Monday, May 11, 2015

አቡነ መልከጼዴቅ-አፈር የማያስበሉት ኢትዮጵያዊ ጻዲቅ

አቡነ መልከጼዴቅ-አፈር የማያስበሉት ኢትዮጵያዊ ጻዲቅ
የጽሑፉ ምንጭ፡- (ገድለ አቡነ መልከጼዴቅ ዘሚዳ-ሊቀ ጠበብት ዘላለም መንግሥቱ ከግእዝ ወደ አማርኛ የተረጎሙትና የገዳሙ እድሳት ኮሚቴ ያሳተመው-2004 ዓ.ም)

በመጀመሪያ በመልከጼዴቅ ስም የሚጠሩ ሁለት ኢትዮጵያውያን ቅዱሳን ናቸው ያሉት- አቡነ መልከጼዴቅ ዘሚዳ እና አቡነ መልከጼዴቅ ዘዋሸራ፡፡ በስም ስለሚመሳሰሉ እንዳይምታታብን ለይተን ማወቅ አለብን፡፡
አቡነ መልከጼዴቅ ዘዋሸራ፡- ከአባታቸው ከዘካርያስና ከእናታቸው ስነ ክርስቶስ የተወለዱት አቡነ መልከጼዴቅ ዘዋሸራ ትውልድ ሀገራቸው ጎጃም ዋሸራ ሲሆን በታላቅ ተጋድሎና በሹመት ያገለገሉትም በዚሁ ነው፡፡ ዲቁናንና ቅስናን ከግብፅ ተቀብለው በዋሽራ 30 ዓመት በሹመት አገልግለዋል፡፡ ጻዲቁ የሚታወቁበት ትልቁ ተጋድሎአቸው በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ ሁልጊዜ ዓርብ ዓርብ ያከፍሉ ነበር፡፡ የመድኃኔዓለምን 13ቱን ሕመማተ መስቀሎች በማሰብ አናታቸውን በድንጋይ እያቆሰሉ ቁስሉ ሲተላ ትሉን ለወፎች ይመግቡ ነበር፡፡ በ40 ቀን ውስጥ አንዷን ቀን ብቻ ነው ውኃ ይጠጡ የነበረው፡፡ ጻዲቁን የቅኔ ተማሪዎች በዋሸራ ይዘክሯቸዋል፡፡

አቡነ መልከጼዴቅ ዘሚዳ፡-
በ13ኘው መ/ክ/ዘ መጨረሻ በንጉሥ ዐፄ በእደ ማርያም ዘመነ መንግሥት የነበሩ እደጃቸው የተቀበረውን ሰው አፈር የማያስበሉ እጅግ ድንቅ ቃል ኪዳን ያላቸው ታላቅ አባት ናቸው፡፡ የአምላካቸውን የክርስቶስን መከራ ለማሰብ ገዳመ ቆሮንቶስን የመሰለ ዋሻ ቆፍረውና በዚያ ገብተው ቀንና ሌሊት ዘግተው በረደኝ ፀሐይ ልሙቅ፣ ጨለመኝ ብርሃን ልይ ሳይሉ በጸሎት ብቻ ዘግተው በመኖር ራሳቸውን በችንካር እያቆሰሉ እግዚአብሔር ወልድ የተገረፈውን ግርፋት እያሰቡ በየቀኑ እስከ 3ሺህ ድረስ ይሰግዱ ሰውነታቸውንም እንዲሁ ይገርፉ እንደነበር መጽሐፈ ገድላቸው ይናገራል፡፡ የክርስቶስን መቸንከር እያሰቡ እጅና እግራቸውን፣ ወገብና ደረታቸውን በብረት ቸንክረው መከራውን ያስቡ ነበር፡፡ ጎኑ በጦር መወጋቱን አስበው አጥንታቸው እስኪሰበር ድረስ ጎናቸውን ወጉ፡፡ ሐሞትና ከርቤ መጠጣቱን አስበው እርሳቸውም መራራ ይጠጡና አንክርዳድን ይመገቡ ነበር፡፡ ሞቱን አስበው ደም እንባን ያነቡ ነበር፡፡ በእንደዚህ ዓይነቱ ተጋድሎ የክርስቶስን መከራ እያሰቡ ነቢያን፣ ሐዋርያትን፣ ሰማዕታትን፣ ደናግል መነኮሳትን መስለው ሁሉን እያከናወኑ እያለ የወዳጆቹን መከራ የማይዘነጋ፣ የሰውን የድካሙን ዋጋ ፈጽሞ የማያስቀር አምላክ ሠራዊተ መላእክትን አስከትሎ መጥቶ ‹‹መገረፍህ፣ ስለ እኔ መገረፍ ይሁንልህ፣ የደምህ መፍሰስ ስለ እኔ ደም መፍሰስ ይሁንልህ፣ መቸንከርህም ስለ እኔ መቸንከር ይሁንልህ፣ ሞትህም ስለ እኔ ሞት ይሁንልህ›› ብሎ የሚከተለውን ቃልኪዳን ሰጥቷቸዋል፡፡
‹‹ከዚህ ቦታ መጥቶ የተሳለመውን እምርልሃለሁ፤ ነፍሱ በአንተ ቃልኪዳን የማይማር በአንተ ቦታ ለመሳለምም፣ ንስሓ ለመግባትም ሆነ ለመቀበር አላቀርብብህም፤ መጥቶም የተቀበረውን ሥጋውን አፈር አይበላውም›› የሚል እጅግ ድንቅ ቃል ኪዳን ነው መድኃኔዓለም የሰጣቸው፡፡ ቃል ኪዳኑንም የሰጣቸው ቅዱሳን መልእክትን፣ ነቢያትን፣ ሐዋርያትን፣ ጻድቃንን፣ ሰማዕታትን፣ ቀሳውስትን፣ ዲያቆናትን፣ ደናግል መነኮሳትን ሁሉ ምስክር አቁሞ እንደሆነ ቅዱስ ገድላቸው ይናገራል፡፡ ይህም ድንቅ ቃልኪዳን ዛሬም በገሀድ እየታየ ነው፡፡ እስከ ዕለተ ምጽዓትም ሲታይ ይኖራል፡፡ በደጃቸው የተቀበረ ሰው አይበሰብስም፡፡ ይህም የሥጋው አለመበስበስ ለሞተው ሰው ለሥጋው ጠቃሚ ሆኖ ሳይሆን የጻዲቁ ቃልኪዳናቸው እስከ ዕለተ ምፅዓት ድረስ ተፈጻሚ መሆኑንና ምልክትን ለሚሻ ለዚህ ዘመን ትውልድ ምልክት ይሆን ዘንድ ነው፡፡ አፈር የማያስበሉትን ጸዲቅ የአቡነ መልከጼዴቅን ቃልኪዳን በማንኛውም ጊዜ ሄዶ ማየት ይቻላል፡፡ ከአ.አ 225 ኪ.ሜ ርቀት ለመራኛ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው የሚዳ አቡነ መልከጼዴቅ ገዳም ተፈጥሮአዊ አቀማመጡ እጅግ አስገራሚ በሆነው ዋሻ ቤተክርስቲያን ውስጥ ሁሉም ነገር በግልጽ ይታያል፡፡ ይህም እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ሁሉ በተለይም እኛ ኢትዮጵያውን በኃጢአት ሳንጠፋበት የመዳኛ መንገድ አድርጎ የሰጠን ድንቅ የቃል ኪዳን አባታችን መሆናቸውን ተረድቶና አውቆ በቃል ኪዳናቸው መጠቀም መቻል በራሱ ዕድለኛነት ነው፡፡ አቡነ መልከጼዴቅ ዘሚዳ ጌታ ዕድሜአቸው ረጅም መሆኑን በምሳሌ እያሳየ ሲነግራቸው ‹‹በዚህ ዓለም መኖር ጥቅሙ ምንድር ነው? ወደ እረፍትህ ውሰደኝ እንጂ›› ብለው ሞታቸውን የለመኑ ቅዱስና ጻዲቅ አባት ናቸው፡፡ የዛፏ ታሪክ በገዳሙ ያለው ሌላው አስደናቂው ነገር ነው፡፡ አንድ ገበሬ ከሄደበት ሲመለስ ከገዳሙ ክልል ውስጥ ገብቶ ለሞፈር የሚሆነውን እንጨት ቆርጦ ወደቤቱ ይዞ ይሄዳል፡፡ እቤቱም ሲደርስ የተሸከመውን የሞፈር እንጨት ሊያስቀምጥ ቢሞክር እንጨቷ ከትከሻው ላይ አልወርድ አለች፡፡ ቢባል ቢባል እንጨቷን ማውረድ አልተቻለም፡፡ ገበሬውም ‹‹ከየት ነው ያመጣኸው?›› ተብሎ ሲጠየቅ ከጻዲቁ ደጅ ቆርጦ እንዳመጣት ተናገረ፡፡ ‹‹በል መልሰህ እዛው ውሰድ›› ተብሎ የቆረጠበት ቦታ ቢያመጣት ዛፏ ራሷ በተአምር ከትከሻው ላይ ወርዳ መጀመሪያ ከተቆረጠችበት ቦታ ላይ በጎን በኩል ተተክላለች፡፡ ዛሬም ምልክቱ በግልጽ ይታያል፡፡ አሁን ደግሞ በቀጥታ ከመጽሐፈ ገድላቸው ውስጥ አንዳንድ ነጥቦች ሙሉ ሀሳቡን በመውሰድ እንመልከት፡-








1. ትልቅ የቅድስና ደረጃ ላይ ቢደረስም እንኳ ራስን ለካህን ማሳየት እንደሚገባ፡- ‹‹አባታችን መልከጼዴቅ ወደ ዋልድባ ገዳም ሔደ፡፡ ወደ እምፍራንዝ ደብር ሔዶ ቤተክርስቲያንን እጅ ነሳ፣ ተሳለመ፣ በውስጧም ጸለየ፡፡ ጸሎቱንም በፈጸመ ጊዜ መድኃኔዓለም ‹አትፍራ፣ በምትሄድበት መንገድ ሁሉ እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁና› አለው፡፡ ሰላምታንም ሰጥቶት ከእርሱ ተሰወረ፡፡ ከቤክርስቲያንም ወጥቶ ከቅዱሳን ሁሉ ጋር እጅ ተነሳሳ፤ ‹አባ አባ ገረምኸን ከየት መጣህ?› አሉት፡፡ ‹እኔ ኃጢአተኛና በደለኛ ስሆን ከምዕራብ አገር ቅዱሳንን ለመጎብኘት መጣሁ› አላቸው፡፡ ይህንንም እየተናገረ እያለ እግዚአብሔርን የምትፈራ አንዲት መነኩሲት ሴት ወደ እርሱ መጣችና እጅ ነሳችው፡፡ እግሩንም ሳመችው፡፡ ዐይነ ስውር ነበረችና ‹የእግዚአብሔር ሰው ወደ እኛ መምጣትህ መልካም ነው፤ ሰላም ለአንተ ይሁን› አለችው፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ አስቀድሞ ነገረኝ ‹የእግዚአብሔር ካህን መልከጼዴቅ ይመጣል፣ እርሱም ይናዘዝሻል አለኝ› አለች፡፡ ይህንን ስትናገር አባታችን መልከጼዴቅ ይህችን ዐይነ ስውርና ጻዲቅ ሴት ከራስ ጠጉሯ እስከ እግር ጣቶቿ በወርቅ ልብስ ተሸልማ በመስቀል ምልክት የተሠራ የብርሃን አክሊል በራስዋ ላይ ደፍታ ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል በቀኟና በግራዋ እየጠበቋት አያት፡፡ አባታችን መልከጼዴቅም ይህን ባየ ጊዜ አደነቀ፡፡ ‹እኔን እንደጻድቅ ሰው አታስመስይኝ፣ ለሴቶች ንስሓ መስጠት ቢቻላቸውስ ኖሮ እኔን በናዘዝሽኝ ነበር› አላት፡፡ ባስጨነቀችውም ጊዜ ንስሓ ሰጣት፡፡ ጻዲቋ ሴት በእርሱ ዘንድ የተናዘዘች ኃጢአት ስለሠራች አይምሰላችሁ ‹በቃልህ የተናዘዘውን ምሬልሃለሁ› ብሎ ለአባታችን ለመልከጼዴቅ እግዚአብሔር በሰጠው በምህረቱ ቃልኪዳን ትጨመርና በረከቱን ትቀበል ዘንድ ነው እንጂ፡፡ ወንድሞቸ ሆይ በደላችሁን ለካህን ማሳየትን አታስታጉሉ፡፡ ጻዲቅ ሰውም እንኳ ቢሆን ራሱን ለካህን ማሳየትን አያስታጉል፡፡ መጽሐፍ ‹እሳት ወርቅን ከሚያጠራው በስተቀር ምን ያደርገዋል?› ይላልና፡፡ ይህችም ጻዲቅ ሴት የዳነች የጠራች ስትሆን እንደ ኃጢአተኛ ተናዘዘችለት፣ በኋላም በማዘን በቅዱስ መልከጼዴቅ ላይ የሚመጣውን ሁሉ ትንቢት ነገረችው››
እንዲሁም በብሔረ ሕያዋን ያለ አንድ የእግዚአብሔር ሰው ወደ ቅዱስ አባታችን ዘንድ መጥቶ ኑዛዜን እንደተቀበለ አቡነ መልከጼዴቅ ለተማሪዎቻቸው ነግረዋቸዋል፡፡ ታሪኩ እንዲህ ይነበባል፡- ‹‹አባታችን መልከጼዴቅ አደሴዋ በምትባል ደብር ሳለ እንዲህ አለ፡- እንደ ነጭ የአውራ በግ ፀጉር ሁለንተናውን የከደነውና ረጅም የሆነ የአካሉ ፀጉር እንደ ግምጃ የነጣ የራሱም ጫፍ ከደመና የሚደርስና ቁመቱ ረጅም የሆነ አንድ ሰው ወደ እኔ መጣ፡፡ ባየሁትም ጊዜ ደነገጥኩና አጋንንትን በማሳድድበት በሥላሴ ስም በመስቀል ምልክት ፊቴን አማተብሁ፤ ከአጠገቤም ጥቂት ፈቀቅ አላለም፡፡ እኔም አንተ ማነህ? ከወዴትስ መጣህ?› አልሁት፡፡ እርሱም ‹እኔ ኃጢአተኛ ሰው ከቀደሙ አባቶች ዘመድ የሆንሁና ከኖኅ ልጆች ወገን ነኝ፣ ስሜም የእግዚአብሔር ሰው ነው፣ በነቢዩ በዳዊት ዘመንም እግዚአብሔር ከሞት በፊት ሰወረኝ፣ በሕያዋን አገርም ከሔኖክ፣ ከኤልያስ፣ ከዕዝራና ከጌታ ወዳጅ ከዮሐንስ ጋር እኖራለሁ፣ ከእርሱም ጋር ሐሰተኛው መሢህ እጅ እሞታለሁ፣ ትናዝዘኝ ዘንድ ወደ አንተ እስከመጣሁበትና እግዚአብሔር ኑር እስካለኝ ጊዜ ድረስ እኖራለሁ› አለኝ፡፡ ለእግዚአብሔርም ያለውን አምልኮትና የሃይማኖቱን ደግነት በሰማሁና እንደ ዕንቈ የሚያበራ የሥጋውን ንጽሕና ባየሁ ጊዜ ምንም እኔ ከጉልበቱ የማልደርስ ብሆንም ዝቅ ብዬ ከእግሮቹ ስር እጅ ነሳሁ፡፡ እርሱም ከእኔ ፈቀቅ ብሎ ራሱን ወደ እኔ አዘነበለ፡፡ በመስቀል ምልክት አማተብሁና ባረክሁት፣ ኑዛዜም ሰጠሁት፡፡ እርሱም እጅ ነሳኝና ከእኔ ተሰወረ፡፡ በዳሞትም፣ በአደሴዋም እንዲሁ ዘወትር ሲጎበኘኝ ነበረ አላቸው፡፡ አባታችን መልከጼዴቅ ለተማሪዎቹ ይህን ነገራቸው፡፡ ጸሎቱና በረከቱ የዚህም የእግዚአብሔር ሰው በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን ዛሬም ዘወትርም ለዘለዓለሙ አሜን፡፡››
2. ኢትዮጵያውያን ሁሉ የቅድስት ድንግል ማርያም የአስራት ልጆች እንደሆንን ጌታችን የተናገረው፡- ‹‹የእግዚአብሔርም ቃል በመልከጼዴቅ ላይ መጣና ‹ወንድምህ አቤል በንጉሡ አዳራሽ ሞተ› አለው፡፡ ያንጊዜም ወደ ገዳም መጥቶ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፡፡ ‹አቤል ወንድሜን ነፍሱን ያኖርህበትን አሳየኝ› አለ፡፡ ጌታችንም መጣና ‹ባስቀመጥሁት በሲኦል ውስጥ ንስሓውን ይፈጽም ዘንድ ተወኝ› አለው፡፡ ጌታችንም ይህን ብሎ ከእርሱ ተሰወረ፡፡ ንስሓስ ከሞት በኋላ ኖሮ አይደለም መልከጼዴቅ እንዲፈጽምለት ነገረው እንጂ፡፡ ከዚህ በኋላ አባታችን መልከጼዴቅ ወደ እግዚአብሔር ይለምንለት ጀመር፡፡ ደሙም በምድር ላይ እንደ ውሃ እስከሚፈስ ድረስ ቁጥር በሌለው ብዙ ግርፋት ተገረፈ፡፡ ደም የተቀላቀለው ዕንባ እያነባ መራራ ልቅሶን አለቀሰ፣ ዐይኑም ታመመ፡፡ ራሱንም በሰንሰለት ቸንክሮ ሰውነቱን በእጅጉ አደከመ፡፡ ከዚህም በኋላ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እርሱ መጣና ‹ስለ ድካምህ ምሬልሃልሁ፡፡ ግርፋትህ በጲላጦስ እጅ እንደተገረፍሁት ግርፋቴ ይሁን፣ ችንካርህም በዕፀ መስቀል ላይ አይሁድ እንደቸነከሩኝ ችንካሬ ይሁን፣ መታሰርህም የደምህም መፍሰስ ስለ ፈሰሰው ደሜ ይሁንልህ፣ ነፍስህን መስጠትህም ስለ ነፍሴ መውጣት ይሁን፡፡ ዛሬም ና የወንድምህን የአቤል ነፍስ ያለችበትን ላሳይህ› አለው፡፡ ያን ጊዜም የመንፈስ ቅዱስ ክንፍ ተሰጠው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እየመራው ሔደና ከሲኦል በር አደረሰው፡፡ ‹እኔ ወደ ሲኦል ወርጄ የጻድቃንን ነፍሳት እንዳወጣሁ አንተም ወደ ሲኦል ውረድና ወንድምህ አቤልን አውጣው› አለው፡፡ አባታችን መልከጼዴቅም ‹እኔ መሬታዊ ሰው ስሆን ወደ ሲኦል መውረድ እንዴት እችላለሁ? አንተስ የኃይል ባለቤት ሁሉ የሚቻልህ ስለሆንህ ከውስጧ ወርደህ የብረት በሮቿን ቀጥቅጠህ ሰባበርህ› አለው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ‹በእኔ የሚያምን እኔ የምሠራውን ይሠራልና እምቢ አትበለኝ ሒድ ውረድ› አለው፡፡
አባታችን መልከጼዴቅም ያንጊዜ መርከብ ወደ ጥልቅ ወንዝ እንደሚወርድ ወደ ሲኦል ወረደ፤ ሲኦልም ደነገጠችና ‹የተሰጡኝን ነፍሳት ይቀማኝ ዘንድ ፈጣሪዬ ዳግመኛ ወረደን?› አለች፡፡ አባታችንም ወንድሙን አቤልን ያዘውና ከውስጧ አወጣው፡፡ ከእርሱ ጋርም ብዙዎች የኃጥአን ነፍሳትን አወጣ፡፡ በእርሱ ላይም የነካው የእሳት ሽታ ምንም አልነበረም፡፡ ወንድሙ አቤልን ከእሳት እንዳወጡት የእንጨት ግንድ ከሰል መስሎ አየው፡፡ ከእርሱ ጋር የወጡት ነፍሳትም እንደ እርሱ ጠቁረው ነበር፡፡ አባታችን መልከጼዴቅም ጌታችንን ‹ወንድሜን እንዲህ ጠቁሮ አየሁት ታዲያ ምኑን ማርህልኝ? እነዚህም ነፍሳት እንዲሁ› አለው፡፡ ጌታችንም መላእክቱን አዘዛቸውና መርተው ወስደው የገነትን ውኃ አሳዩት፡፡ ወንድሙ አቤልንም በዚህ ውስጥ አጠመቀው፡፡ ከእርሱ ጋር የወጡትንም ነፍሳት ሁሉ አጠመቃቸው፡፡ ያንጊዜም ፊቱ ከጸሐይ ሰባት እጅ አበራ፡፡ አምላክን የወለደች እመቤታችን ማርያምም መጣችና አባታችን መልከጼዴቅን ‹ወንድምህ አቤልን ስጠኝ ወደ ርስቴ ልውሰደው፣ እርሱ ዕድል ፈንታዬ የእኔ ድርሻ ነውና› አለችው፡፡ አባታችን መልከጼዴቅም ‹የእኔ ድርሻ ነው፣ ልጅሽም የደምህ ዋጋ ይሁንህ ብሎኛል› አላት፡፡ እሷም ‹ና ወደ ልጄ እንሒድ› አለችውና ሁለቱም ሔደው ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ደረሱ፡፡ እመቤታችንም ‹ይህ ኢትዮጵያዊ ሰው የሰጠኸኝ የእኔ ድርሻ ነው› አለችው፡፡ አባታችን መልከጼዴቅም ‹ለእኔም የደምህ ዋጋ ይሁንህ ብለኸኛል› አለ፡፡ ጌታችንም ‹አንተም ኢትዮጵያዊ፣ እርሱም ኢትዮጵያዊ፣ የኢትዮጵያዊን ሰዎች ሁሉ የእርሷ ድርሻ ይሆኑ ዘንድ ሰጥቻለሁ› አለው፡፡ ወይቤ እግዚእነ አንተኒ ኢትዮጵያዊ ወውእቱኒ ኢትዮጵያዊ እስመ ወሃብክዋ ኰሎሙ ሰብአ ኢትዮጵያ ከመ ይኩኑ መክፈልታ እንዲል መጽሐፍ፡፡ ያንጊዜም በፊቱ ሰግዳ አቤልን ወሰደችውና የብርሃን ልብስ አልብሳ ወደ ገነት ደስታ አገባችው፡፡ ከእርሱ ጋር የወጡትን ነፍሳትም ከጸሐይ ሰባት እጅ አብርተው አባታችን መልከጼዴቅ ወሰዳቸውና ወደ ዘለዓለም ርስቱ አገባቸው፡፡ ለአባታችን መልከጼዴቅ ታላቅ ምህረትን ላደረገለት ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን! ርስቱንም ይክፈለን! እኛንም ዕድል ፈንታው ያድርገን! ለዘለዓለሙ አሜን!››
3. መድኃኔዓለም ክርስቶስ ለአቡነ መልከጼዴቅ የተገለጠበት ልዩ ሁኔታ፡-
ጌታችን በምድር ላይ ተገልጦ ከአቡነ መልከጼዴቅ ጋር እየተነጋገረ ሳለ በክብር ዙፋኖ ሆኖ አንድነቱን ሦስትነቱን እንዳሳያቸው፡-
‹‹የእግዚአብሔር መልአክ አባታችን መልከጼዴቅን ‹በግራርያ አገር ወደምትገኝ የቅዱስ ተክለሃይማኖት ደብር ወደሆነች ወደ ደብረ ሊባኖስ ሒድ› አለው፡፡ አባታችን መልከጼዴቅም በመልአኩ ትእዛዝ ሔዶ ደብረ ሊባኖስ ደረሰና በዚያ ያሉ ቅዱሳንን እጅ ነሳቸው፡፡ ከንቡረ ዕድ እንድርያስም ጋር ተቀመጠ፡፡ ትንሽ ዋሻ በዓትን ሰጠውና ‹ትእዛዛቱን በመጠበቅ እግዚአብሔር ያጽናህ፣ የገደልህንም ፍጻሜ ይስጥህ› አለው፡፡ መልከጼዴቅም ወደዋሻው ገብቶ ምስጋና፣ ጸሎትና ስግደትን ተግቶ ያዘ፡፡ እንደመጀመሪያውም ታስሮ እያለ በየለቱ እስከ ሦስት ሺህ ስግደት ይሰግድ ነበር፡፡ ደሙም በምድር ላይ እስከሚፈስ ድረስ መንታ በሆነ የገመድ ጅራፍ ሰውነቱን ይገርፍ ነበር፡፡ እንባውም እንደክረምት ነጠብጠብ ይፈስ ነበር፣ የዓይኑ ብሌን እስኪገለበጥ ድረስ ያነባ ነበር… እንዲህ ሆኖ መከራ ሲቀበልም እግዚአብሔር ዝም አይልም፣ ሥራውንም ፈጽሞ ያደንቅ ነበር፡፡ ‹ጌታ ሆይ! የተኛሁትን አንቃኝ፣ የደከምሁትን አበርታኝ፣ የጨለምሁትን እኔን አብራኝ› ይል ነበር፡፡ ይህንንም የሚለው ለራሱ ብቻ አይደለም ስለ ዓለሙ ሁሉ ነበር እንጂ፡፡ እርሱስ በኢየሩሳሌም ከሐዋርያት ጋርና በአርያም ካሉ ከሱራፌል ጋር በክህነት የሚያገለግል ፍጹም ንጹሕና ጻዲቅ ሰው ነው፡፡ ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አባታችን ወደ መልከጼዴቅ መጣና ‹ወዳጄ ሆይ! ሰላም ለአንተ ይሁን› አለው፡፡ መልከጼዴቅም ‹አንተ ማን ነህ?› አለው፡፡ ጌታችንም ‹እኔ የድንግል ማርያም ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነኝ› አለው፡፡ ያንጊዜም ከእግሩ በታች ወደቀ፡፡ ጌታም እጁን ይዞ አነሣውና ‹ጽና አትፍራ› አለው፡፡ ያንጊዜም እናቱ ድንግል ማርያም ከቅዱስ ሚካኤልና ከቅዱስ ገብርኤል ጋር፣ ከሱራፌልና ከኪሩቤል ጋር፣ ከነቢያትና ከሐዋርያት ጋር፣ ከጻድቃንና ከሰማዕታት ጋር መጣች፡፡ መድኃኔዓለምም አባታችን መልከጼዴቅን ‹ከእናትህ ማኅፀን ጀምሮ በምስክር ሁሉ ፊት መረጥሁህ፣ ካህንም አደረግሁህ፣ ዛሬም የብዙዎች አባት አድርግሃለሁ፡፡ ኃጢአተኞችንም የምትመልስ ትሆናለህ፡፡ ብሩህ አክሊልና በሰው እጅ ያልተሠሩ የብርሃን ልብሶችን እሰጥሃለሁ፡፡ ርስትህ ከአጥማቂዬ ከዮሐንስ ጋር ይሁን፤ ሹመትህም ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይና ከአስራ ሁለቱ ሐዋርያት ጋር ይሁን› አለው፡፡ ‹ስምህም የእኔ ምሳሌ በሆነው መልከጼዴቅ ይሁን› አለው፡፡ የመጀመሪያው በጥምቀት የተሰጠው ስሙ ኅሩየ ወልድ (በወልድ የተመረጠ) የሚል ነበርና፡፡ ያንጊዜም ቁመታቸው እስከሰማይ የሚደርስ፣ ብርሃናቸው እንደ ፀሐይ የሚያበራ ሦስት የወርቅ መስቀሎችን ሰጠው፡፡ ጌታችንም ‹በላያቸው ላይ ውጣ አለኝ፣ እኔም በእያንዳንዳቸው ላይ ሦስት ጊዜ ወጣሁ፣ እስከ አርያምም አገቡኝ፡፡ በዚያም የእግዚአብሔርን መንበር አየሁ፡፡ በአንድነት በሦስትነት የሚኖር የዘመናት ጌታም በላይ ተቀምጧል፡፡› ይህም ነገር እጅግ ድንቅ ነው ወልድ በምድር ላይ ከእርሱ ጋር እየተነጋገረ ሳለ በአርያም ደግሞ በሦስትነቱ ተቀምጦ አየው፡፡ ጌታም ‹ሥርዓትህ እንዲሁ እንዳየኸው ይሁን፣ እስከ ዕለተ ዕረፍትህም ድረስ ስለ ገድልህ ጽናት የሚሆን ሰጥቼሃለሁ› አለው፡፡ በጸሎቱ የተማጸነውን እንደሚምርለትና ሌላም ብዙ ቃልኪዳን ሰጠው፡፡ ‹እኔም ከአንተ አልለይም፣ መላእክቶቼም ይጠብቁሃል› አለው፡፡ መልከጼዴቅም ይህንን በሰማ ጊዜ በፊቱ ሰገደ፡፡ ‹አቤቱ ለእኔ ለኃጢአተኛው አገልጋይህ ይህን ሁሉ ክብር የሰጠኸኝ ጌታ ሆይ መንግሥትህ ይባረክ› አለው፡፡ ጌታችንም ባርኮት በታላቅ ክብር ወደ ሰማያት ዐረገ፡፡››

ጌታችን ሠራዒ ካህን ሆኖ ከአቡነ መልከጼዴቅ ጋር እንደቀደሰ፡- ‹‹አባታችን መልከጼዴቅ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ገብቶ በመሠዊያው ፊት ቆመ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጠለትና ‹እኔ ሠራዒ ካህን እሆናለሁ፣ አንተም ንፍቅ ሁነኝ› አለው፡፡ አባታችን መልከጼዴቅም ‹ሸክላ (ጭቃ) ሠሪውን አትሥራኝ ማለት ይችላልን? የአንተ ፈቃድ ይሁን› አለው፡፡ እነሆ የወርቅ ማዕድና የወርቅ ጽዋ፣ የወርቅም ዕርፈ መስቀል ከሰማይ ወረደና በመሠዊያው ላይ ተቀመጠ፡፡ ጌታችንም በሰው እጅ ያልተሠራ የቅድስና ልብስ ለበሰ፡፡ ያንጊዜም የሰማይ ኅብስትና የወይን ጽዋ ወረደ፡፡ ኅብስቱን በማዕድ ላይ፣ ወይኑንም በጽዋው ውስጥ ጨመረና የራሱን ቅዳሴ ቅዳሴ እግዚእን ይቀድስ ጀመር፡፡ ‹ቅዱስ› ከሚለው ቃል በደረሰ ጊዜም መላእክት በአንድ ቃል ‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ የአማልክት አምላክ እግዚአብሔር ፈጽሞ በሰማይና በምድር ያለ፣ ወደፊትም የሚኖር፣ ሕያው› እያሉ ጮሁ፡፡ አባታችን መልከጼዴቅም በቅዱሳን ጸሎት እንደ ሱራፌል በወርቅ ማዕጠንት ዕጣን እያጠነ እንደ እነርሱ ‹ቅዱስ› አለ፡፡ የማዕጠንቱም ፍህም ከሰማይ የወረደ እሳት ነው፡፡ የጻድቃን ጸሎትም በሚጤስ ጊዜ ቤቱን ይሞላል፡፡ ይህም ከሟች ሰው ልቡና የተሠወረ እፁብ ድንቅ ነገር ነው፡፡ ጌታም ይህን ኅብስት ለመቁረስ በያዘው ጊዜ ሕፃን ሆነ፣ ከዚያም ተመልሶ በግ ሆነ፣ ከዚያም ተመልሶ ኅብስት ሆነ፡፡ ይህ ኅብስትም ፍህም ሆነ፡፡ አባታችን መልከጼዴቅም ይህን ባየ ጊዜ ፈጽሞ ደነገጠ፣ ተንቀጠቀጠ፣ ይሸሽም ዘንድ ወደደ፡፡ መድኃኔዓለምም ‹ጽና አይዞህ አትፍራ፣ ከእኔ በኋላ አንተ በክህነት በምታገለግልበት ጊዜ በእጅህ እንደዚህ እንደሚደረግልህ አሳይሃለሁና› አለው፡፡ ይህም ነገር ፈጽሞ የሚያስደንቅ ነው፡፡ እርሱ መሥዋዕት አቅራቢ፣ እርሱም ሕፃን ይሆናል፡፡ እርሱም አራጅ፣ እርሱም በግ ይሆናል፡፡ እርሱ ፈታች (ቆራሽ)፣ እርሱም የእሳት ፍህም የተከመረበት ኅብስት ይሆናል፡፡ ከሰው ወገን በሁለት ወይም በሦስት መንገድ መገለጥ የሚችል ማነው? እርሱ ግን ሁሉን ቻይ ነውና ከመንበሩ ሳይነዋወጥ፣ ከሦስትነቱም ሳይለይ በምድር ላይ በብዙ መንገድ ይገለጣል፡፡

መዓዛ ባለው እንጨት ለኄኖክ የታየበት ጊዜ አለ፤ በቀስተ ደመና ለኖኅ የታየበት ጊዜ አለ፤ ከሁለት ሰዎች ጋር በሰው አምሳል ወደ አብርሃም ሔዷል፤ ለይስሃቅ በበግ አምሳል ታይቷል፣ ለመልከጼዴቅ በኅብስትና በወይን አምሳል ታይቷል፤ ለያዕቆብ በመሰላል ላይ በእሳት ነበልባል ተገልጧል፤ ለኤልያስ በቀጭን ፉጨት ተገልጧል፤ ለኢሳይያስ በመንግሥቱ ዙፋን በተቀመጠ ሰው ተገልጧል፤ ለዳንኤል በሽበታም ሰውና በድንጋይ አምሳል ተገልጧል፤ ለሕዝቅኤል ሕብር ያለው በፍታ በለበሰ አምሳል ተገልጧል፤ ለኤርምያስ በለውዝ በትር አምሳያ ታይቷል፤ ለዕዝራ በአንበሳ አምሳል ታይቷል፤ ለአሞፅ በሽበታም ሰው አምሳል ታይቷል፤ ለእመቤታችን ድንግል ማርያም በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል አምሳል እንደጠልም በማኅፀኗ አድሮ ከእርሷ ተወለደና በዚህም ሰው ሆነ፡፡ በአርያም መላእክት በፈለጉት ጊዜም ከአባቱና ከመንፈስ ቅዱስ፣ ከቅዱሳንም ጋር እንደጥንቱ አገኙት፡፡ ለእንድርያስ በመርከብ መሪ (ዋናተኛ) አምሳል በባሕር ላይ፣ ለኤዎስጣቴዎስ በበረቱ ክንዶችና በሕጻን አምሳል በመስቀል ላይ፣ ለእስክንድርያ ሊቀ ጳጳስ ለተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ ልብሱ በተቀደደ በሕጻን አምሳል ተገልጧል፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ክብርና ልዕልናዎቹን ስንቱን እናገራለሁ? እስከዛሬ ድረስ በሁሉም አምሳል ይመሰላልና፡፡ ወደቀደመው ነገር እንመለስ፡፡ ጌታችን ይህንን ኅብስት ሲፈትተው መንፈስ ቅዱስ እንደ እሳት እየነደደ በእርሱ ላይ ወረደ፡፡ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ለማክበር ለመለወጥ መውረዱ እንደማይቋረጥ ተረዳ፣ ታወቀ፡፡ ኅብስቱንም ፈትቶ በጨረሰ ጊዜ ‹ይህ የሕይወት እንጀራ ከሰማይ የወረደ ሥጋዬ ነው› ብሎ ለአባታችን መልከጼዴቅ ሰጠው፡፡ ዳግመኛም በሕይወተ ሥጋና ነፍስ ላሉ ሰጣቸው፡፡ ጌታችንም ‹እንደ ነቢዩ ኢሳይያስ ከንፈርህን አስነካሁህ፤ ከኃጢአትህም አነጻሁህ፡፡ ዛሬ እንዳየኸኝ ነገም አንተ እንዲህ በክህነት አገልግል› አለው፡፡

አባታችን መልከጼዴቅም በአገልግሎት ጊዜ በፈጣሪያችን እጅ የተሠራ ልብሰ ተክህኖ ለበሰ፡፡ እንደ ትናንቱም ማዕድና ጽዋ፣ የወርቅም ዕርፈ መስቀል፣ የሰማይም ኅብስትና ወይን ወረደ፡፡ በማዕዱ ላይ ኅብስቱን አኖረ፤ በጽዋውም ላይ ወይኑን ጨመረ፡፡ የጌታችንንም ቅዳሴ ቀደሰ፡፡ ‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ የአማልክት አምላክ እግዚአብሔር ዘወትር በሰማይና በምድር የሚኖር ነው› ባለጊዜ በዚያ የነበሩና በሰማይም ያሉ መላእክት ‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር› ሲሉ ምድር እስክትነዋወጥ ድረስ የምስጋናቸውን ቃል ሰማ፡፡ የእውነት መንፈስ ቅዱስ ጰራቅሊጦስን ላከው› ባለጊዜም ሰማይ ተከፍተ፣ የኢየሩሳሌምም የቤቷ ጠፈር ተቀደደ፣ መንፈስ ቅዱስም በዚህ ኅብስት ላይ ወረደ፡፡ እርሱም ሕጻን ሆነ፣ መድኃኔዓለምም ‹ይህን ሕጻን ሰዋው፣ ለዓለምም ሁሉ መድኃኒት ይሆን ዘንድ› አለው፡፡ ይህን ሕጻን ሊይዘው በወደደ ጊዜም በግ ሆነ፡፡ እግዚአብሔርም ‹ይህን በግ እረደው› አለው፡፡ ይህንንም በግ ሊይዘው በወደደ ጊዜ ከእሳት ጋር የተዋሐደ ኅብስት ሆነ፡፡ ይህም እጅግ ድንቅ ነገር ነው፡፡ ጌታ ከአገልጋይ ይናገር ዘንድ፣ ጌታ ንፍቅ ቄስ ሆኖ ከመልከጼዴቅ ጋር እየተነጋገረ ቆሞ ሳለ በመሠዊያው ላይ ሕጻን ሆነ፤ ሁለተኛም በግ ሆነ፣ ሦስተኛም ኅብስት ሆነ፡፡ ይህንም ኅብስት በሚፈትተው ጊዜ እንደ እሳት ይነድ ነበር፡፡ አባታችንም ቅዳሴውን በፈጸመ ጊዜ ከዚህ ኅብስት ራሱ ተቀበለ፣ በዚያም ለነበሩ ቅዱሳን ሁሉ አቀበላቸው፡፡ ይህን ታላቅ ክብር ለሰጠው ‹ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይሁን› በማለት አመሰገነ፡፡››
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ጻዲቁ ከጌታ ዘንድ የተሰጣቸውን ልዩ ቃልኪዳንም አብረን ማየት እንችላለን፡-

‹‹በማግስቱም ቅዱስ ጴጥሮስ ከሰማይ በወረደ ኅብስት ካህን በሆነ ጊዜ መልከጼዴቅ ንፍቅ ሆነ፤ እንዲሁ ከሁሉም ሐዋርያት ጋር አሥራ ሁለት ቀን ንፍቅ ሆነ፡፡ ዳግመኛም እርሱ ካህን ሆነ፣ ሐዋርያትም እያንዳንዳቸው አሥራ ሁለት ቀን ንፍቅ ሆኑት፡፡ ለሃያ ስድስት ቀናትም ያህል ሁሉም በኢየሩሳሌም ሆኑ፡፡ ይህንም ተልእኮ በፈጸመ ጊዜ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹እኔ ከእናትህ ማኅፀን መረጥሁህ፣ ከአፌ በወጣ ቃሌም እንደማልዋሽህ ቃልኪዳን ሰጠሁህ› አለው፡፡ ያንጊዜም እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ከቅዱሳን መላእክቶች ጋር መጣች፡፡ መላእክትንና ቀደምት አባቶችን፣ ነቢያትንና ሐዋርያትን፣ ጻደቃን ሰማዕታትን፣ ቀሳውስትና ዲያቆናትን፣ ደናግልና መነኮሳትን፣ ወንዶችንና ሴቶችን ሕጻናትንም ምስክሮች አድርጎ አቆመ፡፡ ሄሮድስ ያስገደላቸው 144,000 ሕጻናት ከአለቃቸው ከቅዱስ ቂርቆስ ጋር መጡ፡፡ ‹በእኔና በአንተ መካከል እነዚህ ሁሉ ምስክሮች ይሁኑ፤ ስምህን የጠራ፣ መታሰቢያህን ያደረገ፣ በእጅህ የተጠመቀ፣ በቃልህ የተናዘዘና በእጅህ የተሳለመ ምሬልሃለሁ፤ የገድልህን መጽሐፍ የጻፈውና ያጻፈውን ምሬልሃለሁ ከአንተም ጋር ርስት እሰጠዋለሁ፤ የቤትህ ልጆች መንግሥተ ሰማያትን ከአንተ ጋር ይውረሱ› አለው፡፡ ዳግመኛም ‹ለምህረት ያልጠራኋትን ነፍስ ለመሳለምም ሆነ ለመባረክ ወይም ለመናዘዝ ወደ አንተ አላቀርብም፤ ከኃጥአንም ወገን አንተ ስለ እነርሱ ከለመንኸኝ እምርልሃለሁ፤ ሥጋቸውንም መሬት አይበላውም› አለው፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ሁሉ ቃልኪዳን በኢየሩሳሌም ከሰጠው በኋላ አባታችን በመንፈስ ክንፎች ተመሰጠ፤ ተነጥቆም አዴሴዋ ከምትባል ከትግራይ ምድር ተመለሰ፡፡ የዚህች አገር ሰዎችም ‹ለምን እስከዛሬ ድረስ ተደበቅኸን?› አሉት፡፡ ‹እኔስ በቤቴ ውስጥ ታምሜ ነበርሁ› አላቸው፡፡ ከእርሱ ጋር ከተነጠቁት በቀርም መንፈስ ቅዱስ ኢየሩሳሌም እንደወሰደው አላወቁም፡፡››
ከጻዲቁ ረድኤትና በረከት ይክፈለን!!!

No comments:

Post a Comment