ጎንድ ተክለ ሐይማኖት ገዳም ከአማራ ክልል ርእሰ መዲና ባህር ዳር ተነስተን ዘንዘሊማ ሐሙሲት ከዚያም የፎገሮቹን አገር ወረታን እያቆራረጥን አዲስ ዘመን
እንደደረስን የጎንደሩን መስመር ተከትለን የጻድቋን እናት ጣራ ገዳም ደንን እያማተርን በውብ የአእዋፍ ዜማ
ተደምመን ከተቻለ መኪናችን ቆም አድርገን ሰላም ለኪ ብለን በአጸዶቿ መአዛ ህሊናችን ሰብስበን ጉዟችን አሁንም
ወደፊት ስንቀጥል የሊቦ ከምከምና የጎንደር ዙሪያ ወረዳ መካለያ የሆነችውን በ'ራሷ ጊዜ መድመቅና ከተሜነት
የጀመረችው ሰንደባ ወንዟን አርኖን ተንተርሳ ውብ የሆነውን አየሯን እየለገሰች ትጠብቃለች ወንዟ አርኖ አመቱን ሁሉ
ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ለአርሶ በሌው ውሐውን ይለግሳል አርሶ አደሩም የተለያዩ ምርቶችን እያመረተ ሲያሻው ወደአዲስ
ዘመን ያልያ ወደእንፍራዝ በትናንሽ ታክሲዎች እያጓጓዘ ለከተማው ማህበረሰብ ይቀልባል። አርኖ የባለፉት ወራሪዎቻችን
የጣሊያን ሰዎች ስያሜውን እንደሰጡት ይናገራል። ከ'ዚህች ትንሽየ የገጠር ከተማ እልፍ እንዳሉ በቅርብ ርቀት ጋርኖን
ተንተርሳ እንፍራዝን ታገኟታላችሁ፡፡ እንፍራዝ ቀደምት ከተማ ስትሆን ከ'ሷ በቅርብ ርቀት የደብሳን ግንብ የጉዛራ
ቤተ መንግስት አጼ ሰርጸ ድንግል በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የከተመበት እንደነበር ታሪክ በየድርሳኑ ይዘግባል።
ከዚህም ጋር በተገናኜ እንፍራዝ የአጼ ቴዎድሮስ እናት ርስት ቦታ ስትሆን ተወላጅነታቸውም 'ዚህች ከተማ አካባቢ
እንደነበረ የታሪክ ዘካሪዎች በየጦማራቸው ከትበውታል፡፡
እንፍራዝ ፍቅር ተዘርቶ የበቀለባት ትንሽ ቦታ ግን ማህበረሰቦቿ ተቻችለውና ተረዳድተው የሚኖርባት ከደረቅ ወደብ ተነስተው የሚመጡ ተሳቢ መኪኖች ጎንደር በር ጣዕመት ወደባህርዳር መውጫ አልሚ ምግብ ቤት እረፍት አድርገው ያሻቸውን በልተው ጠጥተው ይጓዛሉ። ትናንሽ ህጻናት ቆሏቸውን በሰፌድ ብትን አድርገው ይውሰዱ ይብሉ እያሉ በውብ ፈገግታቸው ራብን አፈ ድሜ ያበሉታል። እንዳልኩት እንፍራዝ ካረፉ በኋላ ጉዞዎን እንደቀጠሉ ቁልቋል በር ላይ የሰፈሩትን የወረኢሉ ሙስሊሞች ወሎ ያለን እስኪመስለን ድረስ "ዴ " ን አጥበቀው እየጠሩ በፈገግታ ያስዋኛሉ። መኪና ላይ አያጧቸውም ተሳፍረው አብረው ካገኟቸው እንዴት ከወረኢሉ እንደመጡ 'ዚህ አካባቢ ሰፍረው እንደቀሩና ተላምደው በፍቅር እየኖሩ እንዳሉ በሚያምረው ልሳናቸው ይተርካሉ፡፡ " በል አቦ ጃል ዴርሻለሁ ወገን" ብለው ዳገታማውን ጉዞ ይያያዙታል። ቁልቋል በርን እንደጨረሱ የጎንደር ዙሪያ ወረዳ ርእሰ መዲና ማክሰኝትን ያገኛሉ።
ከዚህን በኋላ መኪና ካልያዙ ወርደው የደጎማ ታክሲ ያልያ አውቶብስ ያገኛሉ። ጉዞዎን ከጎንደርም የመጣ ይሁን ከባህርዳር ጅማሬው ከተማዋ ላይ ነው፡፡ ከከተማዋ 3 ኪሎሜትር በላይ ከተጓዙ በኋላ የአርባያውን መገንጠያ ያገኛሉ። ይህ መነሻ ወደተነሳንበት ጎንድ ተክለ ሐይማኖት ገዳም ይወስደናል፡፡ ከጎንደርም ከባህርዳርም የመጣ ተጓዥ ከአስፓልት ወጥቶ የጠጠር ጎዳናውን ይያዙታል፡፡
ከ'ዚህ መነሻ አስፓልት ተነስተን ጎንድ ለመድረስ 24 ኪሜ አካባቢ የሚርቅ ሲሆን መንገዱን እየተንገራገጩ መጓዝ የግድ ይላል።
ደጎላን ዳስንና ድንዛዝን ከታለፈ በኋላ አስራ ዘጠኝ ሐያ ኪሎ ሜትር እንደተጓዙ የኢብን ኢብራሂም አልቃዚ ( ግራኝ እጁ ) የሞተበትን ስፍራ ያገኛሉ። ይህ ቦታ የፖርቱጋል ወታደሮችን መርቶ የመጣው ክርስቶፎር ደጋማ (የመርከበኛው የቫስኮ ደጋማ ልጅ ) ቱርኮች ቀይ ባህር ቢገሉትም ተተኪው የነበረው በርተለሚዎዝ ዲያዝ የንግስቲቱን ሰብለ ወንጌል ልጅ የአባቱን የልብነ ድንግልን መንበረ ስልጣን እንዲመልስ ከፍተኛ ጉትጎታ ታደርግ ነበርና ክርስቲያኖቹ ፖርቱጋሎች አግዘውት ከ'ዚህ ስፍራ ግራኝንና ተከታዮቻቸውን ድል አደረጉ። ግራኝ በኢትዮጵያ ታሪክ የቆየባቸው 15 አመታት የተረጋጉ አልነበሩም። መጨረሻውም በዚህ ስፍራ በሞት ተቋጭቷል። ያልተረጋጉ የጦርነት ውሎዎች በሟቹ ደጋማ ሰም ከተሰየመችው ከተማ ደጎማ በቅርብ ርቀት ሲከናወን ይህንን ስፍራ የአገሬው ሰዎች "የድል በር " ብለው ይጠሩታል፡፡ ተራራማው የድል በር ላይ ተሁኖ ፊት ለፊት ደጎማን ከበስተኋል አድርገን ስንመለከት ደንቀዝንና የበለሳን ፈፋዎችና የተራራ ሰንሰለቶች ያያሉ። በእውነት የኢትዮጵያዊነት ህብር የሚገለጽበት ስፍራ ወኔ የሚሰነቅበት ስፍራ ቢባል ማጋነን አይሆንም። ከምናብ ትውስታ በኋላ ወደፊት ሁለት ኪሎ ሜትር እንደተጓዙ ጎንዶችን ታገኛላችሁ። ይህ ስፍራ ወደ ከፍተኛ የተራራ ነጥብ መሄድዎትን ይነግርዎታል ጠንካራ ብርድ አለና ጃኬት መያዙዎትን ያረጋግጡ።
ጭራቆ ወንዝ ላይ እግረዎትን ተለቃልቀው ከፈለጉ ደጎማ አርፈው ቢወጡ ጥሩ ነው። ከአፍ የሚጣል አይጠፋምና ያልያ ግን መኪናዎን ደጎማ ትተው የጎንድ ተክለ ሐይማኖትን ገዳማ የእግር ጉዞ ይያያዙታል።
የአየሩ መአዛ ከሌሎች ገዳማት በላቀ ሁኔታ ይጠራዎታል። የቅዱሳኑ መአዛ አለማዊነትን ይደፍቃል በግምት ከተራራማው ክፍል ወደታችኛው የበለሳ ተዳፋት ይምዘገዘጋሉ። መንገዱን የገዳሙ መስራች አባት አባ ዮሐንስ ( ዘግብጽ ) ሲሆኑ እኝህ አባት ለበለሳ በረከት ናቸው። በስጋዊ የህይወት ዘመናቸው በለሳ የወተቱና የወገሚቱ የማሩና የቅቤውን ሁኔታ ስናስብ ልብን ቀስፎ ይይዛል። በጸሎታቸው ጸላኤን ረትተው ሊጥልባቸው የነበረውን የተራራ ናዳ ገስጸው አንጠልጥለውታል፡፡ ዛሬ ድረስ ናዳው ተንጠልጥሎ ይታያል። ከዚህም በላይ ደግሞ ሊያስታቸው የመጣን ጸላኤ አሰልጥነው መንገድና ዘመናዊ ሊባል የሚችል የመስኖ ካናል አሰርተውታል። መልሰው እንደገና በር ቆልፈው በአንዱ ዋሻ ዘግተውበታል።
አቡነ ዮሐንስ ዘግብጽ በረጅም ዘመናቸው በአካለ ስጋ እያሉ ለዚህ ገዳም ስርአት ሰርተው አልፈዋል። በኋላም ጻድቁ ተክለ ሐይማኖት በእንግድነት መጥተው ለጻድቁ ዮሐንስ ስርአተ ምንኩስናን ሰጥተዋል። የቆብ አባትም ጭምር ናቸው፡፡ ትውልድ በዘመን ጅረት ቢያልፍም ጎንድ ( ጉንደ ወይን) ከአስራ አንደኛው አስራ ሁለተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በቅድስና ኖሯል እኛ ደግ አባታችንም በአካለ ስጋ ለረጅም ጊዜ ቆይተዋል። ምንኩስና ሰርተው ህዝብን እየማለዱ ለትውልድ አስተላልፈዋል። ከ400 በላይ መነኮሳት በብህትውና ይኖሩበታል፡፡ እያንዳንዱ መነኩስና መነኮሳይት የተለየ ስፍራ አላቸው። ገዳሙ ሰፊ የሆነ ክልል ያለው ሲሆን መነኮሳቱ ጠንካራ የስራ ባህል ለማየት የሚፈልግ የየትኛውም ማህበረሰብ ክፍል ያለምንም እርዳታ በጾም በጸሎት በርትተው ደግሞ ለአንዲት ማእድ ሲሉ ሰርተው እንጅ ለምነው ያቆሙት ቤት የላቸውም። ነገረ ስራቸው ሁሉ ክርስትና ብቻ ነው የፊታቸው ጥንካሬ አለምን ድል ያደረጉበት ሰይፋቸው ጽናት ይሆናል። ጉንደ ወይን ባለፉት የታሪክ ዘውጋችን ስናነሳ ሲሲኒዮስ ካቶሊክን ሲቀበል " ሲሲኒዮስ ይፍለስ ፋሲለደስ ይንገስ " ያሉት የጉንደ ወይን መነኮሳት ናቸው፡፡ ያሉትም አልቀረ ከደንቀዝ ቤተ መንግስት ተነስተው እስከ ላይማው ሰሜን ድረስ ደማቸውን አፍስሰዋል። (ደንቀዝ የአጼ ሲሲኒዮስ መናገሻ ከተማ የነበረች ሲሆን ከጎንድ በቅርብ ርቀት ትገኛለች፡፡) የገዳሙ መነኮሳት ከሌሎቹ ታላላቅ ገዳማት ጋር የጠበቀ ግንኙነት አላቸው፡፡ በገዳሙ ሁለት አብይት በአላት አሉ፡፡ ነሐሴ 24 የጻድቁ ተክለ ሐይማኖት እረፍት ይዘከራል። በዚህን ወቅት ከተለያዪ ስፍራዎች ተሳላሚዎች ይመጣሉ፡፡ መነኮሳቱ ለመጣው ተሳላሚ ሁሉ ምግብ ያቀርባሉ የማረፊያ ቦታ ያዘጋጃሉ።
ፍራፍሬው በቆሎው እሸቱ እንደልብ ነው። ጉንደ ወይን የተገኘው ሁሉ ይበላል። በሚገርም ሁኔታ በሺዎች የሚቆጠሩ ተሳላሚዎች መጥተው ንፍሮ ቅቅሉን ጠግበው በልተው ለጉዞ ስንቅ ይቋጥራሉ። ጠላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠመቀበት ስፍራ ነው ብንል ማጋነን አይሆንም፡፡ ይህንን ጠላ ደግሞ የሚጠምቁት ወንዶቹ መነኮሳት ናቸው፡፡ ሌላው ከላይ የስራ ባህላቸው ለመነሻ ብጠቅስም መነኮሳቱ ወንዶቹ ያረሱት፥ አያርሙም ፥ ያረሙት አያጭዱም፥ ያጨዱት አይወቁም። ምርት የሚያጓጉዙት ሌሎች ናቸው፡፡ ስርአታቸው ሁሉ ህግ ነው። የሐይማኖታዊ ስርአቶቻችንን ዶግማና ቀኖና በጥብቅ አባታዊ ፍቅር ተምሮ ለመውጣት ጉንደ ወይን መምጣት።
የሚያምረውን ተፈጥሮአዊና ሐይማኖታዊ ስፍራ ይዩ በተጨማሪም በጸበሉ ፈውስን ያገኛሉና ጉንደ ወይን ይምጡ...