Wednesday, April 23, 2014

የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ድንቅ ተአምር በግብጽ ቤ/ክ

     በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን:: በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት የተደረገ ተአምር ይህ ነው::

ለዓይኖቻችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ክፍል የእይታ ድራብ ረቲና የሚባለው ነው:: እይታ ድራብ የሌለው ሰው አንዳችም ነገር ማየት አይችልም:: በመሆኑም ዓይነ ስውር ሆኖ ተወለደ ማለት ነው:: እንዲህ አይነቱ አብሮ የሚወለድ በሽታ ሊድን አይችልም:: ማሪና ከተወለደች ከጥቂት ቀናት በኋላ ወላጆቿ ወደ እርሷ ሲቀርቡ ትደናገጥና ማልቀስ ትጀምራለች:: አንድ ቦታ ላይ አትኩራ አለመመልከቷንና ዓይኖችዋ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴን አለመከተላቸውን ወላጆቿ ይገነዘባሉ:: በአጠቃላይ ዓይኖቿ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ የላቸውም::

     አራት ወር ሲሞላት ወደ ሕክምና ተቋም ትወሰዳለች:: የምርመራውም ውጤትም በዓይኖቿ ውስጥ የ እይታ ድራብ ስለሌለ ዓይነ ስውር ሆኖ መቀጠል እንዳለባት ያረጋግጣል:: የማሪና ወላጆች ከሌሎች ብዛት ያላቸው የሕክምና ባለሙያዎች ጋር ለንደን ድረስ ሔደው በመገናኘት ቢያስመረምሯትም እይታ ደራብ ስለሌላት ልትድን አለመቻሏን ደግመው ያረጋግጡላቸዋል::

   ከአማላጂቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም ጋር ቅርርብ ያላቸው የማሪና ወንድ አያት በዚህ ጉዳይ ክፉኛ ያዝናሉ:: ከዚያም ዘይቱን ውስጥ ወደሚገኘው ወደ እመቤታችን ቤተ ክርስቲያን በቀጥታ በመሄድ በስዕሏ ፊት ተንበርክከው በእናቱ አማላጅነት ተደግፈው እግዚያብሔር የልጅ ልጃቸውን ዓይኖች ያበራ ዘንድ በጸሎት ይማጸኑታል:: በጸሎታቸው "የብርሃን እናት ሆይ: ልጅሽ ማሪና ይህን ብርሃን ሳትመለከት እንድትኖር አታደርጊያትም" ይሉ ነበር:: በዚህ ጊዜ አንዲት እማሆይ ትከሻቸውን ነካ ካደረገቻቸው በኋላ በርኅራሄ ቃል "ልቅሶህ ይብቃ! ማሪናን ያዝና ወደ ሴቶች ገዳም ሂድ" ትላቸውና ከዓይናቸው ትሰወራለች::

    ከዚህ በኋላ የማሪና አያት ድንቅ የሆነ የሰላም ስሜት ሲያድርባቸው ይታወቃቸዋል:: አስቀድመው ይህ ገዳም መኖሩን ፈጽሞ ሰምተው ስለማያውቁ ወደዚያ ያቀኑት አቅጣጫውን እየጠየቁ ነበር;; ከቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ በመውጣትም ላይ ሳሉም ወደ
አንዱ የቤተክርስቲያን አጋልጋይ ጠጋ ብለው እማሆይዋ ወዴት አቅጣጫ እንደሄደች ይጠይቁታል:: እርሱም ምንም ዓይነት እማሆይ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ አለመግባቱንም ሆኖ አለመውጣቱን ያረጋግጥላቸዋል::

   የማሪና አያት የተገለጠላቸው የብርሃን እናት የሆነችው ድንግል ማርያም መሆኗን በማሰላሰል ይገረሙ ይደነቁም ጀመር:: ከዚህ በኋላ በቀጥታ ወደ ሴት ልጃቸው ቤት ሲሄዱ ወደዚሁ ገዳም መሄዷ በመልክት ይነገራቸዋል:: የማሪና ቤተሰቦች ወደ ገዳሙ እንደ ደረሱ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ምልጃና ጸሎት እግዚያብሔር አምላክ የልጃቸውን አይኖች እንዲያበራ አጥብቀው ይማጸኑታል:: ከዚህ በኋላ ልጃቸው ቅባዕ ቅዱስ ትቀባለች:: አብዛኞቹ መነኮሳይት እግዚያብሔር በልጃቸው ላይ እንደሚከብርና ልጃቸውም ማየት እንደምትጀምር ይነግሯቸው ነበር::

    በሚቀጥለው ቀን ጠዋት የክፍሉን መጋረጃዎች ሲገልጡ ልጃቸው ወደ ክፍሉ ለገባው ብርሃን ምላሽ ስትሰጥ ተመለከቷት:: ማሪና ከዚህ ቀደም አድርጋ የማታውቀውን ነገር አጠገቧ ሆኖ ወደሚያጫውታት ሰው ፊቷን ስትመልስ ታየቻቸው::ከዚህ በኋላ ማሪናን ወደ ዓይን ሕክምና ባለሙያ በመውሰድ በዚህ ሙያ የላቀ እውቀት ወዳለው የሕክምና ባለሙያ ቀርበው ስላለፈ የሕክምና ታሪኳ አንድም ነገር ሳይናገሩ እንዲመረምራት ያቀርቡለታል;; ታዋቂው የሕክምና ባለሙያ ምርመራውን ካጠናቀቀ በኋላ "ይህችን ልጅ ወደ እኔ ያመጣችኋት ለምንድር ነው? ልጅቱ እኮ ምንም የሆነችው ነገር የለም" ይላቸዋል::በዚህ ግዜ የማሪና አባት የቀደመውን የምርመራ ውጤት ሲያቀርቡለት ምላሹ እንዲህ የሚል ነበር:: "ለፕሮፌሰሮቹ ሊሰጣቸው የሚገባ ክብር ምንም ሳይጓደል አሁንም ቢሆን ልጅቱ የሆነቸው አንዳች ነገር የለም::"

    በዚህ ግዜ የመጀመርያውን ምርመራ ወዳካሄደላት ታዋቂ ፕሮፌሰር ይዘዋት ይሔዳሉ:: እርሱም በከፍተኛ አድናቆት ተውጦ "አሁን ምን እንደተፈጠረ ማወቅ አልችልም! ሌላ የእይታ ድራብ የተፈጠረላት ነው የምትመስለው:: አዲስ እይታ ድራብ ስለተፈጠረ በርግጥ ተአምር ነው:: ለዚህ ራሱን የቻለ መግለጫ ያስፈልገዋል" አለ::
የማሪና ወላጆች ልባቸው በደስታ እየፈነደቀ ከሕክምናው ተቋም ወጡ:: እግዚያብሔር ስለ በረከቱ ስለ ቸርነቱና የብርሃን እናት በሆነችው በእናቱ በቅድስት ድንግል ማርያም በኩል ላከናወነው የአማላጅነቷ ተአምር አመስግኑት::

ምንጭ
ቅድስት ድንግል ማርያም (ሕይወቷ: ተአምራቷ :መገለጧ)
ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ እና ሌሎች ጳጳሳት እንደጻፉት
አያሌው ዘኢየሱስ እንደተረጎመው
2001, አ.አ

ዛሬ በአታ ለማርያም ሄጄ ይህን ሰምቼ መጣሁ

Holy water at Entoto Kidane Mihret Church የ እንጦጦ ኪዳነምህረት ጸበል

 

No comments:

Post a Comment