በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በደብረ ወልደ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስ እና በመካነ ጎለጎታ ቅድስት ማርያም ጠበል ሰሞኑን ከአንዲት እኅት ከሆዷ
ጥቁር ወፍ ወጣላት፡፡ በክርስትና ስሟ መንበረ ማርያም ተብላ የምትጠራው እኅት ለ20 ዓመታት ያህል በሆድ ሕመማት
ስትሰቃይ መቆየቷን የምትናገረው መንበረ ማርያም፤ ስቃይዋን በዘመናዊው ሕክምና ለማስታገስ ያልሔደችበት ቦታና
ያልወሰደችው መድኃኒት የለም፡፡ ይሁንና የምትወስደው ሕክምና ለጊዜው ስቃይዋን ከማስታገስ በስተቀር ከሕመሟ ልትድን
ባለመቻሏ ከዚህ በኋላ ይግደለኝ እንጂ ሕክም ናም ሆነ መድኃኒት መጠቀም የለብኝም፤ ብላ ጠበል ለመጠመቅ እንደ
ወሰነች ትናገራለች፡፡ በውሳኔዋም መሠ ረት ወደ ወልደ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስ ቤተክርስቲያን ጠበል በመሄድ ስትጠመቅ
በላይዋ ላይ የሰፈሩ 681 አጋንንት እንዳሉ በላይዋ ላይ ያደሩት የሰይጣን ሠራዊት ለፍልፎ በጥቁር ወፍ አምሳል
ከሆዷ ውስጥ ሊወጣላት ችሏል፡፡ ምእመናን በዕለቱ ከሆዷ ውስጥ በትውከትነት እንደ ጥይት ተወርውሮ የወጣውን ጥቁር
ወፍ ከነሕይወቱ በማየት በቪዲዮ በመቅረጽ የእግዚአብሔርን ድንቅ ተአምር እንደ መሰከሩ ተገልጿል፡፡
የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ ሰምቶ ይህንኑ ወፍ የወጣላትን መን በረ ማርያምንና
ያጠመቋትን አባት ሊቀ ትጉኃን ስሙር አሐዱን በማነጋገር ድርጊቱ እንዴትና ምን ይመስል እንደነበር በሰፊው ዘግቧል፡፡
እግዚአብሔር ሥራው ድንቅ ነው፤ ተዓምሩ ዕፁብ ነው፤ ተነግሮ አያልቅም፤ ይህን ሥራውን መመስከር ደግሞ የእኛ ተግባር ነው፡፡ ለረጅም ዓመታት በሕመም ስትሰቃይ የነበረች በስመ ጥምቀቷ መንበረ ማርያም የተባለች ወጣት የእግዚአብሔርን የድንቅ ሥራው መገለጫ ሆናለች፡፡
ለዚህች እህት እግዚአብሔር ያደረገላት ገቢረ ተአምር
ሲሰሙት ለጆሮ የሚከብድ፤ እንዲሁም በወቅቱ ድር ጊቱ ሲፈጸም የተመለከቱ ምእመናንን ሁሉ ያስደመመ ነበር፡፡ «ማን
ያርዳ የቀበረ፤ ማን ይናገር የነበረ» ነውና ሥረ መሠረቱ ምን፣ እንዴትና መቼ ሆነ? የሚለውን ጉዳይ እሷው ባለታሪኳ
እንዲህ ትተርክልናለች፡፡
«ያመኝ የነበረው ገና የአራት ዓመት ልጅ እያለሁ እሰቃይ ነበር፡፡ ለምሳሌ የራስ ምታት፣ ነስር፣ የሆድ ቁርጠት፣ የአንጀት ኢንፌክሽን ወዘተ እየተባለ በመታመም ሁልጊዜ ሐኪም ቤት እመላለስ ነበር፡፡ እናቴ እንደ ነገረችኝ የሕመሙ መነሻ ወተት ነው፡፡ «ወተት ጠጥተሽ የአንጀት ኢንፌክሽን ያዘሽ» ያለችኝ እናቴ በየክሊኒኩ እየወሰደችኝ ስታስመረምረኝ መድኃኒት እንደሚያዙልኝ አጫውታኛለች፡፡ ራሴን ማወቅ ስጀምር ትምህርት ቤት ገብቼ ስማር ሆዴን ያመኛል፡፡ በተለይ በበጋ ወራት ተምሬ ሁለት ወር ክረምት በሚሆንበት ወቅት ክፉኛ ያመኛል» ስትል ተናግራለች፡፡
መንበረ ማርያም እንደገለጸችልን በጤና መታወክ ሳቢያ ለጊዜው ትምህርቷን ብታቋርጥም ለትምህርቷ ያላት ቁጭት ከፍተኛ ስለነበር በሽታው መጣ ሔድ እያለ ቢያስቸግራትም ከዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በመግባት ትምህርቷን በሥራ አመራር የትምህ ርት ዘርፍ ለአራት ዓመታት ያህል ተከታትላ በ1996 ዓ.ም በዲግሪ ተመርቃለች፡፡
ይሁንና ሌላ
ያላሰበችው ችግር ገጠማት፤ ይህስ ምን ይሆን? ለዚህም መንበረ ማርያም ስትናገር «የወር አበባዬ ከመጣበት ጊዜ
አንሥቶ አሁን እስከዳንኩበት ጊዜ ድረስ በየወሩ በጣም እያመመኝ ክፉኛ ያሰቃየኛል፡፡ ስቃዩን ለማስታገሻ እያልኩ
ፓ¬ራሲታሞል ክኒን በየአራት ሰዓት ልዩነት ሁለት ሁለት ፍሬ በመዋጥ በቀን 10 ፍሬ እወስድ ነበር፡፡ ሐኪም ቤትም
ብሔድ የሚሰጡኝ መርፌ ነው፡፡ አልሻል አለኝ፡፡ የሕክምና ባለሙያዎቹ 'አግብታ ትውለድ፤ ሴቶች እንዲህ ዐይነት ሕመም
ሲሰማቸው ይሻላቸዋልና መውለድ አለብሽ' ብለው አስተያየት ይሰጡኛል» ትላለች፡፡
እንደ መንበረ ማርያም አገላለጽ ብዙ ጊዜ መድኃኒትም መዋጥ ሌላ ችግር /Side-effect/ ስላለው መድኃ ኒት መውሰዱን ታቋርጣለች፤ «ከድጡ ወደ ማጡ» እንዲሉ ይባስ ብሎ በየወሩ ያማት የነበረው እንደ አዲስ የማያቋርጥ የማኅፀን ሕመም ይሰማት ጀመር፡፡ በዚህን ጊዜም በታወቁ የማኅፀን ሐኪም በመታየት በወር አበባ ሳቢያ የተነሣ በማኅፀኗ ውስጥ ትናንሽ ዕጢዎች እንዳሉ ይነገራትና የወር አበባዋ ከመምጣቱ በፊት ለአንድ ሳምንትና ከመጣም በኋላ ለአንድ ሳምንት የሚወሰድ ከባድና በጣም ውድ የሆነ መድኃኒት ይታዘዝላ ታል፡፡ ይህ የሆነው ከሁለት ዓመት በፊት ነው፡፡
«በዚህን ጊዜ
የመጨረሻ ቁርጥ ውሳኔ ወሰንኩ» ትላለች መንበረ ማርያም፡፡ «መሞቴ ለማይቀር ነገር ለምን እሰቃያለሁ? በመድኃኒትስ
ለምን እቃጠላለሁ?» በማለት ወደ ጠበል ቦታ ለመሔድ ወሰነች፡፡ ጠበሉን እንድትሞክር ያነሣሣትና ምክንያት የሆነቻት
ደግሞ ጓደኛዋ እንደሆነች ተናግራለች፡፡ «አንድ ጓደኛዬ እንደ እኔ ዓይነት ሕመም ይሰማት ስለነበር ጻድቃኔ ማርያም
ሔዳ ጠበል ጠጥታ እንደዳነች ነገረችኝ፡፡ እኔም ጠበል መጠጣትና መጠመቅ እንዳለብኝ መከረችኝ፡፡ መድኃኒቱን አቋርጬ
ጠበል መጠመቅ ጀመርኩ፡፡ እየጾምኩ በተከታታይ ጠበሉን ስጠጣና ስጠመቅ በየወሩ የወር አበባዬ ሲመጣ ያመኝ የነበረውን
ተወኝ፡፡ በመቀጠል ከማኅፀኔ ሥጋ ነገር ተቆርጦ ወጣ፡፡ በዚህ ጊዜ ቤተሰቦቼ «እጢው ወጣልሽ» በማለት ተአምር
አሉ፡፡ ሥጋ መሰል ባዕድ አካል ከወጣልኝ በኋላ ምንም ዓይነት ስሜት ሳይሰማኝ ጤነኛ ሆንኩ፤ ጠበሉንም አቋረጥኩት»
በማለት ገልጻለች፡፡
በዚህ መልኩ ለውጥ ያገኘችበትን ጠበል ስታቋርጥ ዳግም ሕመሙ ጀመራት፡፡ መንበረ
ማርያም ትናገራ ለች፡፡ «ጠበሉን ለአንድ ዓመት እንዳቋረጥኩ በሽታው በባሰና በሚያስፈራ መልኩ ተመልሶ መጣ፡፡
እንደገና ጠበሉን መጠጣት ጀመርኩ፤ በዚህን ጊዜም ደጋግሞ የሆነ ነገር በሕልሜ ያሳየኛል፤ በሆነ መንገድ ላይ በጣም
ጥቁርና ትልቅ ሰውዬ ዝም ብሎ ቆሞ ዐያለሁ፣ ቀጥሎ እኔ ሕፃን ልጅ ታቅፌ ሳመልጥ እሱ ትልቅ ድንጋይ ይዞ እየተከተለ
በማስፈራራት ሲያሯሩጠኝ ዐያለሁ፡፡ ይህን ያየሁት በድሮው ቤታችን መገናኛ አካባቢ ነው፡፡
የመንበረ
ማርያም ዋናው ታሪክ የሚጀምርው በግንቦት ወር 2001 ዓ.ም ነው፡፡ በዕለተ ሰንበት እሑድ ቀን ቅዳሴ አስቀድሳ
ስትመለስ እንደተለመደው የወር አበባ ይታያትና በቃላት ሊገለጽ በማይችል ሁኔታ በጽኑ ትታመማለች፡፡ መንበረ ማርያም
እንደገለጸችው «መጽሐፈ አርጋኖን ይዛ ከአንዱ ክፍል ወደ አንዱ ክፍል እየተንቆራጠጠች 'ወይኔ! እመቤቴ ኧረ
አድኚኝ' እያለች መኝታ ክፍሏ ሆና ስታጣጥር በድንገት በግድግዳ ላይ የተሰቀለውን የቅዱስ ሚካኤል ሥዕል ታያለች፡፡
እያጣጣርኩ በክፍሌ ውስጥ ቁጭ ብዬ ድንገት የተሰቀለውን የቅዱስ ሚካኤል ሥዕል ቀና ብዬ ማየት ስጀምር የፌዝ ሳቅ
መሳቅ ጀመርኩ፡፡ በዚህን ጊዜ ራሴን እየለወጠኝ ነው፤ አልፎ አልፎ እንጂ ምን እንደምሠራም አላውቅም፤ መጣሁልህ
ይላል፡፡ እንደዛር ማጓራት ጀመርኩ፤ አባቴ ሲሰማ ደነገጠ፡፡ እሱ እንደነገረኝ ሁለት እጄን ይዞ የቅዱስ ገብርኤል
ጠበል እየረጨ 'አንተ ማነህ?' ሲለው 'እባክህ አንተ አታውቀኝም! ዝም ብለህ ነው፤ ተቃጠልኩ ጊዜዬ ሲደርስ
የምለቅበት ቀን አለ፡፡ እሷን የያዝኩት ከማኅፀን ጀምሮ ያሳደግኳት እኔ ነኝ' በማለት ለፈለፈ፡፡ በመቀጠል
'እናቷንም የገደልኩ እኔነኝ' ሲል ራሱን ገለጠ» በማለት መንበረ ማርያም አስረድታለች፡፡ እናቷ በካንሰር ሕመም
ምክንያት በ1995 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውንም ገልጣልናለች፡፡
በቅዱስ ሚካኤል ሥዕል ሳቢያ ማንነቱን የገለጠው ሰይጣን እንደያዛት ስታውቅ፣ የትመጠመቅ እንዳ ለባት ታስባለች፡፡ በመጨረሻም በደብረ ወልደ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን ሔዳ ጠበል መጠመቅና መጠጣት ትጀምራለች፡፡ በአምስተኛው ቀን ያደረባት ርኩስ መንፈስ መለፍለፍ ይጀምራል፡፡ በተለይ ሰኔ 10 ቀን 2001 ዓ.ም በዕለተ ረቡዕ ስትጠመቅ 681 አጋንንት እንደ ሠፈረባት ይለፈልፋል፡፡ ብዙ ሰው እንደጨረሰና አሁንም ብዙዎችን እንደያዘ ገልጾ እርሷ ላይ ሲደርስ ግን እንደተጋለጠ ተናግሯል፡፡ «ምእመናን እንደነገሩኝ ከሆነ «አንቺ ስትጮኺ እንደ አንበሳ ነው፤ የሚያስፈራና ከአንቺ የሚወጣ ድምፅ አይመስልም ብለውኛል፡፡ እኔ ግን በመሐሉ «መድኃኔዓለም መጣ» የሚል ድምፅ ሰማሁ እንጂ ራሴን አላውቅም፡፡
መጨረሻ ላይ ራሴን ሳውቅ ከእኔ የወጣውን ጥቁር ወፍ ይዘው አሳዩኝ፡፡ አላመንኩም፡፡ ሰው እልል እያለ 'አይዞሽ
ተነሽ እመቤታችን ከነልጇ የሠራችልሽ ተአምር በጣም ድንቅ ነው፡፡ ተነሥተሽ ድንቅ ተአምሯን ትመሰክሪያለሽ' አሉ፡፡
ልብሴን ለብሼ ስወጣ ብዙ ምእመናን ቆሞ በሞባይልና በቪዲዮ የወጣውን ጥቁር ወፍ ይቀርጻል፡፡ ከሆዴ የወጣው ትልቅ
አፍ ያለው ወፍ ደም ጎርሶ በሕይወት ለተወሰነ ደቂቃ ልቡ ይመታል፡፡ እኔ ራሴን አላመንኩም፤ ደስታ አይሉት ሐዘን
ተደበላለቀብኝ፣ ሰውነቴ ከላይ እስከታች ይርዳል» ስትል የእግዚአብሔርን ድንቅ ተአምር መስክራለች፡፡
ሰኔ 10 ቀን ከ681 አጋንንት ውስጥ ሰማንያው ጥቁር ወፍ ሆኖ ሲወጣ ሰኔ 12 ቀን ሌሎች ቀሪዎቹ በጉንዳን መልክ ወጥተናል ብለው በመለፍለፍ ለቀቁ፡፡ በወቅቱም የጠበሉ ቦታ በጉንዳን ተወሮ እንደነበር መንበረ ማርያም ገልጻለች፡፡ ያ በሕልሟ ሲያባርራት ያየችው ጥቁር ሰው እርኩስ መንፈስ እንደሆነና ሕፃኑ ደግሞ መድኃኔዓለም ሆኖ እንዳዳናት አምና ተርጉማዋለች፡፡
መንበረ ማርያም ስለተደረገላት ድንቅ ተአምር ሰኔ 10 እና 21 ቀን 2001 ዓ.ም
የእመቤታችን ክብረ በዓል ዕለት በቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ ቤተክርስቲያን በመድረክ ላይ ወጥታ ለሕዝበ
ክርስቲያኑ መስክራለች፡፡
በመጨረሻ ያነሣንላት ጥያቄ «የተደረገልሽን ተአምር እንዴት ትገልጭዋለሽ?» ነበር፡፡ እሷም «እግዚአብሔር ያደረገልኝን ድንቅ ተአምር በቃላት ልገልጸው አልችልም፡፡ ኃያሉ እግዚአብሔር እኔን አድኖኛል ምስጋና ይድረሰው፡፡ እኔ ግን የማተኩረው ስለተደረገልኝ ተአምር መመስከር ብቻ ሳይሆን ስለማስተላለፈው ነገር ነው፡፡ ይኽም እግዚአብሔር እንዲህ ማዳን እየቻለ ሰይጣን ሊሰለጥንብን አይገባም፡፡ በሥራ፣ በትምህርት ቤትና በዕለት ተዕለት ሥራችን ላይ ውጤታማ እንዳንሆን መሰናከል እየሆነ ነው፡፡ ሕይወታችንን እያበላሸ መሆኑን አልተረዳንም፡፡ ስለዚህ ስመ ክርስትና ብቻ ይዘን መቀመጥ ሳይሆን በጾም በጸሎት እግዚአብሔርን ማገልገል ይኖርብናል፡፡ ከንስሓ አባት ጀምሮ የሃይማኖት አባቶችም ማስተማር አለባቸው፡፡ እያንዳንዱ ሰው ራሱን ይመርምር፤ ክፉ መንፈስን መዋጋት አለበት» ብላለች፡፡
«ማየት ማመን ነው» እንደተባለው በወቅቱ በደብረ ወልደ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስና በመካነ
ጎለጎታ ቅድስት ማርያም የጠበል ቦታ ሲያጠምቋት የነበሩትና ድርጊቱን የተመለከቱት ሊቀ ትጉኃን ስሙር አሐዱ
ስለሁኔታው እንዲነግሩን ጠይቀናቸው እሳቸውም ታሪኩን እንዲህ አወጉን፡፡ «ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም፤
ነገሩ ተአምር ነው፡፡ ከዚህ በፊት በእርኩስ መንፈስ የታሰሩ፣ የተተበተቡ ሰዎችን በእግዚአብሔር ኃያልነትና መስቀል
በመታገዝ በላያቸው ያለውን አጋንንት አስለቅቄያለሁ፡፡ ይህ ግን ልዩና በሕይወቴም ገጥሞኝ የማያውቅ ነው፡፡ በዕለቱ
እኅታችን መንበረ ማርያም ወደምትጠመቅበት ክፍል ስትገባ ጀምሮ በጣም ትጮሃለች፡፡ በመስቀል እያጠመቅሁ ምንድን ነህ?
ስለው አጋንንት ነን አሉ፡፡ ቀጥሎ ስንትናችሁ? አልኩት 600 አጋንንት ነን አሉና እውነቱን አውጣ ብዬ አጥብቄ
ስይዘው 680 ብሎ ለፈለፈ፡፡ መጨረሻ ላይ 681ኛ ተልከስካሽ የዛር መንፈስ እንዳለ ገልጾ ከሰኔ 10 ቀን 2001
ዓ.ም ጀምሮ በተከታታይ በአራት ቀናት ውስጥ ተከፋፍሎ ወጣ» ብለዋል፡፡
እንደ እሳቸው አባባል ሰኔ 10
ቀን 2001 ዓ.ም 80ው ጥቁር ወፍ ሆኖ ሲወጣ፤ በነጋታው «593ቱ ጉን ዳን ሆኜ እወጣለሁ» ብሎ ጮኸ፤ ሲለቅ
ወዲያውኑ ከየት መጣ ሳይባል አካባቢውን ጉንዳን ወረረው፡፡ በሦስተኛው ቀን ደግሞ ሰባት ሲወጣ ከሰባቱ አንዷ ብቻ
ሴት ሆና ተገኘች፡፡ እሷም «ከውጭ ሀገር ነው የመጣነው፤ ሥራችን ተመሳሳይ ፆታዎችን ማጋባት ሲሆን በውጭው ዓለም
አጥለቅልቀነው ወደ አፍሪካና ኢትዮጵያ በብዛት እየገባን ነው» ብላ ተናግራለች፡፡
«በመጀመሪያ ዋናውና አለቃው ' አጋንንት ጥቁር ወፍ ሆኖ ሲወጣ 600ው ሠራዊት ነኝ ብሎ ወጣ፡፡ አለ ቃውን አጋንንት» እንዴት ብለህ ነው የምትወጣው» ስለው እንደ አንበሳ አጓርቼ እወጣለሁ አለ፡፡ ልጅቷ እንደ አንበሳ እያጓራች ሳለ ጥቁር ወፍ በደም ተለውሶ ከሆዷ ውስጥ በአፏ ወጣ፤ ሲወጣም ልክ እንደ አየር ሞገድ ተወርውሮ ገንዳ ነገር ላይ አረፈ፡፡ ይህ እርኩስ መንፈስ ወፍ ሆኖ ሲወጣም ግፊት ስለነበረው እኔን ሁሉ ገፍትሮኛል፡፡ የወጣው ጥቁር ወፍ ከነሕይወቱ በመሆኑ ለተወሰነ ደቂቃ የማስካካት ድምፅ አሰምቷል፡፡ ለግማሽ ሰዓት ያህልም በሕይወት ቆይቶ ምእመናን ዐይተውታል፡፡ ድርጊቱ የሁሉንም መንገደኛ ቀልብ የሳበ ስለነበር መናፍቆች ሳይቀሩ ተመልክተው በእመቤታችን ድንቅ ተአምር ተገርመ ዋል፡፡ በተለይ አንድ ከነቀምት የመጣ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ በተአምሩ ተደንቆ ሲያለቅስ ዐይቻለሁ» በማለት ሊቀ ትጉኃን ስሙር አስረድተዋል፡፡
«አጋንንቱ መንበረ ማርያምን እንዴት እንደያዛት ስጠይቀው በተለያየ
ምክንያት በይበልጥ በዛር ውላጅ ሲወርድ ሲዋረድ በዘር ሐረግ የመጣ እንደሆነ ለፍልፏል፡፡ ለ20 ዓመታት ያህል
በሆዷና በማሕፀኗ ላይ ከፍተኛ ጫና በማድረስ ያሰቃያት እንደነበር ዘርዝሯል፡፡ በወር አበባዋ ጊዜ ምጥ እያበዛ
ያሰቃያት እንደነበር ተናግሯል፡፡ እመቤቴ፣ እመቤቴ እያለች የእመቤታችን ማርያምን ስም እየጠራች አስቸገረችኝ እንጂ
ሆዷን ኦፕራሲዮን አስደርጌ በሰበብ ልገድላት ነበር» ሲልም ተናግሯል ይላሉ፡፡
«ድርጊቱ በጣም የሚከብድ
እና በእኔ ላይ የደረሰ ያህል ተሰማኝ፤ እኔም በሁኔታው በጣም ያዘንኩበትና ያለቀስኩበት ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ
ድርጊት በእኔ ላይ ተከስቶ ቢሆን ኖሮ ምን ልሆን እንደምችል ትንሽ ቆም ብዬ ማሰብ ጀመርኩ፡፡ እሷ ግን እጅግ በጣም
ጠንካራ፣ በእምነቷ ጽኑ ነች፡፡ በእምነቷ ጽናት እግዚአብሔር ድንቅ ሥራውን ሠራላት፡፡ አሁን ሙሉ ለሙሉ ጤነኛ ነች
ብለዋል፡፡ እርኩስ መንፈሱ አባቷን ሳይቀር ሌሎች ሰዎችንም ይዣለሁ ብሎ በመለፍለፍ ልጅቷ ቤት ድረስ በመሔድ
መጥተው እንዲጠመቁ ተናግሬያለሁ» በማለት ሊቀ ትጉኃን ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም «የማስተላልፈው መልእክት አለ፡፡ እግዚአብሔር ብዙ ሥራ ይሠራል፤ እግዚአብሔር እኛ እንድንድን የማያደርግልን ነገር የለም፡፡ ከዚች እኅት ትልቅ ትምህርት አግኝተንበታል፤ የክርስቶስ ስልጣን ይህን ዐይነት የሚሠራ ከሆነ እኛ የት ነን? ብለን ማሰብ አለብን፡፡ ትንሽም ብትሆን እምነት ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ወደ እግዚአብሔር በመቅረብ ጠበሉን፣ እምነቱን ልንጠጣ ይገባል፤ ሥጋና ደሙን ልንቀበል ያስፈልጋል፡፡ ይህ ከሆነ መዳን እንዳለ ማመን ይገባል» ሲሉ ሊቀ ትጉኃን ስሙር አሐዱ አስረድተዋል፡፡
በርግጥም መንበረ ማርያምና አጥማቂዋ ሊቀ ትጉኃን እንደገለጡት በየጠበሉ ቦታ ሲታይ በርኩስ መንፈስ በመተት፣ በዛር፣ በአጋንንትና በመሳሰሉት የተያዙ ሰዎች በእግዚአብሔር ኃይል ሲፈወሱ ማየት ጉድ ያሰኛል፡፡ ሰይጣን የምንፈራው ሳይሆን ታግለን የምናሸንፈው መሆኑን ማንም ሰው ሊያውቀውና ሊረዳው ይገባል፡፡ አውቆም በጾም በጸሎት እርምጃ ሊወሰድ ይገባል፡፡ የበለጠ ደግሞ መምህራን ሓላፊነት ወስደው ማስተማር ይኖርባቸዋል፡፡
No comments:
Post a Comment