Tuesday, September 15, 2020

የአየር አጋንንት በልባችን አድሮ እግዚአብሔርን እመቤታችንን እና ቅዱሳኑን ይሳደባል


/ብዙ ወንዶሞቼና እህቶቼ የሚሰቃዩበት ፈተና/
በቀሲስ ሄኖክ ወልደ-ማርያም
አጋንንት በሕይወታችን የሚያደርስብንን ችግር እስክናውቅ እንቸገራለን: ውጊያው እስኪገባን ግራ እንጋባለን: እውነቱ እስኪገለጥልን እውነቱ ሐሰት ይመስለናል።
ሼር በማድረግ በዚህ ፈተና ለሚሰቃዩ ወገኖቻችን አዳርሱ!
ተወዳጆች ሆይ በክፍል ሃያ ስድስት የአየር አጋንንት እና የአዚም መንፈስ በመደበኛና በጸሎት ሕይወታችን እንዴት እንደሚፈትነን አይተናል። በዚህ ክፍል ደግሞ ብዙዎች ለሰው የማይነግሩት የማያወያዩት ግን የሚቸገሩበትን እናያለን። የቅዱሳን አምላክ ምስጢሩን ይግለጽልን። ወዳጆቼ የአየር አጋንንት እና ሌሎቹም ርኩሳን መናፍት በውስጣችን ከገቡ ግራ እስኪገባን ድረስ ቅዱሳንን ይሳደባሉ፡፡ እስኪ ብዙዎቻችንን የምንቸገርበትን የራሳችን ሐሳብ እስኪመስለን የምንሰቃይበትን የአጋንንቱን የፈተና ስልት እንመልከት፡፡ አጋንንት በጌታ ሰው መሆን ወይም ሥጋ መልበስ ላይ መጠራጠር የሳድርብሃል፡፡ ሰው መሆኑም እውነት እንዳይመስልህ ያደርግሃል፡፡
እመቤታችንን ‹እውን በድንግልና ነው የወለደችው›› ብሎ ጥርጥር ያጭርብሃል፡፡  ልትቆጣጠረው በማትችለው ሐሳብ ከውስጥህ ሆኖ እግዚአብሔርን ይሳደባል።  አንተም ይህ ውስጣዊ የአጋንንት ስድብ ካንተ ወይም እራስህ ከልብህ አመንጭተህ የተሳደብክ ይመስልህና ከመጨነቅህ የተነሳ ድንግጥ ትላለህ፡፡ አንዳንዱ በድጋጤ ድርቅ ይላል፡፡ በእመቤታችን ላይ ከውስጥህ ጸያፍ ነገር የሚናገር ድምጽ ትሰማለህ። በተለይ ጸሎት ላይ ሆነህ ስዕሏን ስታይ ስታመሰግናት በማትቆጣጠረው መልኩ ከውስጥ ሲሳደብ ብሎም በሥጋ እንድታስብ ያደርግሃል።
ቅዱሳንን አፍ ባያወጣም ከውስጥ ሲሳደብ ትሰማለህ፣ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የማይሆን ነገር በማሳሰብና የሚያስደነግጥህ ነገር ከውስጥ ሲናገር ትሰማለህ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን አትደናገጥ ቅዱስ ዮሐንስ በራዕዩ ‹‹ታላቅንም ነገርና ስድብን የሚናገርበት አፍ ተሰጠው›› በማለት አጋንንት በፈጣሪና በቅዱሳኖቹ ላይ የስድብን አፍ እንደሚከፍት ተጽፏል /ራዕ 13÷5/
ስድቡ ያናንተ ስላልሆነ እንዳትጨቅ፣ ነፍስህም ከእግዚአብሔር አንድነት የምትለይ አይደለችምና አትጎዳም፡፡ ሰይጣን ከውስጥ ሲሳደብ ነፍስ ትሰማለች ያኔም ትጨነቃለች ትደነግጣለች፡፡ ወዳጄ ነፍስ ፈጣሪዋን ስለምታውቅ ፈጣሪን አትሳደብም፡፡ ስድብ ቀድሞም ከነፍስ የተገኘ አይደለም፣ነፍስ ለዚህ ዓይነት ግብር አልተፈጠረችምና፡፡ ግን ስድቡን በውስጥ ሆኖ የሚናገረው የአየር አጋንንት እና ሌሎች ርኩሳን መናፍስት ናቸው፡፡ በተለይ የአየር አጋንነት: ዓይነ ጥላ እና ዛር ካለ በማያባራ መልኩ ይሳደባል። እንኳን ካንተ ከሰው መስማት የሚዘገንንህን የስድብ ናዳ በልብህ ጓዳ ሲያዘንብ ትሰማለህ።
ወዳጄ ሰይጣን ወደ እኛ ሕሊናና ልቦና ቀርቦ ይሳደባል፡፡ ያኔ ነው ስድቡ ከአንደበታችን ሳይወጣ በውስጥ የምነሰማው፡፡ በርትተን ከጸለይን እየመጣ ስድቡን የሚተነፍስብንን ስለሚተው እኛም ወደ ንጽሐ ጠባያችን እንመለሳለን፡፡
ወዳጄ ሰይጣን ወደ ሕሊናህ ቀርቦ ሲሳደብ ብትሰማ አንዲት ቃል አትናገር አትማረር ይልቁንም ‹‹ይህ ሐሳብ ያንተ ነው›› በለው፡፡ ሐሳቡ የእሱ እንደሆነ ከነገርከው ሥራውን ያውቃልና ይደነግጣል፡፡ አጋንንቱ ከሰው ጋር እያወራህ ድንገት በውስጥህ እግዚአብሔርን፣ እመቤታችንን ቅዱሳንን ሰድቦ ሊያስደነግጥህንና ትኩረትህን ሊያሳጣህ ይችላል፡፡ ያኔም ‹‹ይህ ሐሳብ ያንተ ነው በለው››
ወዳጄ ሰይጣን የሕሊናውን ያውቃልና ስትነግረው ይሰማል በዛም ያፍራል፡፡ መቼም ‹‹ስነግረው እንዴት ይሰማል?›› ትል ይሆናል፡፡ ባንተ ያደረች ላንተ የተሰጠች ጸጋ እግዚአብሔር ታሰማዋለች፡፡ ‹‹እግዚአብሔር ያሳፍርህ›› በለው፡፡ ሰይጣናት በክፉና ባልባሌ ሐሳብ የሚፈትናችሁ ከሆነ አትጨነቁ፡፡ ሰይጣን ልብ ውስጥ ሆኖ ለመሳደብ የዝሙት አጋንንትም ድረሻው ላቅ ያለ ነው፡፡ ፍትወትን በዓይነ ሥጋ እያሳየ የሚያሰቃየን አጋንንት ለስድብ ሰይጣናዊ ምላሱን መዘርጋት አይከብደውም፡፡
በጸሎት ሰዓት የስድብ ናዳ ከልቡ ጓዳ እያመጣ ሲጭንብህ እራስህ እንዳይመስልህ፡፡ ሰይጣን ነውና፡፡ ነፍስም የሷ መስሏት ትጨነቃለች፡፡ ወዳጄ እንደዚህ ያለን ጽኑ ስድብ አንተ/ቺ/ እንኳን የፈጠራችሁን እግዚአብሔርን ቀርቶ የምታውቁትን ሰው አትሰድቡም፡፡ ‹‹ማረኝ፣ ይቅር በለኝ፣ መንግሥትህን አትንሳኝ›› እያለች የምትጸልይ ነፍስ እንዴት ትሳደባለች? ነገር ግን የዚያ የርጉም ሰይጣንን ስድብ ሰምታ ጭንቅ ይሆንባታል እንጂ፡፡
ይህ ፈተና በጸሎት ጊዜ ይበርታ እንጂ በመደበኛው ሕይወትህ ማለትም ሥራ እየሰራህ እየተዝናናህ ከወዳጅህ ጋር እየተጫወትክ ቁም ነገር እያወራክ ድንገት ከውስጥህ ፈንቅሎ ጸያፍ የስድብ አሎሎ ይጭንብሃል። አንተ በሥጋህም በሕሊናህም ሌላ ስራ ይዘህ ሰይጣን ግን በውስጥህ እግዚአብሔርን እመቤታችንን ቅዱሳንን ይሳደባል አንተንም የሕሊና እረፍት ይነሳሃል። አንዳንዱንማ ጨርቅ መጣል ነው የሚቀረው እንጂ በቁሙ ያሳብደዋል። አንዳንዶች አጋንንት ውስጣቸው ሆኖ እግዚአብሔርን እመቤታችንን ቅዱሳንን የሚሳደበውን መቋቋም አቅቷቸው ለከፋ ሕመም የዳረጋቸው አሉ። የማይፈልጉትን እንደ ገደል ማሚቱ ከውስጣቸው የሚጮኸውን ስድብ ክፉ ሐሳብ መቋቋም አቅቷቸው እየተበሳጩ የሚጎዱ አሉ።
ወዳጄ በግልና በማህበር ጸሎት:በቅዳሴ ወዘተ ጊዜ ከውጥህ ሆኖ ወደ ሰማይ የሚሳደበው ለምንድነው? ካልክ አንደኛ ጸሎትህን እርግፍ አድርገህ እንድትተው ነው። ሁለተኛ እግዚአብሔርን እያሰብክ የፍቅርና አባትነት ስሜት ሳይሆን የፍርሃት ስሜት እንዲሰማህ ለማድረግ ነው። ሦስተኛ እግዚአብሔር ምህረት ሰጪ ሳይሆን ቀጪ ነው የሚለውን ክፉ መርዙን ሊተክልብህ ነው። አራተኛ የተሳደብኩት እኔ ስለሆንኩ እግዚአብሔር አይምረኝም ይቅር አይለኝም እንድትል ነው። አምስተኛ ተስፋ አስቆርጦህ ከመንፈሳዊ ሕይወት ሊያስወጣህ ሲፈልግ ነው። ስድስተኛ ነፍስህ በመንፈስ እንዳትቦርቅ ሥጋህ እንድትጨነቅ ስለሚፈልግ ነው። ሰባተኛ ከውስጥህ በሚሳደበው ስድብ አስጨንቆህ እራስህን ከመጉዳት እስከ ሞት ሊያደርስህ ነው።  ስለዚህ ንቃበት!
ከዚህው ጋር በተያያዘ ሰይጣን በሕሊናችን በጸሎት ሰዓት ስለሚሳደብ እኛ የተሳደብን የሚመስለን ለምንድነው? ካልን ከውስጥ ከሚወጣ ምስጋና ጋር ስድብ ስለሚወጣ ነው ከራሳችን የሚመስለን፡፡ ነገር ግን ምስጋናችን ከሰይጣን ስድብ ጋር አይቆጠርም፡፡ እኛ ፈጣሪ ፊት የቆምነው ለስድብ ሳይሆን ለምስጋናና ለጸሎት እንደሆነ ፈጣሪ ያውቃልና፡፡ እግዚአብሔርን የምትወድ ነፍስ ስለያዝክ የሰይጣንን ስድብ እየናቅህ አመስግን፡፡ ያማረ የተወደደ ምስጋናህን ከከዳተኛና ከተሳዳቢ ከሰይጣን ለይቶ የሚያውቅ አምላክ ነው ያለህ፡፡ ምንም የሰይጣን ስድቡ ካንተ ምስጋናና ጸሎት ጋር አንድ የሆነ ቢመስልህም ምስጋናዎችህ በእግዚአብሔር ዘንድ ከስድቡ ጋር አንድነት ስለሌላቸው ንጹሐን ናቸው፡፡
ወደጄ ሰይጣንን እራሱ ውስጥህ ሆኖ ይሳደብና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ጠቅሶልህ ‹‹መንፈስ ቅዱስን የሰደበ ኃጢአቱ አይሰረይለትም›› እያለ ይሞግትኃል ያስጨንቅኃል፡፡ ሰይጣን ይህንን ኃይለ ቃል፣ ብዙዎችን ለማታለል ተጠቅሞበታል፡፡ ‹‹መንፈስ ቅዱስን የሰደበ›› ማለት መንፈስ ቅዱስ ሕፁፅ ያለ፣ ከሦስቱ አካላት አንዱ አይደለም ብሎ የካደ ኃጢአቱ አይሰረይም ማለት ነው፡፡ /ማቴ 12÷31/
ስለዚህ የሰይጣንን ስድብ በውስጥህ ተቃቀመው እንጂ ‹እኔ ነኝ፣ እግዚአብሔር ቢቀስፈኝስ፣ በጠራራ ፀሐይ መብረቅ ቢያወርድብኝስ: ጸሎቴን አይሰማኝም›› እያልክ ነፍስህን አታስጨንቃት ነፍሳዊ ሰላሟንም አታሳጠት፡፡ ይህ ፈተና ያንተ ብቻ ሳይሆን የአብዛኛው ምዕመናን ፈተና ስለሆን ሐሳቡን አታዳምጥ ተቃወመው፡፡
"ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሳ ጠፍቷል" ት.ሆሴ 4÷6
"ከትውልዱ ማን አስተዋለ" ት. ኢሳ 53÷8
ክፍል ሃያ ስምንት
የአጋንንት ፈተና በአጽዋማት ወቅት!
ይቀጥላል .....
ሰኔ 3-10-12
አዲስ አበባ

No comments:

Post a Comment