Saturday, October 17, 2015

አንዳሳ ቅዱስ ጊዬርጊስ ፀበል

በደብረ መንክራት አንዳሳ ቅዱስ ጊዬርጊስ ለበርካታ አመታት ስትሰቃይ የነበረች እህታችን የቅዱስ ጊዬርጊስን ፀበል በመጠጣት እና በመጠመቅ ከሆዷ ውስጥ ሶስት መርፌ እና አንድ ምላጭ ወጦላታል። ይሂን ታምር በአይኔ በማየቴ እግዚአብሄርን አመሰግናለሁ። ፀበሉ በርካታ ታምራትን እያደረገ ሲሆን በተለያዩ ደዌዎች፣በርኩሳን መናፍስት የተጠቁ ወዘተ እየተፈወሱ ይገኛሉ። ክብር ለቅዱስ
ጊዬርጊስ አምላክ ለእየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ጋር ይሁን

Thursday, October 1, 2015

ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ

ግንቦት 14- ሙሽራው ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ ከጫጉላ ቤቱ ወጥቶ የመነነበት ዕለት ስለሆነ በሀዘን የሚያስለቅሰውን ቅዱስ ገድሉን እንመለከታለን፡፡ በተጨማሪም ዛሬ የታላቁ አባት የአባ ጳኩሚስ በዓለ ዕረፍት ነው፣ ድንጋዩን እንደ ጀልባ ተጠቅመው ጣናን የተሻገሩት የአቡነ ያሳይ ዘመንደባም ዕረፍታቸው ነው፡፡
መልካም የበረከት ንባብ!!!
ሙሽራው ገብረ ክርስቶስ፡- ሙሽራው ገብረ ክርስቶስ ወላጅ አባቱ የቍስጥንጥንያው ንጉሥ ቴዎዶስዮስና እናቱ ንግሥት መርኬዛ በስለት ያገኙት ብቸኛ ልጃቸው ስለሆነ ሃይማኖትን እያስተማሩት በምግባር በእጅጉ ተንከባክበው አሳድገውታል፡፡
የአባቱን ንግሥና በመውረስ ቍስጥንጥንያን እንዲገዛላቸው በመፈለግ ወላጆቹ ለአካለ መጠን ሲደርስ የሮሙን ንጉሥ ሴት ልጅ አጋቡት፡፡ እርሱ ግን ዓለምን ፍጹም በመናቅ የክርስቶስን መስቀል ለመሸከም የተዘጋጀ ነበርና የሠርጉ ዕለት ሌሊት የእርሱንም ሆነ የሙሽይቱን ድንግልና እንደጠበቀ ከጫጉላ ቤት ወጥቶ በመርከብ ተሳፍሮ ሩቅ ሀገር በመሄድ በቤተክርስቲያን ተቀምጦ ከነዳያን ጋር ተደባልቆ በመለመን ለምኖ ያገኘውንም ለሌሎች እየመጸወተ በጾም በጸሎት ተጠምዶ 15 ዓመት ኖረ፡፡
እመቤታችን ተገልጻ ለአንድ የቤተክርስቲያኑ አገልጋይ የገብረ ክርስቶስን ጽድቅ ብትነግረው ምሥጢሩን ለሀገሩ ሁሉ አዳረሰበት፡፡ ሙሽራው ገብረ ክርስቶስም ‹‹ግብሬ ታወቀ፣ ከዚህ ውዳሴ ከንቱ ልሽሽ›› በማለት ወደሌላ ሀገር በመርከብ ሲጓዝ ፈቃደ እግዚአብሔር መርከቢቱን ያለ አቅጣጫዋ ወስዶ አባቱ ደጅ አደረሰው፡፡ ማንነቱን እንደደበቀና ዓለምን ምን ያህል እንደናቃት ይረዳ ዘንድ በአባቱና በንጉሡ ደጅ የኔ ቢጤ ለማኝ ሆኖ ለአባቱ ውሾች የሚሰጠውን ፍርፋሪ እየተመገበ አሁንም 15 ዓመት ሙሉ በትዕግስት ተቀመጠ፡፡
የአባቱ አሽከሮች እንኳን እጣቢና ቆሻሻውን ሁሉ እየደፉበት ሲያሠቃዩት የአባቱ ውሾች ግን የእግሩን ቁስል ይልሱለት ነበር፡፡ በአጠቃላይ ገብረ ክርስቶስ እጅግ የተከበረ የታላቅ ንጉሥ ልጅ ሲሆን ነገር ግን ዓለምን ፍጹም በመናቅ ስለ ጽድቅ ተሰዶ እየለመነ ያገኘውን እየመጸወተ በጾም በጸሎት እየተጋደለ 30 ዓመት ሙሉ ተቀመጠ፡፡ በመጨረሻም ጌታችን እመቤታችንን፣ ቅዱሳን መላእክትን ሁሉ፣ ከገብረ ክርስቶስ በፊት የነበሩ ነቢያትን ሁሉ፣ ሐዋርያትን፣ ጻድቃንን፣ ሰማዕታትን ሁሉ አስከትሎ መጥቶ ቃልኪዳን ከገባለት በኋላ ከጌታችን ጋር አብረውት የመጡት ሁሉ በታላቅ ክብርና ምስጋና እያመሰገኑት ጌታችን ክብርት ነፍሱን በእቅፉ ተቀብሎ አሳርጓታል፡፡
የቁስጥንጥንያው ሊቀ ጳጳሳት አባ ቴዎፍሎስ በቅዳሴ ላይ ሳሉ ከንጉሡ ቤት ሄደው የገብረ ክርስቶስን ሥጋ እንዲያመጡ የእግዚአብሔር ድምፅ ከሰማይ በትእዛዝ መጣላቸውና ሄደው ቢያዩ የገብረ ክርስቶስን ሥጋ በንጉሥ አባቱ ደጅ ወድቆ አገኙት፡፡ በገብረ ክርስቶስም እጅ ላይ በጥቅል ወረቀት የተጻፈ ደብዳቤ ነበርና ወስደው ሊያነቡት ሲሞክሩ ወረቀቱ አልላቀቅ ብሎ ፈጽሞ እምቢ አላቸው፡፡ ብዙ ምሕላና ጸሎት ከተደረገ በኋላ ወረቀቱ ከእጁ ላይ ተላቀቀና ሲነበብ ገብረ ክርስቶስ ስለ አምላኩ ፍቅር ብሎ ለ30 ዓመታት ያሳለፈውን እጅግ አሠቃቂ መከራ በተለይም በአባቱ ደጅ ማንም ሳያውቀው ያሳለፈውን እጅግ አሳዛኝ መከራና በኀዘን የሚያስለቅሰውን ታሪኩን በራሱ እጅ በዝርዝር ጽፎት ተገኝቷል፡፡ ንጉሡ አባቱና ንግሥት እናቱም ይህንን ልጃቸው የጻፈውን መልእክት ባነበቡ ጊዜ የሚሆኑት ጠፋቸው፡፡
በጣም የሚገርመው ደግሞ ወላጆቹ ሚስት አድርገው ያመጡለት የሮሙ ንጉሥ ሴት ልጅ ለባሏ ታማኝ ሆና 30 ዓመት ሙሉ በእናት አባቱ ቤት በትዕግስት ስትጠብቀው መኖሯ ነው፡፡ እርሷም ታሪኩ ሲነበብ ብትሰማ እንደ ዕብድ ሆነች፡፡ የቅዱስ ገብረ ክርስቶስን ሥጋውን ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲወስዱ እጅግ አስገራሚ ተአምራት በድውያን ሕመምተኞች ላይ ተፈጽሟል፡፡ ከተአምራቱ የተነሣ መንገዱ በሕዝብ ተጨናንቆ አላሳልፍ ቢላቸው ንጉሡ በመንገድ ዳር ወርቅ እየበተነ ሰው ወርቁን ለማንሳት ሲሄድ በፍጥነት ወደ ቤተ ክርስቲያን አድርሰውታል፡፡ ዕረፍቱም ጥቅምት 14 ቀን ሲሆን ዛሬ ከጫጉላ ቤቱ መንኖ የወጣበት ዕለት ነው፡፡
አቡነ ያሳይ ዘማንዳባ፡- የደብረ በንኰል ገዳም አበምኔት አቡነ መድኃኒነ እግዚእም በአንድ ቀን ለሰባት አባቶች የምንኵስናን ልብስ አልብሰዋቸል፤ አስኬማ ዘመላእክትን አስታጥቀዋል፡፡ እነዚህም ሰባት ታላላቅ አባቶች "ሰባቱ ከዋክብት" በመባል የሚታወቁት ናቸው፡፡ እነዚህም አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ፣ አቡነ ሳሙኤል ዘቆየፃ፣ አቡነ ሳሙኤል ዘጣሬጣ፣ አቡነ ያሳይ ዘማንዳባ፣ አቡነ ዮሐንስ ዘጉራንቋ፣ አቡነ ታዴዎስ ዘባልተዋር እና አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ ዘጉጉቤን ናቸው፡፡ እነዚህም 7ቱ ከዋክብት ከተሰዓቱ (ከዘጠኙ) ቅዱሳን በኀላ መላዋን ኢትዮጵያ በወንጌል ያዳረሱ ታላላቅ ቅዱሳን ናቸው፡፡ አቡነ ያሳይ ዘማንዳባም አንዱ ናቸው፡፡
ጻድቁ ድንጋዩን እንደ ጀልባ ይጠቀሙበት ነበር፡፡ የማንዳባው አቡነ ያሳይ የመድኃኔዓለምን ታቦት ይዘው ወደ ደሴቲቱ የገቡት ትልቁን ድንጋይ እንደ ጀልባ ተጠቅመው በድንጋዩ ላይ ተቀምጠው የጣናን ሐይቅ እየቀዘፉ ነበር፡፡ ትልቁ ጠፍጣፋ ድንገይ ዛሬም ድረስ በገዳማቸው ውስጥ በክብር ተቀምጦ ይገኛል፡፡
ጻድቁ በይበልጥ የሚታወቁት በ"አትማረኝ ዋሻ" ታሪክ ነው፡፡ በገድላቸው ተጽፎ እንደሚገኘው ዋሻው በጣና ሐይቅ ደሴቶች መካከል ከሚገኙ ገዳማት መካከል ከማን እንደ አቡነ ያሳይ መድኀኔዓለም አንድነት ገዳም በስተ ምእራብ አቅጣጫ የጣና ሐይቅን ጉዞ ከገታው አንድ ተራራ ሥር የሚገኝ ነው፡፡
ጻድቁ ከእግዚአብሔር በተሰጣቸውም ጸጋ በጣና ሐይቅ ላይ እንደ ጀልባ በሚጓዙበት አንድ ጠፍጣፋ ድንጋይ ተቀምጠው በጣና ደሴት ላይ ለአገልግሎት በመፋጠን ላይ እያሉ ዛሬ አትማረኝ ዋሻ ተብሎ ወደሚጠራው አካባቢ ሲደርሱ አንድ አባት ዋሻው ውስጥ “አትማረኝ፣ አትማረኝ፣ አትማረኝ” እያሉ ሲጸልዩ ያገኟቸዋል፡፡ አቡነ ያሳይ በሰውዬው ጸሎት በመገረም ቀርበዋቸው “አባቴ ምን ዓይነት ጸሎት ነው የሚጸልዩት? ይበሉ ከዛሬ ጀምረው “ማረኝ” እያሉ ይጸልዩ" በማለት አቡነ ዘበሰማያትን አሰተምረዋቸው ይሄዳሉ፡፡ አትማረኝ እያሉ ይጸልዩ የነበሩት አባትም “ማረኝ” እያሉ መጸለያቸውን ቢቀጥሉም ብዙ መግፋት ሳይችሉ ጸሎቱ ይጠፋባቸዋል፡፡ ጸሎቱን ያስጠኗቸው አባት አቡነ ያሳይ በድንጋዩ ላይ ተቀምጠው ጣናን አቋርጠው ርቀው ሳይሄዱባቸው ከኀላ በውኃ ላይ በባዶ እግራቸው እየተራመዱ በመከተል ይደርሱባቸዋል፡፡ “አባታችን ያስጠኑኝ ጸሎት ጠፋብኝ፡፡ እባክዎ እንደገና ያስተምሩኝ” ይሏቸዋል፡፡ አቡነ ያሳይ የእኚህ አባት መብቃት (በባሕር ላይ በባዶ እግራቸው መራመዳቸውን) ተመልከተው “አባቴ እግዚአብሔር የልብ ነውና የሚመለከተው እንዳስለመዱት ይጸልዩ የእርስዎ ይበልጣል” ብለዋቸው ይሔዳሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ቦታው አትማረኝ ዋሻ ተብሎ ተጠርቷል፡፡
አቡነ ያሳይ እጅግ አስገራሚ ተአምራትን በማድረግ ወንጌልን በሀገራችን ያስፋፉ ሲሆን ተጋድሎአቸውን ፈጽመው ከጌታችን ታላቅ ቃልኪዳን ተቀብለው በዛሬዋ ዕለት ዐርፈዋል፡፡ በረከታቸው ይደርብን!
ኃያል መነኮስ አባ ጳኩሚስ፡- በሥርዓተ ምንኵስና ታሪክ ሌላውን ታላቅ ሥፍራ የያዘው ደግሞ የአባ እንጦንስ ደቀ መዝሙር የነበረው አባ ጳኩሚስ ነው (23ዐ-346 ዓ.ም)፡፡ አባ ጳኩሚስ ግብፅ ውስጥ ኤስና በምትባል መንደር ከአረማውያን ቤተሰቦች በ29ዐ ዓ.ም ተወለደ፡፡
በቆስጠንጢኖስ ዘመነ መንግሥት ለውትድርናም ተመልምሎ አገልግሎት ሰጥቷል፡፡ በውትድርናው ዘመን የክርስቲያኖችን ቆራጥነት፣ ደግነትና ርኀራኄ በማየቱ ልቡ ስለተነካ ግዳጁን ፈጽሞ ሲመለስ በ313 ዓ.ም የክርስትናን እምነት ጠንቅቆ በመማር አምኖ ተጠመቀ፡፡ የአባ ጳኩሚስ ልቡና የቅዱስ እንጦንስ ደቀ መዝሙር በነበረው በአባ ጴላጦንስ ኑሮ ስለተማረከ ወደ በረሃ ወርዶ የብሕትውናን ኑሮና ሥርዓት ሲማር ከቆየ በኋላ በ32ዐ ዓ.ም በዓባይ ወንዝ አጠገብ ታቤኒስ ከተባለው ቦታ የራሱን ገዳም መሠረተ፡፡
እዚህ ጋር የመነኮሳትን ትውልድ መመልከቱ ተገቢ ይሆናል፡፡ ርዕሰ መነኮሳት የሆኑት አቡነ እንጦንስ በእግዚአብሔር ፈቃድና ትእዛዝ ምንኩስናን ከሊቀ መልአኩ ከቅዱስ ሚካኤል እጅ ተቀበሉ፡፡ እንጦንስም ታላቁ መቃርስን አመነኮሷቸው፤ ታላቁ መቃርስም ጳኩሚስን አመነኮሷቸው፤ እንዲህ እንዲህ እያለ የአባቶቻችን የምንኩስና ትውልድ እስከ ጻድቁ አባታችን ተክለ ሃይማኖት የደረሰ ሲሆን እሳቸውም ያመነኮሷቸው እጅግ ብዙዎች ናቸው፡፡



ጳኩሚስም ቴዎድሮስን፣ ቴዎድሮስ ደግሞ አቡነ አረጋዊን(ዘሚካኤልን)፣ አረጋዊ ክርስቶስ ቤዛነን፣ ክርስቶስ ቤዛነ መስቀል ሞዐን፣ መስቀል ሞዐ ዮሐኒን፣ ዮሐኒ ኢየሱስ ሞዐንና ተክለ ሃይማኖትን(በቆብና በአስኬማ)፣ ኢየሱስ ሞዐ
ተክለ ሃይማኖትን(በቅናትና በቀሚስ)፣ ተክለ ሃይማኖት ኢየሱስ ሞዐን (በቆብና በአስኬማ) ወልደዋል፡፡
ዻኩሚስ መጀመሪያ ወደ ምንኩስናው ዓለም የመጣው በታላቁ አባ ዸላሞን አማካኝነት ነው፡፡ ለተወሰነ ጊዜም መንፈሳዊ አባቱን እየረዳ ሕይወተ መነኮሳትን አጥንቷል፡፡ በመንፈሳዊ ሕይወቱና በተጋድሎ እየበረታና እየደረጀ ሲሔድ ከአባ ዸላሞን ተለይቶ ማሕበር መስርቶ ለመኖር አምላኩን ጠይቆ ፈቃድ በማግኘቱ በሕግ የሚመራ የመጀመሪያውን ገዳም መሥርቷል፡፡
ቅዱስ ዻኩሚስ ጸሎቱ አጋንንትን ከአካባቢው አያስቀርባቸውም ነበር፡፡ አካሉ አልቆ በአጥንቶቹ እስኪቆም ድረስ ጾሟል፡፡ ዓርብ ዓርብ የጌታችንን ሕማማት እያሰበ ከእንባ ጋር ይሰግዳል፡፡ እንባውና ላበቱ ከፊቱ እየወረደ አካባቢው ጭቃ ይሆን ነበር፡፡ ጌታችንም መስቀል ተሸክሞ ይታየው ነበር፡፡ አባ ጳኩሚስ ሲሰግድ ወዙ ወርዶ መሬቱን ጭቃ አደረገው፣ ወዲያው ጌታችን ተገለጸለትና ጳኩሚስ "አንተን አገኝ ብዬ እንዲህ እደክማለሁ" አለው ጌታችንም "እኔም እንጂ ላንተ ብዬ እንዲህ ሆኜ ተሰቅያለሁ" ብሎ በዕለተ ዓርብ እንደተሰቀለ ሆኖ ጐኑን እንደተወጋ ደሙ እንደፈሰሰ ሆኖ ታይቶታል፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን በበረሃ ሳለ መልአክ መጥቶ በነሐስ የተጻፈ ሕግ ሰጠው እርሱም በዚሀ የመጀመሪያውን ሥርአተ መነኮሳትን አዘጋጅቷዋል። ከዚህም ባለፈ በርካታ ሥራዎችን ሠርቷል፡፡ ቅዱስ ዻኩሚስ ጫማ ሳይጫማ እሾህን ሳይሰቀቅ ይረግጥም ነበር፡፡
አባታችን ቅዱስ ዻኩሚስ ከርሕራሔው የተነሣ አጋንንት ያደሩባቸውን ሰዎች ሲያገኝ በቀጥታ ከመፈወስ ይልቅ ደዌውን ርኩሳን መናፍስቱንም ወደ እርሱ እንዲገለበጡ ያደርግ ነበር:: ከዚያም በጾም በጸሎትና በስግደት መድረሻ ያሳጣቸዋል፡፡ ያንጊዜ በግዳቸው እየጮሁ ሲወጡ ደጉ አባት "ምነው ትንሽ ቆዩ እንጂ" እያለ ይቀጣጠብባቸዋል፡፡ አንድ ዕለት ቅዱስ ጳኩሚስ አንዲት ሴት ብዙ አጋንንት ሰፍረውባት ስትሰቃይ አየና "አቤቱ ጌታዬ ሆይ ይህን ሁሉ እንዴት ትችለዋለች?" ብሎ በእርሷ ላይ ያለውን የአጋንንት መንጋ ወደ እርሱ እንዲገለበጥ ፈጣሪውን ለመነ፡፡ በዚህ ጊዜ በአንድ ቀፎ ውስጥ ያሉ ንቦች ወደ ሌላ ቀፎ እንደሚገለበጡ እነዚያ አጋንንት በሙሉ ከዚያች ሴትዮ ወጥተው በአባ ጳጉሚስ ላይ ሰፈሩ፡፡ እርሱም ማቅ ለብሶ አመድ ነስንሶ በሥግደት በጾምና በጸሎት አሰቃያቸው፡፡ የዚህን ቅዱስ አባት ትሩፋትና ተጋድሎ ስላልቻሉ አጋንንቱ "እንሂድ እንጂ እንግዲህማ ምን እናደርጋለን" ሲሉ ሰማቸው፡፡ ቅዱስ ጳኩሚስም "ለምን አትቆዩም ሰው እንዲህ ካለ ኃጥእ ወዳጁ ቤት እኮ ጥቂት ጊዜ ያርፋል" ቢላቸው "እኛስ ከገነት ካስወጣነው ከአዳም በቀር እንዲህ ያለ ሰው አላየንም ትሩፋቱ አቃጠለን ሊያስቀምጠን አልቻለም" ብለው መስክረውለት ሄዱ። (ኤፌ.6፥11 "የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ።")
አባ ዻኩሚስ ስለ ክብራቸው መልአክ ነጥቆ ወስዷቸው ገነትንና ሲኦልን አሳይቷቸው መልሷቸዋል።
በዙሪያው ለተሰበሰቡት መነኰሳትም የአንድነት ኑሮ ሕግ አወጣላቸው፡፡ ምንኩስና በእግዚአብሔር ፈቃድ በአባ እንጦንስ ቢመሠረትም ሕይወቱን በማስፋፋት ደረጃ የቅዱስ ዻኩሚስን ያህል የደከመና የተሳካለት ግን የለም፡፡ በአባ እንጦንስ ለተጀመረው የማኀበረ መነኰሳት ኑሮ የተጠናከረ ሥርዓት አውጥቶ የበለጠ ከማስፋፋቱም በተጨማሪ ዘጠኝ የወንድና ሁለት የሴቶች ገዳማት መሥርቷል፡፡ አባ ጳኩሚስ ያወጣው የመነኰሳት የአኗኗር ሕግ ዋናው ቅጂ ሲጠፋ ወደ ላቲን የተተረጐመው ግን እስከዛሬ ድረስ ይገኛል፡፡ ከሕግጋቱ መካከል፡-
፩. መነኮሳት ጠዋትና ማታ በማኀበር እንዲጸልዩ
፪. በኀብረት በአንድነት እንዲሠሩ
፫. ቅዱሳት መጻሕፍትን አዘውትረው እንዲመለከቱ
፬. መነኮሳት ሹመት እንዳይሾሙ ከልክሏል
፭. መነኮሳት የቁም ጽሕፈት እንዲማሩ
፮. ገቢና ወጪአቸው አንድ ላይ እንዲሆን
፯. መነኮሳት በአንድነት እንዲመገቡ
፰. አንድ ዓይነት ልብስ እንዲኖራቸው
፱. መነኮሳት ንጽሕናቸውን ጠብቀው እንዲኖሩ
፲. ከግብፅ ውጪ ምንኩስናን ያስፋፉ አባቶችን አስተምሮ አመንኩሷል፡፡ (ለምሳሌ በኢትዮዽያ ምንኩስናን ያስፋፉት አቡነ አረጋዊ የዚህ አባት ደቀ መዝሙር ናቸው)
፲፩. መነኮሳት ከገዳማቸው በፍጹም እንዳይወጡ ከልክሏል
፲፪የመጀመሪያውን ሥርዓተ መነኮሳት አዘጋጅቷል
፲፫. መነኮሳት ደግነት፣ ፍቅርና ታዛዥነት እንዲኖራቸው...የሚሉት ይገኙበታል፡፡
አንድ ሰው ወደ ገዳማቱ ሲመጣ የሦስት ዓመት አመክሮ ይሰጠውና ጠባዩና ፍላጐቱ ይገመገማል፡፡ ከዚያ በኋላም ብርታቱና ጽናቱ ታይቶ ወደ ማኀበረ መነኰሳቱ ይቀላቀላል፡፡ አባ ጳኩሚስ በዚሁ ዓይነት መንገድ ሥርዓት ሠርተው ሕግ አጽንተው ገዳማትን ካስፋፉና አበምኔት ሁነው 40 ዓመት ካገለገሉ በኋላ ከጌታችን ቃልኪዳን ተቀብለው ለደቀመዛሙርቶቻቸው ቴዎድሮስ ሹመውላቸው በተወለዱ በ56 ዓመታቸው በ346 ዓ.ም በሰላም ዐርፈው ቅድስት ነፍሳቸውን ጌታችን በክብር ተቀብሏታል፡፡
የቅዱሳኑ በረከት በአማላጅነታቸው በምንታመን በሁላችን ላይ ይደርብን አሜን! ይልቁንም እኔን ኀጥኡን ምልጃቸው ሥርየተ ኃጢአትን ያሰጠኝ!!
(ምንጭ፡- ገድለ ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ፣ ገድለ አቡነ ያሳይ-ያለታተመና በገዳሙ የሚገኝ፣ ስንክሳር ዘወርሃ ግንቦት፣ የቅዱሳን ታሪክ፣ መዝገበ ታሪክ)