Showing posts with label አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ያደረጉት ተአምር. Show all posts
Showing posts with label አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ያደረጉት ተአምር. Show all posts

Thursday, July 14, 2016

አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ያደረጉት ተአምር

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈሰ ቅዱስ ስም አሜን
ዛሬ በዓመታዊ የዕረፍታቸው በዓል ታስበው የሚውሉት አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ያደረጉት ተአምር ይህ ነው፡- አምሃራ ሳይንት ቦረና ከአባ ጽጌ ድንግል ገዳም የ5 ሰዓት የእግር መንገድ ከተሄደ በኋላ የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ገዳም ይገኛል፡፡ ይኽ የአቡነ ጽጌ ድንግል ገዳም ከአቡነ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ገዳም ጋር የሚያገናኘው ‹‹የእግዜር ድልድይ›› የተባለ አስገራሚ ታሪክ ያለው ድልድይ አለው፡፡ ሁለቱ ቅዱሳን በመንፈስ ተጠራርተው ለመገናኘት ቢያስቡም ታላቁ የወለቃ ወንዝ ሞልቶ በአካል ሳይገናኙ ቀሩ፡፡ በዚህም ሁለቱ ቅዱሳን አዝነው ከወንዙ ወዲያና ወዲህ ሆነው አፈር ተራጭተው ቢመለሱ ያ የተራጩት አፈር በተአምር ድልድይ ሆነ፡፡ ድልድዩን ሁለቱም በበዓታቸው ሆነው በመንፈስ አዩት፡፡ ጠላት ሰይጣንም ይህንን ሲያይ ድልድዩን በትልቅ ሹል ድንጋይ በስቶ ሊያፈርሰው ሲል አባ ጊዮርጊስ በመንፈስ አዩትና ከጋስጫ ተነሥተው በደመና ተጭነው በመሄድ ሰይጣኑን በግዘፈ ሥጋ ገዝተው ያንን አፈርስበታለሁ ያለውን ትልቅ ድንጋይ አሸክመውት ደብራቸው ጋስጫ ድረስ ወስደውታል፡፡ ያ ድንጋይ ዛሬ በገዳሙ ደወል ሆኖ እያገለግለ ይገኛል፡፡ ድልድዩም እስካሁን ድረስ ለአካባቢው ሙስሊም ማኅበረሰብ ብቸኛው የወለቃ ወንዝ መሻገሪያቸው ሆኖ እያገለገላቸው ይገኛል፡፡

በተአምራት የተሠራው የእግዜር ድልድይ

አባ ጊዮርጊስ የፈለፈሉት ድንቅ ቤተ መቅደስ
 


ሰይጣን ድልድዩን ሊያፈርስበት የነበረው ትልቁ ሹል ድንጋይ አሁን በጋስጫ ገዳም ለመነካካቱ ደወል ሆኖ ያገለግላል
 

ሌላው በእነዚህ ሁለታ ታላላቅ ገዳማት ያየሁት እጅግ አስገራሚ ነገር ቢኖር ሻሾ የሚባለው ነው፡፡ ይኸውም ታማኙ ውሻ ሻሾ በ2006 ዓ.ም እኔ ከአባ ጽጌ ድንግል ገዳም ወደ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ገዳም ለመድረስ የ5 ሰዓት የእግር መንገድ መሄድ ግዴታ በሆነብኝ ሰዓት አሰልቺውን የበረሃ ጉዞ ከአንድ ጓደኛዬ ጋር ስንጓዝ ሙሉውን የ5 ሰዓቱን መንገድ ይመራን የነበረው ታማኙ ውሻ ሻሾ ነበር፡፡ ደክሞን ስናርፍ አብሮን እያረፈ፣ መሄድ ስንጀምርም አብሮን ከፊት ከፊት እየተራመደና መንገዱን እየመራ እዛው ገዳሙ አደረሰን፡፡ ሻሾ ዛሬ ከሰው ይበልጥ ናፈቀኝ፡፡ የጻድቁን የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫን በረከት አንድም ታማኙን ሻሾን ለማግኘት መስከረም ላይ ከግሸን መልስ ለመሄድ አስቤያለሁና አምላከ ቅዱሳን ይፍቀድልኝ፡፡

ከአባ ጽጌ ድንግል ገዳም እስከ አባ ጊዮርጊስ ገዳም ድረስ ያለውን የ5 ሰዓት የእግር መንገድ ከፊት ከፊት እየመራ በረሃውን አቋርጦ የወሰደኝ የገዳሙ ታማኝ ውሻ ሻሾ- ከገዳሙ በቅርብ ርቀት ላይ ከደረሰ በኃላ ሲያሳርፈን፡፡


የግሸን ተጓዞች ይኽን አጋጣሚ ብትጠቀሙ በረከቱ ዕጥፍ ድርብ ይሆንላችኃል፡፡ ከደሴ በግማሽ ቀን ወግዲ የምትባል ከተማ በማደር በቀጣዩ ቀን በአሕዛብ የተከበቡትንና እጅግ አስገራሚ የሆኑትን የአባ ጽጌ ድንግል ገዳምንና የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ገዳምን መሳለም ይቻላል፡፡ እዛው አካባቢ ደግሞ ጸበላቸው ውስጥ እንጨት ሲነከርበት መቁጠሪያ አድርጎ የሚሰጠውን የአቡነ ገብረ እንድርያስን ገዳም መሳለም ይቻላል፡፡