Tuesday, August 18, 2020

የአየር አጋንንት ፈተና በአጽዋማት ወቅት

/ያላወቅነው ያልነቃነው ግን ብዙ በረከት ያጣንበት/
በቀሲስ ሄኖክ ወልደ-ማርያም
አጋንንት በሕይወታችን የሚያደርስብንን ችግር እስክናውቅ እንቸገራለን፣ ውጊያው እስኪገባን ግራ እንጋባለን፣ እውነቱ እስኪገለጥልን እውነቱ ሐሰት ይመስለናል፡፡
ሼር በማድረግ ለወዳጆ አዳርሱ!
ተወዳጆች ሆይ በክፍል ሃያ ሰባት የአየር አጋንንት በልባችን አድሮ እግዚአብሔርን፣ እመቤታችንን እና ቅዱሳንን እንዴት እንደሚሳደብ አይተናል፡፡ በዚህ ክፍል ደግሞ የአየር አጋንንት በአጽዋማት ወቅት እንደሚፈትነን እናያለን፡፡ የቅዱሳን አምላክ ምስጢሩን ይግለጽልን፡፡
ወዳጆቼ የአየር አጋንንት ከመቼውም በበለጠ በተንኮል ሥራ የሚጠመደው በአጽዋማት ወቅት ነው፡፡ እንደ ዓቢይ ፣ ገና፣ ሐዋርያት እና ፍልሰታ ያሉ የአዋጅ አጽዋማት ላይ ከመቼውም በበለጠ በጸሎት ጠንከር ስለምንል አጋንንቱ በፈተና ጠንከር ብሎ ይመጣል፡፡ የአየር አጋንንት በአዋጅ አጽዋማት ወቅት ቤተ ክርስቲያን ሄደን እንዳንጸልይ በማሳነፍ፣ በቤታችን እንዳንጸልይ በማይረባ ምክንያት በማደናቀፍ፣ ጸሎታችንን በማስታጎል የጸሎት በረከታችንን ያሳጣናል፡፡ እንኳን እኛ በገዳም ያሉ አባቶችም የአጋንንት ፈተና የሚበዛባቸው በአጽዋማት ወቅት ነው፡፡
አንዳንዶቻችን የአዋጅ ጾም ሲመጣ በፉከራ ‹‹ይህንን ጾምማ በጾም በጸሎት ነው የማሳልፈው›› ብለን ለራሳችን ቃል እንገባለን፡፡ ግን እንኳን የገባነውን ልንተገብር የባሰ ስንፍናና ኃጢአት ውስጥ ተዘፍቀን ያለ ሰዓት በጠዋት ከጾም እስከ ፍስክ ያሉትን ምግቦች ስልቅጥ አድርገን እንበላለን። መጠጥ የምንጠጣውም ‹‹ይሄን ጾምማ መጠጥ የደረሰበት አልደርስም›› እንላለን፡፡ ከቀናት በኋላ እዛው እንገኛለን፡፡ በሥጋ ፍትወት በዝሙት የምንፈተነውም ‹‹ይሄን ጾም ከዝሙት ርቂ እራሴን ጠብቂ አሳልፋለሁ›› እንላለን ግን ከበፊት የበለጠ በዝሙት ተፈትነን እንወድቃለን፡፡
በተለያዩ ፈተናዎች ጸሎት የተውን ‹‹ጾሙ ብቻ ይግባ ወዳሴ ማርያሙ፣ አርጋኖኑ፣ ሰይፈ ሥላሴው፣ ዳዊቱ ወዘተ አይቀረኝም ተግቼ ጸልያሁ›› እንላለን፡፡ ግን እንኳን ውዳሴ ማርያም፣ ዳዊት ቀርቆ አንድ አቡነ ዘበሰማያት መጸልይ አቅቶች ማታ ስንፍና ተጭኖን ሌሊት እንቅልፍ ጥሎያ ያለ ጸሎት እንውላለን እናድራለን፡፡ ስግደት ለመስገድ በዓለ ሃምሳ ከለከለኝ ይምጣልኝ ጾሙ ብለን የፎከርነው ጾሙ ሲመጣ ስንፍናን እንደ ባርኔጣ እራሳችን ላይ ጭነን፣ የወገብ፣ የጉልበት ችግር አለብኝ ብለን እንኳን የትሩፋት፣ የተጋድሎ ስግደት ልንሰግድ ቀርቶ ጸሎት ከመጀመራችን በፊት ሦስት ጊዜ ለሥላሴ የአምልኮ ስግደት መስገድ የሚያቅተን እንሆናለን፡፡
ንስሐ ለመግባት የስንት ዓመት ቀጠሮ ይዘን ጾሙን ስንጠባበቅ ጾሙ ሲመጣ እንኳን ንስሐ ለንገባ በኃጢአት ተዘፍቀን ግራ ስንጋባ ጾሙ ያልፈናል፡፡ ወሬ ለማውራት ሁለት ሰዓት ብንቆም ጉልበቴን ወገቤን የማንል ጸሎት፣ ስግደት ስንጀምር ሳይሆን ገና ስናስብ እንደ አዛውንት በሕመም መዓት እንያዛለን፡፡ ሌሊት ለጸሎት እነሳለሁ ብለን ማታ በስልካችን አላርም ሞልተን ግን እንደ እከ ለሽሽሽሽ ብለን ተኝተን እኛ ሳንነሳ ነግቶ ወፎ ጩኸት አሰምቶ ይቀድመናል። ወዳጆቼ  ይህ የሚያሳየን በአጽዋማት ወቅት ከፍተኛ የአጋንንት ውጊያ እንዳለብን ነው፡፡ በጾም ወቅት ካሰብነው በባሰ አንዳች መንፈሳዊ ነገር ሳንተገብር ጾሙ ያልፈናል፡፡ እኛም በእጃችን ባለው ጾም ሳንጠቀም ወደ ፊት በሚመጣው ባልጨበጥነው ጾም ተስፋ እናደርጋለን፡፡
አጋንንት የበለጠ የኃጢአት ሕይወት ውስጥ ከትቶ፣ እኛን ከእግዚአብሔር ጋር አለያይቶ ለማስቀርት በአጽዋማት ወቅት በዝሙት፣ በስካር፣ በሱስ ወዘተ ይፈትነናል፡፡ ባለ ትዳሮችንም ከጾሙ በረከት ለማራቅ፣ በፍትወት በማስጨነቅ ይፈትናቸዋል ይጥላቸዋል፡፡ በአዋጅ የታዘዝነውን ጾም በርትተን እንዳንጾም ጥውልውል የሚያደርግ የረሃብ ስሜት እና የተለያየ ሕመም እንዲሰማን በማድረግ ያለ ሰዓት እንድንበላ ብሎም ጾሙን አፍርሰን የፍስግ እንድንበላ ያደርገናል፡፡
አንዳንዶች ሕመማቸው የሚቀሰቀሰው፣ ጨጓራቸውን የሚያማቸው በአጽዋማት ወቅት ነው፡፡ እነዚህ ሕመሞች ለአጋንንቱ ሽፋን ስለሚሆኑ ማንም ጾም በመጣ ቁጥር የሚነሳበትን ሕመም የአጋንንት ፈተና ነው ብሎ ለመቀበል ይቸገራል፡፡ ስለዚህ አጋንንት በደዊያት እየተመሰለ፣በሕመም እያታለለ እንደሚጫወትብን ማሰብ አልቻልንም፡፡ በልቶ እንጂ ጾሞ የሞተ ሰው ስለሌለ ከነችግራችን ልንጾም ይገባል፡፡
ጾም በመጣ ቁጥር አጋንንት የውስጥ ሕመም የሚቀሰቅስብን አንደኛ አጋንንት ጾም ስለማይወድ የእሱን ባሕርይ በቀላሉ ከእኛ ጋር ለማዋሐድ ይመቸዋል፡፡ ሁለተኛ ጾም እንዳንለምድ ያደርገናል፡፡ ሦስተኛ የማንጾም ከሆነ እንበላለን እንጠጣለን ስለዚህ በሥጋ ፍትወት በቀላሉ ለመፈተን ይመቸዋል፡፡ አራተኛ ጾም እግዚአብሔርን የምናገለግልበት በረከት ስለሆነ ከጾም አገልግሎት ለማራቅ ይመቸዋል፡፡ ነቢይት ሐና እግዚአብሔርን በጾም በጸሎት ሰማንያ አራት ዓመታት አገልግላለችና፡፡ /ሉቃ 2÷37/ አምስተኛ በመጾማችን የምናገኘውን በረከት እና መንፈሳዊ ኃይል እንዳይኖረን ያደረጋል፡፡ ስድስተኛ ጾም አጋንንትን ከእኛ የምናርቅበት፣ የምንላቀቅበት መንፈሳዊ የጦር ዕቃ ስለሆነ የማንጾም ከሆነ አጋንንቱ በውስጣችን ተመችቶት ደልቶት ይኖራል፡፡ ሰባተኛ የማንጾም ከሆነ አንጸልይም ስለዚህ እግዚአብሔር እንዳይለመነን ያደርገናል፡፡ ነቢዩ ዕዝራ ‹‹ስለዚህም ነገር ጾምን፣ ወደ እግዚአብሔርም ለመንን፤ እርሱም ተለመነን›› ያለው እግዚአብሔር በጾማችን እንደሚለመነን ያሳየናል፡፡ /ዕዝ 8÷23/
ነቢዩ ዳዊት ‹‹ነፍሴን በጾም አስመረርኳት›› ይላል፡፡ እኛ ግን ነፍሳችንን በጾም ሳይሆን በመብል በመጠጥ ነው የምናስመርራት፡፡ /መዝ 69÷10/ ስለዚህ የአየር አጋንንት እኛ የተለያየ ክፉ መናፍስት በእኛ ሕይወት በመግባት እንዳይፈትነን በጾም መጠንከር አለብን፡፡
‹‹ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሳ ጠፍቶአል›› ት.ሆሴ 4÷6
‹‹ከትውልዱ ማን አስተዋለ?›› ት.ኢሳ 53÷8
ክፍል ሃያ ዘጠኝ
የአየር አጋንንት ራሳችንን እንድናጠፋ ያደርገናል
ይቀጥላል …….
ሰኔ 6-10-12 ዓ.ም
አዲስ አበባ

No comments:

Post a Comment