Wednesday, February 24, 2016

መምሕር ግርማ ከአገልግሎት የታገዱበት ደብዳቤ

መምህር ግርማ ወንድሙ
ከ ላይፍ መጽሄት ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ
የኤልያስ መንፈስ በኤልሳ እንዳደረ ሁሉ የፈለገው ሁሉ ያገኛል፡፡ እኔም የማስተምረው እኮ ክርስቲያኑ ራሱን ችሎ እንዲቆም ነው፡፡ እኔ ነገ የማልፍ ሰው ነኝ ዘላለም አልኖርም ግን ክርስትያኑ ጠላቱን እንዲጋፈጥ ፤ ክፉ መንፈስ እንዲያሸንፍ ፤ የዲያቢሎስ ትውልድ መሆኑ እንዲቆም ፤ ከዚያም በላይ የመንፈስ ቅዱስ ስራ የእግዚአብሔር ክብርና ኃይል እየጨመረ እንዲመጣ ፤ የአለም ጥበብ የእግዚአብሔር ልዩ አሰራር አውቀው ክርስቲያኖች በረከት ውስጥ እንዲገቡ ነው፡፡ ፍላጎቴ ግን እግዚአብሔር በተረገመበት፤ እግዚአብሔር የያድንም የለም በተባለበት ሃገር ውስጥ እግዚአብሔር አለ የሚል ከሆነ፤ እግዚአብሔር አዳኝ ቅዱስ ነው የሚል ከሆነ አንተ እርኩስ ነህ የሚለው ነው የሚበዛውና እውነታው ይሄ ነው፡፡ ይሄን የሚመስል ሁኔታ ውስጥ ነው ያሳለፍነው አሁንም እያሳለፍን ያለነው
ያደረጉት ቃለ ምልልስ..
ላይፍ፡- ሁላችሁም የእግዚአብሔር ቃል የእመቤታንን በረከት የምታስተምሩበት ቤተክርስቲያን ለምን እንዲህ አይነት መከፋፈል መጣ ብለው ያስባሉ ?
መምህር ግርማ፡- በመጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ እንክርዳድ በስንዴው መሀል እንደሚዘራው ሁሉ ያም በቤተክርስቲያን ውስጥ አለ፡፡ ገበሬው መልካም ስንዴን ዘራ የሚለው ከውጭ አይደለም፡፡ ዘሩ እዚያው ቤተክርስቲያን ውስጥ ነው፡፡ ስለዚህ በቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ህይወትና በልቦና ውስጥ መጀመርና በስጋ ህይወት መጀመር ልዩነት አለው፡፡ አምኖ መጀመርና ሳያምኑ መጀመር የእዚያን ያህል ነው፡፡ ሰሞኑን ወደ ቤተክርስቲያን ገብተው የሚኖሩ በጣም ብዙ ናቸው፡፡ እነዚህ ከተለያዩ የአስማት ስራ ጋር ወደ ቤተክርስቲያን ሲጠጉ ብዙ መልካም ነገር አይጠበቅባቸውምና ይህንን የሚመለከት ‹‹በማለዳ መያዝ›› የሚለው መጽሀፌ ላይ ሰፋ ባለ መልኩ አስቀምጬዋለሁ፡፡ ንጹህ የአምልኮት ፍላጎትና እንዲሁ ደግሞ በደብዛዛው በሚመላለሱ ሰዎች መካከል ዲያቦሎስ በደንብ ይሰራል፡፡ በተለይ ኦርቶዶክስ እምነት ላይ ሰይጣን ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣል፡፡ ከታሪክ እውነታም አንጻር እነዚህ ሰዎች ህይወት ውስጥ የተለየ እድል አለ፡፡ ገብቶ ይቀመጥና በጎው መጥላት መልካሙን እንደክፉ ማየት ማሳደድ ያለው መናፍቆች ላይ ሳይሆን እኛ ጋር ነው ያለው፡፡ ይህ ደግሞ የሃይማኖቱ አንዱ በረከት ነው፡፡ ለምን ፈሪሳውያንን ክርስቶስ በመጣ ጊዜ እምነቱን ተራ ወግና ተራ የሆነ የይስሙላ አድርገውት ነበር፡፡ ያ ሂደት ደግሞ እንደዚሁ በቆየን ቁጥር የአዲስ ኪዳንንም ህይወት እንደዚያ ነው የሚሆነው፡፡ ወደ ፈሪሳውያን ጠላት ይሄዳል፡፡ በዚህ ጊዜ እውነቱ እየጠፋ በቤተክርስቲያን ውስጥ ጣልቃ ይገባሉና ያንን ለመለየት የመንፈስ ቅዱስ ስራም የአጋንንት የቅንነትም ስራ ስለሚያስፈልግ ዛሬ ያ ቅንነቱ እና በጎነቱ በክፋት በተንኮል በምቀኝነት የተሞላ ስለሆነ ያ ሂደት ሊያደርገን አልቻለም፡፡
ላይፍ፡- ብዙ ሰባኪያን ወደ እርስዎ ፕሮግራም የማይመጡት ለምንድነው?
መምህር ግርማ፡- ይህንን የፈውስ ሂደት ስላለመዱት ልክ እንደ መተት እንደ ጠንቋይ አሰራር አድርገው እስከዛሬ ድረስ ሲያወሩ እንደቆዩ ያው የተለመደ ነገር ነው፡፡ስላልተለመደ እንግዳ ነገር ነው የሆነው፡፡ በተለይ በግለሰብ ጸጋ አልተለመደም፡፡ ይህንን ያልተለመደ ነገር እንዲህ ሲወጣ ሁሉም እየተረባረበ ማጨለም ነው የሚፈልገው፡፡ የእግዚአብሔር ስራ ደግሞ ስለማይጨልም ሂደቱን ጠብቆ ይበራል፡፡ ከዚህም በፊትም የተደረጉብኝ ዘመቻዎች ብዙ ናቸው ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ይህ እንዲያውም የመጨረሻው ደካማ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ሰዎች መንፈሳዊ አንድነታቸው በክፉ ሰዎች መንፈስ ተመቷል፡፡ በራስ እይታም ተመቷል፡፡ የምቀኝነት መንፈስ አጠናክረው በመያዛቸው ምክንያት የእግዚአብሔር ጸጋ በረከት መለያ መንፈስ አጥተዋል፡፡ አንድነትና ተስማምቶ መዝለቅን በዚህ ዘመን ውስጥ የምንጠብቀው ጉዳይ አይደለም፡፡ ግን እውነት ዞሮ ዞሮ ደረጃዋን ጠብቃ ስለምትወጣ ያን ያህል አስጊ አይደለም ማለቴ ነው፡፡
ላይፍ፡- እርስዎ አለኝ የሚሉት የፈውስ ጸጋ ከየት የመጣ ነው ይላሉ ?
መምህር ግርማ፡- ይህ እኮ አንድና ሁለት ነው እንደሚባለው አይነት ፎርሙላ ወጥ አድርገህ የምታሳየው ነገር አይደለም፡፡ ይህ በጸሎት በስግደት በቅዱስ ቁርባን በመመጽወት ከሰማይ የሚለቀቁት እንጂ ከማንኛውም ሰው የምትገዛው ወይም የምትለውጠው ትርፍ ያለው ነገር አይደለም፡፡ ይህ ከሰማይ የሚሰጥ እንጂ በስጋዊ ጥበብባ ዘዴ ወይም ምርምር ወደ ላብራቶሪ የሚመጣና የሚገኝ አይደለም፡፡ ምክንያቱም የእግዚአብሔር አሰራር ነው፡፡ የእግዚአብሔር አሰራር ደግሞ አለምም ሆነ ስጋውያን አያውቁትም፡፡ መንፈሳውያንም ተቸግረዋል፡፡
ለዛ ነው እምያሳድዱኝ በዚህ ዘመን ያሉ የገዛ አባቶቼ እንኳን ሳይቀሩ ይህንን መንፈሳዊ ጸጋ ለመቀበል በጣም ይቸገራሉ፡፡ ምክንያቱም ከእኛ በኩል ካፈሰሰ ነው እኮ አሁን ችግሩ፡፡ ከእኔ በኩል ካልፈሰሰ እንዴት በዚህ ዘመን ከእግዚአብሔር ይመጣል ፤ የሚል ዋጋ ቢስ እና ተስፋ አስቆራጭ የመንፈሳዊ ህይወት ጉዞን የለመዱት ባህሪ ለማንጸባረቅ ሲሞክሩ ነው አሁን ነገሮች ወደዚህ አይነት አጣብቂኝ ውስጥ የሚገቡት፡፡
ላይፍ፡- እርስዎ ተሰጥቶኛል የሚሉት የመንፈስ ጸጋ ስያሜ ሰጥተውታል ?
መምህር ግርማ፡- እንደዚህ ያለ ነገር የለም እንጂ ምን ስያሜ ይሰጠዋል ? ክፉ መናፍስን የሚቃወም የእግዚአብሔር መንፈስ ነው፡፡ የእግዚአብሔር መንፈስና ክፉ መንፈስ ደግሞ አይገናኙም፡፡ የእግዚአብሔር መንፈስ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ስጦታ ደግሞ ክፉውን መለየት ፤ ክፉው ማስወገድ ነው፡፡ በመጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ አጋንንትን አወጡ ይል የለም እንዴ? በአሁኑ ዘመን አጋንንት አስገቢ ቢባል ሁሉም ይወደኛል፡፡ አጋንንት ማስወጣት እኮ ነው የተለየ ጠንቋይ ያደረገኝ፡፡
ላይፍ፡-አለኝ የሚሉት የመንፈስ ጸጋ ወደ ሌላ ሰው ማስተላለፍ ይችላሉ ? ወይስ እርስዎ ጋር ነው ሊቀር የሚችለው ?
መምህር ግርማ፡- የኤልያስ መንፈስ በኤልሳ እንዳደረ ሁሉ የፈለገው ሁሉ ያገኛል፡፡ እኔም የማስተምረው እኮ ክርስቲያኑ ራሱን ችሎ እንዲቆም ነው፡፡ እኔ ነገ የማልፍ ሰው ነኝ ግን ክርስትያኑ ጠላቱን እንዲጋፈጥ ፤ ክፉ መንፈስ እንዲያሸንፍ ፤ የዲያቢሎስ ትውልድ መሆኑ እንዲቆም ፤ ከዚያም በላይ የመንፈስ ቅዱስ ስራ የእግዚአብሔር ክብርና ኃይል እየጨመረ እንዲመጣ ፤ የአለም ጥበብ ከእግዚአብሔር ልዩ አሰራር አውቀው ክርስቲያኖች በረከት ውስጥ እንዲገቡ ነው፡፡ ፍላጎቴ
ላይፍ፡- አባቶች እርስዎ የሚሰጡት መንፈሳዊ ጉባኤ ተገኝተው በረከት ይሰጡ ነበር ወይ ? መምህር ግርማ፡- እኔ በማገለግለው ላለመገኝት ብዙዎች ይሸሻሉ ተሰልፈው ዝቅ ብለው የህዝብን ችግር ለማየት እስከ አሁን በጎ ህሊና አላገኝሁም፡፡ እንደ አቡነ እስጢፋኖስ የጅማው ኃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አይነቱ በተደጋጋሚ የህዝቡን ችግር ተረድተው በተደጋጋሚ ወደዚያ እየሄድኩ ሳገለግል መንፈሳዊ ድጋፋቸውን ለህዝቡ ካለው ችግር ለልማቱም ከማሰብ ቢርሌ የሰጡት ቦታና ስራ አለ፡፡
ላይፍ፡- አባቶች እርስዎ የሚሰጡት መንፈሳዊ አገልግሎት አስተያየታቸው ምንድነው ? መምህር ግርማ፡- ብዙዎች ይህንን መንፈሳዊ ድርሻ ለመወጣት በማደርጋቸው ጥረቶች ላይ በጎ ድጋፍ የላቸውም፡፡ ከተለያዩ አይነት መንገድ ለመዳንም ይሰጣሉ፡፡ ነገር ግን አንዳዶች እንዲያውም የሸናሻም መተት ይህን ያደርጋል፡፡ የሸናሻም አስማት ይህንን ይሰራል እያሉ ለአስት አሰራር ትልቅ ድጋፍና የሰይጣን አሰራር ትልቅ ሞራል ሲሰጡ ነው የሚሰማው፡፡
ላይፍ፡- ይህንን እርስዎ የሚያደርጉትን መንፈሳዊ አገልግሎት ሌሎች አባቶች ያምኑበታል ?
መምህር ግርማ፡- እኔም በጣም ግራ የሚገባኝ ዲያቢሎስ የሚያደርገው ጥቃት በመጽሀፍ ቅዱስ በረጅሙ እና በስፋት ጥልቀት ባለው ሁኔታ ገልጿል፡፡ ሐዋርያት አጋንንትን እያወጡ የሰዎችን ደህንነት ሲያበለጽጉ ይታያል፡፡ በቤተክርስያንም እደዚሁ በመንፈሳዊ አገልግሎት በመንፈስ ቅዱስ ስራ እንደሚሰራ ይታወቃል፡፡ እንግዲህ ሰዎች በክፉ መንፈስ አሰራር ወይም አያምኑም አልያም በእግዚአብሔር አሰራር አያምኑም፡፡ ይናገሩታል ያስተምሩታል ግን ይህው እግዚአብሔር አዳነ ሲባል ግን አያምኑትም በዚህ መንታ መንገድ ላይ መታየት አሁን አይቻልም፡፡ ምክንያም የእግዚአብሔር ሕዝብ በዲያቢሎስ ተጠቅቷል፡፡ ወይ ዲያቢሎስ እንዲበላ ማድረግ ነው አልያም በቤተክርስቲያን መንፈስና ጸጋ ህዝቡ ችግር ውስጥ ገብቶ ችግሩን ማየት ነው፡፡ ገለልተኛ ሆኖ መኖር አሁን አሁን ጊዜው አይደለም፡፡ ስለዚህ ያምናሉ አያምኑም የሚለው ነገር እርሳው እኔን ቢረዱኝ ደስ ባለኝ፡፡ በተሰጣቸው ጸጋ ክፉ መንፈስ ነው ካሉ የእኔን መንፈስ ማወጣት መቻል፡፡ ሁሉም ቢተባበሩኝ መልእክት አስላልፋለሁ ፡፡ እንዲያውም በቤተክርስቲያን ይኖር የነበረ አስማተኛ መንፈሱን አስወጣንለት ብለው ለአለም ዜና ቢያቀርቡ ደስ ባለኝ ነበር፡፡
ላይፍ፡- ቤተክርስቲያኗ ወታደርና ነጋዴ የቤተክርስቲያን አገልጋይ አይሆንም የሚል ሕገ ደንብ አላት፡፡ እርስዎ ግን መንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ ከመግባትዎ በፊት ወታደር እንደነበሩናይውራል ስለዚህ ምን ይላሉ ?
መምህር ግርማ፡-ዛሬ ሰማዕቱ ሀገር ጠባቂ የምንለው ቅዱስ ጊዮርጊስም የመቶ አለቃ ወታደር ነበር፡፡ ግብጽ ውስጥ ያሉ ብዙ ታላላቅ አባቶችም እንደዚያው ናቸው፡፡ በአሁንም ዘመን ያሉ ብዙ መነኮሳቱ እስከ ጳጳሳቱ ወታደር የነበሩ ናቸው፡፡ ወታደር ማለት የእግዚአብሔርን ስራ አይሰራም ማለት አይደለም ፡፡ እኔ ደግሞ ልቀድስ ላቁርብ አላላኩም ፤ በተሰጠኝ ጸጋ ላገልግል ነው ያልኩት፡፡ ይህንን እንደ አንድ እንደ ትልቅ ነገር ማንሳት በራሱ ምንን ያመለክታል ፤ ምቀኝነትን ነው ፤ ያው ከደማችን ውስጥ የተለመደ ምቀኝነት ስላለ እንጂ ከነዚህ ሁኔታዎች በሙሉ የእግዚአብሔር ስራ እንዳይሰራ የሚያደርጉት አይደለ። ፡፡ ዘፋኝ ብሆን እኮ እሸለም ነበረ፡፡ ሬድዮ ጣብያዉም፤ ቴሌቪዥኑም፤ ካድሬዉም ትልልቁም ትንንሹም ያጨበጭብልኝ ነበር፡፡ ግን እግዚአብሔር በተረገመበት፤ እግዚአብሔር የያድንም የለም በተባለበት ሃገር ውስጥ እግዚአብሔር አለ የሚል ከሆነ፤ እግዚአብሔር አዳኝ ቅዱስ ነው የሚል ከሆነ አንተ እርኩስ ነህ የሚለው ነው የሚበዛውና እውነታው ይሄ ነው፡፡ ይሄን የሚመስል ሁኔታ ውስጥ ነው ያሳለፍነው፡፡ አልጋ በአልጋ የሆነ መንፈሳዊ ህይወት የለም፡፡ አልጋ በአልጋ የሚሆነው ለአርቲስቶች ብቻ ነው፡፡
ላይፍ፡- እርስዎን አስማተኛ እና ጠንቋይ ናቸው የሚሉዎት ሰዎች ምላሽ ምንድነው ?
መምህር ግርማ፡- እኔ አስማተኛ ከሆንኩ እኔ ጋር መጥተው አስማቱን ማውጣት ነው፡፡ እኔ ጋር መጥተው አስማቴ የት ጋር እንደተቀበረ ፈልገው ማውጣት ነው፡፡ ክንዴ ላይ ወይም እግሬ ላይ ወይም ጭንቅላቴ ላይ እንዳለ ደንበኛ ራጅ ይዘው መጥተው ፈልገው ማውጣት፡፡ ወይም መንፈስ ከሆነ ያስወጡልኝ፡፡ ቢረዱኝ እኮ ለእኔም ደስ ይለኛል፡፡ ግልግል ነበር፡፡ እስቲ አስማቴን ኑ እና አስወጡልኝ እባካችሁ ስለ እግዚአብሔር ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ብዬ እለምናችኋለሁ፡፡እንኳን እኔ ይልቅ እና እኔ ባስተማርኩት መስረት እንኳን ብዙዎች ሲፀልዩ ጎደኞቻችው እየራቅዋቸው እንደሆነ ይነግሩኛል 2ተኛው የመምህር ግርማ አስማተኛ የሚባል ቅፅል ስም ይሰጣቸዋል ለምን የመንፍስ አንድነት የላቸውም እርኩሱ ከ ቅዱሱ እንደማይስማማው ሁሉ መባረክ ስትጀምር ለእግዚአብሔር መንበርከክ ስትጀምር ለማይንበረከኩት በቃል ብቻ ለሚኖሩት እራስ ምታት ትሆንባቸዋለህ ይሄ ነው እውነታው!





ኢትዮጵያዊ 350 ሺህ ብር ከኦስትሪያ ለወደቁትን አንሱ የአረጋውያንና የአእምሮ መርጃ ማዕከል ድጋፍ አደረጉ! ድጋፍ ያደረጉት መንበረ አብርሃም የተሰኙ ኢትዮጵያዊ ከኦስትሪያ ሲሆን ከዚህ ቀደም መምህር ግርማ ወንድሙ ለበጎ አድራጎት ድርጅት ድጋፍ ያደረጉትን ፕሮግራም ከተመለከቱ በሆላ እንዲሁም በአባታችን አስተባባሪነት የአባታችን የወንጌል ተማሪ የሆነችው በተወካያቸው በአቶ ታሪኩ ተገኝ አማካይነት ተናግረዋል፡፡ በዚህም አማካይነት 350ሺህ ብር የሚያወጣ ዘመናዊ 65 አልጋዎችን ከነሙሉ ፍራሾች ለአረጋውያኑ ተወካይ በዛሬው ዕለት አስረክበዋል!






ዝቅ ብሎ መምሕር ግርማ ወደ አገልግሎት የተመለሱበት ደብዳቤ ይታያል:: በቅርብ ግን ይህ አገልግሎታቸው በ አባ ማቲያስ 30-06-2008 የተጻፈ የ እገዳ ደብዳቤ እንደሚከተለው ነው::




መምሕር ግርማ ወደ አገልግሎት የተመለሱበት ደብዳቤ

መምህር ግርማ ወንድሙ በደርሰባቸው ክስ ምክኒያት አገልግሎት ተቋርጦ እንደነበር የሚታወስ ነው:: መምህር ግርማ በወስ ጥቅምት 30/2008 ከተለቀቁ በኃላ የካቲት 9/2008 ከ ከደቡብ ም እራብ ሸዋ ሀገረ ስክበት የሥራ ምደባ ተደርጎላቸዋል:: በዚህም ምክኒያት የካቲት 19/20 በ ጀሞ ቅዱስ ኡራኤል ቤተክርስቲያን አገልግሎት ይሰጣሉ::

ጥቅምት 30 ፣ 2008 ከደቡብ ምእራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት የካቲት 9/2008 የተጻፈላቸው ደብዳቤ እንደሚያሳየው ወደ አገልግሎት ተመልሰዋል::

Wednesday, February 10, 2016

በንብና ነብር የምትጠበቀው ሥዕለ ማርያም “ወይኑት”

ኅዳር 10 ቀን 2006 ዓ.ም. 
በእንዳለ ደምስስ

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታላላቅ ገዳማት መካከከል በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ውስጥ የሚገኙት የመርጡለ ማርያም እና ደብረ ወርቅ ገዳማት በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ፡፡ ሁለቱም ገዳማት ጥንት መሥዋዕተ ኦሪት ይከናወንባቸው የነበረና ታላላቅ ታሪካዊ ቅርሶችንም ለትውልድ በማስተላለፍ ረገድ ትልቁን ድርሻ ከያዙት ቅዱሳት መካናት መካከል ይመደባሉ፡፡

መስከረም 29 ቀን 2006 ዓ.ም. በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ማርቆስ ጥሪ መሠረት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የሚመራና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የሚገኙበት የልዑካን ቡድን መርጡለ ማርያም ገዳም አዲስ ለሚሠራው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን የመሠረት ድንጋይ ለማኖር፤ እንዲሁም በደብረ ወርቅ ማርያም ገዳም የተገነባውን መንበረ ጵጵስና ለመመረቅና ለዘመናዊ ትምህርት ቤት ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ለማኖር ከሄደው ልዑክ ጋር ተጉዣለሁ፡፡
በመርጡለ ማርያም ገዳም የነበረን ቆይታ አጭር በመሆኑ መረጃዎችን ለማሰባበሰብ የጊዜ እጥረት ስላጋጠመኝ አልተሳካልኝም፡፡ በደብረ ወርቅ ገዳም ቆይታዬ ከቋጠርኳቸው መረጃዎች መካከል ቅዱስ ሉቃስ ከሣላቸውና ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙት ቅዱሳት ሥዕላት መካከል በንብና ነብር የምትጠበቀው ሥዕለ ማርያም /ምስለ ፍቁር ወልዳ/ “ወይኑት” ስለተሰኘችው ሥዕል ጥቂት ላካፍላችሁ፡፡ ደብረ ወርቅ ማርያም ገዳምን ላስቀድም፡፡

ደብረ ወርቅ ማርያም ገዳም
ደብረ ወርቅ ማርያም ገዳም በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት በእናርጅና እናውጋ ወረዳ ከአዲስ አበባ 290 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ የኦሪት መሥዋዕት ሲሰዋባቸው ከቆዩት ቅዱሳት መካናት አንዷ ናት፡፡ በተለይም ከ250-351 ዓ.ም. መሥዋዕተ ኦሪት ሲሰዋባት እንደቆየች የጽሑፍ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

የጎጃም አፈ ጉባኤ በነበረው ምሑረ ኦሪት ያዕቆብ አማካይነት መሥዋዕተ ኦሪት ሲሰዋባት የቆየ መሆኑን በገዳሟ የሚገኙ የኦሪት ሥርዓት ማከናወኛ የነበሩ እንደ መቅረዝ፤ ስንና ብርት የመሳሰሉ ቅርሶች ከመመስከራቸውም በላይ በገዳሟ ውስጥ የሚገኘው የቤተ ክርስቲያኗ የታሪክ መዝገብ ያስረዳል፡፡

weyenuteእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጇ ከወዳጇ ጋር ወደ ምድረ ግብፅ ስትሰደድ ካረፈችባቸው ቅዱሳት መካናት መካከል አንዷ ደብረ ወርቅ መሆኗንም በድርሳነ ኡራኤል ላይ ተጽፎ ይገኛል፡፡ በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያ የነገሡት ወንድማማቾቹ አብርሃና አጽብሃ ክርስትናን እያስፋፉ ከቦታ ቦታ ይዘዋወሩ በነበረበት ወቅት መርጡለ ማርያምን አቅንተው ክርስትናን መሥርተው ወደ ደብረ ወርቅ በመምጣት ከምሁረ ኦሪት ያዕቆብ ጋር ተገናኝተዋል፡፡ ያዕቆብን ክርስትናን አስተምረው የአዲስ ኪዳን ሥርዓትን በመመሥረት “ያዕቆብ ኤጲስ ቆጶስ ዘኢየሩሳሌም ደብረ ወርቅ” ብለው ሾመውታል፡፡

አብርሃና አጽብሃ ደብረ ወርቅ ላይ ቤተ ክርስቲያን ሳይሠሩ ዐረፍተ ሞት ስለገታቸው በእግራቸው የተተካው ዐፄ አስፍሐ ያልዝ በ351 ዓ.ም. ወደ ደብረ ወርቅ በመምጣት ቤተ ክርስቲያኗን አሰርቷል፡፡ የደብረ ወርቅ ማርያም ገዳም በዮዲት ጉዲት በመቃጠሏ በ1372 ዓ.ም. በዐፄ ዳዊት የገንዘብ ድጋፍ አባ ሰርፀ ጴጥሮስ በተባሉ አባት አማካይነት በድጋሚ ተሠርታለች፡፡ ከጊዜ በኋላም ቤተ መቅደሷን ዐፄ ገላውዴዎስ በኖራና ድንጋይ ሲያሠሯት፤ ቅኔ ማኅሌቷ ደግሞ በስክ እንጨት ካለምንም ምሥማር በዐፄ ተክለ ጊዮርጊስ ተሠርታለች፤ በ1963 ዓ.ም. ዐፄ ኃይለ ሥላሴም አሳድሰዋታል፡፡

ቤተ ክርስቲያኗ 44 ቆመብዕሴ/አምድ/፤ የውጪና የውስጥ 11 በሮች፤ 36 መስኮቶች ሲኖሯት የግድግዳ ላይ ሥዕሎቹ ዐፄ ዮስጦስ /1704 ዓ.ም./፤ 1873 ዓ.ም. የንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ልጅ የሆኑት ራስ ኃይሉ አስለውታል፡፡ በቤተ ክርስቲያኗ ዘመናዊ ሙዚየም ውስጥ በርካታ ታሪካዊና ጥንታዊ ቅርሶችም ይገኛሉ፡፡

“ወይኑት” ቅዱስ ሉቃስ የሣላት ሥዕለ ማርያም
ዐፄ ዳዊት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተሰቀለበት መስቀል ጋር ወደ ኢትዮጵያ ካመጧቸው የቅዱስ ሉቃስ ሥዕላት መካከል “ወይኑት” የተሠነችው ሥዕል አንዷ ስትሆን ዐፄ ዘርዓweyenute 2 ያዕቆብ ለደብረ ወርቅ ማርያም ገዳም አበርክተዋል፡፡ እስከ ዛሬ ድረስም ተጠብቃ ትገኛለች፡፡ በ1660ዎቹ ዓ.ም. በዐፄ አእላፍ ሰገድ /ፃድቁ ዮሐንስ/ ለወይኑት ማስቀመጫ እቃ ቤት ይሆን ዘንድ ባለ ሁለት ፎቅ ሕንፃ በድንጋይና በኖራ በማስገንባት ጣሪያውን የሣር ክዳን በማልበስ አሠርተውላታል፡፡ ፎቁ ላይ ትናንሽ 8 መስኮቶችም ይገኛሉ፡፡

ሥዕለ ሉቃስ “ወይኑት”ን የሚጠብቁ ነጫጭ ንቦች የሚገኙ ሲሆን ጥቋቁር ንቦቹ ደግሞ ከመስኮቶቹ እየወጡና እየገቡ መመልከት የተለመደ ነው፡፡ ንቦቹ ከሕንፃው መሠራት ጋር እንደገቡ የሚነገር ሲሆን ማሩ እስካሁንም ተቆርጦ አያውቅም፡፡ ወይኑት በዓመት ለሦስት ጊዜያት ሕዝቡን ለመባረክ ወደ ቤተ መቅደስ ትወሰዳለች፡፡ መስከረም 21፤ ጥር 21 እና ነሐሴ 16፡፡ ሥዕሏ ወደ ቤተ መቅደስ ሥትወሰድ ንቦቹ አጅበዋት የሚሄዱ ሲሆን ስትመለስም አብረዋት ይመለሳሉ፡፡ ንቦቹ ሕዝቡን የማይተናኮሉ እንደመሆናቸው በተንኮል ወይም ለሥርቆት የመጣ ሰው ካለ ግን እየነደፉ እንደሚያባርሩ ከዚህ በፊት ከተደረጉት ገቢረ ተዓምራት በመነሳት ይገለጻል፡፡

ወይኑትን የሚጠብቁ ከንቦቹ በተጨማሪ ነብሮችም በሕንፃው ጣሪያ ላይ ይገኛሉ፡፡ ቀን እዚያው ተኝተው የሚውሉ ሲሆን ምሽት ላይ ምግብ ፍለጋ እንደሚወጡ ይነገራል፡፡ በአካባቢው የሚገኙ በጎች ወደ ቤተ ክርስቲያኗ ቅጥር ከገቡ ከነብሮቹ ጋር እንደሚጫወቱና እንደማይተናኮሏቸው የዓይን እማኞች ያስረዳሉ፡፡

የዐፄ ዮሐንስ 4ኛ ወታደር ሥዕለ ሉቃስ /ወይኑትን/ ለመሥረቅ ሞክሮ ንቦቹ ነድፈው እንዳባረሩት፤ እንዲሁም ዐፄ ዮሐንስ ከደርቡሽ ጋር ባደረጉት ጦርነት ሥዕለ ማርያምን /ወይኑት/ ይዘው ለመዝመት ባደረጉት ጥረት ንቦቹ ወታደሮቻቸውን- በመንደፍ አስጥለዋታል፡፡ የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዳልሆነ የተረዱት ዐፄ ዮሐንስ ሥዕሏን ወደነበረችበት መልሰው እንደዘመቱ የቤተ ክርስቲያኗ የታሪክ መዝገብ ያስረዳል፡፡ የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት የደብረ ወርቅ ማርያም ገዳምን ለመዝረፍ ዕቃ ቤቱን ሰብረው ለመግባት ያደረጉት ጥረት እንዳይሳካ በማድረግ ጠባቂ ንቦቹ ወታደሮቹን በመንደፍ እንዳባረሯቸው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ 

ይቆየን

Friday, February 5, 2016

Monday, January 4, 2016

ፃድቃኔ ማርያም - ድንቅ ተአምር

ዛሬ ፃድቃኔ ማርያም ሄጄ በአይኔ ያየሁትን ተአምር ልፅፍላችሁ ወደድኩኝ፡፡ ቀኑ ቅዳሜ ነው ፤ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ወደ ፃድቃኔ ለመሄድ የሚነሱበት ቀን ስለሆነ መጀመሪያ የሚወጣው አውቶቡስ እንዳያመልጠን ከባለቤቴ ጋር በጠዋት ነበር አውቶቡስ ተራ የደረስነው ፤ ነገር ግን ሰው እዛ ያደረ ይመስል 12፡00 ላይ አውቶቡሱ ሞልቶ መንቀሳቀስ ጀምሮ ነበር፡፡ ባለቤቴም ‹‹አይ በዚህም ሰዓት ደርሰን አመለጠን ይገርማል ተወው ባክህ እመቤቴ እንደፈቀደች›› አለችኝና ሁለተኛው አውቶቡስ ላይ ገባን፡፡ ይህኛው ደግሞ ቀጥታ ዘላቂ ሰው ስላጣ የመንገድ ሰዎችንም በመጫን ነበር የሞላው፡፡ ጉዞ ወደ ፃድቃኔ ማርያም ፤ ውዳሴዋን ደግመን ጉዞ ጀመርን፡፡ መኪናው ሲያወርድ ፤ ሲጭን 9፡00 አካባቢ ደብረ ምጥማቅ ደረስን ፤ እዚህ እንውረድና በአቋራጭ እንሂድ ተባብለን ሰላ ድንጋይ ሳንደርስ ወረድን ፡፡ እቃችንን ለአንድ የሀገሬው ሰው አሸክመን አቋራጩን ተያያዝነው ፡፡ ልጁ እንዲህ አለን ‹‹ ዛሬ ግን ማደሪያ የምታገኙ አይመስለኝም በጣም ብዙ ሰው ነው የመጣው አለን›› :: ‹‹ችግር የለውም ውጪ አንጥፈን እናርፋለን ለመተኛት መች መጣን›› አልነው፡፡

ደጇን ስንረግጥ ልጁ ያለው አልቀረ የወንዶች ማረፊያ ሁለቱም አዳራሽ ከአፍ እስከ ገደቡ ሞልቷል ፤ በረንዳውን ላይ ብናይ የበረንዳው ይብሳል ፡፡ የኔን ማረፊያ ውጭ አነንጠፍንና የእሷን ለማየት ወደ ሴቶች ማረፊያ እያቀናን ሳለ ፤ አንዲት መንፈስ ያደረባት ሴት ፤ እጇም እግሯም በሰንሰለት ታስራ እንዲ እያለች የእመቤታችንን ማዳን ትመሰክራለች ‹‹ ዛሬ ደግሞ ኪዳነምህረት ድንቅ ነገር ሰርታለች ሂዱነና እዩ›› እያለች ለሰዎች ስትናገር እንደ አጋጣሚ እኔም ሰማሁ፡፡ እሷ የጠቆመችን ቦታ ላይ ስንሄድ አንዲት የ12 ዓመት ህፃን ልጅ እና እህትየዋ አንድ ላይ ቆመው ተመለከትን ፡፡ ጠጋ ብለን ምን ተደርጎላቸው ነው ስል ስጠይቅ ‹‹ የዚች ህፃን አይኗ በራላት›› ሲሉ ነገሩን፡፡ ለኔ የተደረገልኝን ያህል ደነገጥኩኝ፤ በጣምም ደስ አኘኝ፡፡ እህትየዋ የምትይዘውን የምትጨብጠውን ነገር አጥታ ነበር ፡፡ ታናሽ እህቷ የተደረገላትን ነገር እያየች ከአእምሮዋ በላይ ስለሆነ እና ደስታው ፈንቅሏት ታለቅሳለች ፤ እኛም ገርሞን ማደሪያችንን ትተን ልጅቷ ጋር ረዥም ደቂቃዎች ስለሁኔታ ለመስማት እዛው አረፍ አልን ፡፡ እህትየዋም ሰዎች ጥያቄዎችን ሲጠይቋት እንዲህ አለች ፡-

‹‹ ቤት ውስጥ ከእኩያዎቿ ጋር ስትጫወት የበረንዳ ብረት አይኗን መታት ፤ ለጊዜው ከማበጥ ውጪ ምንም አልሆነም ነበር ፤ ነገር ግን በጊዜ ሂደት አይኗ እያበጠ መጣ ፤ እይታዋንም ጋረዳት ፤ ትምህርቷንም አቋርጣ ለ6ወር ያህል ህክምና ፍለጋ አሉ የተባሉ የአይን ስፔሻሊስቶች ጋር ብራችንን አውጥተን ሄድን ፤ መፍትሄ ግን ሊመጣ የልጅቷም አይን ማየት ግን አልቻለም ፤ ቤተሰባችን ጭንቅ ውስጥ ገባ ፤ በመጨረሻ እመቤቴ እንዳደረገች ታድርጋት ብይ እዚህ ይዣት መጣሁ ዛሬ ሶስተኛ ቀናችን ነው ፤ ለሶስት ቀን ያህል ፤ ጠዋት ተሸክሜአት ጸበል እወስዳታለሁ ፤ እምነቱን ከፀበል ጋር ደባልቄ አይኗ ዙሪያው ላይ እቀባታለሁ ፤ ይህው እናንተ እንደምታዩት እግዚአብሄር ፈቅዶ ዛሬ አይኗ ሊያይ ችሏል›› ብላ ለቅሶ፡፡

‹‹ሁሉን የምትገዛ ጌታ አምላክ ሆይ፥ ሥራህ ታላቅና ድንቅ ነው›› ዮሀንስ ራዕይ 15 3-4 ፤ ‹‹ይህች ከእግዚአብሔር ዘንድ ሆነች፥ ለዓይናችንም ድንቅ ናት።›› መዝሙረ ዳዊት118፥23 ከማለት ውጪ ሌላ ምን ይባላል፡፡አምኖ የመጣ እንዲህ ይደረግለታል ፤ ብዙዎቻችን ግን እግዚአብሔር ቤት ስንሄድ በሁለት ልብ ሆነን ነው ፤ ስንመለስም ከሁለት ያጣ የምንሆነው ለዚህ ይመስለኛል፡፡
ያየነውን ነገር ማመን እስኪያቅተን ድረስ እየተገረምን ማረፊያ ፍለጋ ስንንቀሳቀስ ሰዎች ተሰብስበው አየን ፡፡ ሁሌ ማታ 11፡00 ላይ በወንዶች ማረፊያ አካባቢ እና በሴቶች ማረፊያ አካባቢ አዲስ ለመጡ ሰዎች የቦታውን ስርዓት ፤ ምን እንደሚደረግ ፤ ምንስ እንደማይደረግ አባቶች ለ30 ደቂቃ ያህል ያስረዳሉ፡፡ ጠጋ ስንል ተረኛው አባት እንዲህ ሲሉ ነገሩን፡-

‹‹ ይህውላችሁ ልጆች ሀገር አቋርጣችሁ ከተለያየ ቦታ እዚ የመጣችሁት እናንተ ፈልጋችሁ ብቻ አይደለም ፤ እግዚአብሔርም ፈቅዶላችሁ ጭምር ነው፡፡ ስለዚህ እሱ ፈቅዶ እና ወዶ እስካመጣችሁ ድረስ የመጣችሁበትን አላማ የሚያስተጓጉል አንዳች ነገር ማድረግ የለባችሁም ፤ ይህ ቦታ የምህላ ፤ የፀሎት ፤ የሱባኤ ቦታ ነው ፤ እዚህ ቦታ ላይ ከእናንተ የሚጠበቅባችሁ ነገር አለ እርሱም ፡- ወደ ገዳም ስትወርዱ ጫማችሁን አድርጋችሁ መግባት አይቻልም ፤ ሴቶችም ወንዶችም በገዳም ውስጥ ስትመላለሱ ክርስትያናዊ አለባበስ መልበስ አለባችሁ ፤ በማደሪያችሁም ሆነ ገዳም ስትወርዱ ጮክ ብሎ መነጋገር አይቻልም ፤ ብዙ ሰዎች አርምሞ ስለሚይዙ እነሱንም መረበሽ ስለሆነ ይህ አጥብቆ የተከለከለ ነው ፤ የቻለ በቀን ሰባት ጊዜ ፀሎት ማድረስ አለበት፤ ካልቻለህ ግን ሶስቱን ጸሎት ማስተጓጎል የለበትም ፤ ከሰኞ እስከ አርብ ድረስ በሽተኛ ካልሆነ በቀር ምግብ 12 ሰዓት ላይ ነው መብላት የሚቻለው እስከዚያ ሁሌ ጾም ነው(ከበዓለ 50 በቀረ) ፤ የተፈቀዱት ምግቦች ቆሎ ፤ባቄላ ፤ ጥጥሬዎች እና በሶ ከሰኞ እስከ አርብ ሲሆን ቅዳሜ እና እሁድ ዳቦ መብላት ይፈቀዳል ፤ እንጀራ እና ወጥ ገዳም ውስጥ ባላችሁበት ጊዜ መብላት አይቻልም ፤ ጸበል ጠዋ በ11 ይከፈታል ከዚያ በፊት ጸበል መውረድ አይቻልም እስከ ሰባትም ስንትም ሰዓት ይቆያል ፤ እዚህ ቦታ ላይ በዓመት 1ጊዜ ብቻ ነው ቅዳሴ ያለው ፤ ጠዋት ሊነጋ ሲል 11 ሰዓት ላይ ኪዳን ማድረስ ፤ ሲነጋ ትምህርተ ወንጌል መሳተፍ ፤ከ ሰዓት ከ9፡40 ጀምሮ ምህላ ማድረስ አለባችሁ የዛኔ ነው የመጣችሁበትን አላማ እና እናንተ የምትገናኙት ›› እያሉ ብዙ ነገር ነገሩን መከሩን፡፡

እኛ እንኳን ለ3 ቀን ነው የመጣነው ገዳም ውስጥ የሚኖሩ መነኮሳት ይህን ሁሉ ችለው ነው የሚኖሩት? ይገርማል ፤ እግዚአብሔርም አለምን ትተው እሱን ብለው የመጡትን ያስችላቸዋል:: በመጨረሻም ፀሎት አድርገውልን ወደ ማደሪያችን ሸኙን፡፡ ይህን ስመለከት ብዙ ቦታዎች ስንሄድ የቦታውን ስርዓት ሳናውቅ የምናጠፋ ሰዎች እንበዛለን ፤ ልክ እንደ ፃድቃኔ ማርያም ገዳም ቀን በቀን ሳይሰለቹ እንደዚህ አይነት ነገሮች ሁሉም ቦታ ቢለመድ ጥሩ የሚል ሀሳብ አለኝ፡፡

የሚቀጥለው ቀን ጠዋት
ለሊት ኪዳን አድርሰን ወረፋው እንዳይበዛ ፀበል ወረድን ፤ ፀበል ተጠምቀን ስናበቃ ለመጠጣት አንዱ ልጅ ጋር ጠጋ ብዬ ቁጭ አልኩ ፤ ጎንበስ ብዬ ሳየው አንዳች ነገር ጉልበቱ ላይ ትልቅ እጢ ቋጥሮ ተመለከትኩኝ ፤‹‹ወንድሜ ምን ሆነህ ነው›› አልኩት፡፡ እሱም ‹‹ ተወኝ ባክህ ልቤ ደንድኖ አልሰማ ብዬ ነው እንዲ የሆንኩት አለኝ››፡፡ አልገባኝም አልኩት ‹‹ሰው ንስሀ ገብቶ ወደ በፊቱ ምግባሩ ከተመለሰ የባሰውን ነው የሚሸከመው አለኝ›› ይባስ ግራ አጋባኝ፡፡ ቀስ ብለህ ልታስረዳኝ ትችላለህ አልኩት፡፡ እርሱም፡-
‹‹ ትውልዴ አዲስ አበባ ነው የ22 አካባቢ ልጅ ነኝ ፡፡ይህውልህ የዛሬ 2 ዓመት በፊት እጠጣለሁ ፤አጨሳለሁ ፤ እጨፍራለሁ ብቻ ምንም ከሀጢያት የቀረኝ ነገር የለም ሁሉን አደርጋለሁ ፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ ሳለሁ የዚያን ጊዜ ጉልበቴ ላይ ከዚህ በፊት ሆኖ በማያውቅ በልክ ትልቅ እጢ ወጣብኝ ፤ ብዙ ቦታ ብሄድ ኦፕራሲዮን መሆንን ነበር እንደ መፍትሄ ያስቀመጡልኝ ፤ እሱን ደግሞ እኔ አልፈልገውም ፡፡ እናቴ እስኪ ፃድቃኔ ሂድ አለችኝ ፤ ‹‹ምን ማለትሽ ነው ዶክተሮች ኦፕራሲዮን እያሉ እዛ ምን ልሰራ ነው የምሄደው›› ብዬ ከእሷ ጋር ተጣላን ፤ ውዬ አድሬ ሳስበው መሄድ እንዳለብኝ ውስጤ ነገረኝ ፡፡ ከአዲስ አበባ ተነስቼ በሶ እና ቆሎ ብቻ በመያዘ ቀጥታ እዚህ ቦታ መጣሁ ፤ አንድን አባት አግኝቼ ችግሬን ስነግራቸው በደንብ አደመጡኝና ‹‹በል አሁን ጸበል እንዳትጀምር ፤ ንስሀ ግባ፤ ቀኖናህን ስትጨርስ መጠመቅ ትችላለህ›› አሉኝ፡፡ እሺ ብዬ ንስሀዬን ከራሴ ላይ አወረድኩኝ ፤ ቀኖናዬን ጨረስኩ ፤ከዚያ ጸበል መጠመቅ ስጀምር ሰዎች እምነት ሲቀቡ ተመለከትኩኝ ፤ ለምን እኔስ አልቀባም ብዬ ጸበሉን ከእምነት ጋር እየደባለኩ ቁስሉን መቀባት በጀመርኩኝ በሶስተኛው ቀን ተሸክሜ የመጣሁትን እጢ በመግል መልክ ከሰውነቴ ወጥቶ አለቀ ፤ ተሸሎኝ ወደቤቴ ስመለስ እማዬ ስታየኝ ማመን አልቻለችም ነበር ፤ አለቀሰች ፤ እመቤቴን ወላዲተ አምላክን ማመስገኛ ቃላት አጣች ፤ እኔም ለአንድ ዓመት ያህል ከቤተክርስትያን አልራኩም ነበር ፡፡ የሆነ ጊዜ ላይ ግን ከቤቱ ጠፋሁ ፤ ወደ ቀደመ ምግባሬ ቀስ እያልኩ ገባሁበት ፤ የተደረገልኝን ነገር ዘነጋሁ ፤ ይህው አሁን ደግሜ የዛሬ ሁለት ዓመት ይዥው የመጣሁትን እጢ አሁን ተመልሶ መጣብኝ ›› ብሎ ሲነግረኝ ሰውነቴን አንዳች ነገር አራደኝ፡፡

ስንቶቻችን ነን ገብተን የወጣን ፤ ውለታውን የዘነጋን ፤ የተደረገልንን ነገር የረሳን ፤ ከሞት አፋፍ ከጠላት ወጥመድ ጠብቆ አሳልፎን ዛሬ ላይ ከቤቱ ሸርተት ያልን? ቤት ይቁጠረው ፡፡ እኔ አይኔ የልጁ እጢ ላይ ነው ፤ ልጁ ደግሞ አይኑ እኔ ላይ ነው ፡፡ ‹‹ አሁን አኮ ቀንሶ ነው ያየህው›› አለኝ ፡፡ ‹‹ሳይቀንስ ባየው የቱን ያህል ነበር?›› ብዬ ራሴን ጠየኩኝ፡፡እንዲህ ሲል ቀጠለልኝ ‹‹ ትላንት ምልክት አይቻለሁ በጥቂት ቀናት ውስጥ አፍስሳ ትጨርስልኛለች ፤ በአውራ ጣቴ በኩል በቢጫ ፈሳሽ መልክ ትንሽ ትንሽ ሲወጣ ተመልክቻለሁ ፤ ከአሁን በኋላ ግን ወደ በፊቱ ማንነቴ እንዳልመለስ እግዚአብሔር ይጠብቀኝ ፤ እርግጠኛ ነኝ አሁን እድናለሁ አለኝ፡፡›› የልጁ እምነት ገረመኝ፡፡ ስንቶቻችን ነን አፋችንን ሞልተን በእምነት ‹‹እድናለሁ›› ማለት የምንችል ፤ እንዲህ ለማለትም ፍጹም እምነት ያስፈልጋል፡፡ የመጣሁበትን ጉዳዬ እረስቼ ቁጭ ብለን ስለራሱ ፤ አዛው ቦታ ላይ ስላየው ተዓምር ሲነግረኝ ሰዓቱ መዝለቁን አላስተዋልኩም ነበር፡፡ መጨረሻ ላይ ‹‹በል እመብርሀን ወላዲተ አምላክ ትርዳህ ፤እግዚአብሔር በምህረቱ ይጎብኝህ›› ብዬው ወደ ማረፊያየ ለመሄድ ብድግ አልኩ ፡፡መሬት መሬት አቀርቅሬ ፤ የነገረኝን ታሪክ ከራሴ ጋር እያቆራኝውት እንደ ውሻ የተፋሁትን ነገር ደግሜ የላስኩበትን ሁኔታዎች ሳወጣ ሳወርድ ምንም ሳላውቀው ማረፊያዬ ጋር ደረስኩኝ፡፡

የ ኪዳነ ምሕረት ተአምር

የወላዲተ አምላክ ድንቅ ተአምር