Tuesday, July 7, 2020

ለእግዚአብሔር ያልንተንበረከከ፣ በአጋንንት የተማረከ ትውልድ

በቀሲስ ሄኖክ ወልደ-ማርያም
አጋንንት በሕይወታችን የሚያደርስብንን ችግር እስክናውቅ እንቸገራለን፣ ውጊያው እስኪገባን ግራ እንጋባለን፣ እውነቱ እስኪገለጥልን እውነቱ ሐሰት ይመስለናል፡፡
ሼር በማድረግ ለወዳጆ አዳርሱ!
ተወዳጆች ሆይ በክፍል ሠላሳ ሦስት የጠንካራ መንፈሳውያን ሰዎችን የአጋንንት ፈተና ተመልክተናል፡፡ በዚህ ክፍል ደግሞ ከላይ የጠቀስኩትን እናያለን፡፡ የቅዱሳን አምላክ ምስጢሩን ይግለጽን፡፡ አሁን ያለነው ትውልድ በአጋንንት ስውር ደባ ስለተማረክን ለእግዚአብሔር ተገዝተን መንበርከክ አልቻልንም፡፡ የእኛ ትውልድ ከፍተኛ የማንነት ቀውስ ውስጥ እና የአጋንንት የተንኮል ውርስ ውስጥ ገብቷል፡፡ ከእግዚብሔር መንገድ ርቀን በራሳችን መንገድ ታንቀን ስለምንሄድ የአጋንንት ሰለባ እየሆንን ነው፡፡
በተለይ ወጣቱ የአጋንንትን የፈተና ስልት ስላላወቀ በሥጋ ፍላጎቱ እንደታነቀ ይኖራል፡፡ የእኛ ትውልድ አዋቂ ነኝ ይላል ግን ማወቁ ከፈተናው ለመላቀቁ ፍንጭ አልሰጠውም፡፡ ዛሬ መቶ መስገድ የዳገት መንገድ የሆነብን ለምንድን ነው? አንድ ሰዓት ቆመን ስናወራ የማይታክተን ለሃያ ደቂና ውዳሴ ማርያም መጸለይ ያቃተን ለምንድን ነው? ጽኑ እምነት አጥተን ሃይማኖትን በእምነት ሳይሆን በሥጋዊ እውቀት የምንመዝነው ለምንድን ነው? ጆሮአችን ቃለ እግዚአብሔር ሳይሆን ሐሜት ለመስማት ለምን ይዳክራል?
ጓደኛችን ለፍቶ ሠርቶ ከሚለወጥ አፈር ከደቼ በልቶ ቢፈጠፈጥ ደስ የሚለን ምቀኝነት ናላችንን ያዞረን ለምንድን ነው? እለት እለት ከአንደበታችን እውነት ሳይሆን ውሸት የሚወጣው፣ ከውሸት አልፈን ቅጥፈት የለመድነው ለምንድን ነው? ወዘተ …
ለእግዚአብሔር መንበርከክ ትተን ለአጋንንት ስንማለር መገለጫችን መንፈሳዊ በረከቶችን መጠራጠር፣ በእምነት መነጽር አለማየት፣ አለማመን፣ መንፈሳዊ ጸጋን በሥጋ እውቀት ማየት፣ ቸልተኛ፣ ግዴለሽነት፣ በሥጋም በነፍስም ተስፋ መቁረጥ፣ በዶግማና በቀኖና መናወጥ፣ በመንፈሳዊ ሕይወት አለማደግ አለመለወጥ ወዘተ ነው፡፡ ይህን ገዳፋ የምናተርፈው በቤሰተባችን የእምነት ደካማነት እና በአጋንንት ተጽዕኖ ነው፡፡ ወዳጆቼ መንፈሳዊ ጸጋ የራቀን የሥጋዊ ዝቅጠት የተጫነን ለእግዚአብሔር ከመንበርከክ ይልቅ እኛን እስከጠቀመን ድረስ ለአጋንንት ስንማረክ ትርፋችን ይህ ነው፡፡
ሱስና መጠጥ ያሠረው ወጣት ለአጋንንት መጫወቻና የአጋንንት ፍላጎት ማስፈጸሚያ ቢሆን አይገርምም፡፡ ይህ ትውልድ አይወቀስም አወቅን ዘመናዊ ሆንን ያሉ በእግዚአብሔር መባረክን ያልወደዱት ወላጆች የዘሩት ውጤት ነው፡፡ ቤተሰብ ልጆችን በሕፃንነታቸው በዕለተ ሰንበተ ቅዱስ ቁርባን ማቁረብ ትተው ወደ መጫወቻ ቦታ ይዘው በመሄዳቸው የእግዚአብሔርን ጸጋ ሳይሆን የዓለምን ዋጋ እንዲያዩ ነው ያደረጉት፡፡ በዕለተ እሑድ ማስቀደስ ሳይሆን መደነስ የለመደ ወጣት የአጋንንት ቁራኛ ቢሆን አይደንቅም፡፡
ትላንት በልጅነቱ እናት ‹‹ቅዳሴ ሂድ›› ስትለው ልጅ የዓይነ ጥላውና የአፍዝዝና የቤተሰብ ዛር ልጁ ላይ እያለቀሰ ‹‹አልሄድም›› ሲል አባት ‹‹ተይው ካልፈለገ አታስገድጅው፣ እንዲ ሆኖ ቢሄድም ምንም አይጠቅመውም›› በማለት ከቅድስናው ደጅ እያራቀ ሲከላከል የነበረው ቤተሰብ በሕፃኑ ላይ የዘራውን የቸልተኝነት፣ የእንቢተኝነት፣ የመብቱ ነው ጥያቄ ሲያድግ በልጁ መከራ ያጭደዋል፡፡
ትላንት ልጆችን የአጋንንት አረም ሲበቅልባቸው አረሙን ከመንቀል፣ መንፈሳዊ ሕይወታቸውን ከመከታተል ይልቅ ለሥጋዊ ደስታቸው እያደላን ሰማያዊ ደስታቸውን እናጨልማለን፡፡ ልጆቻችን በአጋንንት ምትሐታዊ ፍላጎት እየተነዱ በሕፃንነታቸው የአዋቂን ጸያፍ ሥራ ሲሠሩ ‹‹እሷ ፈጣን ናት፣ እሱ ብልጥ ነው፣ የሕፃን አዋቂ ናቸው›› እያልን በሃይማኖት ሳንገራቸው አሳድገን የሕፃንነት የኃጢአት ሕልማቸውን ከመሬት ብቅ እንዳሉ ያሳዩናል፡፡ ያኔ ቤተ እግዚአብሔር ሄደን ብንጮህ አጉልና የማይሰማ ጩኸት ነው፡፡ብቻ በልጅነታቸው ያሳየናቸውን የጥፋት መንገድ፣ አድገው መከራና ፈተና ሲያሳጭዱን እንኖራለን፡፡ እኛ ተባርከን ልጆቻችንን እንዳናስባርክ፣ እኛው ተሰላችተን አጋንንቱ መንገድ ዘግቶብን ለልጆቻችን የእርግማን መናፍስትን እናወርሳቸዋለን፡፡
በቅዳሴው በቁርባኑ፣በቃሉ ስላላስባረክናቸው አጋንንት እንደ ፈጣን ፈረስ እየሰገራቸው ወደ ጥፋት እና ወደ ኃጢአት ሜዳ ይጋልባቸዋል፡፡ ለልጆቻችን ንብረት እንጂ ሃይማኖታችንን ስለ ማውረስ ስላልተጨነቅን ልጆቻችን ንብረት አጥፊ፣ እግዚአብሔር ላይ አሿፊ ትውልድ ይሆናሉ፡፡ ሠርተን ያወረስናቸው እንጂ ተባርከን የሰጠናቸው መንፈሳዊ ስጦታ ስለሌለ አመንዝራና ሱሰኛ ይሆናሉ፡፡ ይህ የእኛ ድክመት ልጆቻችንን የአጋንንት መሥዋዕት እንዲሆኑ በሩን መክፈት ብቻ ሳይሆን የጥፋትንም መንገድ አሳይተናቸዋል፡፡ ዛሬ በየቤታችን የተሸከምናቸው የልጆቻችን ችግሮች መሠረቱ እኛው ነን፡፡ ስለዚህ ስንዴ ካልዘራንበት እርሻ አረማችንን አጭደን በቤታችን ከምረን መኖራችን ግድ ነው፡፡
በኖኅ ዘመን የነበረው አመንዝራ ትውልድ፣ በሎጥ ዘመን የነበረው ግብረ ሰዶማዊው ትውልድ ቤተሰባቸው አረም ሆነው የዘሩት የጥፋት እና የመቅሠፍት ትውልድ በእኛም ዘመን እያየነው ነው፡፡ ስለዚህ ለእግዚአብሔር ያልተንበረከከ ትውልድ፣ ለሰይጣን የጥፋት እንጨት ሆኖ ሲማገድ፣ በኃጢአት ሲነድ ማየት ግድ ብሎናል፡፡
ወላጆች እስኪ ልጆቻችሁ የሚያዩትን የሕፃናት ፊልሞች ተመለከቱ፡ ምዕራባውያን በሕፃናት ፊልም ሰይጣንን እያለማመዷቸው ነው፡፡ በሕፃናት ፊልም ላይ የሚታዩትን ገጸ ባህሪያት ብናያቸው ወጣ ያሉ፣ የሚያስፈሩ፣ የሉሲፈር ገጽታ ያላቸው ወዘተ ናቸው፡፡ የሚጫወቱት ጌሞች ለንቃተ ሕሊና የሚረዱ ሳይሆን አጋንንትን የሚያለማምዱ ናቸው። እነዚህን ምዕራባውያን የራሳቸውን ትውልድ በሚፈልጉት መንገድ አበላሽተዋቸው ሱሰኛ፣ ሺሻ የሚያጨስ፣ በወጣትነቱ የሚገድል የሚደበድብ እናት አባቱም የማያከብር እንዲሆም አድርገዋል፡፡ አሁን የእኛ ነው የቀራቸው እኛንም ልጆቻችንን በፊልማቸው በአሻንጉሊት ትዕይንታቸው እያደነዘዙን እያፈዘዙን ነው፡፡
እባካችሁ ጨቅላ ሕፃናቶቻችንን በልጅነታቸው የአምልኮ፣የጾም፣የጸሎት፣የስግደት ሥርዓት እያስተማርን አሳድገን ከአጋንንት ምርኮ እንታደጋቸው፡፡
‹‹ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሳ ጠፍቶአል›› ት.ሆሴ 4÷6
‹‹ከትውልዱ ማን አስተዋለ?›› ት.ኢሳ 53÷8
ክፍል ሠላሳ አምስት
በጸሎት የራቀን ዲያብስ፣ ወደ እኛ መመለስ
https://www.facebook.com/memehirhenok

No comments:

Post a Comment