Wednesday, July 1, 2015

ታላቁ ጻድቅ ንጉሥ የዐፄ ካሌብ

ግንቦት 20-ንጽሕናን ከቅድስና ጋር አስተባብሮ በመያዝ እግዚአብሔርንም ሰውንም በቅድስናና በፍቅር ያገለገለው የታላቁ ጻድቅ ንጉሥ የዐፄ ካሌብ ዕረፍት ነው፡፡ እናም ዛሬ በዕረፍቱ ዕለት ገድሉን ትሩፋቱን የቅድስና ሥራውን አብዝተን በመናገር አስበነው እንውላለን፤ በረከቱን እንካፈላለን፡፡ ይኸውም ታላቅ ጻድቅ ንጉሥ ዋጋው እጅግ የከበረውንና በነገሠ ጊዜ በራሱ ላይ የጫነውን የወርቅ ዘውዱን ከጌታችን መካነ መቃብር ላይ ይሰቅልለት ዘንድ ከአደራ ደብዳቤ ጋር ለኢየሩሳሌሙ ሊቀ ጳጳሳት ለአባ ዮሐንስ ከላከለት በኀላ ዓለምን ንቆ፣ ልብሰ መንግሥቱን አውልቆ አንዲት የውኃ መንቀል ብቻ በመያዝ በአባ ጰንጠሌዎን እጅ በመመንኮስ ገዳማቸው አጠገብ ከሚገኝ ዋሻ ውስጥ ገብቶ 12 ዓመት በጾም በጸሎት በብዙ ድካምና ተጋድሎ እግዚአብሔርን ሲያገለግል ኖሮ ዛሬ ግንቦት 20 ቀን በታላቅ ክብር ዐርፏል፡፡
መልካም የበረከት ንባብ ይሁንልን!!! (የጽሑፉ ምንጭ ገድለ አቡነ አረጋዊ፣ ገድለ አቡነ ጰንጠሌዎንና የኅዳርና የግንቦት ወር ስንክሳር ናቸው)

በቍስጥንጥንያ ዮስጢኖስ በነገሠ በ5ኛው ዓመት ዐፄ ካሌብ በኢትዮጵያ ነግሦ ነበር፡፡ የአይሁድም ንጉሥ ፊንሐስ ነበር፡፡ በዚህም ወቅት ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት የኢየሩሳሌሙ አባ ዮሐንስ፣ የቍስጥንጥንያው አባ ጢሞቴዎስ፣ የእስክንድርያውም አባ ጢሞቴዎስ፣ የአንጾኪያው አባ አውፍራስዮስ ነበሩ፡፡ ሳባ የምትባለው አገር በኢትዮጵያ ነገሥታት እጅ ውስጥ ነበረች፡፡
የሮም ነገሥታት አስባስያኖስና ጥጦስ አይሁድን ወረው አሳደዷቸውና ይህችን ሳባን አይሁድ ወረሷት፡፡ በውስጧም በጌታችን የሚያምኑ ብዙ ሕዝቦች ነበሩባት፡፡ በሳባ ውስጥም ክርስቲያኖች የሚኖሩባት ታላቅ ከተማ ነበረች፡፡ የአይሁድ ንጉሥ ፊንሐስም ወደ ከተማዋ ገብቶ በሺህ የሚቆጠሩትን ክርስቲያኖች ገደለ፡፡ ዙሪያ ዳር ድንበሯ በመስቀል ምልክት የታጠረች ስለነበረች ፊንሐስ መጀመሪያ መግባት ሳይችል ሲቀር ‹‹ወደ ውስጥ ገብቼ የከተማዋን አሠራር፣ ገበያዋን፣ አደባባዮቿን መጎብኝት እሻለሁ እንጂ ክፉ አላስብም፣ የማንንም ደም አላፈስም›› ብሎ ምሎ ወደ ውስጥ ገባ፡፡ ከነሠራዊቱ ከገባ በኋላ ግን መግደል ጀመረ፡፡ መጀመሪያውንም አቡነ ኂሩተ አምላክ ‹‹ውሸቱን ነው አታስገቡት፣ ሐሰተኛ ነው ደጁን ከፍታችሁ አታስገቡት›› ብለው ቢነግሯቸውም የሚሰማቸው ጠፋ፡፡ ፊንሐስም እንደገባ የሕዝቡን ገንዘብ ዘረፈ፤ ቀጥሎም በነልባሉ አየር ላይ ደርሶ እስኪታይ ድረስ እሳት አስነድዶ ‹‹ኤጲስ ቆጶሱን አባ ጳውሎስን አምጡልኝ›› ብሎ አዘዘ፡፡ እንደሞቱም ሲነገረው ዐፅማቸውን ከመቃብር አውጥቶ አቃጠለው፤ ቀጥሎም ቀሳውስትን፣ ካህናትን፣ ዲያቆናትን፣ መነኮሳትን ሁሉ በእሳቱ ውስጥ እንዲጨምሯቸው አዘዘ፡፡ አራት ሺህ ሃያ ሰባት ክርስቲያኖችም ወደ እሳቱ ተጥለው በሰማዕትነት ሞቱ፡፡
ፊንሐስም አቡነ ኂሩተ አምላክንና ታላላቅ መኳንንትን ግን አሳስሮ ብዙ አሠቃያቸው፡፡ ‹‹ክርስቶስን ያልካደ ሁሉ ተሠቃይቶ ይሞታል›› የሚል አዋጅ በከተማው እንዲነገር አዘዘ፡፡ አቡነ ኂሩተ አምላክንም አስሮ እያሠቃያቸው በከተማው አዞራቸው፡፡ ሕዝቡም ጌታችንን አንክድም እያሉ ወጥተው ተገደሉ፡፡ በዚህም ጊዜ የተገደሉት ቁጥራቸው 4252 ሆነ፡፡
የአቡነ አቡነ ኂሩተ አምላክን ሚስት ቅድስት ድማህን ከ2 ልጆቿ ጋር ይዞ አሠቃያቸው፡፡ አንደኛዋም የ12 ዓመት ሕፃን ምራቋን በፊንሐስ ላይ ተፋችበት፣ እርሱም ሰይፉን መዞ አንገቷን ቆረጠው፡፡ ለቅድስት ድማህም የልጇን ደም አጠጣት፡፡ ድማህም ‹‹ይህን እንዲሆን የፈቀደ እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን›› ብላ አምላኳን ስታመሰግን ሰምቷት እናቲቱንም አንገቷን ቆረጠው፡፡ አቡነ ኂሩተ አምላክንም ወደ ውጭ አውጥቶ ‹‹የምታመልኩትን ክርስቶስን ካዱ›› አላቸው፡፡ አቡነ ኂሩተ አምላክም ‹‹ክብር ይባውና ጌታዬን ኢየሱስ ክርስቶስን እያለመኩ ስኖር 78 ዓመት ሆነኝ፣ እስከ አራት ትውልድም ለማየት ደርሻለሁ፡፡ ዛሬም ስለከበረ ስሙ ምስክር ሆኜ ስሞት እጅግ ደስ ይለኛል፡፡ ወደዚህ ለመግባት ስትምል እኔም አስቀድሜ መሐላህን እንዳያምኑ ለወገኖቼ ነግሬአቸው ነበር፤ አንተ ሐሰተኛ ነህና ነገር ግን ይህ ሁሉ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው፤ ለዚህ ተጋድሎ ላበቃኝ ለእርሱ ምስጋና ይሁን›› እያሉ ፊንሐስን በተናገሩት ጊዜ ወደ ወንዝ ወስዶ አንገታቸውን አስቆረጠው፡፡ አቡነ ኂሩተ አምላክም በሰማዕትነት ከማረፋቸው በፊት የኢትዮጵያንና የሮምን መንግሥት ያጸና ዘንድ የአይሁድን መንግሥት ግን ያጠፋ ዘንድ ጌታችንን ለመኑት፡፡ ዕረፍታቸውም ኅዳር 26 ቀን ነው፡፡
አቡነ ኂሩተ አምላክም ሕዝቡን ተሰናብተው በተሰየፉ ጊዜ አንዲት ሴት ደማቸውን ለ5 ዓመቱ ልጇ ቀባችው፡፡ ይህንንም ሲያዩ ልጇን ነጥቀው ለንጉሡ ሰጥተው እርሷን ከእሳቱ ውስጥ ጨመሯት፡፡ ንጉሡ ፊንሐስም ሕፃኑን ‹‹እኔን ትወዳለህ ወይስ ክርስቶስ የሚሉት?›› ብሎ ጠየቀው፡፡ የ5 ዓመቱ ሕፃንም ‹‹እኔስ የእጁ ሥራ ነኝና ክርስቶስን እወደዋለሁ፣ ይልቅስ ልቀቀኝና ወደ እናቴ ልሂድና ሰማዕትነቴን ልፈጽም›› አለው፡፡ ፊንሐስም ከእጁ እንዳይወጣ በያዘው ጊዜ እግሩን ነክሶት አምልጦት ሮጦ ሄዶ ከእሳቱ ውስጥ ገባ፡፡ ሁለተኛም የ10 ወር ሕፃን የተሸከመች አንዲት አማኝ ሴት ወደ ልጇ እያየች ‹‹ልጄ ሆይ ዛሬስ ላዝንልህ አልቻልኩም›› ብላ ስትናገር በእቅፏ ያለው የ10 ወሩ ሕፃን ልጇም አንደበቱን ከፍቶ ‹‹እናቴ ሆይ በፍጥነት ወደ ዘላለም ሕይወት እንሂድ ይህችን እሳት ከዛሬ በቀር አናያትምና›› አላት፡፡ እርሷም ልጇን ይዛ ዘላ እሳቱ ውስጥ ተወርውራ ገባች፡፡ የክርስቲያን ወገኖችም ይህን ሁሉ አይተው እኩሉ ወደ እሳት እኩሉ ወደ ሰይፍ ተሽቀዳደሙ፡፡ ራሳቸው የአይሁድ ሠራዊት ዕፁብ ብለው እስኪያደንቁ ድረስ ክርስቲያኖቹ ወደ ሰማዕትነት ተፋጠኑ፡፡ ቁጥራቸው ሃያ ሺህ ነበር፡፡ ክርስቲያኖቹም በሚሞቱበት ጊዜ የረዳቶቻቸውን የቊስጥንጥንያንና የኢትዮጵያን ነገሥታት ስም በጸሎታቸው ይጠሩ ነበር፡፡
ከዚህም በኋላ እሳቱ በሰማይ ውስጥ መልቶ 40 ቀንና 40 ሌሊት ታየ፡፡ ፊንሐስም ወደ ሀገሩ በተመለሰ ጊዜ ወደ ነገሥታቱ ሁሉ በኋይሉ እየተመካ ላከባቸው፡፡ የሮሜው ንጉሥ ዮስጢኖስም ይህን ሰምቶ ወደ እስክንድርያ ሊቀ ጳጳስ ወደ አባ ጢሞቴዎስ መልአክት ላከ፡፡ ለሀገረ ናግራን ክርስቲያኖች ደማቸውን ይበቀልላቸው ዘንድ ለኢትዮጵያው ንጉሥ ለዐፄ ካሌብ መልእክት እንዲልክ ነገረው፡፡ ዐፄ ካሌብም ተጽፎለት መልእክቱ ሲደርሰው ፈጥኖ ተነሣ በዋሻ ከሚኖር ከአቡነ ጰንጠሌዎን በረከትን ተቀብሎ ለአቡነ አረጋዊም በጸሎት እንዲያስቡት ደብዳቤ ጽፎ ከላከ በኋላ ከሠራዊቱ ጋር በመርከብ ተጭኖ ወደ ሀገረ ናግራን ሄደ፡፡
ከመሄዱም በፊት ለአቡነ አረጋዊ የላከላቸው መልእክት እንዲህ የሚል ነው፡- ‹‹ፊንሐስ የተባለ አረማዊ የናግራን ክርስቲያኖችን ደም በከንቱ ያፈሰሰ፣ ቤተክርስቲያንን የመዘበረና ያጠፋ ፍጹም የእግዚአብሔር ጠላት ወደሚሆን ሔጄ እዋጋው ዘንድ ተዘጋጅቻለሁ፡፡ ስለዚህ አባቴ ሆይ! አንተም በበኩልህ ጸሎት አድርግልኝ፣ የጻዲቅ ጸሎት ትራዳለች፣ ኃይልንም ታሰጣለች፣ በጠላት ላይ ድልንም ታቀዳጃለችና›› ሲል ላከበት፡፡
አባታችን አቡነ አረጋዊም ለንጉሡ ጭፍሮች ‹ወደ ጦሩ ግንባር ሒድ፣ እግዚአብሔር ጠላቶችህን ከእግርህ በታች ያስገዛልህ፣ ለአንተም ግርማ ሞገስ ይስጥህ፣ በሰላም ይመልስህ›› ብለው መርቀው ላኩበት፡፡ ከዚህ በኋላ ዐፄ ካሌብ ልብሰ መንግሥቱን አውልቆ ጥሎ ማቅ ለብሶ በፍጹም ልመና ብዙ ጸሎት ካደረገ በኀላ ወደ የመን ሳባ በመርከብ ተጓዘና ከከሐዲው ፊንሐስ ጋር ጦር ገጠመ፡፡ ከሐዲውን ንጉሥ ፊንሐስን ራሱ ዐፄ ካሌብ ገጠመውና በፈረሱ ላይ እንደተቀመጠ በጨበጣ በጦር ወግቶ ገደለውና ወደ ባሕር ገልብጦ ጣለው፡፡
ከዚያም ዐፄ ካሌብ ዛፋር ወደምትባለው ከተማ ሔዶ እርሷንም ተቆጣጠራት፡፡ በእዚያም ያሉ የፊንሐስን ሹማምንቶች እያፈላለገ በአደባባይ እንዲገደሉ በማድረግ የክርስቲያኖቹን ደም በሚገባ ተበቀለ፡፡ የናግራንንም ሕንፃዎቿዋን አደሰ፤ የሰማዕታቱንም መታሰቢያ አቆመ፡፡ ወደ እስክንድርያው አባ ጢሞቴዎስና ወደ ሮሜው ንጉሥ ዮስጢኖስም የድል መልእክት ላከላቸውና እነርሱም ሰምተው እጅግ ተደሰቱ፡፡ በአንጾኪያ፣ በእስክንድሪያ፣ በሮም፣ በቊስጥንጥንያና በዓለም ላይ ያሉ ክርስቲያኖች ሁሉ ይህን ሲሰሙ በእጅጉ ተደሰቱ፡፡ ይህም የሆነው በ525 ዓ.ም ነው፡፡ ጠፍተው የሔዱ ክርስቲያኖችንም ሰበሰባቸውና ወደቀደመ ቦታቸው መለሳቸው፣ ቤተክርስቲያናቸውን አነጸላቸው፡፡ ከሳባ ሀገር የማረከውን ንብረት ሁሉ ለቤተክርስቲያን ሰጥቶ ዓሥር ሺህ ጠባቂ ሠራዊት ሰቷቸው ወደ አክሱም በሰላምና በፍጹም ደስታ ተመለሰ፡፡
ንጉሡ ዐፄ ካሌብ የናግራን ሰማዕታት ደም ተበቅሎላቸው ሁሉንም ነገር አስተካክሎላቸው በደስታ ወደ አክሱም ከተመለሰ በኋላ ‹‹ይህን ያደረገልኝን አምላኬን በምን ላስደስተው?›› ሲል አሰበና ተድላውን፣ ደስታውን ዓለምን ንቆ፣ ልብሰ መንግሥቱን አውልቆ አንዲት የውኃ መንቀልና አንዲት ምንጣፍ ብቻ ይዞ አባ ጰንጠሌዎን ገዳም አጠገብ ከሚገኝ ዋሻ ውስጥ ገብቶ በአባ ጰንጠሌዎን እጅ መንኩሶ ለመቀመጥ ወሰነ፡፡ አባ ጰንጠሌዎንንም ‹‹አመንኩሰኝ›› አላቸውና የመላእክትን አስኬማ አልብሰው አመነኮሱት፡፡ ዐፄ ካሌብም ዳግመኛ ከዋሻው ወጥቶ ዓለምን በዐይኑ እንዳያይ ማለ፡፡ ዋጋው እጅግ የከበረውንና በነገሠ ጊዜ የጫነውን ዘውዱን ከጌታችን መካነ መቃብር ወይም በር ላይ ይሰቅልለት ዘንድ ከአደራ ደብዳቤ ጋር ለኢየሩሳሌሙ ሊቀ ጳጳሳት ለአባ ዮሐንስ ላከለት፡፡ ዳግመኛም ንጉሡ ዐፄ ካሌብ ‹‹አባቴ ሆይ በአንተ ጸሎት በእግዚአብሔር ቸርነት ከጦርነቱ በሰላም ተመልሻለሁ፤ አሁንም የክርስቶስን አርዑተ መስቀል ተሸክሜአለሁና እግዚአብሔር ለፍጻሜው ያብቃህ እያልህ ስለ እኔ ጸልይልኝ›› ብሎ ወደ አባታቸን ወደ አቡነ አረጋዊ ላከበት፡፡ ስለዚህም ነገር አቡነ አረጋዊ በጣም ተደሰቶ ‹‹ልጄ ሆይ! መልካሙንና የበለጠውን አድርገሃል፣ አሁንም እግዚአብሔር የፈቀደከውን ነገር ሁሉ ይፈጽምልህ›› ብለው መረቁት፡፡ ኢትዮጵያዊው ንጉሥ ዐፄ ካሌብ ይህን ዓለም በመናቅ በበረሃ በዋሻ 12 ዓመት በጾም በጸሎት በብዙ ተጋድሎ ከኖረ በኋላ ግንቦት 20 ቀን ዐርፎ እስከ ዘለዓለሙ ድረስ የማያልፍ ሰማያዊ ክብርን ወርሷል፡፡ መካነ መቃብሩም አክሱም በአባ ጰንጠሌዎን ገዳም ምድር ቤቱ ውስጥ ይገኛል፡፡
ይኸውም አባ ጰንጠሌዎን ከተሰዓቱ ቅዱሳን ውስጥ አንዱ ሲሆን በገዳሙ ውስጥ ሳይቀመጥ ሳይተኛ በእግሩ ቆሞ 45 ዓመት የጸለየ የበረከት አባት ነው፡፡ ምድራዊ ወይም ሥጋዊ የሆኑ ፍትወታት ፈጽመው ጠፍተውለታልና ከመላእክትም ማኅበር ጋር አንድ ሆኗልና ከፍጹም ምስጋና በቀር እህል ወይም ውኃ ወይም ቅጠል እንኳ አይቀምስም ውኃም አይጠጣም ነበር፡፡ እርሱም የንጉሥ ልጅ ስለነበር አስቀድሞ ንግሥናን ንቆ የመነነ ነው፡፡ የመንፈስ ወንድሞቹም እንዲሁ፡፡
እነዚህም ተሰዓቱ ቅዱሳን ሁሉም የነገሥታት ልጆች ሲሆኑ በዓለም ነግሠው መኖርን እርግፍ አድርገው ትተው ከያሉበት ከቁስጥንጥንያ፣ ከአንጾኪያ፣ ከግሪክ፣ ከእስያ፣ ከሮምያና ከቂሣርያ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በአንድነት ተሰባስበው በአባ ጳኩሚስ ገዳም ገብተው በምንኩስና ሲኖሩ ኢትዮጵያ በሃይማኖት በምግባር ያጌጠች ቅድስት ሀገር መሆኗን ሲሰሙ ‹‹ይህችንማ ሄደን ማየት አለብን›› ተባበብለው ያላቸውን ሁሉ ይዘው ታቦቶቻቸውን፣ ካህናቶቻቸውን፣ ንዋየ ቅድሳቶቻቸውን፣ መጻሕፍቶቻቸውን ሁሉ ይዘው በዘሚካኤል (አቡነ አረጋዊ) መሪነት በመምጣት በ460 ዓ.ም ጳጳሱና ንጉሡ ካሉበት አክሱም ከተማ ገቡ፡፡
በዚያም ለ12 ዓመታት በፍጹም አንድነት አብረው ከተቀመጡ በኋላ ‹‹እርስ በራሳችን እየተያየን ብንኖር ተድላ ደስታ ይሆንብናልና ተለያይተን እንቀመጥ›› ብለው ተማከረው በተለያየ በዓት በተጋድሎ መኖር ጀመሩ፡፡ አባ ሊቃኖስ በደብረ ቁናጽል፣ አባ ጰንጠሌዎንም በእርሱ ትይዩ በሆነ ቦታ፣ አባ ገሪማ በደብረ መደራ፣ አባ ጽሕማ በደብረ ጸድያ፣ አባ ይምአታ በደብረ ገረዓልታ፣ አባ አፍጼ በደብረ ይሐ፣ አባ አሌፍ በደብረ አኅድአ መኖር ጀመሩ፡፡ አባ አረጋዊ ደግሞ በጣም ርቀው በመሄድ በደብረ ዳሞ በዋሻና በፍርኩታ ውስጥ በተራራም ላይ መኖር ጀመሩ፡፡
ተሰዓቱ ቅዱሳን ብዙ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን ያደረጉ ነበር፣ ተአምራቶቻቸውን መንፈሳዊ ዐይኑ ያልበራለት ሰው ከቶ ሊረዳውና ለገነዘበው አይችልም፡፡ መላእክትም ዘወትር ባለመለየት ይጎበኙዋቸው ነበር፡፡ ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስም ዘወትር እየተገለጠላቸው ይባርካቸውና ቃልኪዳን ይሰጣቸው ነበር፡፡ በጸሎታቸውም አጋንንትን ያስወጣሉ፣ ድውያንን ይፈውሳሉ፣ ዕውራንን ያበራሉ፣ ሙታንን ያስነሣሉ፡፡ ለእያንዳንዳቸውም የሃይማኖታቸውን ኃይል አሳዩ፡፡ ከእነርሱ መካከል ተራራ ያፈለሱ አሉ፣ ባሕሩን ከፍለው ደረቅ መንገድ ያደረጉ አሉ፣ ጠዋት ዘርተው ማታ ሰብስበው የሚያጭዱ አሉ፣ ይኸውም የስንዴውን ነዶ በግራር ዛፍ ላይ አበራይተው የዛፉ ቅጠል ሳይረግፍ በሬዎቹም ከዛፉ ላይ ሳይወድቁ ምርቱ ብቻ እየወረደ በአውድማው ላይ እንዲከማች ያደረጉ አሉ፣ ወዲያውም ስንዴውን ለመገበሪያ ሠይመው ለዘጠኝ ሰዓት መሥዋዕተ ቊርባን ያደረሱ አሉ፡፡
በዓለት ድንጋይ ላይ የወይራ ተክል ተክለው በዚያኑ ጊዜ ጸድቆ ለምልሞ ታላቅ ዛፍ ከሆነ በኋላ በእግዚአብሔር ፈቃድ ግንዱ ደርቆ ቆርጠውና ፈልጠው እንጨቱን አንድደው እሳቱ ፍም ከወጣው በኋላ ፍሙን በቀጭን ሻሽ ወስደው ለዘጠኝ ሰዓት የቅዳሴ ማዕጠንት ያደረሱ አሉ፡፡ ለቤተክርስቲያን አገልግሎት የሚውልና ለሥርዓተ ቊርባን ማከናወኛ የሚሆን ውኃው ሳይፈስ በወንፊት ውኃ የሚቀዱ አሉ፡፡
ከእነሱም አንዱ በዐረፈ ጊዜ የሥጋው ሥርዓተ ግንዘት በመላእክት እጅ የተከናወነ አለ፡፡ ይልቁንም ቁመቱና ርዝመቱ ከታላላቅ ገደል እጅግ በጣም የሚበልጥ የድንጋይ ዓምድ ከወንዝ ማዶ ዘንበል ብሎ መጥቶ ሥጋቸውን በክብር ተቀብሎ በተራራው ጫፍ ላይ እስከዛሬም ድረስ ፈጽሞ ሳይነቃነቅና ሳይናወፅ ቀጥ ብሎ ቆሞ ይገኛል፡፡ የሰዎቹም የመግነዝ ምልክት ጥበበኛ እንደሣለው ሥዕል በድንጋዩ ዓምድ ላይ ተስሎ ወይም ተቀርፆ ይታያል፡፡ ቆመው ጸሎት በሚጸልዩበት ጊዜ ዓሥሩ የእጆቻቸው ጣቶችና ዓሥሩ የእግሮቻቸው ጣቶች እንደፋና የሚያበሩበትና እንደመብረቅ የሚብለጨልጩበት ጊዜ አለ፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ ያለአንዳች ሐዋርያ ስብከት አስቀድማ በክርስቶስ እንዳመነችና በዚህም ምክንያት የልዕልናዋን ታሪክ ለዓለም ለማሳወቅ ፈጥነው የሄዱ አሉ፡፡ የኢትዮጵያ ምድር በእነዚህ የቅዱሳን ኪደተ እግር ተቀደሰች፣ በውስጧም በመመላለሳቸው አውራጃዎቿና አደባባዮቿ ሁሉ ታደሱ፡፡ መዓዛ ትምህርታቸውና ተአምራቶቻቸው በሁሉም አውራጃዎች ተሠራጨ፣ የእምነቷንም መሠረት አጸኑ፡፡
የቅዱሳኑ ምልጃቸውና በረከታቸው በአማላጅነታቸው በምንታመን በሁላችን ላይ ይደርብን! አሜን!!!