Wednesday, February 1, 2017

የእመቤታችን ድንቅ ተአምር

ከዚህ በታች የምታነቡትን ድንቅ ተአምር ያደረገችው የእመቤታችን ስዕለ አድህኖ በሀገራችን በኢትዮጵያ ሰበታ ቤተ ደናገል ጠባባት አንድነት ገደም (ጌቴሰማኔ ማርያም) የሚገኝ ሲሆን ምስለ ስእሏን በ ፎቶም ሆነ በቪድዮ ማንሳት ለክብሯ ሲባል የተከለከለ ነው፡፡ ይህ የምታዩት ግን እዛው ሰበታ መድኃኒአለም ቤተክርስትያን ውስጥ ይገኛል፡፡ ይህችን ተአምረኛ ምስለ ስእል እንዴትና ማን እንዳመጣት እንዲሁም የሰራችውን ተአምር እዛው ሄደው እንዲሰሙና እንዲያዩት እጋብዛለሁ፡፡
(በድጋሜ ፨ እባካችሁ አንተ ታዲያ ፎቶውን እንዴት አነሳኽው ለምትሉ፤ ይሄኛው ሌላ ነው አሳሳሉ ግን ይሄን ታሪክ መሰረት አድርጎ ነው። ተአምረኛዋ ምስለ ስዕል ግን አንድ አጥማቂ አባት (ቡኃላ አቡነ የተባሉ) በቦርሳቸው ይዘዋት ይዞሩ የነበሩ የጣሊያን ጦር ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜ ጥይት ያልጎዳት መጽሐፍ ቅዱስ ነው ምታክለው። ገዳማውያን እናቶች አክብረው አስቀምጠዋታል)

ተአምሪሃ ለእግዝዕትነ ቅድስት ድንግል በ ፪ኤ ማርያም ወላዲተ አምላክ ጸሎታ ወበረከታ የሃሉ ምስሌነ ለዓለመ ዓለም አሜን ልመናዋ ክብሯ በእኛ ለዘላለም በውነት ይደርብንና አምላክን የወለደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የፀናች ክብርት እመቤታችን ያደረገችው ተዓምር ይህ ነው። አምላክን የወለደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የፀናች ክብርት እመቤታችን በሥዕሏ አድራ ያደረገችውን ተዓምር ስሙ ።
ከአፍርንጊያ አገር ( ከአፍሪካ )ማለት ነው በከበረ ልብስና በወርቅ በብርም እጅግ የከበረ አንድ ነጋዴ ነበር ። ያም ሰው ሥጋ የለበሰች የምትመስለውን አምላክን የወለደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የፀናች የክብርት እመቤታችንን ሥዕል ዜና በሰማ ጊዜ ፈጽሞ ደስ አለው ። ገንዘቡን ሁሉና ንግዱንም ትቶ ደኃ መስሎ ወደ ጼዴንያ አገር ሄደ ሥዕሏንም ሠርቆ ወደ አገሩ አፍርንጊያ (አፍሪካ) ይወስዳት ዘንድ ይህንን ምክኒያት አደረገ ሥዕሊቱንም አግኝቶ ወደ አገሩ ይወስዳት ዘንድ የተጠረገ መንገድን ሊያገኝ ደጅ እየጠና በጼዴንያ የተሠራች የእመቤታችንን ቤተ ክርስቲያን ለሁለት ዓመት ያህል ሲያገለግል ኖረ ። እመምኔቲቱ ግን የመነኮሳቱን በር በፍፁም ትጋት ትጠብቅ ነበርና ሥዕሊቱን ይወስዳት ዘንድ እንዳልተቻለው ባወቀ ጊዜ ሾተልን ይዞ እጁን በመስኮት አዝልቆ ከሥዕሊቱ የሥጋ ቁራጭን ያህል ቆረጠ ያን ጊዜም ከሥዕሊቱ ደም ወጣ ። እርሱም የሥጋ ቁራጭን ያህል ይዞ ወጥቶ ተሠወረ ። ያን ጊዜም ሰዎች አውቀው በጭንቅ ፈልገው አግኝተው ያዙት ይገድሉትም ዘንድ ወደዱ ። ያን ጊዜም ከሥዕሊቱ እንዲህ የሚል ቃል ተነገረ "" እኔን ስለ መውደዱ ክብር ሊሆነው ወስዷል እንጂ ይህንንስ በክፋት አላደረገውምና ተዉት አትግደሉት ነገር ግን የተቆረጠውን ሥጋ ከእርሱ ወስዳችሁ ከተቆረጠበት ቦታ ግጠሙት "" ያን ጊዜም እንዲሁ አድርገው አኖሩትና ሥጋው ተጣብቆ ቀድሞ እንደነበረ ሆነ ነገር ግን የደምና የሾተሉ ፍለጋ ምልክቱ እስከዛሬም ድረስ ታውቆ ታይቶ ይኖራል ። በአርያም ለሚመሰገን አምላክን በወለደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ በፀናች በክብርት እመቤታችን አማላጅነትም ይህንን ተዓምር ለገለጸ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይገባል ። ልመናዋ ክብሯ አማላጅነትዋ የልጅዋ የወዳጅዋም ቸርነት በእኛ ለዘለዓለም በውነት ይደርብን ። አሜን

የእመቤታችን መቃብርና ያረገችበት ጣራ - Tomb of The Virgin Mary