Showing posts with label ኩክ የለሽ ማርያም. Show all posts
Showing posts with label ኩክ የለሽ ማርያም. Show all posts

Wednesday, November 12, 2014

ጸሎት ሰሚዋ ኩክ የለሽ ማርያም እና አባ ኃይለ ጊዮርጊስ ዘብሔረ ቡልጋ


አባ ኃይለ ጊዮርጊስ ዘብሔረ ቡልጋ የኩክ የለሽ ማርያም ገዳምን የመሰረቱ ሲሆን በመስከረም 23 ቀን 1908 በቡልጋ ወረዳ ተወለዱ፡፡እግዚአብሔር አምላክ በእርጅና ጊዜአቸው በ64 ዓመታቸው ለመንፈሳዊ አገልግሎት ወደ ቤቱ የጠራቸው በአካለ ሥጋ በነበሩበት ጊዜም ነበር ከቅድስት ድንግል ማርያም ከቅዱሳን መላእክት ከጻድቃን ሰማዕታት ጋር ለመነጋገር የበቁ ታላቅ አባት ነበሩ፡፡
እግዚአብሔር ያከበረውን ማን ያዋርደዋል እንዳለ መጽሐፉ እኚህ ታላቅ አባት በሣርያ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ሲያገለግሉ ቤተክርስቲያን ሲረዱ የቀዩ አባት ሲሆን ከዕለታት አንድ ቀን የቅዱስ ሚካኤልን በዓል ሲያከብሩ በዋዜማው ከቅዱስ ሚካኤል ጋር በመነጋገር የሥላሴን ዙፋን ገንትንና ሲኦልን ለማየት የበቁ አባት ናቸው፡፡

ከዚህ ጊዜ ጀምሮ አባ ኃይለ ጊዮርጊስ በእግዚአብሔር አጋዥነት በቅዱሳን መሪነት ገዳሙን የመሰረቱት ሲሆን ከድንጋይ ፍልፍል አራት / 4 / ቤተመቅደሶችንና ሌሎች የባህታውያን መኖሪያ ዋሻዎች የፈለፈሉ ሲሆን አብረዋቸው ቅዱሳን መላእክት እንደሚያግዟቸው በህይወት በነበሩበት ሰዓት ይናገሩ እንደነበር የገዳሙ አገልጋዮች ይናገራሉ፡፡አራቱ ቤተመቅደሶች፡-

1. የቅዱስ እግዚአብሔር አብ ፍልፍል ዋሻ፡- ይህ ገዳም አባ ኃይለ ጊዮርጊስ በ1972 ዓ.ም ጀምረው በ1976 ዓ.ም ነው ያጠናቀቁት ሲሆን ይህን ያህል ጊዜ ለምን እንደፈጀ የራሱ የሆነ ምክንያት አለውና በቦታው ተገኝተው ሚስጢሩን እንዲያውቁ ይመከራሉ

2. ኩክ የለሽ ማርያም ፍልፍል ዋሻ፡- በ1984 ዓ.ም ጀምረው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ነው ያጠናቀቁት፡፡ኩክ የለሽ ማርያም ማለት የጆሮ ኩክ የሌላት ቶሎ የሰዎችን ችግር የምትሰማ ለጠየቋትም ቶሎ ምላሽ የምትሰጥ እናት ማለት ነው፡፡ይህ ማለት ግን ሌሎች ቅዱሳን አይሰሙም ማለት አይደለም ፡፡ እመቤታችን ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም አባ ኃይለ ጊዮርጊስ እጅግ አብዝታ ስለምትወዳቸው ኩክ የለሽ ማርያም ገዳምን እንዲመሰረቱ አድርጋቸዋለች፡፡ በጸበሏ በእምነቷ ብዙ ተዓምራቶችን እያደረገች ትገኛለች፡፡

3. የቅድስት ሥላሴ ፍልፍል ዋሻ፡- በ1984 ዓ.ም ጀምረው ከኩክ የለሽ ማርያም ፍልፍል ዋሻ ጋር አብሮ በአንድ ዓመት ውስጥ ነው የተጠናቀቀው ድንቅ ተዓምር እየተደረገም ይገኛል፡፡

4. ምን ያምር ቅዱስ ገብርኤል፡- በ1986 ዓ.ም ጀምረው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ነው ያጠናቀቁት፡፡ይህ ገዳም በቅዱስ ገብርኤል መሪነትና አጋዥነት በአባ ኃይለ ጊዮርጊስ ተፈለፈለ፡፡በዚህ ቤተመቅደስ ውስጥ ጸበል ፈልቆ ብዙ ተዓምራትን እያደረገ ይገኛል፡፡በአጠቃላይ በአራቱም ቤተመቅደስ በየእለቱ ማይጠንት ይታጠናል፡፡እንዲሁም በየወሩ ቅዳሴ ይቀደስባቸዋል፡፡ገዳሙ በ1972 ዓ.ም ተጀምሮ በ1986 ዓ.ም መጨረሻ ተጠናቆ በ1987 ዓ.ም በአባቶች ተባርኮ መለኮሳት በምነና ሕይወት ገብተዋል፡፡

እኚህ አባት ገዳሙን መስርተው ብዙ መንፈሳዊ አገልግሎት ካገለገሉ በኃላ በ1997 ዓ.ም መጋቢት 19 ቀን በዓለ እረፍታቸውን ካደረጉ በኃላ አጽማቸው በገዳሙ በጸሎት በአታቸው ውስጥ ይገኛል፡፡ይህ ገዳም ከ25 በላይ መለኮሳት የሚኖሩበት ሲሆን በሽመናና በልማት ስራ ከጸሎት ጎን ለጎን እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ይህን ታላቅ ገዳም የረገጠ ወንደ የ40 ቀን ህጻን ሴት የ80 ቀን ህጻን ይሆናል ተብሎ ቃል ኪዳ ተገብቶለታል እንዲሁም በቦታው የበረከት ሥራ የሰራ ጸሎት ያደረገ እስከ ሰባት ትውልድ ድረስ ምህረት እንደሚደረግለት ቃል ኪዳን ተገብቶለታል እርሶም በቦታው በመገኘት ለቦታው የተገባለትን ቃል ኪዳን ይሸምቱ እኔ ኃጢአተኛ ባሪያችሁ የዚህ ቃል ኪዳን ተካፋይ ሆንኩ ምዕመናንና ምዕመናትም የዚህ ቃል ኪዳን ተካፋይ ይሆን ዘንድ ብዕሬን አንስቼ አካፈልኳችሁ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሐር
ምንጭ፡-ገዳሙ ያሳተመው ብሮሸር
ለበለጠ መረጃ ፡- የቅዱስ እግዚአብሔር ማህበር 0911 133944 ፤ 0922 461145
አድራሻ፡- ደብረ ብርሃን በስተሰሜን ምስራቅ በኩል 5 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች