Showing posts with label የወሊሶ ቤተ ሳይዳ ቅድስት ማርያም ገዳም. Show all posts
Showing posts with label የወሊሶ ቤተ ሳይዳ ቅድስት ማርያም ገዳም. Show all posts

Wednesday, June 10, 2015

የወሊሶ ቤተ ሳይዳ ደብረ ምጥማቅ ቅድስት ማርያም ገዳም

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ምእመናን የተፈወሱባት የወሊሶ ቤተ ሳይዳ ደብረ ምጥማቅ ቅድስት ማርያም ገዳም ቅዳሴ ቤት ይከበራል አትም ኢሜይል
ግንቦት 8 ቀን 2007 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
01w
በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት በወሊሶ ከተማ የምትገኘው የቤተ ሳይዳ ደብረ ምጥማቅ ቅድስት ማርያም ገዳም ሕንፃ ግንባታ ተጠናቅቆ ቅዳሴ ቤቱ ግንቦት 20 እና 21 ቀን 2007 ዓ.ም. ቅዱስ ፓትርያርኩ፤ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፤ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ምእመናን በተገኙበት በድምቀት እንደሚከበር የገዳሙ አስተዳደር ገለጸ፡፡
የወሊሶ ቤተ ሳይዳ ደብረ ምጥማቅ ቅድስት ማርያም ገዳም በ1971 ዓ.ም. በብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የተመሠረተች ሲሆን፤ በ1996 ዓ.ም. በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦ የሕንፃ አሰሪ ኮሚቴ በማዋቀር ግንባታው ቢጀመርም በተለያዩ ምክንያቶች ግንባታው ዘግይቶ በዐሥር ዓመቱ ሊጠናቀቅ እንደቻለ አስተዳሩና የሕንፃ አሰሪ ኮሚቴው ገልጸዋል፡፡

የቤተ ክርስቲያኑን ዲዛይን በማኅበረ ቅዱሳን ባለሙያዎች ተሰርቶ ቀድሞ የነበረውን ዲዛይን በድጋሚ ማስተካከያ በማድረግ የወረዳ ማእከሉ ባለሙያዎች በቅርበት እየተከታተሉት ለሁለተኛ ጊዜ በተዋቀረው ሕንፃ አስሪ ኮሚቴ አማካይነት ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡

01ww01wy
የገዳሙ መሥራች የሆኑት ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ /መምህር ወልደ ትንሣኤ ግዛው/ የሕይወት ታሪካቸው እንደሚያስረዳው መጋቢት 21 ቀን 1911 ዓ.ም. በቀድሞው በተጉለትና ቡልጋ አውራጃ ኢቲሳ ደብረ ጽላልሽ የተወለዱ ሲሆን፤ በ1921 ዓ.ም. ከግብፃዊው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ዲቁና፤ ነሐሴ 24 ቀን 1933 ዓ.ም. በደብረ ሊባኖስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም ምንኩስናን፤ በ1940 ዓ.ም. በታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም ከኢትዮጵያዊው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ይስሐቅ ቁምስና፤ ግንቦት 30 ቀን 1979 ዓ.ም. በብፁዕ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ኤጲስ ቆጶስ ሆነው ተሹመዋል፡፡
በአዲስ አበባ በቀጨኔ መድኃኔዓለም፤ በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም፤ በመናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ፤ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ፤ በድሬደዋ ቅዱስ ሚካኤል፤ በሐረርጌ ሀገረ ስብከት ጅጅጋ፤ ኦጋዴን እና አሰበ ተፈሪ ካገለገሉባቸው አድባራትና ገዳማት ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡ በ1946 ዓ.ም. ወደ ቀድሞው ጨቦና ጉራጌ አውራጃ፤ በአሁኑ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ወሊሶ /ግዮን/ ከተማ በመምጣት አሁን ገዳሙ በሚገኝበት ቦታ ላይ መሬት በመግዛት አዳራሽ ሠርተው ከእግዚአብሔር በተሰጣቸው ጸጋ በአጋንንትን የተያዙ ሕሙማን እየፈወሱ ቆይተዋል፡፡ አገልግሎታቸው ወደ ቀድሞው ንጉሥ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ በመድረሱ የያዙትን ቦታ አስፍተው እንዲያገለግሉ መሬት እንዲሰጣቸው አድርገዋል፡፡

በ1971 ዓ.ም. የሚያገለግሉበት አዳራሽና ሰፊውን ቦታ በደርግ እንደሚነጠቁ የተረዱት ብፁዕነታቸው በሚያገለግሉበት አዳራሽ ጽላት በማስገባት ቤተ ክርስቲያኗ ተመሠረተች፡፡

01www01wwww
ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ከ10 ሚሊዮን በላይ ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በአጋንንት የተያዙ ሕሙማንን ከእግዚአብሔር በተሰጣቸው ሀብተ ፈውስ እንደፈወሱ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ብፁዕነታቸው ጥር 18 ቀን 1989 ዓ.ም. ዐርፈዋል፡፡
ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ግንቦት 20 እና 21 ቀን 2007 ዓ.ም. በቅዱስ ፓትርያርኩ ተባርኮ ጽላቱ የሚገባ ሲሆን፤ ዓመታዊ የእመቤታችን የንግስ በዓል በድምቀት እንደሚከበር ኮሚቴው አስታውቋል፡፡
ምእመናን በዚህ ታሪካዊና የእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ ሲከናወንበት በነበረው ገዳም ተገኝተው የበረከቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ የገዳሙ አስተዳደርና ሕንፃ አስሪ ኮሚቴ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡