በቀሲስ ሄኖክ ወልደ-ማርያም
አጋንንት በሕይወታችን የሚያደርስብንን ችግር እስክናውቅ እንቸገራለን፣ ውጊያው እስኪገባን ግራ እንጋባለን፣ እውነቱ እስኪገለጥልን እውነቱ ሐሰት ይመስለናል፡፡
ሼር በማድረግ ለወዳጆ አዳርሱ!
ተወዳጆች ሆይ በክፍል ሠላሳ የአየር አጋንንት እና የብኩንነት ሕይወትን አይተናል፡፡ በዚህ ክፍል ደግሞ የአየር አጋንንት እንዴት የተረጋጋ መንፈስ እንዳይኖረን እንደሚያደርገን እናያለን፡፡ ወዳጆቼ በዚህ ዘመን የተረጋጋ ሰው የታደለ ነው፡፡ የአየር አጋንነት አንዱ የፈተናው ስልት መረጋጋትን ማሳጣት ነው፡፡ የአየር አጋንንት ሲፈትነን አንድ ቦታ አርፈን አንቀመጥም፣ እንቅበዘበዛለን፣ እንኳን አካላችን ምላሳችንም አይረጋጋም፣ ሰው ሲናገረን ስደበው ተናገረው እያለ ይገፋፋናል፡፡ በተለይ ቤተ ክርስቲያን ስንገባ ውስጣችን ያለው ዓይነ ጥላ ከአየር አጋንንት ጋር በማበር ተረጋግተን እንዳናስቀድስ፣ እንዳንጸልይ፣ እንዳንማር የማስጨነቅ ሥራ በመሥራት ከቤተ ክርስቲያን በሆነ ምክንያት በማሳመን ‹‹ውጣ ውጣ›› ይለናል፡፡ የውሳኔ ሰው መሆን አንችልም፡፡ አንድ ነገር ብንወስንም ልክ ያልሆነ ውሳኔ ነው የምንወስነው፡፡ በስሕተቱ እንጸጸታለን፡፡ በዚህ የተነሳ አጋንንቱ በራስ የመተማመናችንን መንፈስ ያሳጣናል፡፡
የአየር አጋንንት ያለ መረጋጋት ስሜት ሲያሳድርብን ፊታችን የተረበሸ ይመስላል፣ ግራ ይገባናል፣ የደስተኝነት ስሜት አይነበብብንም፣ ያኮረፈ የተቆጣ ፊት እንዲኖር ያደርገናል፡፡ ብዙዎችን የአየር አጋንንት እየፈተናቸው በዓመት አንዴ የስቅለት ስግደት ቀን ጨንቋቸው፣ ሥርዓቱ አላልቅ ብሏቸው ከቤተ ክርስቲያን የሚወጡ አሉ፡፡ ቅዳሴ ለማቋረጥ የሚሞክሩና የሚያቋርጡ አሉ፡፡
ወዳጂቼ የአየር አጋንንተት በጸሎት ጊዜ ሲፈትነን የምናየው ምልክት አሉ፡፡ አንደኛ ጸሎቱ አልገፋ አላልቅ ይለናል፡፡ ሁለተኛ ጸሎቱ ስልችት ይለናል፡፡ ሦስተኛ ልባችንን ሕሊናችንነ ሰውሮ ከተጣላነው ሰው ጋር አንባ ጓሮ አስገጥሞን የጸሎት መጽሐፋችን ገጽ ያስቆጥረናል፡፡ አራተኛ ጸሎት ይዘን መረጋጋት ስንችል እንቁነጠነጣለን፡፡ አምስተኛ ወገባችን፣ ጉልበታችን እግራችን ይብረከረካል መቆም ያቅተናል፡፡ ስድስተኛ ጸሎት እያደረግን ኩንታል እንደተሸከመ ሰው ሰውነታችን ሁለ መናችን ይከብደናል፡፡ ሰባተኛ ጸሎቱ ባለበት ሐሳባችን ልባችን አይኖርም፡፡ ስምንተኛ በጸሎት ሰዓት እግዚአብሔር ፊት ምስጋናችንን አስረስቶ ጸሎታችንን ጭቅጭቅ ያደርግብናል፡፡ ለምሳሌ ‹‹እግዚአብሔር ምን አደረገልህ? ያንቺ ጸሎት ምን አመጣ? እነ እከሌ ጠንቋይ ቤት እየሄዱ ሕይወታቸው ተለወጠ አንቺ ግን እግዚአብሔር ይዘሽ ቤተ ክርስትያን ተመላልሰሽ ይኸው ባዶሽን አለሽ፣ ሥራ የለሽ፣ ትዳር የለሽ፣ ወይ ገዳም አልገባሽ ወይ ሞተሸ አልተገላገልሽ ወዘተ›› እያለ መጸለያችን ሳይታወቀን ጸሎቱን እንጨርሳለን፡፡ ስምንተኛ ሰውነታችን ላይ በተለይ ጀርባችን ላይ የሚርመሰመስ የሚሄድ ስሜት ይሰማናል። ዘጠነኛ ጸልት ይዘን ከፍተኛ የማናውቀው ፍርሃት ይሰማናል። አስረኛ ከፊት ለፊታችን ከጀርባችን ከጉናችን ውልብ ስልብ የሚል የማናውቀው ምስል ይታየናል: ሰው አብሮን የቆመ ሸከክ ክብድ ይለናል።
ለመቀበል የዘገየነው፣ የረሳነው ያበደርነው ገንዘብ ሁሌም ትዝ የሚለን ጸሎት ላይ ነው፡፡ ቀን ስልክ እደውልለታለሁ ያልነው ሰው ትዝ የሚለን ጸሎት ስንጀምር ነው፡፡ ብቻ የረሳነውን ነገር የምናስታውሰው፣ አደርገዋለሁ ብለን ጊዜ ያጣንበት ነገር የሚታወሰን ጸሎት ላይ ነው፡፡ የሚገርመው ቁጭ ብለን የማናስበው የሥራ እቅድ ጸሎት ላይ ሐሳቡ የሚመጣልን፡፡ ነጋዴ ከሆንን ትርፉ ወለል ብሎ የሚታየን፣ ኪሳራውም የሚታወቀን ጸሎት ላይ ነው፡፡ ወዳጆቼ ይህን ሁሉ ሐሳብ የአየር አጋንንት በጸሎት ጊዜ እያመጣ የሚጭንብን የተረጋጋ ጸሎት እና መንፈስ እንዳይኖረን ለማድረግ ነው፡፡ አጅግ የሚገርመው የመንፈስ እርጋታ እና የነፍስ እፎይታ የምናገኝበት ቤተ ክርስትያን ሄደን የባሰ የምንጨነቅ፣ ስሜታችን ዝብርቅርቅ የሚልብን አለን፡፡ ይህ ሁሉ የእሱ ውጤት ነው፡፡
መረጋጋትን ያጣው የአየር አጋንንቱ እኛን ያለመረጋጋት ስሜት ውስጥ ይከተናል፡፡ እኛን እንዲህ ያድርገን እንጂ መነኮሳትን ከባዕታቸው ከገዳማቸው ሰላም በማሳጣት ያለመረጋጋት ስሜት ወስጥ እየከተታቸው እየረበሻቸው ክፉኛ ይፈትናቸዋል፡፡ እነሱም የአየር አጋንንቱን ያለመረጋጋት ፈተና መቋቋም ሲያቅታቸው በምክንያት ከገዳማቸው ይወጣሉ፡፡
የአየር አጋንንት ሰውን በማንከራተት የተጠመደ ነው፡፡ መነኮሳትን ንቀውና ጥለው የመጡትን ዓለም እንደ ገነት በማሳየት፣ ከገዳም ይልቅ የጽድቅ ሥራ በዓለም እንዳለ በማሳሰብ፣ ከገቡበት ገዳም በማስወጣት በዓለም እንዲንከራተቱ ያደርጋቸዋል፡፡ አጋንንቱ በፈተና ምክንያት ዓለም ውስጥ ከከተታቸው በኋላ ዓለማዊ ሕይወትን በማለማመድ፣ በቁሳዊ ነገር በመጥመድ በተንኮሉ መዳፍ ያስገባቸዋል፡፡ በገዳም ያለውን ፈተና ሳይቋቋሙ አጋንንቱ በሰፈረበት ዓለም ፈተናውን የሚቋቋሙት ምናልባት በእግዚአብሔር ፈቃድ በዓለም እንዲኖሩ የተፈቀደላቸው ብቻ ናቸው፡፡ የአየር አጋንንት ሰፍሮብን ብዙ ነገር ካለማመደን በኋላ ወደ ቀደመ ሕይወታችን ለመመለስ እጅጉን እንቸገራለን፡፡ እያንከራተተ ያኖረናል፡፡
አንድ መንፈሳዊ ሰው የተረጋጋ መንፈስ ከሌለው አንኳን ከሰው ከእግዚአብሔር ጋር አይስማማም፡፡ መረጋጋት የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ የመላበስ ምልክት ነው፡፡ በመንፈሳዊ ሕይወት ያለ መረጋጋት ካለ ለስሕተት እና ለኃጢአት እጅጉን የተጋለጥን ነን፡፡ ስለዚህ በሕይወታችን ያለመረጋጋት ክሥተት ከታየብን ቆም ብለን ራሳችንን መቃኘት፣ወደ ሰማይ አምላክ መመልከት ያስፈልገናል፡፡ የመረጋጋት መንፈስ ልግስና ከሰማይ አምላክ ነውና፡፡
‹‹ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሳ ጠፍቶአል›› ት.ሆሴ 4÷6
‹‹ከትውልዱ ማን አስተዋለ?›› ት.ኢሳ 53÷8
ክፍል ሠላሳ ሁለት
በአየር አጋንንት እና በሌሎች ሥራችንና ዕቅዳችን ይበላሻል
/ሩቅ አሳቢዎች ቅርብ አዳሪዎች፣አመድ አፋሾች/
ይቀጥላል …..
ሰኔ 8-10-12 ዓ.ም
አዲስ አበባ
No comments:
Post a Comment