Thursday, June 2, 2016
Wednesday, June 1, 2016
መጻሕፍቶቻችን ስለ ቅ/ያሬድ ምን ይላሉ?
መጻሕፍቶቻችን ስለ ቅ/ያሬድ ምን ይላሉ?
ኢትዮጵያ ተለይታ ከምትታወቅባቸው እና ቤተ ክርስቲያናችንም ለሀገሪቱ ካበረከተቻቸው ብዙ ነገሮች አንዱ ያሬዳዊ ዜማ ነው። የዚህ ልዩ ሀብት ጀማሪ የሆነው ግንቦት ፲፩ ቀን ክብረ በዓል የሚደረግለት ቅ/ያሬድ ኢትዮጵያዊ ቅዱስ፣ ካህን፣ ሊቅ፣ መዓርዒረ ዜማ፣ ደራሲ (የዜማ እና የመጻሕፍት)፣ የመጻሕፍት መምህር
፣ ባለቅኔ (በድጓው ውስጥ ያሉ
ቅኔዎችን መዘርዘር ይቻላል)፣ ሰማዕት (ያሬድ ማኅሌተ እግዚአብሔርን ሲያደርስ ንጉሡ ገብረ መስቀል ተመስጦ እግሩን
ስለወጋው ደሙን አፍስሷልና) ወዘተ. የሚሉት ስለ ክብሩ የሚቀጸሉ መጠሪያዎቹ ናቸው። ኢትዮጵያ ተለይታ ከምትታወቅባቸው እና ቤተ ክርስቲያናችንም ለሀገሪቱ ካበረከተቻቸው ብዙ ነገሮች አንዱ ያሬዳዊ ዜማ ነው። የዚህ ልዩ ሀብት ጀማሪ የሆነው ግንቦት ፲፩ ቀን ክብረ በዓል የሚደረግለት ቅ/ያሬድ ኢትዮጵያዊ ቅዱስ፣ ካህን፣ ሊቅ፣ መዓርዒረ ዜማ፣ ደራሲ (የዜማ እና የመጻሕፍት)፣ የመጻሕፍት መምህር
ቅ/ያሬድ ሲነሳ ሁሌም ቀድሞ በአእምሯችን የሚመጣው በኢትዮጵያ ውስጥ ዜማን የጀመረ መሆኑና ግእዝ፣ ዕዝል፣ አራራይ ብሎ በሦስት መደብ መክፈሉ ነው። ዜማው ከዛሬ 1500 ዓመታት በፊት ተጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ የማይሰለችና ልዩ መንፈሳዊ ሐሴትን የሚያጎናጽፍ ሰለሆነ በእርሱ ዜማ የመመሠገነው ልዑል አምላክ፣ አመሥጋኞቹ ካህናትንም ምድራውያን መላእክት የሚያሰኝ ነው። ቅ/ያሬድ ከመነሳቱ በፊት በኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ውርድ ንባብ ያለ ትሑት ቃል እንጂ ምልክት ያለው በዜማ የሚደርስ ማሕሌት አልነበረም። ስለዚህ ዜማ ሲነሳ ያሬድ መጠራቱ አይቀሬ መሆኑን ሁሉም የሚስማማበት ነው። ሌላው የቅ/ያሬድ አስተዋጽኦ እና በብዙዎች ዘንድ የማይታወቀው ሥራው በኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመሪያው ደራሲ እሱ መሆኑ ነው። እስካሁን በተደረገው ጥናት የኢትዮጵያ ጽሑፎች እስከ ያሬድ መነሳት ድረስ ትርጉሞች (በተለይ ከግሪክ ቋንቋ) ነበሩ። ብሔራዊ ድርሰትን (ሀገር በቀል) በኢትዮጵያ የጀመረ ያሬድ ነው። ለዛሬ የማቀርበው ጽሑፍ ቅ/ያሬድ የደረሳቸውን መጻሕፍትና የኋላ ሊቃውንት ስለ እርሱ ክብር የጻፉትን በመጠኑ ይመለከታል። (ስለ ሕይወት ታሪኩ በብዙ ቦታ ስለተጻፈ ብዙም አልዳስሰውም።)
በሀገራችን ከሚገኙት መጻሕፍት ስለ ቅዱስ ያሬድ የሚናገሩ መጻሕፍት በርካታ ናቸው፤ በጥቅሉ በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች እንመድባቸዋለን። የመጀመሪያዎቹ ራሱ ቅ/ያሬድ የጻፋቸው የዜማ መጻሕፍት ሲሆኑ፤ ሁለተኛዎቹ ስለ ቅ/ያሬድ ክብር የተደረሱ የምሥጋና ድርሰቶች፤ ሦስተኞቹ የቅ/ያሬድን ታሪክ የያዙ ሌሎች መጻሕፍት ናቸው። ዝርዝራቸውን ቀጥሎ እንመልከት።
ሀ) እርሱ የጻፋቸው፤
ከላይ በመግቢያው እንዳልነው ቅ/ያሬድ የምሥጋና እና የአምልኮ መግለጫ የሆኑ የዜማ መጻሕፍትን በግዕዝ ቋንቋ ጽፏል። እነዚህም በስፋት የሚታወቁት አምስቱ የዜማ መጻሕፍቱና በታሪክና በትውፊት የተቀበልናቸው ሌሎች መጻሕፍት ናቸው። እነርሱም፥
1) ድጓ - ከቅ/ያሬድ ድርሰቶች ውስጥ ትልቁ የዜማ መጽሐፍ ድጓ ሲሆን በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች የተከፈለና በቤ/ክ ከዓመት እስከ ዓመት የሚደርስ ምስጋና ነው። በተለያዩ ዘመናት የተገለበጡ የድጓ ቅጂዎች በኢትዮጵያ የሚገኙ ሲሆን አንዳንድ ጠቃሚ እና ትክ የማይገኝላቸው ቅጂዎች ከባሕር ማዶ ተሻግረው ይገኛሉ (ለምሳሌ ቫቲካን [Vat. Aeth. 28]፣ በርሊን [Orient. 1000])። በሀገራችን ከሚገኙት ዕድሜ-ጠገብ ድጓዎች መካከል በላሊበላ ቤተ-ጊዮርጊስ የሚገኘው (12ኛ መ/ክ/ዘ)፣ በጣና ቂርቆስ የሚገኘው (13 መ/ክ/ዘ)፣ በደብረ ብርሃን የሚገኘው (16ኛመ/ክ/ዘ)፣ የሐይቁ ድጓ (17መ/ክ/ዘ)) ይጠቀሳሉ። “መጽሔተ፡ ጥበብ” በመባል የሚታወቀው የቅ/ቤተልሔም (ደ/ጎንደር) ድጓ ለምስክር አብነት ነው።
2) ጾመ ድጓ - በዐቢይ ጾም የሚደርስ ምሥጋና ነው። ጾመ ድጓ በዋናው ድጓ (ከአስተምህሮ ድጓ) ክፍል ተካቶ ይገኛል። ክፍሉ በዓቢይ ጾም ውስጥ ባሉት ሰንበታት ልክ ሲሆን ተራቸውም፤ ዘወረደ፣ ቅድስት፣ ምኵራብ፣ መጻጕዕ፣ ደብረ፡ ዘይት፣ ገብር፡ ሔር፣ ኒቆዲሞስ እና ሆሣዕና የሚል ነው።
3) ምዕራፍ - ይህ የዜማ መጽሐፍ ከመዝሙረ ዳዊት የተውጣጡት ምሥጋናዎችን በመስመር በመስመር እየከፈለ የሚደርስ የስብሐተ እግዚአብሔር መጽሐፍ ነው።
4) ዝማሬ - ማሕሌት ሲቆም የሚደርስ ሆኖ በጊዜ ቅዳሴ ከድርገት በኋላ የሚቀርብ ምሥጋና ነው። ዝማሬ አምስት ክፍሎች ያሉት ሲሆን እነዚህም ኅብስት፣ ጽዋ፣ መንፈስ፣ አኮቴት እና ምስጢር የሚባሉት ናቸው። የዚህ የዝማሬና የመዋሥዕት ማስመስከሪያ ቤተ ጉባኤው ቅ/ያሬድ ባስተማረበት ቦታ በዙርአባ አረጋዊ ቤ/ክ (ደቡብ ጎንደር) ነው።
5) መዋሥዕት - ካህናት በተዋሥኦ (በመቀባበል) የሚያዜሙት ሲሆን በተለይ በጸሎተ ፍትሐት ጊዜ እና በቀዳም ሥዑር ዕለት የሚደርስ ምሥጋና ነው።
6) አንቀጸ ብርሃን - ቅ/ያሬድ ይህን የእመቤታችንን ምሥጋና ያደረሰው በአክሱም ጽዮን ቤ/ክ ውስጥ ከታቦተ ጽዮን ፊት ቆሞ ሲሆን ድርሳኑ ይህንን እንዲህ ይገልጻል “ወሶቤሃ፡ ቦአ፡ ያሬድ፡ ውስተ፡ ታቦተ፡ ሕጉ፡ ለእግዚአብሔር፡ እንተ፡ ይእቲ፡ ገበዘ፡ አክሱም፡ ወአንበረ፡ ፪እደዊሁ፡ ውስተ፡ ርእሰ፡ ታቦት፡ ወከልሐ፡ በልዑል፡ ቃል፡ እንዘ፡ ይብል፡ ቅድስት፡ ወብፅዕት፡ ስብሕት፡ ወቡርክት፡ ክብርት፡ ወልዕልት፡ አንቀጸ፡ ብርሃን፡ መዓርገ፡ ሕይወት፡ እስከ፡ ተፍጻሜቱ። ..... ።” ገድሉ እና ተአምሩ (ሦስተኛው) እመቤታችንን እየለመነ አንቀጸ ብርሃንን በዕዝል ዜማ ሲያደርስ ቁመቱ አንድ ክንድ ያህል (“ተለዓለ፡ መጠነ፡ እመት፡”) ከምድር ወደ ላይ ከፍ ይል እንደነበር መዝግበውታል። ለዚህ ጸሎት ምላሽ እመቤታችንም ተገልጻ በቃል ታናግረው ነበር።
7) የሦስት ቅዱሳንን ገድል ጽፏል፤ በትውፊት እንደሚታወቀው ቅ/ያሬድ ከዘጠኙ ቅዱሳን መካከል የሦስቱን ቅዱሳን ገድል ጽፏል። እነዚህም ገድለ አረጋዊ፣ ገድለ ጽሕማ እና ገድለ ይምአታ ናቸው።
8) ቅዳሴ - የታተሙት ቅዳሴያት 14 በብዛት ይታወቃሉ፤ ነገር ግን ያልታተሙ ሌሎች ስድስት ቅዳሴያትም አሉ፤ የቅ/ያሬድ ቅዳሴም ካልታተሙት አንዱ ነው።
ለ) ስለ ቅ/ያሬድ ክብር የተጻፉ
ከኢትዮጵያ ቅዱሳን ሊቃውንት ግንባር ቀደም የሆነው ማሕሌታይ ያሬድ በዜማ ደራሲነቱ በዓለም ደረጃ የሚታወቅ ሲሆን ካበረከተው ዘመን ተሻጋሪ ሥራ አኳያ ስናየው ግን ስለ እርሱ ክብር የተጻፈው አነስተኛ ነው። ድርሳን እና ገድል ተጽፎለታል ሆኖም በጣም አጫጭር ናቸው። እስካሁን ከተገኙት ውስጥ ዕድሜ ጠገብ የሆነው በሐይቅ ገዳም (ደቡብ ወሎ) ከሚገኘው “ገድለ ቅዱሳን” ውስጥ የሚገኘው “ድርሳን ወገድል ዘቅ/ያሬድ” ሲሆን የተጻፈበት (የተቀዳበት) ዘመኑም በ16ኛው መ/ክ/ዘ ነው። በሁለተኛ ደረጃ ጥንታዊ የሚባለው የቅ/ያሬድ ድርሳን እና ገድል በ17ኛው መ/ክ/ዘ/ የተጻፈው እና በሀገረ እንግሊዝ የሚገኘው ሲሆን፤ ሦስተኛው ደግሞ በዘመዶ ማርያም (ሰሜን ወሎ) የሚገኘው ሲሆን ዘመኑም በ18ኛው መ/ክ/ዘ ነው። በ19ኛው እና በ20ኛው መ/ክ/ዘ ሌሎች በርካታ ቅጂዎች በብዙ ቦታዎች ይገኛሉ። በውጭ ሀገር ከሚገኙት ቅጂዎች ውስጥ በፓሪስ ቤ/መጻሕፍት የሚገኘውን ገድል ኮንቲ ሮሲኒ የሚባል ምሁር ከግዕዝ ወደ ላቲን ተርጉሞ እ.ኤ.አ. በ1904 አሳትሞታል። ድርሳን፣ገድል፣ ተአምር እንዲሁም መልክአ ያሬድን ይዟል። ቀጥለን በዝርዝር እንመልከታቸው፤
1) ድርሳነ ያሬድ - ለቅዱስ ያሬድ ታሪክ ዋና ምንጭ ሆኖ የሚጠቀሰውና ከገድሉ ይልቅ ስፋት ያለው ድርሳኑ ነው። ሲጀምር እንዲህ ይላል፥ “በስመ፡ አብ፡ ወወልድ፡ ወመንፈስ፡ ቅዱስ፡ ፩አምላክ። ድርሳን፡ ዘቅዱስ፡ ያሬድ፡ ካህን፡ ቀርነ፡ ቤተ፡ ክርስቲያን፡ ዘይጼውዖሙ፡ ለመሃይምናን፡ ከመ፡ ይሴብሕዎ፡ ለእግዚአብሔር፡ በክላሕ፡ ወበዓቢይ፡ ቃል፡ ከመ፡ ሱራፌል። ....”
2) ገድለ ያሬድ - የቅ/ያሬድን የሕይወት ታሪኩንና ተጋድሎውን ዜና በአጭሩ የሚዘክር ሲሆን ሲጀምር እንዲህ ይላል፥ “በስመ፡ አብ፡ ወወልድ፡ ወመንፈስ፡ ቅዱስ፡ ፩አምላክ። ገድል፡ ወስምዕ፡ ዘቅዱስ፡ ወንጹሕ፡ ወብፁዕ፡ ወኅሩይ፡ ያሬድ፡ ካህን፡ ጸሎቱ፡ ወበረከቱ፡ ወሀብተ፡ ረድኤቱ፡ የሀሉ፡ ምስሌነ፡ ....”
3) ተአምረ ያሬድ - ካህኑ ያሬድ የፈጸማቸው ገቢረ ተአምራት በርካታ ቢሆኑም በገድሉ ላይ ተመዝግበው የምናገኛው ግን ሦስት ናቸው።
4) መልክአ ያሬድ - የኋላ ሊቃውንት ስለ ቅ/ያሬድ ክብር እንዲሆን “መልክእ” ደርሰውለታል። ሲጀምር እንዲህ ይላል፥ “በስመ፡ እግዚአብሔር፡ ሥሉስ፡ ዘበሰማያት፡ አቡነ። በምግባር፡ ወግዕዝ፡ ዘወለደነ። ያሬድ፡ ወጠንኩ፡ ለመልክእከ፡ ድርሳነ። አብርህ፡ ኅሊናየ፡ ወዘልብየ፡ ዓይነ። ወበልሳንየ፡ ጸሐፍ፡ ሐዲሰ፡ ልሳነ።” ... ይህ መልክእ በብዙ ቦታ የሚገኝ ሲሆን እኔ ማስተያየት የቻልኩት ፓሪስ ከሚገኘው እና ኮንቲ ሮሲኒ (1904) ካሳተመው ነው።
5) የግንቦት ፲፩ ስንክሳር ንባብ - የግዕዙ ስንክሳር (እንዲሁም የባጅ - እንግሊዝኛ ትርጉም 1928፣ የኮሊ - የፈረንሳይኛ ትርጉም 1997፣ የትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት ሕትመት - የአማርኛ ትርጉም 1993 ዓ.ም.) ስለ ቅ/ያሬድ ሕይወት ይዘረዝራል። ሲጀምር እንዲህ ይላል፤ “ወበዛቲ፡ ዕለት ካዕበ፡ አዕረፈ፡ ያሬድ፡ ማኅሌታይ፡ አምሳሊሆሙ፡ ለሱራፌል። ወዝንቱ፡ ቅዱስ፡ እምአዝማዲሁ፡ ለአባ፡ ጌዴዎን፡ ውእቱ፡ እምካህናተ፡ አክሱም፡ ....”
6) ነግሥ ዘያሬድ - ለቅ/ያሬድ ካተደረሱት የ“ነግሥ” ምሥጋናዎች መካከል አንዱ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ የደረሰው ብሎ ይጀምራል፥ “ያሬድ፡ ቀሲስ፡ መዓርዒረ፡ ዜማ፡ ማኅሌታይ። መዓንዝር፡ ከመ፡ ወልደ፡ ዕሴይ። .....” ሁለተኛው ደግሞ አፄ ዘርአ ያዕቆብ የደረሰው ምሥጋና ሲሆን እንዲህ ይላል “ሰላም፡ እብል፡ ለያሬድ፡ ቀሲስ፡ ምሉዐ፡ መንፈስ፡ ለኢትዮጵያ፡ ነደቀ፡ በሃሌ፡ ሉያ፡ ምድራስ። አስተባልሐ፡ ደቂቃ፡ በዜማ፡ ሠላስ። መኃልይሁ፡ ውዱስ። በስብሐት፡ ሐዲስ።”
7) አርኬ - ፓሪስ የሚገኘው (ኮንቲ ሮሲኒ ያሳተመው) እና በትንሣኤ ማሳተሚያ የታተመው የስንክሳሩ አርኬ ስለ ቅ/ያሬድ ምሥጋናውን እንዲህ ብሎ ይጀምራል - “ሰላም፡ ለያሬድ፡ ስብሐተ፡ መላእክት፡ ለሕዋጼ። እንተ፡ አዕረገ፡ በልቡ፡ ሕሊና፡ መንፈስ፡ ረዋጼ።...”። በ17 መ/ክ/ዘ የተጻፈውና ለንደን (ብሪቲሽ ቤ/መ) የሚገኘው የስንክሳር አርኬ እንዲህ ይላል፤ “ሰላም፡ ለዝክረ፡ ስምከ፡ ዘተጸውዖቱ፡ መዓር።...”
ሐ) ስለ ቅ/ያሬድ የሚያስረዱ ሌሎች መጻሕፍት
1) ገድለ አረጋዊ - ከላይ እንዳየነው በትውፊት የገድለ አቡነ ጸሐፊ ቅ/ያሬድ እንደሆነ ይነገራል። የታተመው ገድለ አረጋዊ የጸሐፊነቱን ሚና ለሌላ ይሰጠዋል፤ ሁለቱን ሃሣቦች ስናገናዝባቸው ሊሆን የሚችለው መጀመሪያ ያሬድ ጽፎት በኋላ ሌሎች ገልብጠውታል ማለት ነው። ወደ ገድለ አረጋዊ ስንዘልቅ በርካታ ቦታዎች ላይ የቅዱስ ያሬድን ታሪክ መዝግቦት ይገኛል። ያሬድ በዘመነ ገብረ መስቀል ማሕሌቱን እንደጀመረ፣ ድርሰቱን ከብሉይ ከሐዲስ እንዳውጣጣው፣ ዜማውን ከመላእክት እንደሰማው፣ ወዘተ.... ይዘረዝራል። እንዲሁም ወደ ደብረ ዳሞ ወጥቶ ሕንጻ ቤ/ክ ሲመለከት “ወከልሐ፡ በቃለ፡ መዝሙር፡ ወይቤ፡ ይሔውጽዋ፡ መላእክት፡ እስመ፡ ማኅደረ፡ መለኮት፡ ይእቲ፡ ዖድክዋ፡ ዖድክዋ፡ ዖድክዋ፡ ወርኢኩ፡ ሥነ፡ ሕንጼሃ፡ ለቅድስት፡ ቤተ፡ ክርስቲያን።” ብሎ እንደዘመረ፡ ይናገራል።
2) ድርሳነ ዑራኤል - የቅ/ያሬድን ታሪክ ከያዙት የቤ/ክ መጻሕፍት መካከል አንዱ ድርሳነ ዑራኤል ሲሆን እመቤታችን ተገልጻ ቅ/ኤፍሬምንና አባ ሕርያቆስን “ዜማ እንዲደርስልኝ ውዳሴዬንና ቅዳሴዬን ለያሬድ ስጡት” ብላ እንዳዘዘቻቸውና ቅ/ያሬድም በተሰጠው ሀብተ ዜማ እንደዘመረ ይናገራል። ለቅ/ያሬድ ጽዋዓ ልቡና ያጠጣው መራሔ ብርሃናት ዑራኤል እንደሆነ ድርሳነ ዑራኤል ይገልጻል።
3) መጽሐፈ አክሱም - ይህ መጽሐፍ የአክሱም ጽዮንን ታሪክ እና የርስት ጉልቷን ሥሪት የሚናገር ሲሆን ስለ ቅ/ያሬድ ዜማ ድርሰት ይናገራል። እንዲሁም ከላይ በድርሳነ ዑራኤል የተገለጸውን ታሪክ (እመቤታችን ተገልጻ ቅ/ኤፍሬምንና አባ ሕርያቆስን “ዜማ እንዲደርስልኝ ውዳሴዬንና ቅዳሴዬን ለያሬድ ስጡት” ያለችውን) መዝግቧል።
4) ታሪከ ነገሥት - የኢትዮጵያን ታሪክ ከያዙት መጻሕፍት አንዱ የሆነው የዙርአባ (ዙራምባ) ታሪከ ነገሥት የቅ/ያሬድን ታሪክ የያዘ ሲሆን በተለይ በዑራኤል መሪነት ከአጼ ገ/መስቀልና አባ አረጋዊ ጋር ወደ ዙርአባ ተራራ እንደወጡ፣ በዙርአባ ለሦስት ዓመታት ቅ/ያሬድ ዝማሬና መዋሥዕትን እንዳስተማረ ይናገራል።
የቅዱስ ያሬድ በረከት ከሁላችን ላይ ይደርብን፤
ግንቦት ፳፻፰
Monday, May 30, 2016
ፖርት ሳይድ ማርያም ፡ ዘይት የምታፈልቀው ስእል
እህታችን ማሕሌት መኮንን በግብጽ ፖርት ሳይድ ማርያም ተገኝታ ዘይት የምታፈልቀውን የእመቤታችንን ስእል ተኣምሩን በ ምስል ወድምጽ ታቀርብልናለች፥፥ ከዚህ በፊት ስለዚህ ተኣምር በሚከተሉት ፖስቶች ኣስነብበን ስለነበር በተያይዝነት ብታነቡት ሙሉ ተኣምሩን ትረዳላችሁ::
ከእጇ ዘይት የሚፈልቅ የቅድስት ኤልሳቤጥ አስገራሚ ታሪክ
ፖርት ሳይድ ማርያም በግብጽ
Subscribe to:
Posts (Atom)