Tuesday, August 4, 2020

የአየር አጋንንት እና የብኩንነት ሕይወት

በቀሲስ ሄኖክ ወልደ-ማርያም
አጋንንት በሕይወታችን የሚያደርስብንን ችግር እስክናውቅ እንቸገራለን፣ ውጊያው እስኪገባን ግራ እንጋባለን፣ እውነቱ እስኪገለጥልን እውነቱ ሐሰት ይመስለናል፡፡
ሼር በማድረግ ለወዳጆ አዳርሱ!
ተወዳጆች ሆይ በክፍል ሃያ ዘጠኝ የአየር አጋንት እና የቤተሰብ ዛር እራሳችንን እንድናጠፋ እንደሚያደርገን አይተናል፡፡ በዚህ ክፍል ደግሞ አጋንንት እንዴት በሕይወታችን ብኩን እንደሚያደርገን እናያለን፡፡ የቅዱሳን አምላክ ምስጢሩን ይግለጽልን፡፡ ወዳጆቼ በሰፊው እንዳየነው የአየር አጋንንት በተንኮል የተካነ ስለሆነ በሕይወታችን ብኩን እንድንሆን ያደርገናል፡፡  አጋንንት ቀድሞ በተሰጠው ጸጋ ስላልተጠቀመ እኛም በሕይወታችን እግዚአብሔር በሰጠን ጸጋ መክሊት እንዳንጠቀም ያደርገናል ያባክነናል፡፡ ሕይወታችን ብኩን፣ ትዳራችን ብኩን፣ ገንዘባችን ብኩን፣ የጨበጥነው እንደ ጉም እየተነነ፣ የያዝነው እየመነመነ ባዶ ያደርገናል፡፡ የአየር አጋንንት ከሰላቢ መንፈስ ጋር በማበር የምናገኘውን፣ የያዝነውን ይስልብብናል፡፡
ወዳጆቼ ስለ ብኩንነት ካነሳን አጋንንት በተለያየ እና በማናውቀው መንገድ ብኩን ያደርገናል፡፡ አንዳንዶቻችንን ለዘመናት በመጠንቀቅ እና በመጠበቅ ይዘን የቆየነውን ለተክሊል ክብር ያሰብነውን ድንግልና በማባከን በዝሙት ለክፎን የማንወጣበት ሕይወት ውስጥ ከቶ ያባክነናል፡፡ ሌሎቻችንን ገዳማት፣ አብያተ ክርስትያናት በመሄድ፣ በመጸለይ፣ በመመጽወት ያገኘነውን ጸጋ በዝሙት ጥሎን ጸጋችንን አስጥሎን የመንፈሳዊ ብኩን ያደርገናል፡፡ የበረቱትን ቅዱስ ቁርባን በመቀበል ያገኙትን መለኮታዊ ጸጋ በሐሜት፣ በምቀኝነት ጸጋቸውን አስጥሎ የቆራቢ ወረኛ አድርጎ ብኩን ያደርጋቸዋል፡፡ ወጥተው ወርደው፣ ሌት ተቀን እንቅል አጥተው ሠርተው ያገኙትን ገንዘብ በመጠጥ፣ በአልባሌ ውሎ፣ በመልካም ጓደኝነት አስመስሎ ገንዘባቸውንም ሕይወታቸውንም ብኩን ያደርጋል፡፡ ብቻ የአጋንንትን ተንኮሉን፣ ውጊያውን ካላወቅን በሥጋም በነፍስም ብኩን እንሆናለን፡፡ 
ወዳጆቼ አንዳንዴ በኪሳችን፣ በቦርሳችን ያያዝነው ገንዘብ የረባ ነገር ሳንገዛበት፣ ምኑንም ሳናውቅ ገንዘቡ የለም፡፡ አንዳንድ ሞኞች ‹‹አሁን አጋንንት ገንዘብ የሚሰልበው እንደ ሰው አይጠቀምበት፣ምን ይሠራለታል›› እያሉ እየተሰለቡ ይሟገታሉ፡፡ ወዳጄ አጋንንት ኑሮህን ለማቃወስ፣ በገንዘብህ ያሰብክበት ቦታ እንዳትደርስ ገንዘብህን ይሰልበዋል፡፡ ያኔ በማታውቀው ስልት ገንዘብህ ከእጅህ ሲወጣ፣ የመደናገጥ ጣጣ ይመጣል፡፡ አሥራት ያልወጣበት ገንዘብ፣ ጸሎት የሌለበት ሕይወት፣ የእግዚብሔር ረድኤት ስለማይኖረው የአጋንንት መጫወቻ ነው የሚሆነው፡፡
በተለይ አንዳች ጥሩ ነገር ካለን፣ ባለን ለመለወጥ ስንጥር፣ አጋንንት የማጨናገፊያ ድንበር እየሠራ የሙሉ ጎዶሎ ያደርገናል፡፡ ያለንን ይነጥቀናል፣ ያገኘነውን ያባክንብናል በዚህም ሕይወት ለእኛ የቀን ጨለማ ይሆናል፡፡ ግን አሁንም በመባከን ሕይወት ውስጥ ካለን ወደ እግዚአብሔር በንስሐ ተመልሰን፣ በጸሎት የምንማልል ከሆነ እግዚአብሔር በአጋንንት የተንኮል ሴራ የባከነ ሕይወታችንን በመቀየር አዲስ የሕይወት ምዕራፍን ይከፍትልናል፡፡
ብዙዎቻችን በአንድም በሌላም ብኩን ሆነናል፡፡ የእውቀት ብኩን፣ የማስተዋል ብኩን፣ የጊዜ ብኩን፣ የቸርነት ብኩን፣ የአዛኝነት ብኩን፣ የዕድሜ ብኩን፣ የበረከት ብኩን፣ የፍቅር ብኩን፣ የስኬት ብኩን፣ የትዕግሥት ብኩን፣ የሥራ ብኩን፣ ወዘተ ሆነናል፡፡ አጋንንት በተለያየ የፈተና ስልት ሕይወታችንን ሲያባክን ከመንቃት እና ወደ እግዚአብሔር ከመጠጋት ይልቅ ሥጋዊ አስተሳሰብ ተጭኖን በራሳችን ላይ ያለ ቀስቃሽ ተኝተናል፡፡
ጌታችን ዛሬ የምንኖረውን የብኩንነት ሕይወት በሉቃስ ወንጌል ላይ በምሳሌ አስተምሮናል፡፡ ከወላጅ አባቱ ‹‹ገንዘቤን አካፍለኝ›› ብሎ የተለየው ወጣት ገንዘቡን ይዞ ወደማያውቀው ሀገር ተሰዶ በዚያም ገንዘቡን በትኖ ኖረ፡፡ ገንዘቡ ሲያልቅ የሚበላው ቢያጣ ከአንዱ ጋር ተዳበለና የእርያ ጠባቂ ሆነ፡፡ ከረሃቡ ጽናት የተነሳ የእሪያዎችን አሰር ለመብላት ተመኘ፡፡ ግን እሪያዎች የሚበሉትን አሰር የሚሰጠው ጠፋ፡፡ በመጨረሻም ወደ ልቡ ተመልሶ፣ በስሕተቱ አልቅሶ ወደ አባቱ ቤት በክብር ተመልሷል፡፡ /ሉቃ 15÷11-32/
እኛም ከእግዚብሔር ጋር ስንለይ ነው ከአጋንንት ጋር የምንዳበለው፡፡ ከእግዚአብሔር ስንለይ፣ የአጋንንት ሲሳይ እንሆናለን፡፡ አጋንንቱም እንደ ጠፋው ልጅ የእኛንም ውድ ሕይወት እያባከነ፣ ጸጋችንን በኃጢአት እያስበተነ ብኩን ያደርገናል፡፡ የጠፋው ልጅ ወደ ልቡ ተመልሶ ወደ አባቱ ቤት በመምጣቱ ከቀድሞው የተሻለ ሽልማት እና ሕይወት አግኝቷል፡፡
እኛም ከመባከን ሕይወት ወጥተን፣ ወደ አባታችን ወደ እግዚአብሔር ከተመለስን አዲስ የበረከት ሕይወት ይኖረናል፡፡ የጠፋው ልጅ የአባቱን ቤት ማዕድ ንቆ፣ የእሪያን አሰር ለመብላት ናፍቆ ነበር፡፡ ወደ አባቱ ቤት ሲመለስ ግን ፍሪዳ አርዶለት ደግሶ ነው የተቀበለው፡፡ እኛም የእግዚአብሔርን የበረከት ሕይወት ረግጠን፣ ንቀን የአጋንንትን የመከራ እንጀራ ነው የበላነው፡፡ ግን ወደ እግዚአብሔር ከተመለስን ከመለኮት ማዕድ ከቅዱስ ቁርባን ተቋድሰን፣ በጸጋው ተሸልመን በክብር እንኖራለን፡፡
ስለዚህ አጋንንት የነጠቀንን ሊመልስልን የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ አጋንንት የወሰደብንን ሊሰጠን የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር መለየት ልዩ ብኩንነት ነው፡፡ እኛ ብኩን የሆነው አጋንንት ሲጠናወተን ሳይሆን እግዚአብሔር ሲለየን ነው፡፡ ከእግዚብሔር መለየት ብኩንነት ብቻ ሳይሆን የቁም ሞት ነው፡፡ እኛ በቁማችን ለአጋንንቱ ሞተንለት ነው እርሱ የሚገድለን፡፡ ስለዚህ ከሕይወት ብኩንነት ለመውጣት ወደ እግዚአብሔር መጠጋት ያስፈልጋል፡፡
‹‹ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሳ ጠፍቶአል›› ት.ሆሴ 4÷6
‹‹ከትውልዱ ማን አስተዋለ?›› ት.ኢሳ 53÷8
ክፍል ሠላሳ አንድ
የአየር አጋንንት የተረጋጋ መንፈስ እንዳይኖረን ያደርጋል
ይቀጥላል ……
ሰኔ 8-10-12 ዓ.ም
አዲስ አበባ

No comments:

Post a Comment