ እነዚያ አጋንንት በሙሉ ከዚያች ሴትዮ ወጥተው በአባ ጳጉሚስ ላይ ሰፈሩ፡፡ እርሱም ማቅ ለብሶ አመድ ነስንሶ በሥግደት በጾምና በጸሎት አሰቃያቸው፡፡ የዚህን ቅዱስ አባት ትሩፋትና ተጋድሎ ስላልቻሉ አጋንንቱ "እንሂድ እንጂ እንግዲህማ ምን እናደርጋለን" ሲሉ ሰማቸው፡፡ ቅዱስ ጳኩሚስም "ለምን አትቆዩም ሰው እንዲህ ካለ ኃጥእ ወዳጁ ቤት እኮ ጥቂት ጊዜ ያርፋል" ቢላቸው "እኛስ ከገነት ካስወጣነው ከአዳም በቀር እንዲህ ያለ ሰው አላየንም ትሩፋቱ አቃጠለን ሊያስቀምጠን አልቻለም" ብለው መስክረውለት ሄዱ። (ኤፌ.6፥11 "የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ።")
አባ ዻኩሚስ ስለ ክብራቸው መልአክ ነጥቆ ወስዷቸው ገነትንና ሲኦልን አሳይቷቸው መልሷቸዋል።
በዙሪያው ለተሰበሰቡት መነኰሳትም የአንድነት ኑሮ ሕግ አወጣላቸው፡፡ ምንኩስና በእግዚአብሔር ፈቃድ በአባ እንጦንስ ቢመሠረትም ሕይወቱን በማስፋፋት ደረጃ የቅዱስ ዻኩሚስን ያህል የደከመና የተሳካለት ግን የለም፡፡ በአባ እንጦንስ ለተጀመረው የማኀበረ መነኰሳት ኑሮ የተጠናከረ ሥርዓት አውጥቶ የበለጠ ከማስፋፋቱም በተጨማሪ ዘጠኝ የወንድና ሁለት የሴቶች ገዳማት መሥርቷል፡፡ አባ ጳኩሚስ ያወጣው የመነኰሳት የአኗኗር ሕግ ዋናው ቅጂ ሲጠፋ ወደ ላቲን የተተረጐመው ግን እስከዛሬ ድረስ ይገኛል፡፡ ከሕግጋቱ መካከል፡-
፩. መነኮሳት ጠዋትና ማታ በማኀበር እንዲጸልዩ
፪. በኀብረት በአንድነት እንዲሠሩ
፫. ቅዱሳት መጻሕፍትን አዘውትረው እንዲመለከቱ
፬. መነኮሳት ሹመት እንዳይሾሙ ከልክሏል
፭. መነኮሳት የቁም ጽሕፈት እንዲማሩ
፮. ገቢና ወጪአቸው አንድ ላይ እንዲሆን
፯. መነኮሳት በአንድነት እንዲመገቡ
፰. አንድ ዓይነት ልብስ እንዲኖራቸው
፱. መነኮሳት ንጽሕናቸውን ጠብቀው እንዲኖሩ
፲. ከግብፅ ውጪ ምንኩስናን ያስፋፉ አባቶችን አስተምሮ አመንኩሷል፡፡ (ለምሳሌ በኢትዮዽያ ምንኩስናን ያስፋፉት አቡነ አረጋዊ የዚህ አባት ደቀ መዝሙር ናቸው)
፲፩. መነኮሳት ከገዳማቸው በፍጹም እንዳይወጡ ከልክሏል
፲፪የመጀመሪያውን ሥርዓተ መነኮሳት አዘጋጅቷል
፲፫. መነኮሳት ደግነት፣ ፍቅርና ታዛዥነት እንዲኖራቸው...የሚሉት ይገኙበታል፡፡
አንድ ሰው ወደ ገዳማቱ ሲመጣ የሦስት ዓመት አመክሮ ይሰጠውና ጠባዩና ፍላጐቱ ይገመገማል፡፡ ከዚያ በኋላም ብርታቱና ጽናቱ ታይቶ ወደ ማኀበረ መነኰሳቱ ይቀላቀላል፡፡ አባ ጳኩሚስ በዚሁ ዓይነት መንገድ ሥርዓት ሠርተው ሕግ አጽንተው ገዳማትን ካስፋፉና አበምኔት ሁነው 40 ዓመት ካገለገሉ በኋላ ከጌታችን ቃልኪዳን ተቀብለው ለደቀመዛሙርቶቻቸው ቴዎድሮስ ሹመውላቸው በተወለዱ በ56 ዓመታቸው በ346 ዓ.ም በሰላም ዐርፈው ቅድስት ነፍሳቸውን ጌታችን በክብር ተቀብሏታል፡፡
የቅዱሳኑ በረከት በአማላጅነታቸው በምንታመን በሁላችን ላይ ይደርብን አሜን! ይልቁንም እኔን ኀጥኡን ምልጃቸው ሥርየተ ኃጢአትን ያሰጠኝ!!
(ምንጭ፡- ገድለ ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ፣ ገድለ አቡነ ያሳይ-ያለታተመና በገዳሙ የሚገኝ፣ ስንክሳር ዘወርሃ ግንቦት፣ የቅዱሳን ታሪክ፣ መዝገበ ታሪክ)

Tuesday, September 1, 2015

አቡነ ኤዺፋንዮስ

ግንቦት 17- ዕረፍቱ ለአቡነ ኤዺፋንዮስ፡- "ኤዺፋንያ" ማለት የመለኮት መገለጥ ሲሆን "ኤዺፋንዮስ" ማለት ደግሞ ምሥጢረ መለኮት የተገለጠለት ማለት ነው::
ቅዱስ ኤዺፋንዮስ የተወለደው ክርስቶስን ከሚጠሉ አይሁዳውያን ቤተሰቦች ሲሆን ቤተሰቦቹ ከአንድ አህያ በቀር ምንም የሌላቸው ድኆች ነበሩ፡፡ በዚያ ላይ በልጅነቱ አባቱ በመሞቱ ከእናቱና ከአንዲት እህቱ ጋር በረኃብ ሊያልቁ ሆነ፡፡ ሕጻኑ ኤዺፋንዮስ በአህያው እንዳይሠራ አህያው ክፉ ነበርና በእናቱ ምክር ሊሸጠው ገበያ አወጣው፡፡ ሊሸጠውም ከአህያው ጋራ ሲጓዝ ፊላታዎስ ከሚባል ጻዲቅ ክርስቲያን ጋር ተገናኘ፡፡ ፊላታዎስም ሊገዛው ፈልጎ ለግዢ ሲደራደሩ አህያው የኤዺፋንዮስን ኩላሊቱን ረግጦት ለሞት አደረሰው፡፡ በዚህ ጊዜ አብሮት ያለው ጻድቁ ክርስቲያን ፊላታዎስ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ብሎ በትእምርተ መስቀል አማትቦ በቅፅበት አዳነው፡፡ አህያውንም "ስለ እኛ በተሰቀለው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ትሞት ዘንድ ይገባሃል" ብሎ በቃሉ እንዲሞት ቢያዘው አህያው ወዲያው ሞተ፡፡ ኤዺፋንዮስም እነዚህን አስገራሚ ሁለት ተአምራት ካየ በኀላ ጻድቁን ክርስቲያን "በስሙ ተአምራት የምታደርግበት የተሰቀለው ኢየሱስ ክርስቶስ ማነው?" አለው፡፡ ፊላታዎስም ክርስቶስን ሰበከለት፣ ኤዺፋንዮስም እያደነቀ ሔደ፡፡
ከወራት በኀላ ሀብታም አይሁዳዊ አጎቱ ወሰደውና ገንዘቡን ሁሉ አውርሶት ስለሞተ ኤዺፋንዮስ ገና በ16 ዓመቱ ባለጠጋ ሆነ፡፡ የኦሪትን ሕግ ሁሉ እየተማረ ቢያድግም ያቺ ገበያ ላይ ያያት ተአምር ግን በልቡ ውስጥ ትመላለስ ነበር፡፡
በአንዲት ዕለትም ስሙ ሉክያኖስ ከሚባል ጻድቅ መነኩሴ ጋር ተገናኘ፡፡ አብረው ሲሔዱም አንድ ነዳይ አገኙና ምጽዋትን ጠየቃቸው፡፡ ጻድቁ ሉክያኖስም ገንዘብ ስለሌው የሚለብሰውን የጸጉር ዐፅፉን አውልቆ ለድኃው መጸወተው፡፡ በዚያን ጊዜ የብርሃን ልብስ ከሰማይ ሲወርድለት መላእክት ሲያለብሱት ኤዺፋንዮስ ተመለከተ፡፡
ይህንንም ድንቅ ነገር ከተመለከተ በኀላ ኤዺፋንዮስ ከመነኩሴው እግር ሥር ሰግዶ ክርስቲያን እንዲያደርገው ለመነው፡፡ መነኩሴውም ወስዶ ለኤጲስቆጶሱ ሰጠውና አስተምሮ አጠመቀው፡፡ መመንኮስም አንደሚፈልግ ቢነግረው "ሀብት ንብረት እያለህ መነኩሴ መሆን አይገባህም" አሉት፡፡ ከዚህ በኀላ ኤዺፋንዮስ እኅቱን አምጥቶ አስጠመቃትና ገንዘቡን ሁሉ ሸጦ ለድኆችና ጦም አዳሪዎች መጸወተው፡፡ በተረፈው ደግሞ ቅዱሳት መጻሕፍትን ገዛ፡፡ ከዚህም በኀላ መነኮሰና ለእርሱም ለእኅቱም ለጥምቀት ምክንያት ወደሆነው ስሙ ሉክያኖስ ወደተባለው መነኮስ ገዳም ገባ፡፡ በዚህም ጊዜ ዕድሜው 16 ብቻ ነበር፡፡
ከዚህም በኀላ ሽማግሌውን አባ ኢላርዮስን አገኘውና ሕግጋትን ሁሉ አስተማረው፡፡ ከዚህም በኀላ መናንያኑ እስኪያደንቁት ድረስ በፍጹም ትጋትና ቅድስና ተጋደለ፡፡ ብዙ አስገራሚ ተአምራትን አደረገ፡፡ ድውያንን ፈወሰ፣ በጸሎቱ ሙታንን አስነሣ፣ ከደረቅ መሬት ላይ ውኃን አፈለቀ፡፡ ያለጊዜውም ዝናም አዘነመ፡፡ ብዙ አይሁዶችንም ተከራክሮና በተአምሩ እያሳመነ አጠመቃቸው፡፡
ከዚህም በኀላ መምህሩ ኢላርዮስ በነገረው ትንቢት መሠረት በቆዽሮስ ደሴት ላይ ዻዻስ ሆኖ ተሾመ፡፡ ብሉይን ከሐዲስ የወሰነ እጅግ ምጡቅ ሊቅ ነውና ብዙ መጻሕፍትን ተረጎመ፡፡ በሺሕ የሚቆጠሩ እጅግ ጠቃሚ ድርሳናትን ደረሰ፡፡ በአፍም በመጽሐፍም ብሎ መናፍቃንንና አይሁድን ምላሽ በማሳጣቱ ቤተ ክርስቲያን "ጠበቃየ" ትለዋለች፡፡ ከደረሳቸው መጻሕፍት መካከል "ሃይማኖተ አበው ዘኤዺፋንዮስ፣ መጽሐፈ ቅዳሴውና አክሲማሮስ (ስነ ፍጥረት የሚተነትን) በዋነኛነት ይጠቀሳሉ፡፡ በተለይም አክሲማሮስ በተሰኘው ድርሰቱ ስነ ፍጥረትን እንዴት አድርጎ እጅግ ጥልቅ በሆነ መንገድ እንዳብራራው በቃላት ለመግለጽም አስቸጋሪ ነው፡፡ እጅግ በጣም የሚደንቅ ነው በእውነት፡፡ እግዚአብሔር ለቅዱሳኑ የሚገልጥላቸውን ሰማያዊ ዕውቀት ከማድነቅ ውጭ ልላ ምን ማለት እንችላለን!!!
ሊቁ ቅዱስ ኤዺፋንዮስ በመልካም እረኝነትና በሚደነቅ ቅድስና ሲያገለግል ኖሮ በ406 ዓ/ም ዐርፏል፡፡ የዕረፍቱን ሁኔታ በተመለከተ ከዮሐንስ አፈወርቅ ጋር የተገናኘ ታሪክ አለው፡፡
በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ዘመን የነበረችው ጨካኟና አረመኔዋ ንግሥት አውዶክሲያ የድሃ ንብረት እየቀማች ተወስድ ስለነበር ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም ዘወትር ይመክራትና ይገሥጻት ነበር፡፡ አንድ ቀን አንዱ ድሃ ሄዶ ለዮሐንስ አፈወርቅ ነግሮት ሄዶ ‹‹የድሃውን ንብረት መልሺለት›› ቢላት እምቢ ስትለው ከቤተ ክርስቲያን እንዳትገባና ከክርስቲያኖችም ህብረት እንዳትቀላቀል አወገዛት፡፡ ‹‹ከግዝትህ ፍታኝ›› ብትለውም ‹‹የድሃውን ገንዘብ ካልመለሽ አልፈታሽም›› ስላላት ‹‹በከንቱ አወገዘኝ አባት ያስተምራል እንጂ እንዲህ አያደርግም›› እያለች ታስወራበት ጀመር፡፡ ለቅዱስ ኤጲፋንዮስም ‹‹ዮሐንስ ያለ አግባብ አውግዞኛልና መጥተህ አስፈታኝ አለዚያ ሃይማኖቴን እቀይራለሁ፣ ቤተ ክርስቲያንንም አቃጥላለሁ›› ብላ ላከችበት፡፡ ቅዱስ ኤጲፋንዮስም ሄዶ ዮሐንስ አፈወርቅን ‹‹ሰይጣን በልቧ አድሮባታል ያሰበችውንም ያስፈጽማታልና ለአገልግሎታችንም እንቅፋት እንዳትሆን ፍታት›› ቢለው ቅዱስ ዮሐንስም እምቢ አለው፡፡ እርሷም በየከተማው እየዞረች ‹‹ተመልከቱ ዮሐንስ ኤጲፋንዮስንም አወገዘው›› እያለች በውሸት ታስወራ ጀመር፡፡ ኤጲፋንዮስም እንዲህ ማለቷን አልሰማም ነበርና ከዮሐንስ ጋር በኋላ ተሰነባብተው ሊለያዩ ሲሉ ዮሐንስ ‹‹ለምን በነገሬ ገባህብኝ›› አለው፡፡ ኤጲፋንዮስም ‹‹አልገባሁም›› ቢለው በንግግር ሳይግባቡ ቀርተው ተጣሉ፡፡ በዚህም ጊዜ ሁለቱም የሚሞቱበት ጊዜና የሚሞቱበት በምን ዓይነት ሁኔታ እንደሆነ ተገልጦላቸው አንዳቸው ለአንዳቸው ትንቢት ተነጋግረዋል፡፡ ዮሐንስ ኤጲፋንዮስን ‹‹ሄደህ ከቤትህ አትገባም ከመንገድ ላይ አንበሳ ሰብሮ ይገድልሃል›› አለው፡፡ ኤጲፋንዮስም ለዮሐንስ ‹‹የእኔን ትላለህ አንተም እንጂ ደግሞ ተግዘህ በከሃዲዮች ተወግዘህ በአንጾኪያ ደሴት ታስረህ ተሠቃይተህ ትሞታለህ›› አለው፡፡ በተነጋገሩትም ትንቢት መሠረት ኤጲፋንዮስ ወደ በዓቱ ሲሄድ አንበሳ ገደለውና የአንበሳ ሆድ መቃብሩ ሆነለት፡፡ ስንክሳሩ ግን በመርከብ ሲሄድ እንዳረፈ ይገልፃል፡፡ ዮሐንስም በግዞት ታስሮ ብዙ ከተሠቃየ በኋላ ግንቦት 12 ቀን ዐረፈ፡፡ ጨካኟና አረመኔዋ ንግሥት አውዶክሲያም ‹‹ዮሐንስ ኤጲፋንዮስን አውግዞት ወደ ሀገሩ አባሮት በመንገድ ላይ እንዲሞት አደረገው›› እያለች በሀሰት አስወርታ የቤተ ክርስቲያን ጠላቶች የሆኑትን ሰዎች ሰብስባ ዮሐንስን እንዲያወግዙት ካደረገች በኋላ በግዞት ታስሮ እንዲኖርና ተሠቃይቶ እንዲሞት አድርጋዋለች፡፡
የቅዱስ ኤዺፋንዮስ ምልጃና በረከቱ በምልጃው በምንታመን በሁላችን ላይ ይደርብን! አሜን!!!
(የግንቦት ወር ስንክሳር፣ የቅዱሳንታሪክ-37-39፣ መዝገበ ታሪክ፣ የዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ጽሑፍ)

Thursday, August 20, 2015

ፖርት ሳይድ ማርያም በግብጽ

ከስዕልዋ ዘይት የሚፈልቅበት ተአምር አድራጊዋ የእመቤታችን ስዕል ፖርት ሳይድ ማርያም በግብጽ; በረከትዋ ይደርብን:: መጋቢ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ




ከእጇ ዘይት የሚፈልቅ የቅድስት ኤልሳቤጥ አስገራሚ ታሪክ

Tuesday, August 18, 2015

አቡነ ሐራ ድንግል ገድል



ከሁሉ አስቀድመን የአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንልጆች የሆን እኛ የክርስቶስ ወገኖች ሰዎች ነገርን ከማብዛት በማሳነስ ነገርን ከማስረዘም በማሳጠር ክቡርና ልኡል ትሩፋቱ ፍፁም ገድሉም ብዙ የሆነ ምስራቃዊ የክብር ኮከብ አርያማዊ የፅድቅ ጸሀይ የኦርቶዶክሳዊ ሀይማኖት ዓምድ የመንፈሳዊ ምግባርማደሪያ የሆነየአባታችን ሐራ ድንግልን ገድሉንና ትሩፋቱን የፅድቁንም ስራ እንጽፍ ዘንድ ህይወትን ሰጪ በሚሆን በባታዊ አድሮ በሚኖር ገዳማዊውን በሚጎበኝ የአለማዊውንም ሰው በደል በመለኮታዊ ስልጣኑ በሚያስተሰርይ በአምላክ ፈቃድ ለመጀመር ተግተን ተመኘን፡፡ ለሁላችንም የጥምቀት ልጆች ከኦሪታዊው ከሙሴና ከወንጌላዊው ከዮሀንስ ጋር አሸናፊ እግዚአብሄርን በቀናች ሀይማኖትና በመልካም ምግባር ካገለገሉት ከጻድቃንና ከመነኮሳትም ጋር ሰማያዊ የነፍስ ደስታ እድልን ያድለን ክብር ምስጋና ለእርሱ ይሁን ለዘላለሙ አሜን፡፡ አቡነ ሐራ ድንግል አስቀድመን በመጻፋችን የጠራነው የዚህ ጻድቅ አባቱና እናቱ በላጉና ምድር ይኖሩ ነበር ፡፡ እርስዋም ከደራ ምድር አንድ ክፍል ናት:: አባቱም ዮሐንስ የሚባል የሬማ ቄስ ነበር:: እናቱም ወለተ ጊዮርጊስ ትባል ነበር ሁለቱምበወገን ከከበሩ ቤተሰቦች ነበሩ እነርሱም ጻድቃንና ደጋግ ሰዎች እግዚአብሄርን የሚፈሩ ነበሩ ከክፋትም ስራም ሁሉ የራቁ ነበሩ በበጎ ምግባርም ሁሉ የጸኑ ነበሩ ሶስት ወንዶች ልጆች ነበሯቸው ከእነርሱም አንዱ የአለም መብራት የኢትዮጵያ ብርሀን ሐራ ድንግል ነበር ይህንም ገድለኛ ልጃቸውን ከመውለዳቸው አስቀድሞ ገንዘባቸውን ለድሆችና ለጦም አዳሪዎች ለባልቴቶችና ለሙት ልጆች ለካህናትና ለምእመናን ለህዝበ ክርስቲያኑ ሁሉ ይሰጡ ነበር :;ይህንም ያደርጉ ነበር ስጡ ይሰጣችኋል ዳግመኛም ለሌለው ይስጥ የሚለውን የወንጌል ቃልና ሌላውም መጽሀፍ ካለህ ስጥ ከሌለህም እዘን የሚለውን ቃል አስበው ነው:: በዚህም ነገር ላይ እንዲህ እያሉ ይጸልዩ ነበር አንተን ደስ የሚያሰኝ ፈቃድህንም ሁሉ የሚያደርግ በደግነቱም ለፍጥረትህም ሁሉ የሚጠቅም ሰሎሞን:-ብልህልጅ አባቱን ደስ ያሰኛል ሰነፍ ልጅ ግን እናቱን ያሳዝናል ብሎ እንደተናገረ የእኛንም ልብ ደስ የሚያሰኝ ጠቃሚ ልጅ ስጠን ጸሎትም እንደሚጠቅም ከቅዱሳት መጻህፍት ምሳሌ አግኝተው ይህን ሁሉ ጸሎት ጸለዩ:: ሀና በአንደኛ መጽሀፈ ነገስት ለሚጸልይ የጸሎትን መልስ ይሰጠዋል የጻድቃኑንም እድሜ ያረዝማል ብላለች ዳዊትም:-66 መዝሙር መንገድህን ለእግዚአብሄር ግለጥ በእርሱ ታመን እርሱም ያደርግልሀል ብሏል፡፡

ከዚህም በኋላ እግዚአብሄር ጽሎታቸውን ልመናቸውንና እንደ ጣፋጭ ዕጣንና እንደ ንጹህ መሥዋዕት በተቀበላቸው ጊዜ በዚያች ዕለት በጋብቻ ስርአት ተገናኙ ሁለቱም በንጽህና ሐብል የታሰሩ ነበሩና ዝሙትንና ሀጢያትንም አያውቁም ነበርና ነገር ግን :-ወንድ ሁሉ በሚስቱ ጸንቶይኑር ሚስትም በባልዋ ጸንታ ትኑር በሚለው የመጽሀፍ ስርዓት እርስ በርሳቸው ይጠባበቁ ነበር፡፡ በዚያችም በተገናኙባት እለትም ወለተ ጊዮርጊስ መልካም ስራው እንደጸሀይ አወጣጥ የሚያበራ የኢትዮጵያ ብርሀን ሐራ ድንግልን ጸነሰችው ከጸነሰችውም በኋላ በዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በንጉስ አጽናፍ ሰገድ ወለደችው:እርሱንም በወለደች ጊዜ እጅግ ደስ አላት አባቱና ዘመዶቹም እጅግ ደስ አላቸው ሀሴትም አደረጉ ሃጥአንን በእግዚአብሄር ዘንድ በጸሎቱ የሚያስምራቸውና ዳዊት በ111ኛው መዝሙሩ :-መልካም ዛፍ መልካም ፍሬ ያፈራል ክፉ ዛፍ ግን ክፉ ፍሬን ያፈራል ዛፍ ከፍሬው ይታወቃልና ብሎ እንደ ተናገረ ወላጆቹን በምእመናን ሁሉ አንደበት የሚያመሰግናቸው የተባረክ ልጅ ተወልዶላቸዋልና በአርባኛው ቀንም ይህን ልጃቸውን ሐዋርያት በኢየሩሳሌም አንድ ሆነ እንደ አዘዙትሥርዓት የዚያች ቤተክርስቲያን ወሰዱት ያንጊዜም በጥምቀት ፀጋ የወለደው ስሙን ሐራ ድንግል ብሎ ሰየመው:: ከዝያም በኋላ አባቱና እናቱ ተቅብለው ወደ ቤታቸው ወሰዱት በህግና በሥርዓትም አሳደጉት የሰሎሞንን ቃል አውቀው ቅዱሳት መጽሀፍትን ብሉይ እስክ ሀዲስ የዳዊትንም መዝሙር ለሚያስተምር መምህር ሰጡት ያም ህፃን ቅዱሳት መጽሀፍትን ይሚሉትን አውቆ ስላስተዋለ እስኪያድግና አቅመ አዳም እስኪደርስ ድረስ ለትምህርት የተጋ ሆነ በመምህሩ ፈቃድ የድቁና ሹመት ከጳጳሱ ይቀበል ዘንድ በዚያ ወራት ሄደ የድቁና ሹመትም ተቀብሎ በደስታና በሀሴት በሰላምና በህይወት ወደ መንደሩ ተመልሶ ገባ
የጥበባት ባህርና የቋንቋ ባለቤት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም የትምህርት ምንጭ ለሆነው ለደቀ መዝሙሩ ለጢሞቴዎስ በላከው መልእክቱ:-የዲያቆናት ንጹሓን ይሁኑ ለጸሎትም የነቁና የተጉ ይሁኑ ብሎ እንደተናገረ በንጽህናና በቅድስና በጸሎትና በጭምተኝነት በፍቅርና በትህትና እግዚአብሄርን ያገለገለው ጀመር፡፡ አባታችን ሐራ ድንግልም በእነዚህ የብሉይና የሐዲስ መጽሀፍት ቃላት ጸንቶ ሲኖር ክቡር ዳዊት 88 መዝሙር ሞትን ሳያይ በህይወት የሚኖር ማነው? ዳግመኛም 143 መዝሙር ሰውስ ከንቱ ይመስላል ዘመኑም እንደ ጥላ ያልፋል ብሎ እንደተናገረ:: በአቤልና በሴት ከተጀመረው ከዚህ ሞት የሚድን ስለሌለ አባቱና እናቱ ከዚህ ዓለም ድካም ዓረፉ ወደ ዘላለም ህይወትም ሄዱ አባታችን ሐራ ድንግልም በወላጆቹ ሞት የመረረ ልቅሶን አለቀሰ አዘነም፡፡ አባታችን ሐራ ድንግልም ከአባቱና እናቱ ሞት በኋላ ሬማ በምትባል ደሴት እየተመለለሰ በቤታቸው ውስጥ ለጥቂት ወራት ተቀመጠ ከሬማም ወደ ዘጌ ይሄድ ነበር ከዘጌም ወደዚያው ወደ ሬማ ይመለስ ነበር እንደዚህ አለም ሰዎችም ሚስት ሊያገባ አልወደደም ነገር ግን በድንግልና ኖረ::ልብሰ ምንኩስናም ሳይለብስ አርባ ዓመት ሆነው ከዚህም በኋላ በጽኑዕ ደዌ ታመመ የንዳድ በሽታም ያዛው ክደዌው ጽናት የተነሳም በስጋውና በነፍሱ ከእግዚአብሄር ፈውስን ያገኝ ዘንድ ልብሰ ምንኩስናን ለመልበስ ወደደ መዓዛ ድንግል የተባለውን የሬማ መምህር ልብሰ ምንኩስናን ይሰጠው ዘንድ ለምኖ ነገረው እርሱም ልብሰ ምንኩስናን አለበሰው ለወጣንያን ለማእከላውያንና ለፍፁማንም መነክኮሳት የሚገባቸውን የምንኩስናን ህግ ሁሉ ሰጠው ከዚህም በኋላ እግዚአብሄርን ከሞት ስላዳነው ከደዌው ተፈወሰ::ከዚህም በኋላ የቅስና ማረግን ከዚያ ጳጳስ ከተቀበለ በኋላ በዚሁ ደስ እያለውናሀሴት እያደረገ ከመንገዱ ተመልሶ ወደ ቤቱ ገባ እግዚአብሄር እርሱ የተመኘውንና የፈለገውን አድርጎለታልና በዚህ ሁኔታ እያለ ወደ አለም መመልስ አልፈለገም ተመልሶ ከዘመዶቹና ከሀገሩ ሰዎች ተሰውሮ ወደ ሸዋ ሊሄድ ወደደ ወደ አሰበበት ለምድረስ በመንገድ ላ ሲሄ ዘመዶቹ ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ያገኙትና ከ እነርሱም አንዱ የወንድሙ ልጅና የልቡ ወዳጅ ስለንበር ሁሉንም ያነሳሳቸው አርከ መርዓዊ ይባላል እነርሱም ግራርያ በተባለ ሀገር ያዙትና ወዴት ትሄዳለህ አሉት እባክህ ወደ ሀገርህ ተመለስ ለሀገርና ለዘመዶችህ የሚቀርብ ገዳም እንፈልግልሃለን አንተም እንዳዘዝከን እንደርጋለን እንጂ ከፈቃድህ አንወጣም አንተ አባታችን ጽድቀህ እኛንም በጽድቅህ እንድታጸድቀን ትሉ ከማያንቀላፋ እሳቱም ከማይጠፋ ከገሀነም እሳት እንድታድነንም እንወዳለንና እንደማንሸነግልህ ም በአምላካችን በ እግዚአብሄር ስም እንምልልሀለን ይሄን ቃላቸውን ከሰማ በኋላ እሺ አላቸው::እንሱም 7 ምሳሮች ይዘው ከቁስቋም ጀምረው ገዳም እስካደረገው ድረስ መንገዱን ይጠርጉ ዛፎችንም ይቆርጡ ጀመሩ ወደ ገዳሙ በደረሱ ጊዜ ማረፊያዬ ይህች ናት በድካሜም ጊዜ የማርፍበት ትንሽ ቤት ስሩልኝ እንጂ ከዚህ ወደ ሌላ አትሂዱ እስከሞቴ ድረስ በ እርሷ እንድኖር እግዚአብሄር አዞኛልናየስጋዬንም በድን እስከ ሙታን ትንሳኤ ድረስ በውስጧ ይኖራል አላቸው በዚያችም ቀን ዕንጨቱን ቆርጠው መሬቱን ቆፍረው አጥር አጠሩለት እርሱንም በገዳሙ ትተውት ወደ ቤታቸው ሄዱ አባታችን ሐራ ድንግልም በተራበ ጊዜ እንጀራ አይበላ ነበር ጥቂት ምስር አተርና አደንጓሬ ይበላ ነበር ብትንሽ ጽዋ መክደኛ ጽዋ ሰፍሮ በትንሽ ድስት ይቀቅለው ነበር ያም በጽዋው መክደኛ ሰባት መስፈሪያ ነበር በሶስት አንድ ቀን ይመገበው ነበር ከምድርም ፍራፍሬም በበላ ጊዜ እሼ የሚባል ፍሬ ይመገብ ነበር ከምናኔው በኋላ ግን ከውሃ በቀር ሌሎች መጠጦችን አልጠጣም ነበር::ያንጊዜም ብዙዎች አራዊት አንበሶች ነብሮች ዝሆኖች ተኩላዎችና ጅቦች የዱር እንስሳዎች ያስፈራሩት ዘን ወደ እርሱ መጡ እርሱ ግን እግዚአብሄር ከእርሱ ጋር ስለነበር ከፊቱ እንዲሸሹ አስፈራርቶ አስደነገጣቸው እንጂ አልፈራቸውም ይህም ነገር ከሆነም በኋላ የቅል ዓይነት ተክልና ወይን ሎሚና ኮክ ተከለ እነዚህንም ተክሎች ከሩቅ ወንዝ ውሃ በእጁ ቀድቶ በትከሻው ተሸክሞ ያጠጣቸው ነበር መንገዱም ሩቅ ስለነበር አባታችን ሐራ ድንግል እንዲህ ብሎ ጸለየ ከ እናቴ ማህጸን ያወጣሀኝ እስከ እዚች ሰአት ያደረስከኝ ፈጣሪዬ እግዚአብሄር ሆይ እስራኤል ከግብጽ በወጡ ጊዜ ሙሴ ከዓለት ውሃን እንዳወጣ ከዚህ ምድር ውሃን አውጣ ዘንድ ጸሎቴንና ልመናዬን ስማኝ ይህን ብሎ በሁለት ረድፎች ምድሩን ቆፈረ በመስቀልም ምልክት ባረካቸው ወዲያውኑ ከሁለቱም ረድፎች ውሃዎች ፈሰሱ በፈለቁት ውሃዎች በየጊዜው እንዲያፈሩና ሊያዩት ወደ እርሱ ለሚመጡት ሰዎች ምግብ እንዲሆኑ እንዚህን ተክሎች አጠጣቸው ለሚልውምኑትም ድሆችም ቅጠሉ ፍሬ ያፈራውን አይነት በገበያ አሽጦምጽዋት ይሰጣቸው ነበር::በዚያ ጊዜም የበጎ ነገር ጠላት ሰይጣን በሴት አምሳል በንጭ ሀር በወርቅበብር በጉትቻዎችና በቀለበቶች አጊጦ መጣና እንዲህ አለው ለምን ብቻህን ትኖራለህ ? ሁለት ሆነው መኖር ሰዎች ልማዳቸው ነውና ከ እኔ ጋር ብትኖር አይሻልህምን? አባታችንም ትቆጣ የ እግዚአብሄርን ቃል በሚጸልይበት በጠበል እቃ የነበረውን ውሃ በሰይጣ ረጨበት ሰይጣንም ድንግጦ ሸሸ በባህርም ስጠመ አባታችን እስኪሰማ ድረስ ባህሩን አወከው አባታችንን ለማሳት ሰባት ጊዜ መጣ ነገር ግን በ እግዚአብሄር ሀይል ድል ተደረገ::
አንዲት ሚዳቆ ነብር እያባረራት መጣች ወደ አባታችን ሐራ ድንግል ቤትም ገብታ በእርሱ ተመአጥና ከ እግሩ በታች ተጋደመች አባታችንም ወደ ፈጣሪው ወደ እግዚአብሄር እየጸለየና እየለመነ ተቀምጦ ነበር ያቺን ሚዳቆ የሚያባርራት ነብርም መጣ አባታችን ወዳለበት ደርሶ በደጁ ቆመ አባታችንንም ባየው ጊዜ ጊዜው ቀን ስለ ነበረ ፈርቶ ወደ ውስጥ አልገባም ያም ነብር ተቆጥቶ በዚያው ቦታ ተፍገመገመ አባታችን ነብሩን ገድለህ ትበላት ዘንድ እግዚአብሄር አልሰጠህም ነብሩም ይህን ነገር ከአባታችን ቃል ሰምቶ ሳይገድላት ሄደ በዚያች ሌሊት በእርሱ ዘንድ አደረች በማግስቱም ከቤቱ ወጥታ በደጅ ስትመላለስ አባታችን ባያት ጊዜ እንዲህ ብሎ አሰናበታት ከቦታሽ አባርሮ ያሳደደሽ ወደ እኔም ያደረሰሽ ያ ነብር ትናንት ስለሄደ ወደ ቦታሽ ሂጂ ይህንም ሰምታ ወደ ቦታዋ ተመለሰች:;
አባታችንም ሁለት ደቀመዝሙሮች ነበሩት ወንዱ እሱን ያዘዘውን የሚፈጽም ነበር ተስፋዬ እና አመተ እግዚእ አለምን ንቃወደ ገዳብ የገባች ነበረች እርሳውም ከአባታችን ቤት ትንሽ በሚርቀው ቤት ተቀምጣ ከምናኔዋ ጀሮ በሞት እስከ ተለየች ድረስ ረዳትና አገልጋይ ሆና ራሷን ለአባታችን ሰጠች እርስዋም በስጋ ዝምድና ከሚቀርቡት አንድዋ ነበረች እርሷም በአገልግሎቷና በታዛዥነቷ እንደዚህ ይሁን የሚለውን ፈቃዱን በመፈጸም እጅግ ደስ አሰኘችው በምግባርዋ ደግ በነገሯም እውነተኛ በልቡናዋም ብልህ ነበረች::
ከዚህም በሃላየአንዲት ታቅ ሴት አሽከሮች ወደ አባታችን መጡ ሊጣሉትም ወደቤቱ ገቡ አንተ ከንጉሱ ፈቃድ ወጥተህ በአመጽ የምትኖር የንጉስ ከዳተኛ አይደለህምን እያልይ ፈጽመው ሰደቡት ከገቡበትም ወጥተው የ አባታችን የወይን ዘለላም ምንም ሳያስቀሩለት ቆረጠው ወሰዱ አባታችንም ምንም አልተናገራቸውም የወሰዱትንም ወይን ለእመቤታቸው የወይኑ ዘለላ ሰጡ እመቤታቸውም ይሀ ወይን ከማን አመጣችሁ ሐራ ድንግል ከሚባለው መንኮስ ነው አላት አንዱንም የሆድ በሽታ ይዞ አንጀቱን ቆረጠው እመቤታቸውም እነዚህን አንተን ያስቀየሙ የበደሉና ማርልኝ ብላ አሽከሮችን ላከች እግዚአብሄር ይቅር የሚላቸውና በደላቸውና የሚተውላቸው ከሆነ ይቅር እላቸዋለሁ አሽከርም በተመለሰ ጊዜ ሆዱን የቆረጠው ሞተ ጻድቁ አባታችንን ስለተሳደበ እግዚአብሄር ትቆጥቶታልና ይህ የሰሙትን የተደረገውን ባዩ ጊዜ አደነቁ:: ይህ ድንቅ ነገር ከሆነ ረዥም ወራት በሃላ አመተ ወልድ የተባለች አንዲት ሴት ታመመች እርስዋም በዚሁ በሽታ ሞተች መላእክተም ሞትም ነፍስ ወሰዱ ያችንም ነፍስ እያጣደፉና እያዳፉ ወደ ፈጣሪዋ አደረሳት በዚች ሰአትም አባታችን ሐራ ድንግል ወደ ፈጣሪው ወደ እግዚአብሄር እንዲህ እያለ ጸለየ አለቀሰም ይህችን ዛሬ የሞተችውን ሥጋዋም በመሬት ተጥሎ በነፍስዋ ወደ አንተ የመጣችውን ማርልኝና አንሳልኝ ነፍሴንና ስጋዬን በአንተ ላይ ጥያለሁ ብላ በእኔ ላይ እንደ ተማጠነች አቤቱ አንተ ራስህ ታውቃለህና በህይወት ሳለችም እንዳገለገችኝ አንተ ራስህ ታውቃለህ አባታችንም ይህን ጸሎት ጸልዮ ዝም አለ እግዚአብሄርም ይህችን ነፍስ ለምን ወደ እኔ አመጣችሃት የሕራ ድንግል አደለች የ እርሱ ስለሆነች ወደ እርሱ መልሳት እርሳም በስማይ ሳለች ከፈጣሪዋ አንደበት ከሰማች በኋላ የመላእክት ቅዱስ ገብርኤልን ለወዳጄ ሐራ ድንግል ሶስት ጊዜ እንዲህ ብለህ አዋጅ ንገር ሲለ ከዚያ ከፈጣሪ አንደበት ሰማች:: ሐራ ድንግል ሆይ በ እጅህ የተባረከውንና በቃልህ የተጽናናውን ስምህን የጠራውንና መታሰቢያህን ያደረገውን ለተራቡትም ለተጠሙትም እህልና ውሃ በመስጠት በዓልህን ያከበረውን ሀጢአተኛና በደለኛ ሳለም በጸሎትህና በቃል ኪዳንህ የታመነውን የገድልህንም መጽሀፍ ያጻፈውን ያነበበውንና የተረጎመውን የሰማውንና ለሰዎች ያሰማውን አጽምህንም እየጠበቀ በገዳምህ የተቀመጠውን አንተን ወድዶ ከሩቅ ወይም ከቅርብ ሀገር በመምጣት ገዳምህን የጎበኘውን ወንድ ልጁንና ሴት ልጁንም በስምህ የጠራውን እነዚህ ሁሉ በየወገናቸው ከስጋና ከነፍስ ባርነት ነጻ የወጡ ይሆኑ ዘንድ እስከ ሰባት ትውልድ ምሬልሃለሁ አንተ አገልግለሃልና ከህፃንነትህም ጀምረህ እስከዚች ሰአት ፈቃዴን ፈጽመሃልና:: በሞት ከሥጋዋ የተለየች ያች ነፍስም ይህን ነገር በሰማች በኋላ ከሰማይ ተመለሰች ከሥጋዋ ጋር ተዋህዳ በአባታችን ጸሎት ተነሳች ለወዳጄ ሐራ ድንግል ሂድና አዋጅ ንገር ብሎ መላኩ ገብርኤልን ሲያዝዘውከ እግዚአብሄር የሰማችውን ቃል ኪዳን ለሰዋች ተናገርች አባታችን ሐራ ድንግልም በጸጋ አወቀ የእግዚአብሄር ምስጢር ባየችው በዚች ሴት መነሳት ደስ አለው::እግዚአብሄርም ለአባታችን ሁለት ቃል ኪዳን ሰጠው አንደኛው ያቺ ሴት ናት ሁለተኛውም ከዚህ አለም በሞት ተለይቶ ወደ ዘላአለም ህይወት በሄደ ጊዜ እግዚአብሄር የሰጠው ነው:: የአባታችን ሐራ ድንግልም የእረፍቱ ቀን በደረሰ ጊዜ እግዚአብሄር የምህረትና የይቅርታ ቃል ኪዳንን ይሰጠው ዘንድ ከሰማይወደ እርሱ መጥቶ ወዳጄ ሐራ ድንግል ሆይ ስለ እኔ ብዙ አመታትን ደክመሃል እኔም እንዲህ ብዬ ቃልኪዳ እስትሃለሁ:: ሐራ ድንግል ሆይ በ እጅህ የተባረከውንና በቃልህ የተጽናናውን ስምህን የጠራውንና መታሰቢያህን ያደረገውን ለተራቡትም ለተጠሙትም እህልና ውሃ በመስጠት በዓልህን ያከበረውን ሀጢአተኛና በደለኛ ሳለም በጸሎትህና በቃል ኪዳንህ የታመነውን የገድልህንም መጽሀፍ ያጻፈውን ያነበበውንና የተረጎመውን የሰማውንና ለሰዎች ያሰማውን አጽምህንም እየጠበቀ በገዳምህ የተቀመጠውን አንተን ወድዶ ከሩቅ ወይም ከቅርብ ሀገር በመምጣት ገዳምህን የጎበኘውን ወንድ ልጁንና ሴት ልጁንም በስምህ የጠራውን እነዚህ ሁሉ በየወገናቸው ከስጋና ከነፍስ ባርነት ነጻ የወጡ ይሆኑ ዘንድ እስከ ሰባት ትውልድ ምሬልሃለሁ አንተ አገልግለሃልና ከህፃንነትህም ጀምረህ እስከዚች ሰአት ፈቃዴን ፈጽመሃልና::
አባታችን ሀራ ድንግል ይህን ቃል በሰማ ጊዜ እግዚአብሄርን ሲያመሰግን እንዲህ አለ አምላኬ ሆይ ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ ቅዱስ ስምህንም ለዘላለም አከብራለሁ ሁልጊዜ አመሰግንሃለሁ ስምህንም ለዘላለም ዓለም አከብራለሁ ደግ ወይም ክፉ ቢሆን በእኔ የተማጠነ ሰው ሁይድን ዘንድ ይህን ቃል ኪዳን ሰጥተሀኛል እግዚአብሄርም ይህን ምስጋና ከእርሱ ከተቀበለ በኋላ ከእርሱ ዘንድ ሄደ:: ገዳሙንም እንዲህ እያለ ባረካት የአብና የወልድ የመንፈስ ቅዱስም በረከት በገዳሜና ስሜን በሚተሩ ሁሉ ላይ ይደር አምላክን በወለደች የ እመቤታችን የማርያም በረከትም በገዳሜና እኔን በሚወድዱ ሁሉ ላይ ይደር የሚካኤልና የገብርኤል በረከት የማያንቀላፉ ትጉሃን ዝም የማይሉና አመስጋኞች የሆኑ የሱራፍኤልና የኪሩቤል በረከት በገዳሜና በእኔ በሚማጸኑ ሁሉ ላይ ይደር የ እስጢፋኖስ የጊዮርጊስ የመርቆርዮስ የፋሲለደስ የቴዎድሮስና የገላውዴዎስ የድል አድራጊዎች ሰማእታት ሁሉ በረከት በገዳሜና ፈቃዴን በሚፈጽሙት ሁሉ ላይ ይደር የ አባታችን አቡነተክለሀይማኖትና የ አባታችን አዎስጣቴዎስ የ አባታችን የገብረ መንፈስ ቅዱስና በኢትዮጵያ ውስጥ በገዳማትና በአድባራት በደሴቶችም የሚኖሩት ሁሉ በረከት በገዳሜና በውስጥዋ ሆነው አስከሬኔን በሚጠብቋት ሁሉ ላይ ይደር የሀይማኖት አምድና የቸርነት መዝገብ የሆነው እንደ መላእክትም በንጽህና የተሸለመው አባታችን ሐራ ድንግል ይህን ቃለ ቡራኬ ከተናገረ በኋላ በኢያቄምና በሐና በፋሲለደስና በገላውዴዎስ በፊቅጦርም በዓል ጥር አስራ አንድ ቀን ከዚህ ከሀላፊው ዓለም ድካም አረፈ:: በአሉም ጥር 11 ቀን በታላቅ ድምቀት በባህርዳር ይከበራል፡፡
ምንጭ ገድለ አቡነ ሐራ ድንግል ጽሎቱና በረከቱ ከሁላችን ከህዝበ ክርስቲያን ጋር ይኑር ለዘለዓለሙ አሜን!

Tuesday, August 11, 2015

ጉዞ ከፕሮቴስታንት ወደ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ (ምስክርነት)

እህታችን የፕሮቴስታንትን ድርጅት ሃይማኖቷ እንዲሆን እና ድርጅቱን እንድትከተል የሆነበት ምክንያቱ እንዲህ ነው….. በእንጀራ አባቷ ጓደኛ ምክንያት በመታለል ሲሆን የኦርቶዶክስ ሃይማኖቷን እንድትክድ እና ወደ ፕሮቴስታንት ድርጅት እንድትቀላቀል፤ የፈለገችውን ገንዘብ ያህል እንደሚሰጧት፤ ልብስ፤ ጫማ፤ ትምህርቷን በሰፊው እየከፈሉ ሊያስተምሯት ቃል ገብተው ነበር። እንደወሰዷትም የኑፋቄን ትምህርት ለሦስት አመታት በተከታታይ አስተማሯት፤ ገንዘብም ሰጧት፤ ማህተቧን ከአንገቷ በጥሳ እንድትጥል እና እንድትረግጥ አደረጉ….መላእክትን እንዳትፈራ እንደተራ ነገር እንድትቆጥር አደረጉ፤ ቅዱሳንን ማቃለል ሥራየ ብላ እንድትይዝ አደረጉ፤ እመቤታችንን መዝለፍን አስተማሯት……እንደ ልጅቱ አገላለጽ ወይም በአንደበቷ እንደመሰከረችው ፓስተር ተብየዎች የፕሮቴስታንትን ድርጅት የሚከተሉ ወጣቶች እና እሷን ጭምር ትዳር ከመያዛችሁ በፊት ሴክስ አርት ስለሆነ ኑና እናስተምራችሁ አያሉ ያስቸግሯቸው እንደነበር እና ሌሎችም የተደበቁ የተሐድሶ አጀንዳዎችን በይፋ ነገረችን ….ያሳዝናል። ከእኛ ወገን መስለው ያሉ ነገር ግን ልባቸው መናፍቅ የሆኑ ስንቶችን ዘረዘረቻቸው……..ብቻ የአቡነ ተክለሃይማኖት አምላክ ይጠብቀን…..አጽራረ ቤተክርስቲያንን ያስታግስልን አሜን። መረጃዎችን ለወደፊቱ ለሚከተለው ክፍል እንደምትሰጥ ቃል ገብታለች። እኛም ለመስማትም ለማየትም እንፈልጋለን እንጠብቃለን። የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር ቤተክርስቲያናችንን ይጠብቅልን አሜን።
እግዚአብሔር ፈቅዶ ከዚህች የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ የነበረች እህት ጋር ለተወሰነ ቀናት ተነጋግሬ፤ ስህተቷን አምና ወደ ቀደመችው እና ትክክለኛ ሃይማኖቷ እንድትመለስ ምክንያት ብሆንም ይህን ላደረገ የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይገባዋል። ምስክርነቷን ከተጠመቀች በኋላ ነሐሴ 3 ቀን 2007 ዓ.ም ጎንደር አደባባይ አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን ሰጥታለች።

ተአምር በ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ከርስቲያን /ሽሬ/

Monday, August 3, 2015

አቡነ ዳንኤል ዘገዳመ አስቄጥስ

ግንቦት 8-ዕረፍቱ ለአቡነ ዳንኤል ዘገዳመ አስቄጥስ
አቦ ገድሉ ከማር የሚጣፍጠውን የዚህን ታላቅ ጻድቅ ታሪክ ያንብቡና ነፍስዎትን እርክት ያድርጉ!
አቡነ ዳንኤል በመቃርስ ገዳም በደብረ ሲሐት ይኖር የነበረ ሲሆን እርሱም እጅግ ገድለኛ አባት ነው፡፡ 40 ዓመት በአስቄጥስ ገዳም ሲኖር ከቅጠል በቀር ተመግቦ አያውቅም፡፡ በአስቄጥስ ገዳም ዜናው ሁሉ በዓለም በተሰማ ጊዜ የነገሥታት ልጆችም ወደ እርሱ እየመጡ እየተባረኩ ይሄዱ ነበር፣ ግማሾቹም በዚያው ይመነኩሱ ነበር፡፡ ይህም አባ ዳንኤል ስሟን እንጣልዮስ አስብላ የነበረች ንግሥት የነበረችውን ቅድስት በጥሪቃን የገነዛት ነው፡፡ እርሷም ወንድ የነበረች ሲሆን ይህም የታወቀው ከሞተች በኋላ ነው፡፡ አውሎጊስ የሚባለውን የወፍጮ ድንጋይ እየወቀረ በመሸጥ ለድኆች የሚመጸውትን ጻድቅ ሰው ዋስ እሆነዋለሁ በማለት ከእግዚአብሔር ዘንድ ለምኖ ሥልጣንና ብዙ ወርቅ እንዲያገኝ ያደረገው ይህ አባ ዳንኤል ነው፡፡ በኋላም አውሎጊስ ሀብቱና ንብረቱ ከእግዚአብሔር የሚያርቀው ቢሆን አባ ዳንኤል በጸሎቱ መልሶ ሀብቱን እንዲያጣ አድርጎታል፡፡ አውሎጊስ የሚባል ጻድቅ የወፍጮ ድንጋይ እየወቀረ (እየጠረበ) በመሸት የሚየገኘውን ለድኆችና ጦም አዳሪዎች ይመጸውት ነበር፡፡ አባ ዳንኤልም የአውሎጊስን መልካም ሥራ ተመልክቶ እጅግ ደስ ብሎት ለአውሎጊስ የሀብቱን መጠን እንዲጨምርለትና ይበልጥ እንዲመጸውት በማሰብ ወደ እግዚአብሔር በጸሎት አሳሰበ፡፡ ለአውሎጊስም ዋስ ሆነውና ሀብቱ ተጨመረለት፡፡ አንድ ቀን የሚወቅረውን ድንጋይ ሲፈቅል በሸክላ ዕቃ የተደፈነ ሙሉ ወርቅ አገኘ፡፡ ወደ ቁስጥንጥንያም ከተማ ሄዶ ለንጉሡ አስረከበና የንጉሡ የሠራዊት አለቃ ሆኖ ተሾመ፡፡ ከተሾመም በኋላ የቀድሞውን የጽድቅ ሥራውን ተወ፡፡ አባ ዳንኤልም ስለ እርሱ ሰምቶ ሊያየው ቢሄድ በፈረስ ላይ ተቀምጦ በሠራዊት ታጅቦ በትዕቢት ተመልቶ አገኘው፡፡ ክፉ የትዕቢት መንፈስ አድሮበት ነበር፡፡ አባ ዳንኤልም አውሎጊስ ሀብት እንዲያገኝ በመለመኑ አዘነ፡፡ በሌሊትም የአውሎጊስ ነፍስ በእርሱ ምክንያት እንደጠፋች ራሱ አባ ዳንኤልም ሲሰቀልና እመቤታችን ስለ እርሱ ስትማልድ ራእይ አየ፡፡ ከእንቅልፉም በቃ ጊዜ የአውሎጊስ ሀብት እንዲጠፋና ወደ ቀደመ ግብሩ እንዲመለስ በጾም ጸሎት ሱባኤ ያዘ፡፡ መልአክም ተገልጦለት በእግዚአብሐር የፍርድ ሂደት ውስጥ ጣልቃ በመግባቱ ከገሠጸው በኋላ አውሎጊስም ምሕረት እንደሚያገኝ ነገረው፡፡ አውሎጊስን የሾሸመው ንጉሥም ሞተና ሌላ ንጉሥ ነገሠ፡፡ አውለጊስንም ንብረቱን ሁሉ ቀምቶ ነፍሱንም ለመግደል አሳደደው፡፡

አውሎጊስም ነፍሱን ለማዳን ሽሽቶ ወደ ሀገሩ በመግባት የቀድሞ ሥራውን መሥራት ጀመረ፡፡ ነዳያንንም እንደዱሮም መመገብ ጀመረ፡፡ አባ ዳንኤል ከታለቁ ጻድቅ ንጉሥ ከቅዱስ አኖሬዎስ ጋር የተገናኘ ታሪክ አለው፡፡ ይኸውም አባ ዳንኤል 40 ዓመት ሙሉ በአስቄጥስ ገዳም ሲኖር ከቅጠል በቀር ተመግቦ አያውቅም ነበርና ከጽድቁና ከብቃቱ የተነሣ ከብዙ ዘመን በኋላ የመመካት ክፉ ሀሳብ መጣበት፡፡ ‹‹በገዳም ውስጥ እንደእኔ ትርሕምትን ገንዘብ ያደረገ ይኖር ይሆን?›› ብሎም አሰበ፡፡ ሰውን ወዳድ የሆነ ጌታችንም ይህን ክፉ ሀሳቡን ሊያርቅለት ሽቶ ብርሃናዊ መልአኩን ላከለት፡፡ መልአኩም አባ ዳንኤልን ስለ ትምክህቱ ቢቆጣውም አባ ዳንኤል መልአኩን መልሶ ‹‹ጌታዬ ከእኔ የሚሻል ካለ ንገረኝ፣ ወደ እርሱ ሄጄ አየው ዘንድ እወዳለሁ፣ በመመካቴም ወደ ፈጣሪዬ በልመና እመለስ ዘንድ›› አለው፡፡ መልአኩም ‹‹እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው የሮሜና የቁስጥንጥንያ ንጉሥ አኖሬዎስ በመንግሥተ ሰማያት ባልንጀራህ ነው›› አለው፡፡ ‹‹ንጉሥ አኖሬዎስም የመነኮሳትን ሥራዎች ሁሉ ስለሚሠራ ከልብሰ መንግሥቱ ሥር በሥጋው ላይ ማቅ ይለብስ ነበር›› ተብሎ በስንክሳሩ ላይ የተጻፈለት ጻድቅ ንጉሥ ሲሆን ሰማያውያን የሆኑ ቅዱሳን መላእክትም ቅድስናውን የመሰከሩለት በንግሥና ያለ ታላቅ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነው፡፡ አባ ዳንኤልም ይህ በሰማ ጊዜ መሬት ላይ ወድቆ በራሱም ላይ አመድ ነስንሶ የዚህን የሮም ንጉሥ አኖሬዎስን ግብር ያሳየው ዘንድ ጌታችንን ለመነ፡፡ ደመናም መጥታ ነጥቃ ወሰደችውና ንጉሥ አኖሬዎስ ደጅ አደረሰቸውና ንጉሡን በዙፋኑ ላይ ሆኖ ባየው ጊዜ ከግርማው የተነሣ አይቶት በታላቅ ፍርሃት ውስጥ ሆኖ ከእግሩም በታች ሰገደለትና አኗኗሩንም ይነግረው ዘንድ በጌታችን ስም አማፀነው፡፡ ንጉሥ አኖሬዎስም ሰሌን በመታታት በእጅ ሥራው ደክሞ ከሚያገኘው በቀር ምንም ሳይበላና ሳይለብስ 40 ዓመት እንደሆነው፣ ሰሌን ታቶ ሸጦ ካገኘውም ውስጥ ከዕለት ምግቡ መግዣ የሚተርፈውን ለድኆችና ለጦም አዳሪዎች እንደሚመጸውት፣ ምግቡም እንጀራና ጨው፣ ቅጠል መጻጻም እንደሆነ፣ የማንንም ንብረት ፈጽሞ እንዳልንካ፣ ድንግልናውንም ጠብቆ እንደሚኖር ነገረው፡፡ አባ ዳንኤልም ድጋሚ ከእግሩ ሥር ወድቆ ሰግዶለት ስለ ትምክህቱም ፈጽሞ እያዘኑ ወደ በዓታቱ ተመልሷል፡፡ አባ ዳንኤል አንድ ቀን ከረድኡ ጋር ወደ እስክንድርያ ሲጓዝ ስሙ ምህርካ የሚባል እብድ አገኘ፡፡ ብዙ እብዶችም ይከተሉት ነበር፡፡ እርሱም ለአገሩ ሰዎች ሁሉ በእውነት ያበደ ይመስላቸው ነበር፡፡ አባ ዳንኤልም እጁን ይዞ ወደ ሊቀ ጳጳሳቱ ወስዶ ትሩፋቱን ተጋድሎውን ነገረው፡፡ ከሊቀ ጳጳሳቱም ጋር ሆነው እብዱን ስለራሱ እንዲነግራቸው በእግዚአብሔር ስም ባማሉት ጊዜ ከዝሙት ጦር በመሸሽ ራሱን እብድ እንዳስመሰለ ነገራቸው፡፡
አንድ ቀን አባ ዳንኤል በሌሊት በበረሃ ውስጥ በጨረቃ ብርሃን ሲጓዝ በተራራ ላይ ተቀምጣ ጠጉሯ መላ ሰውነቷን የሸፈናት በዚያም በረሃ ስትኖር በተሰነጠቀ ዓለት ውስጥ 38 ዓመት ብቻዋን ማንም ሳያያት የኖረች ጻድቅ እናት አግኝቶ ምሥጢሯን ሁሉ ነግራዋለች፡፡ እርሷም ቅድስት አመተ ክርስቶስ ናት፡፡ አባ ዳንኤልም 38 ዓመት ሙሉ በዚህ በረሃ ምንም ሰው ሳታይ የኖረችበትን ተገድሎዋን በዝርዝር ነግራቸዋለች፡፡ እርሳቸውም ወደ ገዳማቸው ተመልሰው ለአበ ምኔቱና ለመነኮሳቱ ታሪኳን በመንገር ልብስ ይዘውላት ቢመጡ ዐርፋ አግኝተዋታል፡፡
አባ ዳንኤል የልዮንን የክህደት ደብዳቤ ወታደሮቹ አምጥተው በመነኮሳቱ ፊት ሲያነቡ ደብዳቤውን ተቀብሎ በሕዝቡ ፊት ቀዶታል፡፡ ወታደሮቹም አባ ዳንኤልንደብደበው ከገዳሙም አሳደውታል፡፡ ብዙ ሥቃይም አድርሰውበታል፡፡ አባ ዳንኤል በአንዲት ዕለት ከደናል ገዳም ደርሶ ደጁን አንኳኳ፡፡ እነርሱም አባ ዳንኤል መሆኑን ዐውቀው ከፈቱለት፡፡ አንዲት ሴትም ራሷን ዕብድ አስመስላ በደጅ የምትተኛ ሴት ነበረች፡፡ እርሱም ዕብድ መስላ በደጅ ስለተቀበጠችው ሴት አበምነቷን ሲጠይቃት እብድ መሆኗን ነገረችው፡፡ አባ ዳንኤል ግን ዕብድ የመሰለቻቸው ሴት እብድ ሳትሆን በድብቅ በታላቅ ተጋድሎ የምትኖር ቅድስት ሴት መሆኗን ነገራት፡፡ ዕብድ የተባለችውም ሴትም አባ ዳንኤል ምሥጢሯን እንደገለጠባት በስውር ዐውቃ ወዲያው ደብዳቤ ጽፋ ይኸውም ‹‹የተከበራችሁ እኅቶቼ ስላስቀየምኳችሁና ስላሳዘንኳችሁ ይቅር በሉኝ›› ብላ ጽፋ ደብዳቤውን አስቀምጣ ጥላቸው ጠፋች፡፡ እነርሱም ከዚያ በኋላ ዳግመኛ አላዩአትም፡፡ ደናግል ወደሚኖሩበት ገዳም አንድ የወንበዴዎች አለቃ ሰይጣን አነሳስቶት ወደ ገዳሙ በአባ ዳንኤል ተመስሎ ቆቡን ደፍቶ በሩን አንኳኳ፡፡ ደናግላኑም ሊዘርፋቸው መምጣቱን ምንም ባለማወቅ ይልቁንም አባ ዳንኤል መጣ ብለው በሩን ከፈቱለትና አስገቡት፡፡ እግሩንም አጥበው ለበረከት ብለው የእግሮቹን ዕጣቢ በፊታቸው ላይ ረጩት፡፡ ከመካከላቸውም አንዷ ዐይነ ሥውር ነበረችና ዐይኗ ወዲያው በራላት፡፡ በዚህም ደናግሉ እጅግ ተደስተው ‹‹አባ ዳንኤል አንተ ንዑድ ክቡድ ነህ›› ብለው ሰገዱለት፡፡ ይህን ጊዜ የሽፍቶቹ አለቃ በጣም ደንግጦ በመጸጸት ወደ አባ ዳንኤል ዘንድ ሄዶ ያደረገውን ሁሉ በመናገር ንስሓ ገባ፡፡ መንኩሶም በታላቅ ተጋድሎ መኖር ጀመረ፡፡ እርሱም ተአምራት እስከማድረግ ደርሶ በሰላም ዐረፈ፡፡ የአባ ዳንኤልም ተጋድሎና ተአምር ምን ቢጽፉት የሚያልቅ አይደለም፡፡ ዕረፍቱም በደረሰ ጊዜ ጌታችን ታላቅ ቃልኪዳን ሰጥቶት ቅድስት ነፍሱን ወደ እርሱ ወስዷታል፡፡ ዕረፍቱም ግንቦት 8 ቀን በታላቅ ክብር ተፈጽሟል፡፡
በረከቱ ይደርብን! ምልጃው ከይለየን አሜን!!!
ስምን ስም ያነሳዋልና በዚሁ አጋጣሚ ኢትዮጵያዊውን ጻድቅ የትግራይ ገርዓልታውን አቡነ ዳንኤልንም ይወቋቸው፡፡ አቡነ ዳንኤል ዘገርዓልታ አባታቸው መልክአ ሥላሴ እናታቸው ዓመተ ጽዮን ሲባሉ የትውልድ ሀገራቸው ትግራይ ገርዓልታ ነው፡፡ በ7 ዓመታቸው የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ተምረው አጠናቀው በ13 ዓመታቸው መነኮሱ፡፡ ሊቃውንቱ ‹‹ማኅቶተ ገዳም›› እያሉ የሚጠሯቸው ገድለኛ አባት ናቸው፡፡ አስገራሚው ባለ 4 ዓምዱና 40 ያሸበረቁ ሥዕላት ያሉት አስደናቂው ገድላቸው የት እንዳለ አይታወቅም፣ እኛ ሀገር ገድላቸው የለም፡፡ 2ኛውን ገድላቸውን ፖርቹጋሎች ከጠባቂው ገዝተው ወስደው በሀገራቸው አሳትመውታል፡፡ ገድሉን የሸጠው ጠባቂም ሆዱ ተነፍቶ በስብሶ ተልቶ ከቤተ ክርስቲያኑ በራፍ ላይ ወድቆ ሞቷል፡፡ የጻድቁ የዕረፍታቸው ዕለት ኅዳር 6 ቀን ትግራይ በሚገኘው ገዳማቸው በደማቅ ሁኔታ ይከበራል፡፡ ገዳማቸው የሚገኘው እጅግ ከፍተኛ ተራራ ላይ ሲሆን ከላይ ሆነው ወደታች ሲመለከቱ መሬት የሚደረስባት አትመስልም፡፡ እስቲ ከፎቶው ላይ ይመልከቱት!
(ምንጭ፡- የታኅሣሥና የግንቦት ወር ስንክሳር;መለከት 14ኛ ቁ5-1998 ዓ.ም፣ የቅዱሳን ታሪክ-108 &166)

አባ ዮሐንስ ተስፋ ማርያም - የወንቅሸት ቅዱስ ገብርኤል አንድነት ገዳም

አባ ዮሐንስ ተስፋ ማርያም የወንቅሸት ቅዱስ ገብርኤል አንድነት ገዳም አበምኔት፤፤ አባ ዮሃንስ ተስፋ ማርያምን ማነጋገር ከፈለጉ ፡ከዚህ ዌብሳይት ሂደዉ www.wonkshet.com ኮንታክት አስ ከሚለው ላይ ኢሜይል ያርጉልንና ስልካቸውን እንልክልዎታለን፤፤
This is the testimony at Wonkshet Adame Yordanos Kidus Gabriel Monastery by Aba Yohannes Tesfamaryam. For more information, visit www.wonkshet.com

Wednesday, July 22, 2015

አባ ገዐርጊ

ግንቦት 18-ጌታችን መልአኩን ልኮ ‹‹ተጋድሎህ በመጠን ይሁን›› በማለት ተጋደሎውን እንዲቀንስ ያዘዘው የአባ ገዐርጊ ዕረፍት ነው፡፡
ጻድቁ የክርስቲያን ወገን ሲሆን ወላጆቹም ደጋግ ቅዱሳን ጻድቃን ናቸው፡፡ በአደገም ጊዜ የወላጆቹን በጎች የሚጠብቅ እረኛ ሆነ፡፡ ነገር ግን እርሱ የምንኩስናን ልብስ ይለብስ ዘንድ በልቡ ይመኝ ነበር፡፡ 14 ዓመትም በሆነው ጊዜ የእግዚአብሔር ጸጋ አነሳሳችውና በጎቹን ትቶ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔደ፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣል›› እንዳለው (2ኛ ቆሮ 11፡14) አባ ገዐርጊ ወደ ገዳሙ እየተጓዘ ሳለ በሽማግሌ አምሳል ከይሲ ሰይጣን ተገለጠለትና ከዓላማው ሊያደናቅፈው ፈተነው፡፡ እንዲህም አለው ‹‹ልጄ ሆይ ስለ አንተ አባትህ ልብሱን ቀዶ አየሁት፣ የዱር አውሬ ነጥቆ የበላህ መስሎት አባትህ ያዝናል፣ ያለቅሳል፡፡ ተመልሰህ የአባትህን ልብ ልታጽናና ይገባሃል›› አለው፡፡ አባ ገዐርጊም ደንግጦ አንድ ሰዓት ያህል ሳይንቀሳቀስ ቆመመ፡፡ ከዚህም በኋላ የከበረ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌሉ ‹‹ከእኔ ይልቅ አባት እናቱን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይባውም ደቀ መዝሙሬም ሊሆን አይችልም›› ብሏል ብሎ አሰበ፡፡ ማቴ 10፡37፡፡ ይህንንም ባሰበ ጊዜ ሰይጣን እንደጢስ ሆኖ ተበትኖ ጠፋ፡፡ አባ ገዐርጊም ሰይጣን እንደሆነ ዐወቀ፡፡ ‹‹በመጠን ኑሩ ንቁም፣ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና ለእግዚአብሔር ተገዙ፣ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል›› 1ኛ ጴጥ 5፡8፣ ያዕ 4፡7፡፡

በዚያን ጊዜም አስቀድሞም ተገልጦለት የነበረው የብርሃን ምሰሶ ተገለጠለት፣ የእግዚአብሔርም መልአክ በመነኩሴ አምሳል ተገለጠለትና አብሮት ተጓዘ፡፡ መልአኩም አባ ገዐርጊን አባ አርዮን ገዳም አደረሰው፡፡ አባ ገዐርጊም ጽኑ ተጋድሎውን ጀመረ፡፡ በገዳሙ 14 ዓመት በታላቅ ተጋድሎ ሲኖር እህል አይቀምስም ውኃም አይጠጣም ነበር፡፡ ለ14 ዓመትም ከመቀመጥ በቀር ምንም አልተኛም፡፡ ከዚህም በላይ ተጋድሎውን በጨመረ ጊዜ እግዚአብሔር መልአኩን ልኮ ‹‹በመጠን ተጋደል›› ብሎታል፡፡ መልአኩም ተገልጦለት ‹‹‹ሥጋህ እንዳይደክም በመካከለኛ ተጋደል› ብሎሃል ጌታ›› ካለው በኋላ ሊሠራው የሚገባውን ሥርዓት ሠራለት፡፡ ሁልጊዜም እስከሚመሽ እንዲጾም፣ ትንሽም እንጀራን እንዲበላ፣ ከእራት ሰዓት እስከ መንፈቀ ሌሊት ስለሥጋው ዕረፍት እንዲተኛ በቀረው ሌሊት እስቲነጋ ተግቶ እንዲጸልይ ሥርዓት ሠራለት፡፡
መልአኩ በሠራለት በዚህ ሥርዓት ብዙ ዘመን ሲጋደል ከኖረ በኋላ በበረሃ ውስጥ ብቻውን ወሊኖር ወዶ በጫካ ውስጥ እየተመላለሰ ሁለት ዓመት ተቀመጠ፡፡ ነገር ግን ጌታችን ተገልጦለት ወደ ቀደመ ቦታው እንመለስ አዘዘው፡፡ ደብሩም ከከበሩ መክሲሞስ ዱማትዮስ ገዳም አጠገብ ነበር፡፡ ወደ ደብሩም በተመለሰ ጊዜ አብርሃም ከተባለ ደገኛ ቅዱስ ጋር ተገናኙና ሁለቱም በጋራ ለመኖር ተስማምተው ወደ አስቄጥስ ገዳም አበ ምኔት ወደ አባ ዮሐንስ ዘንድ ሄዱ፡፡ እርሱም ቦታ ሰጥቷቸው በውስጧ በተጋድሎ መኖር ጀመሩ፡፡ ያችም ቦታ እስከዛሬ ታውቃ ትኖራለች፡፡ ስሟም በግቢግ ትባላለች፡፡ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጣሪያዋን ሰንጥቆ ወደ እነዚህ ሁለቱ ቅዱሳን የወረደባት ናት፡፡ እነርሱም በክብር ሰገዱለት፡፡ ጌታችንም ባርኳቸውና አጽናንቷቸው ዐረገ፡፡ በዚያችም ጌታችን በወረደባት መስኮት ብርሃን ተመለከቱ፡፡ እስከዛሬም ድረስ የተከፈተች ሆና ትታያለች፡፡ እነዚህም ሁለት ቅዱሳን (አባ ገዐርጊና አባ አብርሃም) ለመኮሳት የሚሆኑ ብዙ ድርሳናትንና ተግሣጻትን ደረሱ፡፡ ከዚህም በኋላ አባ አብርሃም ጥር 2 ቀን ዐረፈ፡፡ ከእርሱም በኋላ አባ ገዐርጊ በ72 ዓመቱ ግንቦት 18 ቀን ዐረፈ፡፡
የአቡነ ገዐርጊ ምልጃና በረከቱ በምልጃው በምንታመን በሁላችን ላይ ይደርብን! አሜን!!!
(ምንጭ፦ የግንቦት ወር ስንክሳር)

Tuesday, July 21, 2015

ጩጊ ማርያም- ከጸበሉ ጠጥተው ስጋቸው ያልፈረሰ ፍየሎች

❖❖❖ በስመ ሥላሴ ❖❖❖

እነሆ ጌታ ፈቅዶ የሰማሁትን ያየሁትን እነግራቹ ዘንድ ጀመርኩ የዘንድሮዉን የሰኔ ጎሎጎታ ክብረ በዓል አከብር ዘንድ ወደ ቅዱሱ እና በጌታ ፍቅር በተጠመደዉ እና ከልጅነቱ ጀምሮ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት ፀንቶ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎችን አፍርቶ በፀጋ ከፍ ወዳለዉ የነ አቡነ አምደሥላሴ ወዳጅ ወደነበሩት ወደ አቡነ ምዕመነድንግል ገዳም ነበር የተጓዝኩት ። የኚ አባት ገዳም ልዩ መታወቂያ ስሙ ጩጊ ማርያም በመሰኘት ይታወቃል ። ከጎንደር 25 km ርቀት ያላት ሲሆን ኮሶዬ ከተባለች አካባቢ ሲደርሱ ለበረታ የ2 ሰዓት ለደከመ ከ 2ሰዓት በላይ ሚያሰኬደዉን መንገድ ይጀምራሉ ። አቡነ ምዕመነድንግል እንደ ቀደምት አበዉ ጠንካራ እና ለሃይማኖተ ክርስቶስ ቀናተኛ የነበሩና በዋልድባ ገዳም በአበምኔትነት ያገለገሉ ኀላም ውዳሴ ከንቱን በመሸሽ ከገዳሙ ርቀዉ አሁን ወዳሉበት ብዙ ፅድ እና ወይራ ወዳለባት /ጩጊ / መጥተዋል በዚህ ስፍራ ለረዥም ግዜ ተጋድሎ አርገዉበታል ። በዚህ ስፍራ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ከድንግል ማርያምና ከቅዱሳን ሁሉ ጋር ተገልጦ ለአባታችን ቃል ኪዳን ሰጥቶአቸዋል፣ አንዲሁም እንደ ትንሽ ብላቴና አቅፎአቸዉ ስሞአቸዋል ፣እንዲሁም በጌታ አዳኝነት አምነዉ በቅዱሱ አቡነ ምዕመነድንግል ፀሎት ሚታመኑ ሁሉ ፈዉስ ይሆናቸዉ ዘንድ ሁለት ማየ ዮርዳኖስ አፍልቆላቸዋል ከዚ ማየ ዮርዳኖስ የጠጡ ሁሉ ከደዌ ከመፈወሳቸዉ በተጨማሪ በድን ስጋቸዉ አይፈርስም አይበሰብስም ለዚ እንደማሳያ የሚሆኑ 16 ፍየሎች ከዚ ማየ ዮርዳኖስ ጠጥተዉ አሁንም ድረስ ሰዉነታቸዉ ሳይፈርስ አሁንም በሕይወት ያሉ ይመስላሉ ። አባታችን አቡነ ምዕመነድንግል አካሄዳቸዉን በጌታ ቃል እና ትምህርት ስላፀኑ ሞትን ሳያዩ እንደነ ሄኖክ ፣ ኤልያስ ፣ አቡነ አረጋዊ ፣ቅ.ያሬድ ተሰዉረዋል ።  አምላከ አቡነ ምዕመነድንግል እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ ይማረን ፣ ይባርከን ። አሜን !!

Wednesday, July 1, 2015

ታላቁ ጻድቅ ንጉሥ የዐፄ ካሌብ

ግንቦት 20-ንጽሕናን ከቅድስና ጋር አስተባብሮ በመያዝ እግዚአብሔርንም ሰውንም በቅድስናና በፍቅር ያገለገለው የታላቁ ጻድቅ ንጉሥ የዐፄ ካሌብ ዕረፍት ነው፡፡ እናም ዛሬ በዕረፍቱ ዕለት ገድሉን ትሩፋቱን የቅድስና ሥራውን አብዝተን በመናገር አስበነው እንውላለን፤ በረከቱን እንካፈላለን፡፡ ይኸውም ታላቅ ጻድቅ ንጉሥ ዋጋው እጅግ የከበረውንና በነገሠ ጊዜ በራሱ ላይ የጫነውን የወርቅ ዘውዱን ከጌታችን መካነ መቃብር ላይ ይሰቅልለት ዘንድ ከአደራ ደብዳቤ ጋር ለኢየሩሳሌሙ ሊቀ ጳጳሳት ለአባ ዮሐንስ ከላከለት በኀላ ዓለምን ንቆ፣ ልብሰ መንግሥቱን አውልቆ አንዲት የውኃ መንቀል ብቻ በመያዝ በአባ ጰንጠሌዎን እጅ በመመንኮስ ገዳማቸው አጠገብ ከሚገኝ ዋሻ ውስጥ ገብቶ 12 ዓመት በጾም በጸሎት በብዙ ድካምና ተጋድሎ እግዚአብሔርን ሲያገለግል ኖሮ ዛሬ ግንቦት 20 ቀን በታላቅ ክብር ዐርፏል፡፡
መልካም የበረከት ንባብ ይሁንልን!!! (የጽሑፉ ምንጭ ገድለ አቡነ አረጋዊ፣ ገድለ አቡነ ጰንጠሌዎንና የኅዳርና የግንቦት ወር ስንክሳር ናቸው)

በቍስጥንጥንያ ዮስጢኖስ በነገሠ በ5ኛው ዓመት ዐፄ ካሌብ በኢትዮጵያ ነግሦ ነበር፡፡ የአይሁድም ንጉሥ ፊንሐስ ነበር፡፡ በዚህም ወቅት ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት የኢየሩሳሌሙ አባ ዮሐንስ፣ የቍስጥንጥንያው አባ ጢሞቴዎስ፣ የእስክንድርያውም አባ ጢሞቴዎስ፣ የአንጾኪያው አባ አውፍራስዮስ ነበሩ፡፡ ሳባ የምትባለው አገር በኢትዮጵያ ነገሥታት እጅ ውስጥ ነበረች፡፡
የሮም ነገሥታት አስባስያኖስና ጥጦስ አይሁድን ወረው አሳደዷቸውና ይህችን ሳባን አይሁድ ወረሷት፡፡ በውስጧም በጌታችን የሚያምኑ ብዙ ሕዝቦች ነበሩባት፡፡ በሳባ ውስጥም ክርስቲያኖች የሚኖሩባት ታላቅ ከተማ ነበረች፡፡ የአይሁድ ንጉሥ ፊንሐስም ወደ ከተማዋ ገብቶ በሺህ የሚቆጠሩትን ክርስቲያኖች ገደለ፡፡ ዙሪያ ዳር ድንበሯ በመስቀል ምልክት የታጠረች ስለነበረች ፊንሐስ መጀመሪያ መግባት ሳይችል ሲቀር ‹‹ወደ ውስጥ ገብቼ የከተማዋን አሠራር፣ ገበያዋን፣ አደባባዮቿን መጎብኝት እሻለሁ እንጂ ክፉ አላስብም፣ የማንንም ደም አላፈስም›› ብሎ ምሎ ወደ ውስጥ ገባ፡፡ ከነሠራዊቱ ከገባ በኋላ ግን መግደል ጀመረ፡፡ መጀመሪያውንም አቡነ ኂሩተ አምላክ ‹‹ውሸቱን ነው አታስገቡት፣ ሐሰተኛ ነው ደጁን ከፍታችሁ አታስገቡት›› ብለው ቢነግሯቸውም የሚሰማቸው ጠፋ፡፡ ፊንሐስም እንደገባ የሕዝቡን ገንዘብ ዘረፈ፤ ቀጥሎም በነልባሉ አየር ላይ ደርሶ እስኪታይ ድረስ እሳት አስነድዶ ‹‹ኤጲስ ቆጶሱን አባ ጳውሎስን አምጡልኝ›› ብሎ አዘዘ፡፡ እንደሞቱም ሲነገረው ዐፅማቸውን ከመቃብር አውጥቶ አቃጠለው፤ ቀጥሎም ቀሳውስትን፣ ካህናትን፣ ዲያቆናትን፣ መነኮሳትን ሁሉ በእሳቱ ውስጥ እንዲጨምሯቸው አዘዘ፡፡ አራት ሺህ ሃያ ሰባት ክርስቲያኖችም ወደ እሳቱ ተጥለው በሰማዕትነት ሞቱ፡፡
ፊንሐስም አቡነ ኂሩተ አምላክንና ታላላቅ መኳንንትን ግን አሳስሮ ብዙ አሠቃያቸው፡፡ ‹‹ክርስቶስን ያልካደ ሁሉ ተሠቃይቶ ይሞታል›› የሚል አዋጅ በከተማው እንዲነገር አዘዘ፡፡ አቡነ ኂሩተ አምላክንም አስሮ እያሠቃያቸው በከተማው አዞራቸው፡፡ ሕዝቡም ጌታችንን አንክድም እያሉ ወጥተው ተገደሉ፡፡ በዚህም ጊዜ የተገደሉት ቁጥራቸው 4252 ሆነ፡፡
የአቡነ አቡነ ኂሩተ አምላክን ሚስት ቅድስት ድማህን ከ2 ልጆቿ ጋር ይዞ አሠቃያቸው፡፡ አንደኛዋም የ12 ዓመት ሕፃን ምራቋን በፊንሐስ ላይ ተፋችበት፣ እርሱም ሰይፉን መዞ አንገቷን ቆረጠው፡፡ ለቅድስት ድማህም የልጇን ደም አጠጣት፡፡ ድማህም ‹‹ይህን እንዲሆን የፈቀደ እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን›› ብላ አምላኳን ስታመሰግን ሰምቷት እናቲቱንም አንገቷን ቆረጠው፡፡ አቡነ ኂሩተ አምላክንም ወደ ውጭ አውጥቶ ‹‹የምታመልኩትን ክርስቶስን ካዱ›› አላቸው፡፡ አቡነ ኂሩተ አምላክም ‹‹ክብር ይባውና ጌታዬን ኢየሱስ ክርስቶስን እያለመኩ ስኖር 78 ዓመት ሆነኝ፣ እስከ አራት ትውልድም ለማየት ደርሻለሁ፡፡ ዛሬም ስለከበረ ስሙ ምስክር ሆኜ ስሞት እጅግ ደስ ይለኛል፡፡ ወደዚህ ለመግባት ስትምል እኔም አስቀድሜ መሐላህን እንዳያምኑ ለወገኖቼ ነግሬአቸው ነበር፤ አንተ ሐሰተኛ ነህና ነገር ግን ይህ ሁሉ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው፤ ለዚህ ተጋድሎ ላበቃኝ ለእርሱ ምስጋና ይሁን›› እያሉ ፊንሐስን በተናገሩት ጊዜ ወደ ወንዝ ወስዶ አንገታቸውን አስቆረጠው፡፡ አቡነ ኂሩተ አምላክም በሰማዕትነት ከማረፋቸው በፊት የኢትዮጵያንና የሮምን መንግሥት ያጸና ዘንድ የአይሁድን መንግሥት ግን ያጠፋ ዘንድ ጌታችንን ለመኑት፡፡ ዕረፍታቸውም ኅዳር 26 ቀን ነው፡፡
አቡነ ኂሩተ አምላክም ሕዝቡን ተሰናብተው በተሰየፉ ጊዜ አንዲት ሴት ደማቸውን ለ5 ዓመቱ ልጇ ቀባችው፡፡ ይህንንም ሲያዩ ልጇን ነጥቀው ለንጉሡ ሰጥተው እርሷን ከእሳቱ ውስጥ ጨመሯት፡፡ ንጉሡ ፊንሐስም ሕፃኑን ‹‹እኔን ትወዳለህ ወይስ ክርስቶስ የሚሉት?›› ብሎ ጠየቀው፡፡ የ5 ዓመቱ ሕፃንም ‹‹እኔስ የእጁ ሥራ ነኝና ክርስቶስን እወደዋለሁ፣ ይልቅስ ልቀቀኝና ወደ እናቴ ልሂድና ሰማዕትነቴን ልፈጽም›› አለው፡፡ ፊንሐስም ከእጁ እንዳይወጣ በያዘው ጊዜ እግሩን ነክሶት አምልጦት ሮጦ ሄዶ ከእሳቱ ውስጥ ገባ፡፡ ሁለተኛም የ10 ወር ሕፃን የተሸከመች አንዲት አማኝ ሴት ወደ ልጇ እያየች ‹‹ልጄ ሆይ ዛሬስ ላዝንልህ አልቻልኩም›› ብላ ስትናገር በእቅፏ ያለው የ10 ወሩ ሕፃን ልጇም አንደበቱን ከፍቶ ‹‹እናቴ ሆይ በፍጥነት ወደ ዘላለም ሕይወት እንሂድ ይህችን እሳት ከዛሬ በቀር አናያትምና›› አላት፡፡ እርሷም ልጇን ይዛ ዘላ እሳቱ ውስጥ ተወርውራ ገባች፡፡ የክርስቲያን ወገኖችም ይህን ሁሉ አይተው እኩሉ ወደ እሳት እኩሉ ወደ ሰይፍ ተሽቀዳደሙ፡፡ ራሳቸው የአይሁድ ሠራዊት ዕፁብ ብለው እስኪያደንቁ ድረስ ክርስቲያኖቹ ወደ ሰማዕትነት ተፋጠኑ፡፡ ቁጥራቸው ሃያ ሺህ ነበር፡፡ ክርስቲያኖቹም በሚሞቱበት ጊዜ የረዳቶቻቸውን የቊስጥንጥንያንና የኢትዮጵያን ነገሥታት ስም በጸሎታቸው ይጠሩ ነበር፡፡
ከዚህም በኋላ እሳቱ በሰማይ ውስጥ መልቶ 40 ቀንና 40 ሌሊት ታየ፡፡ ፊንሐስም ወደ ሀገሩ በተመለሰ ጊዜ ወደ ነገሥታቱ ሁሉ በኋይሉ እየተመካ ላከባቸው፡፡ የሮሜው ንጉሥ ዮስጢኖስም ይህን ሰምቶ ወደ እስክንድርያ ሊቀ ጳጳስ ወደ አባ ጢሞቴዎስ መልአክት ላከ፡፡ ለሀገረ ናግራን ክርስቲያኖች ደማቸውን ይበቀልላቸው ዘንድ ለኢትዮጵያው ንጉሥ ለዐፄ ካሌብ መልእክት እንዲልክ ነገረው፡፡ ዐፄ ካሌብም ተጽፎለት መልእክቱ ሲደርሰው ፈጥኖ ተነሣ በዋሻ ከሚኖር ከአቡነ ጰንጠሌዎን በረከትን ተቀብሎ ለአቡነ አረጋዊም በጸሎት እንዲያስቡት ደብዳቤ ጽፎ ከላከ በኋላ ከሠራዊቱ ጋር በመርከብ ተጭኖ ወደ ሀገረ ናግራን ሄደ፡፡
ከመሄዱም በፊት ለአቡነ አረጋዊ የላከላቸው መልእክት እንዲህ የሚል ነው፡- ‹‹ፊንሐስ የተባለ አረማዊ የናግራን ክርስቲያኖችን ደም በከንቱ ያፈሰሰ፣ ቤተክርስቲያንን የመዘበረና ያጠፋ ፍጹም የእግዚአብሔር ጠላት ወደሚሆን ሔጄ እዋጋው ዘንድ ተዘጋጅቻለሁ፡፡ ስለዚህ አባቴ ሆይ! አንተም በበኩልህ ጸሎት አድርግልኝ፣ የጻዲቅ ጸሎት ትራዳለች፣ ኃይልንም ታሰጣለች፣ በጠላት ላይ ድልንም ታቀዳጃለችና›› ሲል ላከበት፡፡
አባታችን አቡነ አረጋዊም ለንጉሡ ጭፍሮች ‹ወደ ጦሩ ግንባር ሒድ፣ እግዚአብሔር ጠላቶችህን ከእግርህ በታች ያስገዛልህ፣ ለአንተም ግርማ ሞገስ ይስጥህ፣ በሰላም ይመልስህ›› ብለው መርቀው ላኩበት፡፡ ከዚህ በኋላ ዐፄ ካሌብ ልብሰ መንግሥቱን አውልቆ ጥሎ ማቅ ለብሶ በፍጹም ልመና ብዙ ጸሎት ካደረገ በኀላ ወደ የመን ሳባ በመርከብ ተጓዘና ከከሐዲው ፊንሐስ ጋር ጦር ገጠመ፡፡ ከሐዲውን ንጉሥ ፊንሐስን ራሱ ዐፄ ካሌብ ገጠመውና በፈረሱ ላይ እንደተቀመጠ በጨበጣ በጦር ወግቶ ገደለውና ወደ ባሕር ገልብጦ ጣለው፡፡
ከዚያም ዐፄ ካሌብ ዛፋር ወደምትባለው ከተማ ሔዶ እርሷንም ተቆጣጠራት፡፡ በእዚያም ያሉ የፊንሐስን ሹማምንቶች እያፈላለገ በአደባባይ እንዲገደሉ በማድረግ የክርስቲያኖቹን ደም በሚገባ ተበቀለ፡፡ የናግራንንም ሕንፃዎቿዋን አደሰ፤ የሰማዕታቱንም መታሰቢያ አቆመ፡፡ ወደ እስክንድርያው አባ ጢሞቴዎስና ወደ ሮሜው ንጉሥ ዮስጢኖስም የድል መልእክት ላከላቸውና እነርሱም ሰምተው እጅግ ተደሰቱ፡፡ በአንጾኪያ፣ በእስክንድሪያ፣ በሮም፣ በቊስጥንጥንያና በዓለም ላይ ያሉ ክርስቲያኖች ሁሉ ይህን ሲሰሙ በእጅጉ ተደሰቱ፡፡ ይህም የሆነው በ525 ዓ.ም ነው፡፡ ጠፍተው የሔዱ ክርስቲያኖችንም ሰበሰባቸውና ወደቀደመ ቦታቸው መለሳቸው፣ ቤተክርስቲያናቸውን አነጸላቸው፡፡ ከሳባ ሀገር የማረከውን ንብረት ሁሉ ለቤተክርስቲያን ሰጥቶ ዓሥር ሺህ ጠባቂ ሠራዊት ሰቷቸው ወደ አክሱም በሰላምና በፍጹም ደስታ ተመለሰ፡፡
ንጉሡ ዐፄ ካሌብ የናግራን ሰማዕታት ደም ተበቅሎላቸው ሁሉንም ነገር አስተካክሎላቸው በደስታ ወደ አክሱም ከተመለሰ በኋላ ‹‹ይህን ያደረገልኝን አምላኬን በምን ላስደስተው?›› ሲል አሰበና ተድላውን፣ ደስታውን ዓለምን ንቆ፣ ልብሰ መንግሥቱን አውልቆ አንዲት የውኃ መንቀልና አንዲት ምንጣፍ ብቻ ይዞ አባ ጰንጠሌዎን ገዳም አጠገብ ከሚገኝ ዋሻ ውስጥ ገብቶ በአባ ጰንጠሌዎን እጅ መንኩሶ ለመቀመጥ ወሰነ፡፡ አባ ጰንጠሌዎንንም ‹‹አመንኩሰኝ›› አላቸውና የመላእክትን አስኬማ አልብሰው አመነኮሱት፡፡ ዐፄ ካሌብም ዳግመኛ ከዋሻው ወጥቶ ዓለምን በዐይኑ እንዳያይ ማለ፡፡ ዋጋው እጅግ የከበረውንና በነገሠ ጊዜ የጫነውን ዘውዱን ከጌታችን መካነ መቃብር ወይም በር ላይ ይሰቅልለት ዘንድ ከአደራ ደብዳቤ ጋር ለኢየሩሳሌሙ ሊቀ ጳጳሳት ለአባ ዮሐንስ ላከለት፡፡ ዳግመኛም ንጉሡ ዐፄ ካሌብ ‹‹አባቴ ሆይ በአንተ ጸሎት በእግዚአብሔር ቸርነት ከጦርነቱ በሰላም ተመልሻለሁ፤ አሁንም የክርስቶስን አርዑተ መስቀል ተሸክሜአለሁና እግዚአብሔር ለፍጻሜው ያብቃህ እያልህ ስለ እኔ ጸልይልኝ›› ብሎ ወደ አባታቸን ወደ አቡነ አረጋዊ ላከበት፡፡ ስለዚህም ነገር አቡነ አረጋዊ በጣም ተደሰቶ ‹‹ልጄ ሆይ! መልካሙንና የበለጠውን አድርገሃል፣ አሁንም እግዚአብሔር የፈቀደከውን ነገር ሁሉ ይፈጽምልህ›› ብለው መረቁት፡፡ ኢትዮጵያዊው ንጉሥ ዐፄ ካሌብ ይህን ዓለም በመናቅ በበረሃ በዋሻ 12 ዓመት በጾም በጸሎት በብዙ ተጋድሎ ከኖረ በኋላ ግንቦት 20 ቀን ዐርፎ እስከ ዘለዓለሙ ድረስ የማያልፍ ሰማያዊ ክብርን ወርሷል፡፡ መካነ መቃብሩም አክሱም በአባ ጰንጠሌዎን ገዳም ምድር ቤቱ ውስጥ ይገኛል፡፡
ይኸውም አባ ጰንጠሌዎን ከተሰዓቱ ቅዱሳን ውስጥ አንዱ ሲሆን በገዳሙ ውስጥ ሳይቀመጥ ሳይተኛ በእግሩ ቆሞ 45 ዓመት የጸለየ የበረከት አባት ነው፡፡ ምድራዊ ወይም ሥጋዊ የሆኑ ፍትወታት ፈጽመው ጠፍተውለታልና ከመላእክትም ማኅበር ጋር አንድ ሆኗልና ከፍጹም ምስጋና በቀር እህል ወይም ውኃ ወይም ቅጠል እንኳ አይቀምስም ውኃም አይጠጣም ነበር፡፡ እርሱም የንጉሥ ልጅ ስለነበር አስቀድሞ ንግሥናን ንቆ የመነነ ነው፡፡ የመንፈስ ወንድሞቹም እንዲሁ፡፡
እነዚህም ተሰዓቱ ቅዱሳን ሁሉም የነገሥታት ልጆች ሲሆኑ በዓለም ነግሠው መኖርን እርግፍ አድርገው ትተው ከያሉበት ከቁስጥንጥንያ፣ ከአንጾኪያ፣ ከግሪክ፣ ከእስያ፣ ከሮምያና ከቂሣርያ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በአንድነት ተሰባስበው በአባ ጳኩሚስ ገዳም ገብተው በምንኩስና ሲኖሩ ኢትዮጵያ በሃይማኖት በምግባር ያጌጠች ቅድስት ሀገር መሆኗን ሲሰሙ ‹‹ይህችንማ ሄደን ማየት አለብን›› ተባበብለው ያላቸውን ሁሉ ይዘው ታቦቶቻቸውን፣ ካህናቶቻቸውን፣ ንዋየ ቅድሳቶቻቸውን፣ መጻሕፍቶቻቸውን ሁሉ ይዘው በዘሚካኤል (አቡነ አረጋዊ) መሪነት በመምጣት በ460 ዓ.ም ጳጳሱና ንጉሡ ካሉበት አክሱም ከተማ ገቡ፡፡
በዚያም ለ12 ዓመታት በፍጹም አንድነት አብረው ከተቀመጡ በኋላ ‹‹እርስ በራሳችን እየተያየን ብንኖር ተድላ ደስታ ይሆንብናልና ተለያይተን እንቀመጥ›› ብለው ተማከረው በተለያየ በዓት በተጋድሎ መኖር ጀመሩ፡፡ አባ ሊቃኖስ በደብረ ቁናጽል፣ አባ ጰንጠሌዎንም በእርሱ ትይዩ በሆነ ቦታ፣ አባ ገሪማ በደብረ መደራ፣ አባ ጽሕማ በደብረ ጸድያ፣ አባ ይምአታ በደብረ ገረዓልታ፣ አባ አፍጼ በደብረ ይሐ፣ አባ አሌፍ በደብረ አኅድአ መኖር ጀመሩ፡፡ አባ አረጋዊ ደግሞ በጣም ርቀው በመሄድ በደብረ ዳሞ በዋሻና በፍርኩታ ውስጥ በተራራም ላይ መኖር ጀመሩ፡፡
ተሰዓቱ ቅዱሳን ብዙ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን ያደረጉ ነበር፣ ተአምራቶቻቸውን መንፈሳዊ ዐይኑ ያልበራለት ሰው ከቶ ሊረዳውና ለገነዘበው አይችልም፡፡ መላእክትም ዘወትር ባለመለየት ይጎበኙዋቸው ነበር፡፡ ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስም ዘወትር እየተገለጠላቸው ይባርካቸውና ቃልኪዳን ይሰጣቸው ነበር፡፡ በጸሎታቸውም አጋንንትን ያስወጣሉ፣ ድውያንን ይፈውሳሉ፣ ዕውራንን ያበራሉ፣ ሙታንን ያስነሣሉ፡፡ ለእያንዳንዳቸውም የሃይማኖታቸውን ኃይል አሳዩ፡፡ ከእነርሱ መካከል ተራራ ያፈለሱ አሉ፣ ባሕሩን ከፍለው ደረቅ መንገድ ያደረጉ አሉ፣ ጠዋት ዘርተው ማታ ሰብስበው የሚያጭዱ አሉ፣ ይኸውም የስንዴውን ነዶ በግራር ዛፍ ላይ አበራይተው የዛፉ ቅጠል ሳይረግፍ በሬዎቹም ከዛፉ ላይ ሳይወድቁ ምርቱ ብቻ እየወረደ በአውድማው ላይ እንዲከማች ያደረጉ አሉ፣ ወዲያውም ስንዴውን ለመገበሪያ ሠይመው ለዘጠኝ ሰዓት መሥዋዕተ ቊርባን ያደረሱ አሉ፡፡
በዓለት ድንጋይ ላይ የወይራ ተክል ተክለው በዚያኑ ጊዜ ጸድቆ ለምልሞ ታላቅ ዛፍ ከሆነ በኋላ በእግዚአብሔር ፈቃድ ግንዱ ደርቆ ቆርጠውና ፈልጠው እንጨቱን አንድደው እሳቱ ፍም ከወጣው በኋላ ፍሙን በቀጭን ሻሽ ወስደው ለዘጠኝ ሰዓት የቅዳሴ ማዕጠንት ያደረሱ አሉ፡፡ ለቤተክርስቲያን አገልግሎት የሚውልና ለሥርዓተ ቊርባን ማከናወኛ የሚሆን ውኃው ሳይፈስ በወንፊት ውኃ የሚቀዱ አሉ፡፡
ከእነሱም አንዱ በዐረፈ ጊዜ የሥጋው ሥርዓተ ግንዘት በመላእክት እጅ የተከናወነ አለ፡፡ ይልቁንም ቁመቱና ርዝመቱ ከታላላቅ ገደል እጅግ በጣም የሚበልጥ የድንጋይ ዓምድ ከወንዝ ማዶ ዘንበል ብሎ መጥቶ ሥጋቸውን በክብር ተቀብሎ በተራራው ጫፍ ላይ እስከዛሬም ድረስ ፈጽሞ ሳይነቃነቅና ሳይናወፅ ቀጥ ብሎ ቆሞ ይገኛል፡፡ የሰዎቹም የመግነዝ ምልክት ጥበበኛ እንደሣለው ሥዕል በድንጋዩ ዓምድ ላይ ተስሎ ወይም ተቀርፆ ይታያል፡፡ ቆመው ጸሎት በሚጸልዩበት ጊዜ ዓሥሩ የእጆቻቸው ጣቶችና ዓሥሩ የእግሮቻቸው ጣቶች እንደፋና የሚያበሩበትና እንደመብረቅ የሚብለጨልጩበት ጊዜ አለ፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ ያለአንዳች ሐዋርያ ስብከት አስቀድማ በክርስቶስ እንዳመነችና በዚህም ምክንያት የልዕልናዋን ታሪክ ለዓለም ለማሳወቅ ፈጥነው የሄዱ አሉ፡፡ የኢትዮጵያ ምድር በእነዚህ የቅዱሳን ኪደተ እግር ተቀደሰች፣ በውስጧም በመመላለሳቸው አውራጃዎቿና አደባባዮቿ ሁሉ ታደሱ፡፡ መዓዛ ትምህርታቸውና ተአምራቶቻቸው በሁሉም አውራጃዎች ተሠራጨ፣ የእምነቷንም መሠረት አጸኑ፡፡
የቅዱሳኑ ምልጃቸውና በረከታቸው በአማላጅነታቸው በምንታመን በሁላችን ላይ ይደርብን! አሜን!!!

ገድለ ቅዱሳን

ግንቦት 19 ዕለት ታስበው የሚውሉ 6 ታላላቅ ዓመታዊ በዓላት አሉ፡፡
፩. ጌታችን 5 ጊዜ ከሞት እያስነሣውና ስለ ስሙ ምስክር የሆነለት የ12 ዓመቱ ሕጻን የቅዱስ ኤስድሮስ ዕረፍት ነው
፪. በወሎ ላስታ ሰውንና ዝንጀሮን በቃልኪዳን ያስተሳሰሩት እና እመቤታችን ዕጣን እየሰጠቻቸው ከ24ቱ ካህናተ ሰማይ ጋር የሥላሴን መንበር ያጠኑት የአቡነ ዮሴፍ ዘእጂፋት ዕረፍት ነው
፫. ዳግመኛም ጌታችን ነገልጦ ‹‹ለእናቴ ዓሥራት የሰጠኋት፣ ለወዳጄ ለጊዮርጊስ፣ ለባለሟሌ ለገብረ መንፈስ ቅዱስ ዓሥራት የሰጠኋት ይህችን ቅድስት ሀገር ያሬድንና ጊዮርጊስን ያፈራችውን ኢትዮጵያን በጸሎትህ ጠብቅ›› ብሎ ያዘዛቸው የአቡነ ዮሴፍ ዘአክሱም ዕረፍት ነው
፬. ስመ እግዚአብሔር ሲጠራባቸው ስለ ስሙ ሲሉ ራሳቸውን ለሞት አሳልፈው የሰጡት በጸሎታቸውም ውኃውን ደም ያደረጉት የአቡነ ዓቢየ እግዚእ ዕረፍት ነው
፭. ጸሎታቸውን ሲጀምሩ ሰማያት ተከፍተው የመላእክትን አገልግሎት በግልጽ የሚያዩት እና ሰይጣን ለመጀመሪያ ጊዜ ከጳውሎስ ሳምሳጢን ጀምሮ እስከ ንስጥሮስንና ልዮን ድረስ ያስተማራትን የክህደት ት/ት ከሀገራችን ያጠፉልን የአቡነ ብስጣውሮስ ዘሐይቅ ዕረፍት ነው
፮. ዳግመኛም ቤተ መቅደሱን በባሕር ላይ የሠራውና በምድራዊ ስንዴና ወይን ያይደለ መላእክት ሰማያዊ ኅብስትና ጽዋ እያመጡለት 22 ዓመት ሥጋ ወደሙን ሰፈትት የኖረው የጻድቁ ንጉሥና ካህን የቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ ልደት ነው፡፡ 

የእነዚህን ቅዱሳን የሁሉንም ሙሉ ገድላቸውን በዝርዝር በደንብ እንመለከታለን በእርጋታ ሆናችሁ በተመስጦ አንብቡት፡፡ መልካም የበረከት ንባብ ይሁንልን!!! 

የጽሑፉ ምንጮች፡-
፩. ገድለ አቡነ ብስጣውሮስ ዘሐይቅ
፪. ገድለ አቡነ ዓቢየ እግዚእ
፫. ገድለ ቅዱስ ላሊበላ
፬. ገድለ ቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ
፭. ገድለ ቅዱስ ቂርቆስ ወኢየሉጣ
፮. ስንክሳር ዘወርሃ ግንቦት
፯. የቅዱሳን ታሪክ-107፣140
፰. መዝገበ ታሪክ ናቸው፡፡

ሕጻኑ ሰማዕት ቅዱስ ኤስድሮስ፡- ሀገሩ እስክንድርያ ሲሆን አባቱ በድላዖን እናቱ ሶፍያ ከቤተ መንግሥት ወገኖች ናቸው፡፡ አባቱ የዲዮቅልጥያኖስ መኰንን ነበር፡፡ ከሀዲው ዲዮቅልጥያኖስ በክርስቲያኖች ላይ እጅግ አሠቃቂ መከራ ባደረሰ ጊዜ አባቱ በድላዖን ምስፍናውን ትቶ ሚስቱንና ልጆቹን ይዞ ገዳም ገባ፡፡ ዲዮቅልጥያኖስም ጭፍሮቹን ልኮ አስመጣውና እምነቱን እንዲክድ ጠየቀው፡፡ በድላዖንም ‹‹ክርስቶስን በተውከው ሰዓት እኔም አንተን ተውኩህ›› አለው፡፡ ወዲያም አንገቱን በሰይፍ አስቆረጠው፡፡ ቅዱስ ኤስድሮስ የ12 ዓመት ሕፃን ልጅ ነበርና ይመለስ ይሆናል በሚል በእሥር ቤት እንዲቆይ ተደረገ፡፡ በማግሥቱም ‹‹ክርስትናህን ትተህ የንጉሡን ሃይማኖት ተቀበል›› ብለው ሲያባብሉት እምቢ ቢላቸው በንጉሡ ፊት አቅርበው ደሙ እንደ ውኃ እስኪወርድ ድረስ አሠቃቂ ግርፋትን ገረፉት፡፡ እናቱ ሶፍያም የሕፃኑን ልጇን ደም በዲዮቅልጥያኖስ ፊት ላይ እረጭታ እረገመችው፡፡ ዲዮቅልጥያኖስም በንዴት ከሴት ልጇ ጋር ከወገባቸው ላይ ከሁለት አስቆረጣቸውና ሰማዕትነታቸውን ፈጸሙ፡፡
ቅዱስ ኤስድሮስም ተሰቅሎ ሳለ በእናቱና በእኅቱ የሆነውን ነገር ይመለከት ነበር፡፡ ሆዱን ሰንጥቀው በመቅደድ አንጀቱን አውጥተው ወስደው በተራራ ላይ ጣሉት፡፡ ጌታችንም ከሞት አሥተነስቶት እንደ ቀድሞው ሕያውና ፍጹም ጤነኛ አደረገው፡፡ ኤስድሮስም ተመልሶ ሄዶ ከከሃዲው ንጉሥ ፊት ቆመ፡፡ አሁንም በብረት አልጋ ላይ አስተኝተው ከሥር እሳት አነደዱበት፡፡ ሁለተኛም በብረት ላይ አስተኝተው ፈጩት፡፡ ጌታችንም አስነሣው፡፡ ብዙዎችም በኤስድሮስ አምላክ አመኑ፡፡ ዳግመኛም በእርሱ አምላክ ካመኑት ከ800 ነፍሳት ጋር ሰቀሉት፡፡ አሁን ጌታችን አድኖ አሥነሳው፡፡ በሥቃይም ብዛት አልሞት ቢላቸው አንገቱን በሰይፍ ቆረጡት ነገር ግን አሁንም ለ3ኛ ጊዜ ከሞት አሥነሣው፡፡
ትልቅ ድንጋይ በአንገቱ ላይ አስረው ወደ ባሕር ጣሉት፡፡ ቅዱስ ሚካኤልም ከባሕሩ ውስጥ አውጥቶ በንጉሡ ፊት አቆመው፡፡ ዳግመኛም ወደ ከተማም ወስዶ ሰቅሎ ገደለው፣ ጌታችንም ለ4 ጊዜ አሥነሣው፡፡ ለተራቡ አንበሶች ሲሰጡት እነርሱም ምንም ሳይነኩት ቀሩ ይልቁንም አክብረው ሲሰግዱለት ቢመለከቱ በንዴት ሰውነቱን ቆራርጠው ወደ ባሕር ጣሉት፡፡ ጌታችንም ከቅዱስ ሚካኤልና ከቅዱስ ገብርኤል ጋር ተገልጦለት ለ5ኛ ጊዜ ከሞት አሥነሣው፡፡ ንጉሡም እጅግ አፈረና የሚያደርገው ቢያጣ በግዞት ወደ ሰሎንቅያ ሀገር ላከው፡፡ በዚያም ብዙ ካሠቃዩት በኋላ ወደ ንጉሡ መለሱት፡፡ ንጉሡም በእሥር ቤት በርሀብ እንዲሠቃይ አደረገው፡፡ በመጨረሻም ቅዱስ ኤስድሮስ ግንቦት 19 ቀን የሰማዕትነት ፍጻሜው ሆነና ተሰቅሎ ዐረፈ፡፡ የኖረበት ዘመን 12 ዓመት ነው፡፡ በቅዱስ ኤስድሮስ ምክንያት በጌታችን አምነው ከኤስድሮስ ጋር አብረው በሰማዕትነት የሞቱት ሰዎች ብዛት ከ8 መቶ ሺህ በላይ ናቸው፡፡ ጌታችን ለሕፃኑ ሰማዕት ለቅዱስ ኤስድሮስ አስደናቂ ቃል ኪዳን ገብቶለታል፡፡
አቡነ ዮሴፍ ዘእንጂፋት፡- ተአምረኛው ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ ዮሴፍ ዘእንጂፋት አባታቸው ንጉሡ ዐፄ ዳዊት እናታቸው ዳግም ሞገሳ ይባላሉ፡፡ ትውልድ ሀገራቸው ወሎ መቄት እንጂፋ ነው፡፡ ሲወለዱ በርካታ ሙታን ተነሥተዋል፡፡ ጻድቁ ያላዩት የቅዱሳን ቦታ ያልተሳለሙት ገዳም የለም፡፡ በወሎ ላስታ ሰውንና ዝንጀሮን በቃልኪዳን ያስተሳሰሩ ታላቅ አባት ናቸው፡፡
ከዕለታት በአንዱ ቀን ዝንጀሮዎቹ ተሰብስበው መጥተው እጅ ነሷቸው፡፡ አቡነ ዮሴፍም ጌታችንን ‹‹ምን አበላቸዋለሁ?›› ብለው በጸሎት ጠየቁ፡፡ ጌታችንም ‹‹አንተን ያጅቡ፣ ቅጠሉን ቃርሚያውን ይብሉ›› ብሎ አዘዛቸው፡፡ ዝንጀሮዎቹም ጻድቁን ተከትለው ይጓዙ ጀመር፡፡ አንድ ቀን በመንገድ አብረው ሲሄዱ ዝንጀሮዎቹ ‹‹ራበን›› ብለው ለአባታቸን ቢነግሯቸው ድንጋዩን በጸሎታቸው ባርከው ምግባቸው አድርገው መግበዋቸዋል፡፡ አሁንም ድረስ ላስታ ውስጥ በሚገኘው በጻድቁ ገዳም አካባቢ እህሉ በሚትረፈረፍበት ቦታ ዝንጀሮዎች በብዛት ይገኛሉ፡፡ ዝንጀሮዎቹ የሰውን እህል እንዳይበሉ፣ ገበሬውም ቃርሚያውን እንዳያነሳ በአቡነ ዮሴፍ ቃልኪዳንና ግዝት ተይዘዋል፡፡ በዚህም መሠረት አሁንም ድረስ ዝንጀሮዎቹም የሰውን እህል አይበሉም፣ ገበሬውም ቃርሚያውን አያነሳም፡፡ ገበሬው ቃርሚያውን ቢያነሳ ግን ዝንጀሮዎቹ የእሱን እህል ብቻ ለይተው ይበሉበታል፡፡
በአካባቢው አደገኛና መርዛማ እባቦች በብዛት ቢኖሩም በጻድቁ የገዳሙ ክልል ውስጥ ግን በፍጹም ሰውን አይነኩም፡፡ አቡነ ዮሴፍ ለ40 ቀን ከሰው ጋር ሳይገናኙ ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም በደመና እየተመላለሱ ጸሎት ያደርጉ ነበር፡፡ አባታችን የተለያዩ ተአምራትን እያደረጉ ባሕር ከፍለው እየተሻገሩ ሙታንን እያስነሱ ወንጌልን ዞረው አስተምረዋል፡፡ ወደ ሰማይም ተነጥቀው እመቤታችን ዕጣን ሰጥታቸው ከ24ቱ ካህናት ጋር አጥነዋል፡፡ ጻድቁ ያመነኮሷቸው መነኮሳት በጣም በርካታ ናቸው፡፡ አቡነ ዮሴፍ ከብዙ ተጋድሏቸው በኋላ ቃልኪዳን ተቀብለው በመጨረሻ ግንቦት 19 ቀን በክብር ዐርፈው በዚያው በገዳማቸው ተቀብረዋል፡፡
አቡነ ዮሴፍ ዘአክሱም፡- የአቡነ ዮሴፍ ዘአክሱም ልደታቸውና ዕረፍታቸው በተመሳሳይ ግንቦት 19 ቀን ነው፡፡ ልጅ ሆነው እየተጫወቱ ሳለ መልአክ መጥቶ ለወላጆቻቸው የዓለም ሰው እንዳልሆነ ስለነገራቸው ወስደው ለሊቀ ጳጳሱ ሰጧቸው፡፡ በአክሱም ሲማሩ አድገው በ22 ዓመታቸው መንኩሰዋል፡፡ አንጋፋ ከተባሉት የኢትዮጵያ ቅዱሳን አንዱና ዋነኛው ናቸው፡፡
ጻድቁ በጸሎት ላይ እንዳሉ ጌታችን ተገልጦላቸው እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹ትወደኛለህን?›› ብሎ ሲጠይቃቸው ‹‹ጌታዬ ባለወድህማ ኖሮ መች ዓለምን ንቄ እከተልህና ገዳም እገባ ነበር›› አሉት፡፡ ቀጥሎም ጌታችን ‹‹ከወደድከኝስ ለእናቴ ዓሥራት የሰጠኋት፣ ለወዳጄ ለጊዮርጊስ ዓሥራት የሰጠኋት፣ ለባለሟሌ ለገብረ መንፈስ ቅዱስ ዓሥራት የሰጠኋት ይህችን ቅድስት ሀገር ያሬድንና ጊዮርጊስን ያፈራችውን ኢትዮጵያን ጠብቅ›› ብሏቸው ተሰወረ፡፡ ጻድቁም ጌታችን ይህን ከነገራቸው በኋላ እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ ስለ ሀገራችን ቆመው ጸልየዋል፡፡ ሸዋ ቡልጋ ፈጠጋር ውስጥ ለሚገኙት ወንድማቸው ለታላቁ ጻድቅ ለአቡነ ዘካርያስም ስለ ኢትዮጵያ አብዝተው እንዲጸልዩ መልእክት ስለላኩባቸው አቡነ ዘካርያስም ዕድሜ ልካቸውን የጸለዩአት ጸሎት ‹‹የኢትዮጵያን ሕዝብ ማር›› የምትል ነበረች፡፡ የአቡነ ዘካርያስ ገዳም ቡልጋ ውስጥ ይገኛል፡፡ አቡነ ዮሴፍ ዘአክሱም የሀገራችንን ሊቃውንትና ሕዝቡንም ለብቻ ሰብስበው የሮማውያን የሀሰት ትምህርት ነፍስን ለሲኦል የሚዳርግ ፍጹም ክህደት መሆኑን አጥብቀው አስተምረዋል፡፡ ጻድቁ በአንድ ወቅት ርሀብ በሆነ ጊዜ የገዳሙን ድንጋዮች ባርከው ዳቦ አድርገው ሕዝቡን የመገቡ ታላቅ አባት ናቸው፡፡
አቡነ ብስጣውሮስ ዘሐይቅ፡- ሙሉ ስማቸው ዓቃቤ ሰዓት አቡነ ብስጣውሮስ ተብለው የሚጠሩ ሲሆን የትውልድ ሀገራቸው መቅደላ ነው፡፡ አባታቸው ፍተ ድንግል እናታቸው ጽዮን ሞገሳ የሚባሉ ደጋግ ቅዱሳን ናቸው፡፡ አቡነ ብስጣውሮስ በ17ኛው ምእት ዓመት የነበሩ ታላቅ ጻድቅ ሲሆኑ የታላቁና የጥንታዊው ትምህርት ቤትና የሥርዓተ ገዳም ተቋም የደብረ ሐይቅ ቅዱስ እስጢፋኖስ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ገዳም አበምኔት ነበሩ፡፡ በልጅነታቸው ትምህርት ቤት ገብተው የሐዋርያትን ሥርዓትና የቅዱሳት መጻሕፍትን ትርጓሜ በሚገባ ተምረዋል፡፡
በዘመናቸው የሃይማኖት ስደት ስለነበር አባታቸው ፍተ ድንግል ስለ ሃይማኖታቸው በዐላውያን ሰማዕት ሆነው ሲገደሉ አቡነ ብስጣውሮስ የአባታቸውን ዐፅም ይዘው በመሸሽ ወደ ላስታ ሄደው በእመቤታችን ስም በተሠራች ገዳም በደብረ ዠመዶ ወስደው ቀበሯቸው፡፡ በኋላ በዐፄ ፋሲል ዘመን ሃይማኖት ሲመለስ ዐፅማቸውን አፍልሰው አምጥተው አገራቸው ቀብረዋቸዋል፡፡ ከዚህም በኋላ እናታቸው በግድ ሚስት አጭተውላቸው የነበረ ቢሆንም ብዙ ሳይቆዩ ሚስታቸው ስለሞተች ቀድሞም የተመኙትን የምንኩስና ሕይወት ለመኖር ወኑ፡፡ አንድ ቀን አንዱ የደብረ ሐይቅ መነኩሴ የገዳሙን ምርት ገበያ ለመሸጥ ይዘው እንደሄዱ አንድ ቀማኛ ወንበዴ አግኝቶ ሊቀማቸው ሲል አቡነ ብስጣውሮስ ደርሰው አዳኑት፡፡ መነኩሴውንም ወደ ቤታቸው ወስደው በመልካም መስተንግዶ አሳደሯቸው፡፡ መነኩሴውም በዚያች ሌሊት ስለ አቡነ ብስጣውሮስ ብዙ ነገር ከተመለከቱ በኋላ አቡነ ብስጣውሮስን ስለ ምንኩስና አስተማሯቸው፡፡ መነኩሴው በማግስቱ ሲሄዱ ወደ ሐይቅ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ገዳም መጥተው እንዲጎበኟቸውና እንዲባረኩ ነግረዋቸው ሄዱ፡፡ አቡነ ብስጣውሮስም እግዚአብሔር መንገዳቸውን ይመራቸው ዘንድ ብዙ ከጸለዩ በኋላ ወደ ሐይቅ ገዳም ገቡ፡፡ በገበያ ያገኘውና በቤቱ ያሳደረውም መነኩሴ ሲያያቸው ደስ ተሰኝነቶ የገዳሙ አበምኔት ዓቃቤ ሰዓት አባ ዘወልደ ክርስቶስ ዘንድ ወሰዳቸው፡፡ አበምነቱም አቡነ ብስጣውሮስን ገና እንዳዩአቸው ጸጋ እግዚአብሔር እንዳደረባቸው አይተው በጣም ደስ ተሰኙ፡፡ አቡነ ብስጣውሮስም መመንኮስ እንደሚፈልጉ ለአበምኔቱ ሲነግሯቸው አበምኔቱ ‹‹የምንኩስና ሥራ ቀላል አይምሰልህ፣ ብዙዎች ወደ እኛ መጡ ነገር ግን መታገስ ተስኗቸዋል…›› በማለት የምንኩስና ሕይወት ከባድ ፈተና እንዳለበት ነገሯቸው፡፡ የእግዚአብሔር ሰው ብስጣውሮስም ‹‹በልዩ ልዩ ዓይነት ፈተናዎች ፈትኑኝና ሥራዬን ካዩ በኋላ ያመነኩሱኛል›› አሏቸው፡፡ ከዚህም በኋላ አቡነ ብስጣውሮስ በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደት እየተጋደሉ ገዳሙን በጉልበት ሥራ ብዙ ካገለገሉ በኋላ ከገዳሙ አበምኔት ከዓቃቤ ሰዓት አባ ዘወልደ ክርስቶስ እጅ ምንኩስናን ተቀበሉ፡፡ ተጋድሎአቸውንም ከበፊቱ ይበልጥ በማብዛት መኖር ጀመሩ፡፡
እናታቸው የልጃቸውን መመንኮስ ሰምተው ወደ ሐይቅ መጡ ነገር ግን አቡነ ብስጣውሮስ እናታቸውን ወጥተው ላለማየት ተሠወሩ፡፡ አበምኔቱም በብዙ ፍለጋ አግኘተዋቸው ‹‹ልጄ እናትህ አንተን ለማየት ከሩቅ ሀገር መጥታለችና ሄደህ አግኛት›› ሲሏቸው አቡነ ብስጣውሮስም ‹‹አባቴ ሆይ ጌታችን በወንጌል ያለውን አያስታውሱምን? ‹እነሆ እናትና ወንድሞችህ በውጭ ቆመዋል ባሉት ጊዜ ጌታችን በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ ከሚፈጽም በቀር እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው?› ብሎ ተናግሮ የለምን? ስለዚህ ወደ እናቴ አልሄድም›› ብለው ለአበምኔቱ መለሱላቸው፡፡ አበምንቱም ‹‹ከመንገዱ ርቀት የተነሣ እናትህ በብዙ ድካም መጥታለችና ልታያት ይገባል›› ብለው ግድ አሏቸው፡፡ አቡነ ብስጣውሮስም ሄደው እናታቸውን ካገኟቸው በኋላ እናታቸውም በዛው መንኩሰው በባሕሩ ዙሪያ ካለው ከሴቶች ገዳም ገብተው ማገልገል ጀመሩ፡፡
አቡነ ብስጣውሮስ ከመልካም የጉልበት ሥራ ጋር ቀን ቀን የዳዊትን መዝመር፣ የነቢያትን መጻሕፍትና መኅልየ መኅልይን ሲደግሙ ይውላሉ ሌሊት ሌሊት ሐይቁ ውስጥ ገብተው እጅግ አብዝተው ሲጸልዩ የብርሃን ዓምድ ተተክሎ ይታይ ነበር፡፡ ጸሎታቸውንም ሲጀምሩ ሰማያት ይከፈቱ ነበር፡፡ ቅዱሳን መላእክትንም ሲወጡ ሲወርዱ ያዩአቸዋል፡፡ አቡነ ብስጣውሮስ በእንደዚህ ዓይነቱ ተጋድሎ ብዙ ሲያገለግሉ ዜና ትሩፋታቸው በሁሉ ዘንድ በዓለም ተሰማ፡፡ አስተዳዳሪው ዓቃቤ ሰዓቱ አቡነ ዘወልደ ክርስቶስም እርጅና ሲጫናቸው ማኅበሩን ሰብስበው ‹‹በእኔ ቦታ አባት የሚሆናችሁን ምረጡ›› አሏቸው፡፡ እነርሱም ‹‹እግዚአብሔር ያመለከተህን አንተ ሹምልን›› አሏቸው፡፡ አባ ዘወልደ ክርስቶስም በጸሎት ከጠየቁ በኋላ ‹‹እግዚአብሔርና እኔ አባት ይሆኑላችሁ ዘንድ አቡነ ብስጣውሮስን መርጠንላችኋል›› አሏቸው፡፡ ቀጥሎ አበምኔቱ ስለ አቡነ ብስጣውሮስ እንዲህ በማለት ትንቢት ተናገሩ፡- ‹‹እርሱ ሃይማኖቱ የቀና ምግባሩ ያማረ በተጋድሎም የጸና በጸሎቱ ሀገርን ይጠብቃል፣ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን በነገሥታቱና በመኳንንቱ ፊት ያደርጋል›› እያሉ ለማኅበሩ በነገሯቸው ጊዜ እጅግ ደስ ተሰኙ፡፡ አቡነ ብስጣውሮስ ግን ይህን ሲሰሙ የመረረ ልቅሶን አለቀሱ፤ ከእነርሱም ዘንድ ይሸሹ ዘንድ ወጥተው በመርከብ ተጭነው ሄዱ፡፡ ነገር ግን ደርሰው ይዘው በእግዚአብሔር ፈቃድ ይሾሟቸው ዘንድ ይዘው አሰሯቸው፡፡ በዚህም ጊዜ ከሰማይ ‹‹ብስጣውሮስ የአባትህን የአበምኔቱን ቃል አታስተሐቅር›› የሚል ቃል ተሰማ፡፡ ማኅበሩም ይህንን ከሰማይ የመጣውን ቃል በሰሙ ጊዜ እጅግ ተደስተው እግዚአብሔርን አመሰገኑ፡፡ ከዚህም በኋላ አቡነ ብስጣውሮስን እንደ ሕጋቸውና እንደ ሥርዓታቸው የሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም አበምኔትና ዓቃቤ ሰዓት በማድረግ ሾሟቸው፡፡
አቡነ ብስጣውሮስም በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ወንበር በተቀመጡ ጊዜ የተሰወረውን ሁሉ የሚያዩ ሆኑ፡፡ ፊታቸውም እንደ ጨረቃ የሚያበራበት ጊዜ ነበር፣ ለአገልግሎትም ወደ ቤተ መቅደስ በገባ ጊዜ ቅዱሳን መላእክት ክንፋቸውን እየጋረዱ ይቀበሉት ነበር፡፡ ጻድቁ ጸሎተ ዕጣን ሲያሳርጉ እያለቅሱ ነበር፤ የጌታችንን መከራ እያሰቡ ሰውነታቸውን በድብቅ ይገርፋሉ፤ ድኆችንና ጦም አዳሪዎችን ሁሉ የሚንከባከቧቸው አባት ሆኗቸው፡፡ ገዳሙንም አፍርሰው ሊዘርፉ የመጡትን ወራሪዎች አባታችን ወደ መቅደስ እየገቡ በጸሎት እያሰሯቸው አሳፍረው ይመልሷቸው ነበር፡፡ አቡነ ብስጣውሮስ በእንዲህ ዓይነት ተጋድሎ ገዳሙንና ሀገራችንን እየጠበቁ ሲኖሩ በመሀል የቅብዐት እምነት ነገር በገዳሙ ተነሣ፡፡ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችንን አምላካችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ‹‹ከትስብእት ጋር ከተዋሐደ በኋላ መንፈስ ቅዱስ ተቀባ፣ በዚህም ቅብዐት በጸጋ ልጅ፣ ንጉሥም፣ ነቢይም፣ ሊቀ ካህናትም ተባለ›› የሚሉ ከሃዲያን ተነሡና የእግዚአብሔር ሰው ብፁዕ አባታችን ብስጣውሮስ ይህንን የክሕደት ትምህርት ሰምተው እጅግ እያዘኑና እያለቀሱ የካዱትን ሰዎች በብዙ ምሳሌ እያደረጉ ማስተማር ጀመሩ፡፡ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ ቅብዐት በጸጋ ልጅ እንዳልሆነ፣ ነገር ግን በባሕርይው የአብ ልጅ እንደሆነ፣ እርሱ ራሱ ቅብ፣ እርሱም ራሱ ቀቢ፣ እርሱ ራሱ ተቀቢ እንደሆነ በብዙ ምሳሌ እያደረጉ የቀደሙ የአባቶቻችንንም ትምህርት ሁሉ እየጠቀሱ አስተማሯቸው፡፡ ነገር ግን ሰይጣን አንድጊዜ አስክዷቸዋልና አንዳንዶቹ እምቢ አሏቸው፡፡ በዚህም ጊዜ ሐዋርያት ከመሠረቷት አንዲት ቤተ ክርስቲያን አውግዘው ለዩአቸው፤ ቤተ ክርስቲያንም ሰላም ሆነች፡፡ በዚህም አባታችን ከሃድያንን የሚዘልፉ ዳግማዊ ቄርሎስ ተባሉ፡፡ ይህም ክህደት መጀመሪያ ሰይጣን ለጳውሎስ ሳምሳጢን ያስተማረው ነው፡፡ ጳውሎስ ሳምሳጢን በገዳም ቅጠል እየበላ የሚኖር ተሐራሚ መናኝ ነበር፡፡ በጾም በጸሎት ሲኖር ሰይጣን ራሱን ሰውሮ መጥቶ ተገለጠለትና ‹‹ጸሎትህ በእግዚአብሔር ዘንድ ተሰምቶልሃል፤ ነገር ግን አምላክ ያለሩካቤ በድንግልና የተወለደ አይምሰልህ በሩካቤ ተወለደ እንጂ፤ ይህም ልጅ ደግ ሰው ሆነ፣ በ30 ዘመኑ በዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ተጠመቀ፣ መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል በራ ላይ ተቀመጠ፣ ያን ጊዜም ይህ ሰው በጸጋ የሥላሴ ልጅ ሆነ›› ብሎ አስተማረው፡፡ ጳውሎስ ሳምሰጢንም ሰይጣን የነገረውን ነገር በልቡ አምኖ ለደቀ መዝሙሩ ለተያስሮስ አስተማረው፡፡ ተያስሮስም ለድያድርስ አስተማረው፡፡ ድያድርስም ለንስጥሮስ አስተማረው፡፡ ንስጥሮስም ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችንን አምላካችንን ‹‹መንፈስ ቅዱስ ያደረበት ዕሩቅ ብእሲ ነው›› ብሎ ለልዮንና ለመርቅያን አስተማራቸው፡፡
ንስጥሮስ ይህን አዲስ የክህደት ትምህርት እንዳመጣ በሰሙ ጊዜ 200 ኤጲስ ቆጶሳት በቅዱስ ቄርሎስ ዘእስክንድርያ መሪነት በኤፌሶን ተሰብስበው ሲያስተማሩት እምቢ ቢላቸው አውግዘው ለዩት፡፡ ንስጥሮስም ሰውነቱ መግሎ ክፉ አሟሟት ሞተ፡፡ በኋላም መርቅያን ሲነገሠና ልዩንም የሮም ሊቀ ጳጳስ ሲሆን ሁለቱም አባታቸው ንስጥሮስ ያስተማራቸውን ሃይማኖት ማስፋፋት ቻሉ፡፡ እነ ልዮንም ንስጥሮስ በተወገዘበት ጉባዔ ላይ የነበሩትና አሁን ለሥጋቸው የፈሩ አባቶችን ይዘው ከንስጥሮስ ክህደትና ከቅዱስ ቄርሎስ ትምህርት አወጣጥተው የራሳቸውን የረከሰ ሃይማኖታዊ ድንጋጌ አወጡ፡፡ ‹‹ክርስቶስ ሁለት አካል ነው፣ አንዱ የማርያም ልጅ አንዱ የእግዚአብሔር ልጅ በመቀራረብ አንድ ሆኑ ያለውን አውጥተው ከቅዱስ ቄርሎስም ቃልና ከንስጥሮስ ክህደት ቀላቅለው መለኮት የመለኮትን ሥራ ይሠራል፣ ትስብእትም የትስብእትን ሥራ ይሠራል፤ በሁለት መንገድ አንዱ ተአምራትን ያደርጋል ሁለተኛው መከራን ይቀበላል ስለዚህም ትስብእት ከመለኮት ያንሳል›› ብለው ጻፉ፡፡ ይህንንም የክህደት ጽሕፈታቸውን ለቅዱስ ዲዮስቆሮስ ላኩለት፡፡ እርሱም ሄዶ ከክህደታቸው እንዲመለሱ አስተማራቸው፡፡ ‹‹በአንዱ ክርስቶስ ላይ ለምን የሁለትነት ነገር ትናገራላች? ወደ ሠርግ ቤት ተጠርቶ የሄደው ውኃውንም የወይን ጠጅ ያደረገው እርሱ አንዱ ክርስቶስ ነው…›› እያለ በብዙ ምሳሌ ካስተማራቸው በኋላ ልዮንንና መርቅያን የጻፉትን የክህደት ጽሕፈት በፊታቸው ቀደደው፡፡ እነርሱ ግን አንድ ጊዜ ክደዋልና የቅዱስ ዲዮስቆሮስን ፂሙን ነጭተው ጥርሱን አውልቀው ብዙ አሠቃዩት፡፡ እርሱም የነጩትን ፂሙንና ያወለቁትን ጥርሱን ሰብስቦ ‹‹እነሆ የሃይማኖቴን ፍሬ ተቀበሉ›› ብሎ ለእስክንድርያ ክርስቲያኖች ላከላቸው፡፡ ከሃዲያኑም ወደ ጋግራ ደሴት አጋዙትና በዚያው ዐረፈ፡፡
ሰይጣን ለመጀመሪያ ጊዜ ለጳውሎስ ሳምሳጢን ያስተማራትን ያችን ክህደት በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ሰይጣን የሚያድርባቸው ሰዎች እየተቀባበሏት እስከ ንስጥሮስንና እስከ ልዮን ድረስ ከደረሰች በኋላ የልዮን ልጅ በሆነው በአውፍንስ አማካኝነት በዐፄ ሱስንዮስ ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ ገባች፡፡ አውፍንስም ክህደቱን ለሁለት የሀገራችንን መነኮሳት አስተማራቸው፡፡ ለአንደኛው ‹‹ወልድ ሦስት ልደት አለው፣ በመጀመሪያ ከአብ ተወለደ ዳግመኛም በመንፈስ ቅዱስ ሥጋ ከድንግል ተወለደ ሦስተኛም በቤቴልሔም ተወለደ›› ብሎ ካስተማረውና ካስካደው በኋላ ስሙን ‹‹ተክለ ሃይማኖት›› ብሎ ጠራው፡፡ ሁለተኛውንም መነኩሴ ለብቻው ጠርቶት ‹‹ልጄ ሆይ ስማኝ ልብ አድገህም ዕወቅ፣ ወልድ በመንፈስ ቅዱስ ቅብዐት የከበረ ነው፣ ይኸውም ሳይዋሃድ ማደር ነው›› ብሎ ካስተማረውና ካስካደው በኋላ ስሙን ‹‹ኤዎስጣቴዎስ›› ብሎ ጠራው፡፡ እነዚህም የካዱ ሁለቱ መነኮሳት በየሀገሩና በየአውራጃው እየዞሩ ሀገራችን ኢትዮጵያን በክህደት ትምህርታቸው አጥፍተዋት ነበር፤ ነገር ግን ብዙ ቅዱሳን አባቶቻችንና እናቶቻችን ይህን ክህደት በትምህርታቸውና በተአምራታቸው እንዲገታ አድርገውታል፡፡ አቡነ ብስጣውሮስም እነዚያን ከሃዲዎች አውግዘው ለዩአቸው፡፡ ከዚህም በኋላ ከሃዲያኑ አባታችንን ከሰሷቸውና ከጎንደሩ ንጉሥ ጋር አጣሏቸው፡፡ ንጉሡም የእነዚያን ካሃዲዎች እምነት አምኖ ተቀብሎ ነበርና አባታችንን ወደ ጎንደር እንዲያመጧቸው ጭፍሮቹን ላከ፡፡ አቡነ ብስጣውሮስም ነገሩን አውቀው ስለ ቀናች ሃይማኖት ይመሰክሩ ዘንድ አንደበት እንዲሆናቸው ጌታችንን በጸሎት ሲጠይቁ ጌታችንም ‹‹ልጄ ብስጣውሮስ ሆይ አይዞህ እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፣ እኔ ስለመሠረትኳት አንዲት ሃይማኖት ጽና›› አላቸው፡፡ አባታችንም ወደ ንጉሡ ዘንድ ሄዱና ንጉሡ ሰዎቹን ስለማውገዙ ጠየቃቸው፡፡ አባታችንም ንጉሡን ስለ ቀናች ሃይማኖት እየመሰከሩለት አስተማሩት፡፡ ንጉሡም በብዙ ስጦታና ሽንገላ ሊያታልላቸው ሞከረ ነገር ግን አባታችን አጥብቀው ተቃወሙት፡፡ ንጉሡም ዕውቀታቸውንና ጽናታቸውን ባየ ጊዜ አባታችንን በእግር ብረት አሳስሮ አሥር ቤት ውስጥ ጣላቸው፡፡ በዚህም ጊዜ የእግር ብረቱ እንደሰም ቀልጠ፡፡ ወታደሮቹም ይህንን ተአምር አይተው ፈርተው ሄደው ለንጉሡ ነገሩት፡፡ ንጉሡም ሰምቶ ደነገጠ፤ እየፈራና እየተንቀጠቀጠ ወደ አባታችን መጥቶ ሰገደና ‹‹አባቴ ሆይ ይቅር በሉኝ የሃይማኖትንም ነገር እንደገና አስተምሩኝ›› አላቸው፡፡ እሳቸውም አስተምረው ባረኩት፡፡ በመከራቸውም ታግሰው ለልጆቻቸውና ለእኛም የሐዋርያትን ሃይማኖት አጸኑልን፡፡ ዕድሜአቸውም 90 ዓመት በሆነው ጊዜ ዕረፍታቸው እንደደረሰ ዐውቀው የቀናች ሃይማኖት በሀገራችን ለዘለዓለም ጸንታ ትኖር ዘንድ ጌታችንን አጥብቀው ለመኑት፡፡ ጌታችንም በደሙ የመሠረታት የቀናች ሃይማኖት በሀገራችን ጸንታ እንደምትኖርና ሌላም የምሕረት ቃልኪዳን ከገባላቸው በኋላ ግንቦት 19 ዐረፉ፡፡
በዚያችም ዕለት ሐይቅ አለቀሰች፤ የሐይቅም ባሕር ሦስት ዓመት በኃይል ስትታወክ አቡነ አላኒቆስ ይህ ሁሉ የሆነው ስለ አባታችን ስለ ብስጣውሮስ ማረፍ መሆኑን ዐውቀው ወደ ንጉሡ ሄደው የአባታችንን ዐፅም እንዲሰጣቸው ጠየቁት፡፡ ንጉሡ ግን ‹‹በረድኤታቸው ይጠብቁኛልና አልሰጥም›› አላቸው፡፡ ንጉሡ ስለከለከላቸው አቡነ አላኒቆስም ቁስቋም ወደምትባል በወርቅና በከበረ ዕንቁ ወደተሸለመች ወደ እመቤታችን ቤተ ክርስቲያን ሄደው በእመቤታችን ሥዕል ሥር ወድቀው አለቀሱ፡፡ ሥዕሏም በሰው አንደበት አናግራ ካጽናናቻቸው በኋላ የአባታችን ዐፅም ከመሠዊያው በስተቀኝ በኩል እንደሚገኝ ነገረቻቸው፡፡ አቡነ አላኒቆስም ዐፅማቸውን አፍልሰው ወደ ሐይቅ በተመለሱ ጊዜ የመዓዛው ሽታ የንጉሡን አገር ሁሉ መላው፤ መቃብሩ በነበረበት ቦታም የብርሃን ዓምድ ተተክሎ ታየ፡፡ ንጉሡም መነኩሴው የአባታችንን ዐፅም እንደወሰዱ ባወቀ ጊዜ መነኩሴውን ይዘው ከአባታችን ዐፅም ጋር ያመጡለት ዘንድ ብዙ ፈረሰኛ ወታደሮቹን ላካቸው፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር በጥበቡ ሰውሯቸዋልና አቡነ አላኒቆስን ሊያገኟቸው አልቻሉም፡፡ አቡነ አላኒቆስም የቅዱስ አባታችንን ዐፅም ወስደው በሐይቅ በመሠዊያው በስተቀኝ በኩል በቀበሩት ጊዜ በፊት ያስቸግር የነበረው የበሐሩ ኃይለኛ ንውጽውጽታ በአንድ ጊዜ ጸጥ አለ፡፡ ሌላም ብዙ ተአምራት ተደርገው ታዩ፡፡ ይኸውም ፍልሰተ ዐፅማቸው የካቲት 8 ቀን የተፈጸመ ነው፡፡
የአራቱ ቅዱሳን ነገሥታት፡- ከላስታ (ከዛጉዌ) ነገሥታት መካከል ቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ፣ ቅዱስ ገብረ ማርያም፣ ቅዱስ ላሊበላና ቅዱስ ነአኵቶለአብ እነዚህ አራቱ ነገሥታት እንደ መልከጼዴቅ (ዘፍ 14፡18) ክህነትን ከንግሥና፣ ቅድስናን ከንጽሕና ጋር አንድ አድርገው በመያዝ እግዚአብሔርንም ሰውንም በቅድስና አገልግለው አልፈዋል፡፡ በንግሥናቸው ሀገርን በመልካም ሥራና በቅድስና ከማስተዳደራቸው በተጨማሪ ቅዱሳን ጻድቃን ሆነው እግዚአብሔርን በብዙ ድካም በመልካም ተጋድሎአቸው ያገለገሉና አገልግሎታቸውም ሆነ ቅድስናቸው በእግዚአብሔር ዘንድ ስለተመሰከረላቸው ጌታችን የሰጣቸውን ቃልኪዳን መሠረት በማድረግ ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን የቅድስና ማዕረግ ሰጥታ፣ በስማቸው ቤተክርስቲያን አንጻ፣ ጽላት ቀርፃ በዓላቸውን እያከበረች መታሰቢያቸው ተጠብቆ ለዘለዓለም እንዲኖር አድርጋለች፡፡
ቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ፡- ግንቦት 19 ቀን ሲወለድ እንደነ ተክለሃይማኖትና እንደነ ዜና ማርቆስ ወደ ምሥራቅ ዞሮ አምላኩን ያመሰገነ ሲሆን ቤቱም በብርሃን ተሞልቶ ታይቶ አዋላጆቹን ሁሉ አስገርሟል፡፡ እርሱ ገና ሳይወለድ በፊት አጎቱ ጠንጠውድም በንግሥና ላይ ሳለ ‹‹ከአንተ በኋላ የሚነግሠው ይምርሃነ ክርስቶስ የሚባል ሰው ነው›› ተብሎ ሲነገረው ‹‹እንዲህ የሚባል ሰው በቤተ መንግሥቴ አለን?›› በማለት ቢጠይቅም እንደነቢዩ ኤርሚያስ ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ የተመረጠ ሕፃን እንደሚወለድ ነግረውታል፡፡ አርባ ዓመት የነገሠው ጠንጠውድም ቀድሞ በትንቢት እንደተነገረው ‹‹ይምርሃነ ክርስቶስ›› የሚባል የወንድሙ ልጅ መወለዱን ሲሰማ ‹‹የወንድሜን ልጅ አየው ዘንድ አምጡልኝ›› ብሎ ላከ፡፡ ባየውም ጊዜ ደም ግባቱ እጅግ ያምር ስለነበር ‹‹ይህስ መንግሥቴን ይውረስ፣ በእውነት ልጄ ነው›› ብሎ ባረከው፡፡ ሆኖም ከእርሱ ጋር ስምንት ቀን ተቀምጦ በወለዳቸው ልጆቹ መካከል በተመለከተው ጊዜ በልቡ ሰይጣን አደረበትና በቅናት ሆኖ ‹‹እርሱ ነግሦ ልጆቼ ወታደሮቹ ሊሆኑ ነው›› በማለት ይገድለው ዘንድ አሰበ፡፡ ሆኖም ግን ‹‹ለጊዜው ምንም አያውቅም ለወደፊቱም የንግሥና ምሥጢር እንዳያውቅ ወደ እናቱና አባቱ ዘንድ መልሰው በዚያ ከብት ሲያግድ ያድጋል እንጂ ሥርዓተ ንግሥናን አያውቅም›› በማለት ስለተመከረ ወደ እናቱ ላከው፡፡ በኋላም በጥበብና በብልሃት አስተዋይ ሆኖ ማደጉን በሰማ ጊዜ ሊገድለው አሽከሮቹን ላከ፡፡ እናቱም ተላኩት አሽከሮች ምግብ አቅርባ እርሷ ግን ነገሩን እንዲገልጽላት እግዚአብሔርን በስውር አልቅሳ ስትለምን የንጉሡ ተንኮል ስለተገለጠላት ልጇን ደበቀችው፡፡ በስውርም ወስዳ ከጳጳሱ ዘንድ ዲቁና እንዲቀበል ካደረገችው በኋላ ‹‹ልጄ ሆይ! አጎትህ ሊገድልህ ይፈልግሃልና በፊቴ ከሚገድልህ ርቀህ ብትሄድ ይሻላል፣ ያዕቆብን ከኤሳው የጠበቀ አንተንም ይጠብቅህ›› ብላ ሸኘችው፡፡ ንጉሡ አጎቱም ‹‹ይምርሃነ ክርስቶስን ፈልጎ ላገኘልኝ የመንግሥቴን እኩሌታ እሰጣለሁ›› ብሎ ቢያውጅም ይምርሃነ ክርስቶስ ግን ወደ ኢየሩሳሌም ተሰደደ፡፡ በዚያም የሌዋውያን ወገን የምትሆን ቅድስት ሕዝባን አግብቶ ቅስናም ተቀብሎ ሥጋዊውንና መንፈሳዊውን ጥበብ ተምሮ ካጠናቀቀ በኋላ ወንጌልን እየሰበከ፣ በተአምራቱም ሕመምተኞችን እየፈወሰ እግዚአብሔር እያገለገለ ኖረ፡፡ እግዚአብሔርም አጎቱ ንጉሥ መሞቱንና በንጉሡም ዙፋን እርሱ እንደሚነግሥ ነግሮት በመልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል መሪነት ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ መጥቶ በላስታ ወረዳ ሳይ (ዛሬ ሸጐላ ማርያም) ከምትባል ሀገር ደርሶ በዚያ ወንጌልን እያስተማረ፣ ድውያንን እየፈወሰ ተቀመጠ፡፡ ትምህርቱንና ተአምራቱን ያዩት የአካባቢው ሰዎች ‹‹ነፃነትና ፍቅር የሚገኝብህ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ! እኛ ሰላማዊ ብርሃናዊ ብለን ስም አወጣንልህ፣ ያንተ ግን ስምህ ማን ይባላል ንገረን›› አሉት፡፡ እርሱም ‹‹ስሜ ይምርሃነ ክርስቶስ ነው›› ባላቸው ሰዓት ሕዝቡ ሁሉ በሹክሹክታ ‹‹ይምርሃነ ክርስቶስ የሚባል ሲነግሥ ሃይማኖት ይቀናል፣ ፍርድ ይስተካከላል፣ በዘመኑም የሮም ሰዎች ለኢትዮጵያ ይገዛሉ›› ሲሉ አባቶቻችን ሰምተናል አሉ፡፡ ከጠንጠውድምም ሞት በኋላ ማንም እንዳልነገሠ ሲያረጋግጡ የማን ልጅ እንደሆነ እንዲነግራቸው በእግዚአብሔር ስም ለመኑትና ‹‹የጠንጠውድም የታናሽ ወንድምና የዣን ስዩም ታላቅ ወንድም የሆነው የግርማ ስዩም ልጅ ነኝ›› አላቸው፡፡ እነርሱም ‹‹የተነገረው ትንቢት ደርሷልና ሳንዘገይ እናንግሠው›› ብለው ሥርዓተ መንግሥቱን ፈጽመው በዙፋን ላይ አስቀመጡት፡፡
ለቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ መስቀል ከሰማይ እንደወረደለት፡- ቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ በትረ መንግሥቱንም ከያዘ በኋላ ሁሉም ሰው እንደወንጌሉ ቃል በአንድ ለአንድ ጋብቻ ብቻ ተወስኖ እንዲኖር በግዛቱ ሁሉ አወጀ፡፡ እግዚአብሔርም የሚመሰገንበት ቤት መሥራት አሰበና የተፈቀደለትን ቦታ እንኪያገኝ ድረስ ዛዚያ በምትባል ልዩ በሆነች ስፍራ ድንኳን ተክሎ እንደሙሴ እግዚአብሔርን ማገልገል ጀመረ፡፡ ዘጸ 33፡7፡፡ ሰኔ 21 ቀንም ቀድሶ ሕዝቡን ከማቁረቡ በፊት ኅብስቱንና ጽዋውን የእግዚአብሔር መልአክ ሕዝቡን ከሚባርክበት ሰማያዊ መስቀል ጋር ከሰማይ አምጥቶለታል፡፡ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ሕዝቡን ከሰማይ በወረደለት መስቀል እየባረከና ሰማያዊውን ኅብስትና ጽዋ እያቆረበ ለ22 ዓመት በድንኳኗ ውስጥ ኖሯል፡፡ ዛሬም ድረስ ያንን ሰማያዊው መስቀል በቤተመቅደሱ የሚያገለግሉት ካህናት አባቶች ቤተመቅደሱን ለመሳለም የሚመጣውን ሕዝበ ክርስቲያን በበዓል ቀን ይባርኩበታል፡፡
መድኃኔዓለም ክርስቶስ ለይምርሃነ ክርስቶስ ተገልጦለት ቤተመቅደሱን ሥራ ብሎ እንደነገረውና ቃልኪዳን እንደሰጠው፡- ቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ ሰማያዊ ኅብስትና ጽዋ እየወረደለት ለ22 ዓመት በድንኳኗ ውስጥ ካገለገለ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በክብር ተገልጦለት እንዲህ አለው፡- ‹‹ወዳጄ ይምርሃነ ክርስቶስ ይህን ሥፍራ (ዛዚያን) ልቀቅ፣ ከእንግዲህ ወዲህ በዚህ ቦታ ሰማያዊ ኅብስትና ሰማያዊ ጽዋ አይወርድልህም፡፡ ወደማሳይህ ቦታ ተነሥተህ ሂድ፣ በዚያም እስከ ዕረፍትህ ቀን ድረስ ሰማያዊ ኅብስትና ሰማያዊ ጽዋ ይወርድልሀል፡፡ ይህን ዓለም ለማሳለፍ እስከምመጣበት እስከ ዕለተ ምፅዓት ድረስ የእኔ ጌትነት የአንተም የቅድስና ሕይወት የሚነገርበት፣ የሥጋህ የዕረፍት ቦታ የሚሆንበት፣ ለምትሠራው መቅደስ ክዳን የሚሆን ሣር የማይፈልግ ሰፊ ዋሻ አለ፣ በዚያ ቤተ መቅደሴን ሥራ፣ እኔም በምትሠራው ቤተ መቅደስ ከአንተ ጋር ለዘለዓለም ቃልኪዳኔን አቆማለሁ፡፡ በምታንጸው ቤተ መቅደስ ውስጥ ‹አቤቱ የይምርሃነ ክርስቶስ አምላክ ሆይ! ስለወዳጅህ ስለ ቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ ብለህ ይቅር በለኝ› እያለ ‹አባታችን ሆይ!› የሚለውን ጸሎት የሚጸልይ ዕለቱን እንደተጠመቀ አደርገዋለሁ፡፡ ወደ አንተ በእምነት ከኃጢአቴ እነፃለሁ ብሎ በእምነት የሚመጣውን ሁሉ ከእናትቱ ማኅፀን እንደተወለደ ሕፃን ልጅ አድርገዋለሁ፤ ኃጢአቱንም ይቅር እለዋለሁ፣ ኃጢአቱ ከባድ ጭነት እንደያዘች መርከብ ቢከብድም እንደገለባ አቀልለታለሁ፣ እንደቀይ ግምጃ ቢሆንም እንደነጭ ፀምር (ግምጃ) እንደጥቁር በርኖስ ቢሆንም እንደበረዶ አነፃዋለሁ፤ በስምህ የለመነኝን ሁሉ እሰጠዋሁ፣ ወደ መቃብርህም ቦታ እኔና የባሕርይ አባቴ አብ የባሕርይ ሕይወቴ መንፈስ ቅዱስ በፍቅር ካልሳብነውና በረድኤት ካላቀረብነው በቀር ሊመጣ የሚችል የለም፡፡ በመቃብርህ እየዞረ ‹የቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ አምላክ ሆይ! ስለወዳጅህ ስለ ቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ ብለህ ይቅር በለኝ፣ ይምርሃነ ክርስቶስ ሆይ በቃልኪዳንህ ጠብቀኝ (ይምርሃ ፍታኝ)› እያለ የሚጸልየውን አንተ በከበርክበት ክብር አከብረዋለሁ፡፡ የእኔን ጌትነት፣ የአንተን የቅድስና ሕይወት የሚንቅ የሚያቃልል ግን ንስሐ ካልገባ በቀር ከሰማያዊ ክብር የተለየ ይሆናል፡፡ የዕረፍትህን መታሰቢያ የሚያደርግ፣ በአማላጅነትህ ለሚታመን፣ ገድልህን የሚጽፍና የሚያጽፍ የዘላለም ክብርን አጐናጽፈዋለሁ፤ ገድልህን የሚያነብ በአንዷ ቃል ሰባት እጥፍ ክብር በመንግሥተ ሰማያት እሰጠዋለሁ፤ ወደዚህች ቦታ አንተን ብሎ የመጣውን እንግዳ ሁሉ ካላሰበበት ቦታ አላሳድርብህም፤ በምታንጸው ቤተ መቅደስ በዕረፍትህ መታሰቢያ ቀን ከጠዋት እስከ ማታ ተግቶ የሚጸልይ በስሜ ከሞቱ ከ144,440 የቤቴልሔም ሕፃናት ጋር እቆጥረዋለሁ፤ ለቤተ መቅደስህ ዕጣን ያገባ ሥጋዬ እንደተገነዘበት እንደ ኒቆዲሞስ ሽቱ እቀበለዋለሁ፣ አልባሳት የሚያገባ ኒቆዲሞስና ዮሴፍ ሥጋዬን እንገነዙበት መግነዝ አደርግለታለሁ፤ ለመሥዋዕት የሚሆን ንጹሕ የግብር ስንዴ፣ ወይን (ዘቢብ) የሚያመጣውን እንደ መልከጼዴቅ እቀበለዋለሁ፤ ለመብራት የሚሆን ጧፍ፣ ሰም ሌላም የቤተ መቅደስ መገልገያዎችን ሁሉ ለቤተ መቅደስህ የሚያገባ በሰማያዊ ክብር አከብረዋለሁ፡፡ ነገ ማለዳ ተነሥተህ ወግረ ስሂን ወደሚባለው የዕረፍትህ ቦታ ወደሚሆነው ዋሻ ሕዝብህን አስከትለህ ሂድ፤ በዚያም ቤተ መቅደሴን ሥራ›› ብሎ ጌታችን ቃልኪዳን ከሰጠው በኋላ ሰላምታ ሰጥቶት በክብር ወደ ሰማይ ዐርገ፡፡ ቤተመቅደሱንም አንጾ ሲጨርስና በዕረፍቱም ቀን በድጋሚ ተገልጦለት ይህንን ቃልኪዳን ደግሞለታል፡፡
ይምርሃነ ክርስቶስ ቤተ መቅደሱን የሚሠራበትን ቦታ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል እንዳሳየው፡- ቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ ከመድኃኔዓለም ክርስቶስ ቃልኪዳን ከተቀበለ በኋላ አገልጋዮቹን አስከትሎ ሲጓዝ ቀድሞ ግፃት ትባል ከነበረችው ዛሬ ግን ወግረ ስሂን ከምትባለው ሰፊ ዋሻ ሲደርስ ቅዱስ ሩፋኤል ‹‹እግዚአብሔር ያዘዘህ ቦታ ይህ ነው፣ በዚህ ቤተ መቅደሱን ሥራ›› አለው፡፡ ዙሪያው በደን የተሸፈነ ስለነበር የዋሻውን መግቢያ እያስቆረጠ ሲሄድ የአካባቢው ሰዎች ደም እያፈሰሱ ለአጋንንት መሥዋዕት የሚያቀርቡበት አንድ ወይራ ነበርና አገልጋዩ ክርስቶስብነ ያንን ዛፍ ሲቆርጠው በውስጡ ያደረው ሰይጣን ክርስቶስብነን አንቆ ጣለው፡፡ ነገር ግን ቅዱስ ሩፋኤል አዛፍ ከሚባል ሀገር ወስዶ ጣለው፡፡ የቅድስት ኢየሉጣ ልጅ ሰማዕቱ ቅዱስ ቂርቆስም በአፀደ ነፍስ ብፁዕ ይምርሃነ ክርስቶስን ረድቶታል፡፡ ይህም ታሪክ በገድለ ቅዱስ ቂርቆስ 3ኛ ተአምር ላይ በሰፊው ተጠቅሷል፡፡ ይህንንም ቀጥሎ ባለው ርዕስ ላይ እናየዋለን፡-
በቅዱስ ቂርቆስ ገድል ላይ ሕፃኑ ቂርቆስ ቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስን እንደረዳው ተጽፏል፡- ‹‹በቅድስት ሀገር በሮሐ ከአምላኩ ዘንድ የክህነትን ሥልጣን የተቀበለ የዓለምን ተድላ ደስታ ንቆ መንግሥቱን ከተወ በኋላ በገዳም ሲኖር ለ40 ዓመት ያህል በበዓላትና በየሰንበቱ ከሰማይ ኅብስትና ወይን የወረደለት አንድ ጻድቅና ካህን ነበር፡፡ የጽድቁም ምልክት እስካሁን ክቡር ሥጋው ካረፈበት ሥፍራ አለ፡፡በመንግሥቱ ሳለ በእግዚአብሔር ፈቃድ መንፈስ ቅዱስ ባመለከተው ቦታ በባሕር ላይ ቤተ ክርስቲያን ሊያንጽ ተነሣ፡፡ ንጉሥ ይምርሃነ ክርስቶስን የቤተ ክርስቲያኑን መሠረት ለማሳመር ሁሉ እያንዳንዱ ደንጊያና ሸክላ አንጨትም እንዲሸከም ትእዛዙን ይነግር ዘንድ በግዛቱ ዓዋጅ ነጋሪ አዞረ፡፡ ንጉሡም ከባሕር ዳርቻ ቆሞ አገልጋዩ በባሕሩ ላይ ለቤተክርስቲያኑ መሠረት ርብራብ ሊያደርግ ከባሕሩ ገባ፡፡ ይህንንም ሲያደርግ የባሕር ጋኔን ወጥቶ መታው፣ ፈጥኖም ሞተ፡፡ ንጉሥ ይምርሃነ ክርስቶስ የሰይጣንን መተነኳኮል አይቶ አብዝቶ አዘነ፡፡ በዚህ ጋኔን ስለሞተ አገልጋዩ ስለ ቤተክርስቲያንም መታነጽ የሚያደርገውን ሲያስብ ስለጽድቅ የተጋደለ ማር ቂርቆስ ድንገት በታላቅ ክብር ተገልጦ ‹የተቀባህ ንጉሥ የከበርህም ካህን ሆይ! በአምላኬ ሥልጣን የሞተ አገልጋይህን እኔ አስነሣልሃለሁ፣ ጋኔኑንም እበቀለዋለሁ፣ አንተም ኃይል በተደረገልህ ሥፍራ በምትሠራት መቅደስ ውሰጥ በስሜ የተሠየመ ታቦት ታኖራለህ› አለው፡፡ ንጉሡም ‹የክርስቶስ ሰማዕት ሆይ! እንዳልኸው አደርጋለሁ› ብለ መለሰ፡፡ ያንጊዜም ማር ቂርቆስ እጁን ዘርግቶ የጋኔኑን የራስ ጠጉር ይዞ ከባሕር ውስጥ አወጣው፡፡ ቁመቱ ፈጽሞ ረጅም፣ ሁለንተናውም በእሳት እንዳቃጠሉት የእንጨት ግንድ ጥቁር ነበር፡፡ ከቅድስት ሀገር ከሮሐ ወደ ጎጃም ምዕራባዊ ክፍል እንደ ድንጊያ ወረወረው፣ በዚያም ሞተ፤ የሞተው የንጉሡ አገልጋይ ግን ከሞት ተነሣ፡፡ ንጉሡም ፈጽሞ ደስ ተሰኘ፡፡ አምስት ጊዜ ከሩቅ የዞጴ እንጨት እየተሸከመ ያችን መቅደስ ሠራት፡፡ ከአገልጋየቹም ጋር ሲሠራ ይውል ነበር፡፡ ጌታ ኢየሱስም የመቅደስ ሥራዋን እያመለከተው ከእርሱ ጋር ነበረ፡፡ የመቅደስ መታነጽም ከተፈጸመ በኋላ ንጉሥ ይምርሃነ ክርስቶስ በከበረ ሕፃን ቂርቆስ ስም የተሠየመ ታቦት በውስጧ አኖረ፡፡ ኅብራቸው ባማረ የከበሩ ጌጦችና ልብሶችም አስጌጣት፡፡ በውስጧም በጥቅምት 19 ቀን ቀደሰ፡፡›› (ገድለ ቅዱስ ቂርቆስ ወኢየሉጣ ገጽ 98-100)
ወደ ቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ ገድል እንመለስና ጻዲቁ ንጉሥ ጌታችን እንዳዘዘው ቤተመቅደሱን ሊሠራ መንገዱን አስመንጥሮ ወደ ዋሻው ሲደርስ ትልቅ ባሕር አገኘ፡፡ ‹‹በዚህ ላይ እንዴት ቤተመቅደስ ልሠራ እችላለሁ?›› ብሎ ሲጨነቅ ከሰማይ ‹‹በባሕሩ ላይ እንጨት፣ በእንጨቱ ላይ ሣር፣ በሣሩ ላይ ጭቃ፣ በጭቃው ላይ ደረቅ አፈር አድርገህ ደልድለህ ቤተ መቅደሴን ሥራ›› የሚል ቃል መጣለት፡፡ ቀድሞውንም በነቢዩ ዳዊት ላይ አድሮ ‹‹ምድርን በውኃ ላይ ያጸና ምሕረቱ ለዘለዓለም ነውና›› (መዝ 135፡6) እንደተባለ አሁን ደግሞ በዚህ ጻዲቅ ንጉሥ እጅ ቤቱን በባሕር ላይ እንዲሠራ ፈቀደ፡፡ ቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስም በታዘዘው መሠረት መሥሪያዎቹን ሲሰበስብ የቅድስና ሕይወቱን የሰሙ የግብፅና የሮም ሰዎች ለመስኮት የሚሆኑ የከበሩ ድንጋዮችን (ዕምነ በረዶችን) አመጡለት፡፡ ውድ የሆኑና የከበሩ ዓለቶችንና እንጨቶችን አምጥቶ በኪነጥበባዊ ቅርጻ ቅርጾችና በሥነ ሥዕል እጅግ ውብ አድርጎ በተፈጥሮአዊ አቀማመጡ ፍጹም አስደናቂ የሆነውን ቤተመቅደሱን ሠርቶ እንደጨረሰ ሲራዳው የነበረውን የቅዱስ ቂርቆስን ታቦት አስገብቶ ከሰማይ በወረደለት መስቀሉ ሕዝቡን እየባረከ፣ ሰማያዊ ኅብስትና ሰማያዊ ጽዋ እየወረደለት እግዚአብሔርንና ሰውን ሲያገለግል ኖረ፡፡ ቅዱስ ሩፋኤልም በዘመኑ ሁሉ ይራዳው ነበር፡፡
ቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ ያሳነጸውን ቤተመቅደስ እንደገና በወርቅና በብር አክብሮ ለማነጽ ወደ እግዚአብሔር በጸሎት ቢጠይቅ ጌታችን ተገልጦለት ‹‹ቤተ መቅደስህ የታጸበትን የከበረ ድንጋይ ከወርቅና ከብር ከዕንቁም ይልቅ አከበርኩልህ፣ በወርቅና በብር ያነጸከው እንደሆነ የኋላ ሰዎች ወርቅና ብሩን ሲሉ ቤተክርስቲያንህን ያፈርሱብሃል›› ብሎታል፡፡ ቤተመቅደሱ የተሠራው በባሕር ላይ ለመሆኑ ማሳያ ይሆን ዘንድ ከቤተ መቅደሱ ሰሜናዊ ጫፍ በኩል ወደ ታች ወደ ምድር ውስጥ የምትከፈት ትንሽ መስኮት አለች፣ እርሷ ስትከፈት ውኃው ከሥር ይታያል፡፡ ይህን ግን ማሳየት የሚችሉት አባቶች ብቻ ናቸው፡፡ በዋሻው በቤተልሔሙ በኩል ውስጥ ለውስጥ እስከ አቡነ ዮሴፍ ተራራ ድረስ የሚወስድ ፍጻሜው ያልተገኘ መንገድ አለ፡፡ የቤተክርስቲያኑ አገልጋዮች በዋሸው ውስጥ ለውስጥ የ4፡30 መንገድ ያህል በመብራት ከተጓዙ በኋላ የያዙት መብራት ስላለቀባቸውና ፍርሃትም ስለያዛቸው የመንገዱን ፍጻሜ ሳያገኑት ተመልሰዋል፡፡
ቁጥራቸው ከ5ሺህ በላይ የሆኑ የሮምና የግብፅ ጳጳሳት የይምርሃነ ክርስቶስን በረከት ሊቀበሉ እንደመጡ፡- ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔርን ጌትነትና የይምርሃነ ክርስቶስ የቅድስና ሕይወት በዓለም ሁሉ መሰማት ጀመረና የሮም ሰዎችም ወደ እርሱ መጥተው 55 ውድ መስቀሎችን በስጦታ ገበሩለት፡፡ እግዚአብሔር በእርሱ ላይ የሚያደርገውን ተአምርና ቅድስናውን የሰሙ ቁጥራቸው 5740 የሆኑ የግብፅና የሮም ጳጳሳትና ኤጲስቆጶሳት፣ ቀሳውስትና ዲያቆናት እንዲሁ መነኮሳት ቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ የሚወርድለትን ሰማያዊ ኅብስትና ሰማያዊ ጽዋ በእጁ ለመቀበልና በመስቀሉ ለመባረክ መጡ፡፡ የግብፁ ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ አትናቴዎስም ‹‹ከዚህ ቅዱስ የእግዚአብሔር አገልጋይ እጅ በረከትን መቀበል እሻለሁ›› ብሎ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ከቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ ጋር ተገናኝቶ ሁለቱም በረከትን አንዳቸው ከአንዳቸው ተቀብለዋል፡፡ ቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስም ወደ እርሱ ለመጡት 5740 ደጋግ ጳጳሳትና ኤጲስቆጶሳት፣ ቀሳውስትና ዲያቆናት እንዲሁ መነኮሳት ሁሉ ቀድሶ ሰማያዊውን ሥጋ ወደሙን አቀብሏቸዋል፡፡ እነርሱም ሰማያዊውን ሥጋና ሰማያዊውን ደሙን ከተቀበሉ በኋላ ‹‹ይህን ባየንበትና በቀመስንበት ሌላ አናይም አንቀምስም ብለው የተወሰኑት ወደሌላ የሀገራችን ገዳማት የሔዱ ሲሆን ብዙዎቹ ደግሞ ከእርሱው ጋር አብረው በዚያው ዐርፈው ተቀብረዋል፡፡ ዛሬም ድረስ የእነዚህ ቅዱሳን አፅም ቤተ መቅደሱ ካለበት ጀርባ በኩል በሚገኘው ትልቅ ዋሻ ውስጥ በክብር ተቀምጦ ይገኛል፡፡
የቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ መካነ መቃብር፡- ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስን ዕረፍቱ እንደደረሰ ነግሮት ታላቅ ቃልኪዳን ከሰጠው በኋላ ቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ ጥቅምት 19 በታላቅ ክብር ዐርፏል፡፡ የቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ መካነ መቃብር የሚገኘው ራሱ ባሳነጸው መቅደስ በስተ ደቡብ አቅጣጫ ሲሆን በግምጃ የተሸፈ ነው፡፡ ለጻዲቁ ንጉሥ በተሰጠው ቃልኪዳን መሠረት አማኞች መእመናን መቃብሩን እየዞሩ ‹‹የቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ አምላክ ሆይ! ስለወዳጅህ ስለ ቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ ብለህ ይቅር በለኝ፣ ይምርሃነ ክርስቶስ ሆይ በቃልኪዳንህ ጠብቀኝ (ይምርሃ ፍታኝ)›› እያሉ በመዞርና አባታችን ሆይ የሚለውን ጸሎት እየጸለዩ ከቃልኪዳኑ በረከት ይሳተፋሉ፡፡
የአቡነ ዓቢየ እግዚእን ገድል ደግሞ አንዴ ለራሴ ልዝለቀው እመለስበታለሁ፡፡ ደሞ እየጻፍኩት ሳለ መብራት ጠፋ....እይይ...ምቀኛ!
መብራት ሄዶ ቆይቶ አሁን ስለመጣ የአቡነ ዓቢየ እግዚእን ገድል አሁን አካትቼዋለሁ፡፡
አቡነ ዓቢየ እግዚእ፡- አባታቸው ያፍቅረነ እግዚእ እናታቸው ጽርሐ ቅዱሳን ይባላሉ፡፡ ሁለቱም ሃይማኖታቸው የቀና ምግባራቸው ያማረ በእግዚአብሔር የተወዱ ናቸው፡፡ በወርቅ በብር የከበሩ ቢሆኑም ልጅ ግን አልነበራቸውም፡፡ በእመቤታችን ስም ለተቸገሩ ምጽዋትን በመስጠት ዘወትር ይማጸኑ ነበር፡፡
አንድ ቀን ድንቅ የሆነ ራእይ አየና ፈቃደ እግዚአብሔርን ሲጠባበቁ ነሐሴ 7 ቀን ጽርሐ ቅዱሳን ፀነሰችና ግንቦት አንድ ቀን እንደ ፀሐይ የሚያበራ ልጅ ወለደችና በ40 ቀኑ ሲጠመቅ ስሙን ዓቢየ እግዚእ አሉት፡፡ ያጠመቁትም የአክሱሙ ሊቀ ጳጳስ መተርጉም ሰላማ ሲሆኑ እሳቸውን ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ሕጻኑን እንዲያጠምቁት በማዘዝ በክንፎቹ ተሸክሞ ከአክሱም ወደ ተንቤትን ምድረ መረታ አመጣቸውና አጠመቁት፡፡ እርሳቸውም ‹‹ይህ ሕጻን ድውይ የሚፈውስ ሙታንን የሚያነሣ ቅዱስ ይሆናል›› ብለው ትንቢት ተናግረዋል፡፡ ያፍቅረነ እግዚእ እና ጽርሐ ቅዱሳን እንግዳን መቀበል ልማዳቸው ነበርና አንድ ቀን ሦስት አጋንንት በሽማግሌ አምሳል ሆነው በእንግድነት እቤታቸው ገቡና ‹‹ልጃችሁን የሐዋርያትን መጻሕፍትን መዝሙረ ዳዊትንና አርጋኖንን እንድናስተምርላችሁ ስጡን›› አሏቸው፡፡ ወላጆቹም ገና ሕጻን መሆኑን በመናገር ሲከራከሩ ቅዱስ ሚካኤል ደርሶ እነዚያን አጋንንት አጠፋቸው፡፡ አጋንንቱም ይህንን ዘዴ ተጠቅመው ሕጻኑን ዓቢየ እግዚእ ወስደው ሊገድሉት ነበር ምክንያቱም በእርሱ ምክንያት ነፍሳት እንደሚድኑ ዐውቀዋልና፡፡
ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ የእግዚአብሔርን ከጠሩበት ምንም ነገር ከማድረግ ወደኋላ አይልም ነበር፡፡ ከልጆችም ጋር ሲጫወቱ ልጆቹ ‹‹ስለ እግዚአብሔር ብለህ ይህን አድርግልን…›› ሲሉት ያደርግላቸዋል፡፡ በእረኝነት ሳሉ ምሳውንም ሆነ እራቱን ለምስኪኖች ይሰጣል፡፡ ለእግዚአብሔር ስም እጅግ ቀናተኛ ስለነበሩ ስሙን ይፈሩ ስለነበር ስመ እግዚአብሔርን ጠርተው ‹‹ይህን ክፉ ነገር በራስህ ላይ አድርግ›› ባሏቸው ሰዓት እንኳን በራሳቸው ላይ አንዳች ክፉ ነገር ወይም አደጋ ለማድረስ ወደኋላ አይሉም ነበር፡፡ ይህንን ሊፈትኗቸው ብለው አንድ ቀን ስለታማ ጦር አምጥተው ‹‹ስለ እግዚአብሔር ብለህ እስቲ ራስህን በዚህ ስለታማ ጦር ትወጋ ዘንድ ና›› ባሏቸው ጊዜ አብርሃም ልጁን ይስሃቅን ሊሠዋ በኅሊናው እንደወሰነ እርሳቸውም በቁርጥ ኅሊና ሆነው ራሳቸውን በጦሩ ሊወጉ ሲሉ ዘለው ያዟቸው፡፡ በሌላም ጊዜ እንዲሁ ሊፈትኑት በጭነት ምክንያት ጀርባው የቆሰለ አህያ አምጥተው ‹‹ዓቢየ እግዚእ ስለ እግዚአብሔር ብለህ የዚያችን አህያ ቁስሏን ላስ›› አሉት፡፡ እርሱም ያን ጊዜ ‹‹ርኩስን ብስም ኃጢአት ይሆንብኛል፣ አይሆንም ካልኳቸው ደግሞ ስመ እግዚአብሔርን ጠርተንበት እምቢ አለ ስለሚሉ የፈጣሪዬን ስም መዳፈር ይሆንብኛል ብሎ በልቡ አሰበና ያን ጊዜ ይስም ዘንድ ተመለሰ፡፡ ባልንጀሮቹም በቁርጥ ኅሊናው እንደወሰነ ባወቁ ጊዜ ሊያደርገውም ሲሄድ ተመልከተው ቶሎ ብለው ሮጠው ከኋላው ያዙት፡፡ እርሱም ‹‹እኔስ የፈጣሪዬን ስም እፈራለሁ ስሙን ተደፋፍሬ በምድር በሕይወት ከምኖር ሞት ይሻለኛል›› አላቸው፡፡
ከዚህም በኋላ ወላጆቹ ለመምህር ዘርዐ ሚካኤል ሰጡትና ብሉያት ሐዲሳት መጻሕፍትን ሌሎችንም አስተማረው፡፡ ከዚህም በኋላ መምህሩንና ዓቢየ እግዚእን ቅዱስ ሚካኤል ነጥቆ ወስዶ አክሱም አደረሳቸውና ዓቢየ እግዚእ ከአባ ሰላማ መተርጉም እጅ ዲቁናና ቅስና ተቀበሉ፡፡ ከብዙ ዘመንም በኋላ የሃሌ ሉያው አባ ሳሙኤል ቆብንና አስኬማን ሰጠው፡፡ ለአባታችን አንበሶችና ነብሮች አራዊትም ሁሉ እንደ ጓደኛ ሆነው ታዘዙለት፡፡ ቶራዎችም በሰው አንደበት ያናግሩታል፡፡ ቶራዎቹም ከነብሮች ጋር ተስማምተው እንዲኖሩ ያደርጋቸዋል፡፡ እርሱም እህልን ሳይቀምስ በቤት ጣሪያም ውስጥ ገብቶ ሳይቀመጥ ተጋድሎውን በማብዛት ብዙ ደከመ፡፡ የመላእክት ክንፍ ተሰጥቶት በሦስት ሰዓት ውስጥ የሕያዋንን መኖሪያ አይቶ ይመለሳል፡፡ በዋልድባ ገዳም ስውር ቤተ ክርስቲያን አለ ነገር ግን የሚያገኘው አልነበረም፡፡ አባታችን ዓቢየ እግዚእ ግን 40 ቀንና 40 ሌሊት ከጾመ ከጸለየ በኋላ አራዊት ተሸክመውትና አጅበውት እዚያች ስውር ቤተ ክርስቲያን ዘንድ ደረሰ፡፡ በውስጧም የሚንቀሳቀስ ብርሃን አየ ይኸውም የዚህ ዓለም ብርሃን አይደለም፡፡ በውስጧ ያሉ ስውራን ቅዱሳንንም አገኛቸውና ከእነርሱ ተባረከ፡፡ ከዚህም በኋላ የተለያዩ አስደናቂ ተአምራትን እየሠራ ወንጌልን በመስበክ ብዙ አገለገለ፡፡ የተከዜን ባሕር ለሁለት ከፍሎ በመሻገር በአካባቢው ያሉ ኢስላሞችን በተአምራቱ አሳመናቸው፡፡ ከደረቅ ጭንጫም ላይ ውኃን አፈለቀ፡፡ በተሰሰጠውም ክንፍ ብሔረ ሕያዋንና የጌታችን መካነ መቃብር ዘንድ እየሄደ ከቅዱሳን ጋር ጸሎት ያደርጋል፡፡ ደቀ መዛሙርቶቹም ‹‹እገሌ ሞቷልና የት እንቅበረው? ባሉት ጊዜ እርሱ ግን ከጸለየ በኋላ ከሞት ያስነሣዋል፡፡ የሐማሴኑ መስፍንም እንዲሁ በጦርነት ወቅት ሞቶ ባለሟሎቹ አስክሬኑን ተሸክመው ወደ ሀገሩ ሲወስዱት ሰላምጌ ከምትባል የላስታ ምድር ደረሱና በመንገድ አባታችንን አገኛቸውና ‹‹ይህን በድን ወዴት ትወስዱታላችሁ?›› አላቸው፡፡ እነርሱም ‹‹ሐማሴን ይባላል በንጉሡ ትእዛዝ ወደ ጦርነት ዘምተን ሳለ እርሱ ሞቶ ወደ ሀገሩ እየወሰድነው ነው›› አሉት፡፡ አባታችንም ያስቀምጡት ዘንድ አዘዛቸውና ውኃ አምጡልኝ አላቸው፡፡ ስመ እግዚአብሔርንም ጠርቶ ከጸለየና በውኃው ካጠመቀው በኋላ ሐማሴንን ከሞት አስነሣው፡፡ ሐማሴንንም ስለ አሟሟቱ ሲጠይቁት ‹‹መልአከ ሞት ወስዶ ለፍርድ ሳያቆመው በፊት ይህ ጻዲቅ መነኩሴ ስለ እኔ ሲለምን አየሁት፤ በጸሎቱም እግዚአብሔር ማረኝና ነፍሴን ወደ ሥጋዬ እንድትገባ አዘዘ›› ብሎ የሆነውን ሁሉ በዝርዝር ነገራቸው፡፡ አባታችንም ሐማሴንን ‹‹በሰላም ወደ ሀገርህ ሂድ›› ብሎ አሰናበተው፡፡ ያ ሹም ግን ገንዘቡን ሁሉ ለድኆች መጽውቶ ወደ አባታቸን ዘንድ መጣ፡፡ የአባታችንን ጽድቁንና ትሩፋቱን የሰሙ ሁለት ሺህ ሰዎችም አብረውት ከሹሙ ጋር መጡና አባታችንን ‹የምንኩስና ልብስ ልንለብስ እንወዳለን›› ባሉት ከፈተናቸው በኋላ አመነኮሳቸው፡፡ ያንንም መስፍን ፍኖተ ሕይወት-የሕይወት መንገድ ብሎ ሰየመው፡፡ የአባታችንም ያችን ደብር ሰጠውና አበ ምኔት ሆኖ ብዙ አገልግሎ ዘመኑን ጨረሰ፡፡ ዳግመኛም አባታችንን በደብረ መድኃኒት በምትባል ደብር ሳለ ስሟ ቡሩክት ማርያም የምትባል ልጁ ሞታ አባታችን አለቀሰላት፡፡ ተነሥቶም ወደ ዋሻ ገብቶ በሩን ዘግቶ አመድ ነስንሶ ደረቱን እየደቃ እየጸለየ ሳለ ቡሩክት ማርያም ከሞት መነሣቷን ደቀ መዛሙርቱ ሮጠው መጥተው ነገሩትና ሄዶ አገኛት፡፡ ‹‹ምን አየሽ?›› ቢላት እርሷም ‹‹‹ስለአገልጋዬ ዓቢየ እግዚእ ልቅሶና መቃተት ይህች ነፍስ ወደ ሥጋዋ ትመለስና እስከምታረጅ ትኑር› የሚል ቃል ሰማሁ›› አለችው፡፡ እርሷም አባታችን ካረፉ በኋላ በምድረ ዠመዶ ኖራ በኋላ በሰላም ዐረፈች፡፡ ከዕለታትም በአንደኛው ቀን ብፁዕ አባታችን ከ6 መነኮሳት ልጆቻቸው ጋር ይሰግዱ ዘንድ ሲሄዱ ርዝመቱ 120 ስፋቱ 12 ክንድ የሆነ ዐይኖቹ እንደሚነድ እሳት የሆኑ ከአፉም ነበልባል የሚወጣ እንደንስርም ክንፍ ያለው ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ መጠኑም ተራራ የሚያክል አውሬ በቁጣ ሊውጣቸው አፉን ከፈተ ምላሱን አውለበለበ፡፡ መነኮሳቱም እጅግ ደንግጠው ሳለ አባታችን ግን በስመ ሥላሴ አማትበው በአውሬው ላይ የተገለጠውን ያንን ከይሲ ለሁለት ሰነጠቁት፡፡ አንዲት እናት ወደ አባታችን መጥታ ‹‹የአንተን የጸሎት ውኃ ስጠኝ?›› አለችው፡፡ አባታችንም ‹‹ምን ልታደርጊው ነው?›› ሲላት ‹‹ልጠጣው ነው›› አለችው፡፡ እርሱም ስመ እግዚአብሔርን ጠርቶ ‹‹…አቤቱ ይህንን የጸሎት ውኃ ለሚጠጣው ሁሉ የሚያድን አድገው…›› ብሎ ጸልዮ በስመ ሥላሴ አማትቦ ሰጣት፡፡ እርሷም ወደቤቷ ወስዳ ሌላኛዋን ሴት ‹‹ይህንን የጸሎት ውኃ እጠመቅ ዘንድ በላየ ላይ አፍሽልኝ›› አለቻት፡፡ ሁለተኛዋም ሴት በላይዋ ልታፈስ ውኃውን አነሣች፣ ከፍም አደረገችው፡፡ ነገር ግን ውኃው የረጋ ደም ሆነ፣ አልፈሰሰምም፡፡ እነዚያም መበለታት እጅግ ደንግጠው ‹‹በኃጢአታችን ውኃው ደም ሆነ፣ ወደ አባታችን ሄደን አንንገረው›› ተባብለው ሄደው ነገሩት፡፡ አባታችንም ‹‹ያደረጋችሁት ምንድነው?›› ሲላቸው ሴቷ ‹‹በራሴ ላይ አፍስሽልኝ ከማለቴ በስተቀር ምንም ያደረግነው የለም›› አለችው፡፡ አባታችንም ‹‹ቃልን ከመለወጥ በላይ ሌላ ኃጢአት ምን የለም፣ ቃልሽን ስለለወጥሽ ደም ሆነ፣ እኔን ‹የምጠጣው የጸሎት ውኃ ስጠኝ› አልሽኝ እኔም እንዳልሽኝ ሰጠሁሽ›› አላት፡፡ እርሱም ‹‹አምጭው›› አላትና ሰጠችው፡፡ ተቀብሎ በስመ ሥላሴ ሦስት ጊዜ ቢባርከው ያንጊዜ እንደቀደሞው ንጹሕ ውኃ ሆነ፡፡ ያችንም መበለት ‹‹ልትጠጪ ከወደድሽ ውሰጂ›› አላት፡፡ እነዚያም መበለታት ከምድር ላይ ወድቀው ‹‹ይቅር በለን›› ሲሉት እርሱም እጁን አንሥቶ ባረካቸው፡፡ አባታችን አንድ ቀን ደብረ ሊባኖስ ገዳም ገብቶ ሳለ ገዳማውያኑ ‹‹አንድ መነኮስ ብናገኝ ሥጋወደሙ በተቀበልን…›› ሲባባሉ አገኛቸውና ባረካቸውና ‹‹ዛሬ የተዘጋጀ ቁርባን አለን?›› አላቸው፡፡ እነርሱም ‹‹አዎን›› አባሉት ጊዜ አዘጋጂተው እንዲያመጡ አዘዛቸው፡፡ አዘጋጅተው አመጡና አባታችንን ‹‹ገብተህ ቀድስ›› አሉት፡፡ እሱም ‹‹ባርኩኝ›› አላቸውና ‹‹እንደ መልከጼዴቅ፣ እንደ አቤል መሥዋዕትህን ይቀበልልህ…›› ባሉት ጊዜ ሚመጠን አለ፡፡ ይህንንም ባለ ጊዜ ኅብስትና ጽዋ ከፃሕል ጋር ተዘጋጅቶ ከላይ ከሰማይ ወረደ፡፡ ይህንንም ያዩና ከእርሱ ጋር የነበሩ ሁሉ ‹‹ይህ ኅብስትና ጽዋ ከየት መጣ›› እያሉ አደነቁ፡፡ አባታችንም የሐዋርያትን ቅዳሴ ቀድሶ አቆረባቸው፡፡ አባታችንም ወጣና ደመናውን ጠቅሶ በደመና ተጫነ፡፡ እነርሱም ‹‹አቤቱ ስለ እግዚአብሔር ብለህ ስምህን ንገረን›› አሉት፡፡ እርሱም ‹‹ስሜ ዓቢየ እግዚእ ይባላል የምንኩስና ስሜ የመረታ ሀገር እንጦንስ ነኝ›› አላቸውና ባረኳቸው ሄደ፡፡ ያም ፃሕልና ጽዋ ዛሬም ድረስ አለ፡፡ ቅዱስ አባታችን በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ የተለያዩ አስደናቂ ተአምራትን እየሠራ ወንጌልን በመስበክ እገዚአብሔርን ካገለገለ በኋላ ከፈጣሪው ታላቅ ቃልኪዳን ተቀብሎ በዛሬዋ ዕለት በክብር ዐርፏል፡፡
የቅዱሳኑ ምልጃቸውና በረከታቸው በአማላጅነታቸው በምንታመን በሁላችን ላይ ይደርብን! አሜን!!!

የእግዚአብሔር መንግሥት መውረሻ ብቸኛ መንገድ በሆነችው በመጀመሪያዋ ንጽሕት ቅድስት በሆነችው በአባቶቻችን ሃይማኖት ያጽናን በእውነት!!! ተዋሕዶ ብቸኛና ፍጽምት ነሽ!