Tuesday, August 11, 2020

የአየር አጋንንት እና የቤተሰብ ዛር ራሳችንን እንድናጠፋ ያደርገናል

በቀሲስ ሄኖክ ወልደ-ማርያም
አጋንንት በሕይወታችን የሚያደርስብንን ችግር እስክናውቅ እንቸገራለን፣ ውጊያው እስኪገባን ግራ እንጋባለን፣ እውነቱ እስኪገለጥልን እውነቱ ሐሰት ይመስለናል፡፡
ሼር በማድረግ ለወዳጆ አዳርሱ!
ተወዳጆች ሆይ ዛሬ በራሴ በግል ጉዳይ በመዘግየቴ ይቅርታ እጠይቃለሁ። በክፍል ሃያ ስምንት የአየር አጋንንት በአጽዋማት ወቅት እንዴት ባለ ፈተና እንደሚፈትነን አይተናል፡፡ በዚህ ክፍል ደግሞ የአየር አጋንንት እና ግብር የለመደ የቤተሰብ ዛር እራሳችንን እንዴት ለሞት እንደሚዳርገን እናያለን፡፡ የቅዱሳን አምላክ ምስጢሩን ይግለጽልን፡፡ ወዳጆቼ የአየር አጋንንት እና የቤተሰብ ዛር የመጨረሻው ግባቸው እኛን የሰው ልጆች አሰቃይቶ መግደል ነው፡፡ ይህንን ተንኮሉን በብዙዎች ላይ እየተገበረ ነው፡፡ በዓለማችን ላይ ራስን የማጥፋት ችግር እየባሰ መጥቷል፡፡ ሞልቶናል ተርፎናል የሚሉት ምዕራባውያን ራስን የማጥፋት ችግር ግራ እያጋባቸው ይገኛል፡፡
ምዕራባውያን ምንም ሳይቸግረው ራሱን በሚያጠፋ ዜጋቸው ግራ እየተጋቡ ነው፡፡ ምክንያቱም በራሱ ፈቃድ ለመሞት ምክንያት የሌለው ሰው ራሱን እያጠፋ ስለመጣ ነው፡፡ ይህ ድርጊት እኛም ሀገር እየተለመደና ለቤተሰብ የእግር እሳት እየሆነ መጥቷል፡፡ ብዙዎቻችንም በተለይ የምናውቀው፣ በደንብ የምንቀርበው ሰው ራሱን ካጠፋ ‹‹እንዴት ራሱን ያጠፋል? ምን ነካው?›› እያልን ሟች ላይ እንበይናለን፡፡
ግን ራሱን ካጠፋው ሰውዬ ጀርባ ያለውን አጋንንት በመንፈሳዊ ዓይን ካየን ሟች የአየር አጋንንት እና የቤተሰቡ ግብር የቀረበት ዛር የሞት ሰለባ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ በሰፊው እንዳየነው የአየር አጋንንት አእምሮንና ልቦናን ተቆጣጥሮ ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው ‹‹የማልፈልገውን አደርጋለሁ፣ ይህን የማደርገው እኔ ሳልሆን በእኔ ያለ ኃጢአት ነው›› ብሎ የገለጠው አጋንንት ሰው ልብና እና አእምሮ ውስጥ በመግባት ልቡን ሰውሮት ራሱን እንዲያጠፋ ያደርገዋል፡፡
ማንም በራሱ ላይ ጨክኖ ራሱን ለማጥፋት የሚሞክር የለም፡፡ ግን በተፈጠረብን ችግር፣ ባጋጠመን አስቸጋሪ ነገር ውስጣችን የገባው የአየር አጋንንት እያበሳጨን፣ ራሳችንን መቆጣጠር እያቃተን፣ እያወቅን ግን ልቦናችንን ሰውሮ ራሳችንን በገመድ አልያም በመድኃኒት፣ በመርዝ: ከፎቅ ላይ በመወርወር እና በሌሎች ዘዴዎች ራሳችንን እንድናጠፋ ያደርገናል፡፡ የዘንድሮ አጋንንት ትንሽ ለየት ያለ ይመስለኛል፡፡ በፊት መርዝ በማጠጣት እና በገመድ ነበር የሚገድለው ዘንድሮ ከሳይንስ ተባብሮ ሰዎችን በቀላሉ እራሳቸውን የሚያጠፉበትን በማስተማር የእጅ ደም ስርን በማስተልተል ይገድላል፡፡ በዚህ ስልት ስንቱ ወጣት ለሞት በቅቷል፡፡
ወዳጆቼ መንፈስ ቅዱስ የራቀው፣ አጋንንት የቀረበው ሰው ራሱን ያጠፋል፡፡ እኛ ደግሞ የአጋንንቱ የሞት ደባ ስለማይታየን ሟቹን ተጠያቂ እናደርጋለን፡፡ ይህ ብቻ አይደለም የአየር አጋንንት ልቦናችንንና ሕሊናችንን ከተቆጣጠረ መኪና ሥር በመክተት፣ ከባሕር፣ ገደል በመክተት፣ ራሳችንን በመሣሪያ በመምታት እንድናጠፋ ያደርገናል፡፡ ዛሬ ስንቱ በአየር አጋንንት ግፊት ራሳቸውን እያጠፉ አጋንንቱ ሳይሆን ሟቹ እየተወቀሰ ይኖራል፡፡ የአየር አጋንንት ውስጣችን ከገባ ምንም ሊያደርገን ስለሚችል በመንፈሳዊ ተጋድሎ በመበርታት ልናርቀው እና እኛም ልንርቀው ይገባል፡፡
ወዳጆቼ ከላይ እንደጠቀስኩት በተለይ ግብር ለምሳሌ ደም፣ እርድ የለመደ የቤተሰብ ዛር ካለ ቤተሰቦቻችን የዛሩን ግብር ትተው፣ ንስሐ ገብተው ሲተዉት አጋንንቱ ልጆች እና የልጅ ልጆች ላይ በመደር እርስ በእርስ በማባለት፣ ደም በማፋሰስ፣ የሰውንም ደም በማፍሰስ እና እራሳቸውን እንዲያጠፉ ያደርጋቸዋል፡፡ አጋንንት ስንቱን በተኙበት በማነቅ ለሞት ዳርጓል፡፡ ቡና እየጠቱ አጋንንት አንቋቸው የሞቱ አሉ፡፡ አንዳንድ የዋሆች ‹‹አጋንንት የመግደል ሥልጣን የለውም፣ እኔን መፈተን እንጂ መግደል አይችልም›› ይላሉ፡፡ አጋንንት በጾም፣በጸሎት በስግደት ተጠምዶ፣ ሕገ እግዚአብሔር ወዶ እና ፈቅዶ የሚፈጽም ከሆነ በእውነትም ሥልጣን የለውም፡፡
ግን ያለ ጾም፣ ጸሎት፣ ስግደት እና ያለ ትሩፋት የሚኖር ከሆነ አይደለም በሥጋው መግደል፣ በነፍሱ ሲዖል መዶል ይችላል፡፡ ሰው በቀጥታ ከእግዚአብሔር ሲርቅ በተዘዋዋሪ ከአጋንንት በመጣበቅ ነው የሚኖረው፡፡ ትዝ ካላችሁ ጌታችን እኛን ለማዳን በቀራንዮ በተሰቀለ ጊዜ የማያፍረው ሰይጣን በሕማም፣ በስቃይ እና በሞት አፋፍ ያለውን ፈጣሪ ፍጡር መስሎት ቀረብ ብሎ ‹‹ሥጋውን ከነፍሱ ለይቼ፣ ሥጋውን በመቃብር ነፍሱ በሲዖል ገዝቼ እኖራለሁ›› ብሎ ቀርቦ ውርደት ተከናንቦ ሄዷል፡፡ ልብ በሉ በፈተና፣ በችግር፣ በቤተሰብ ሐዘን፣ በማጣት ወዘተ በድንገት እራሳችሁን አጥፉ አጥፉ እያለ ሞት ሞት ከሸተታችሁ ቆም ብላችሁ አስቡ፡፡ እንዲህ ዓይነት ክፉ የሞት ሐሳብ የእናንተ ሳይሆን ሕይወታችሁን ሳይሆን ሞታችሁን የሚፈልገው የአጋንንት ክፉ ሐሳብ እንደሆነ አውቃችሁ ተጠንቀቁ ንቁ፡፡
ወዳጆቼ በተረታችን ‹‹የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም›› አይደል የምንለው፡፡ ተስፋ የቆረጠ፣ የእኛን ነፍስ በሲዖል እየዋጠ የሚኖረው አጋንንት እኛን ለመግደል እና ለማጥፋት የሚቦዝን ስላልሆነ በጸሎት መበርታት እና መትጋት እንኳን ከአጋንንት ከሲዖል ሞት ያድነናል፡፡
‹‹ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሳ ጠፍቶአል›› ት.ሆሴ 4÷6
‹‹ከትውልዱ ማን አስተዋለ?›› ት.ኢሳ 53÷8
ክፍል ሠላሳ
የአየር አጋንንት እና የብኩንነት ሕይወት
ይቀጥላል …..
ሰኔ 7-10-12
አዲስ አበባ

No comments:

Post a Comment