Tuesday, October 6, 2020

የአየር አጋንንት እና የአዚም መንፈስ

በቀሲስ ሄኖክ ወልደ-ማርያም
አጋንንት በሕይወታችን የሚያደርስብንን ችግር እስክናውቅ እንቸገራለን፣ ውጊያው እስኪገባን ግራ እንጋባለን፣ እውነቱ እስኪገለጥልን እውነቱ ሐሰት ይመስለናል፡፡
ሼር በማድረግ ለወዳጆ አዳርሱ!
ተወዳጆች ሆይ በክፍል ሃያ አምስት የአየር አጋንንት በጸሎት ሰዓት በማዞር፣ በማቅለሽለሽ እና ሌሊት በእንቅልፍ በማስፈራራት እንዴት እንደሚፈትነን አይተናል፡፡ በዚህ ክፍል ደግሞ የአየር አጋንንት እና የአዚም መንፈስ የጸሎት ሕይወታችንንና ሌላውንም እንዴት እንደሚያቃውስ እናያለን፡፡ የቅዱሳን አምላክ ምስጢሩን ይግለጽልን።
ወዳጆቼ የአየር አጋንንት በራሱ በጸሎት ሰዓት ፈታኝ ቢሆንም ከአዚም ወይም ከአፍዝ አደንዝዝ መንፈስ ጋር በማበር በጸሎታችን እንቅፋት ይሆናል፡፡ የአዚም መንፈስ የምንለው የማፍዘዝ፣ የማደንዘዝ፣ ቸልተኛና ግዴለሽ የሚያደርገን መንፈስ ነው፡፡ የዚህ መንፈስ ታላቁ ጥቃት በመላው በመንፈሳዊ ሕይወታችን ላይ ቢሆንም በጸሎት ሰዓት እጅጉን በርትቶ ይታይብናል፡፡ እንዲሁም መንፈሳዊ ተግባራትን ለማከናወን ለምሳሌ ለመስገድ፣ ለማስቀደስ፣ ጉባኤ ሄደን ለመማር፣ ለመመጽወት እና ሌላም በጎ ምግባር ልንሠራ ስንነሳሳ መንፈሱ ክንውናችንን ገና በሐሳብ ደረጃ የማኮላሸት እና ለእኛ አሳማኝ በሚመስል ምክንያት የማበላሸት ሥራን ይሠራል፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ በገላትያ የሚኖሩ ሰዎችን አስተምሮ አጥምቆ በጌታችን አሳምኗቸው ነበር፡፡ እነሱም እግዚአብሔርን በሃይማኖት አውቀው ብዙ ታምራት እስከ ማድረግ ደርሰው ነበር፡፡ ግን ቅዱስ ጳውሎስ ከሔደ በኋላ ሐሰተኛ ክርስቲያኖች ገላትያ ገብተው ‹‹ክርስቶስ ዕሩቅ ብእሲ ነው እንጂ የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ አይደለም›› ብለው ስላሳቷቸው በገላትያ ክታቡ ላይ ‹‹የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ፣ በዓይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው?›› በማለት ይጠይቃቸዋል፡፡ /ገላ 3÷1/
ወዳጆቼ ከዚህ ከቅዱስ ጳውሎስ መልእክት የምንረዳው አዚም የሚባል እንዳናስተውል የሚያፈዝ፣ አንዳች ነገር እንዳንሠራ የሚያደነዝዝ መንፈስ መኖሩን ነው፡፡ ሌላው ‹‹ማን አደረገባችሁ?›› ያለው የአዚም መንፈስ በሰው ላይም የሚደረግ መንፈስ መሆኑን ያስረዳናል፡፡ ጠንቋዮች የአዚም መንፈስ በመሳብ ሰዎች ፈዘው፣ ደንዝዘው እንዲኖሩ ያቆራኙታል፡፡
የአዚም መንፈስን ካነሳን እስኪ ወደ ኃላ ሂዱና የትምህርት ቤት ጊዜያችሁን አስታውሱ? ትዝ ካላችሁ ትምህርት ቤት እየተማራችሁ ድንገት እንቅልፍ እንቅልፍ የሚል ስሜት፣ መደበት፣ አስተማሪው በሚያስተምረው ግራ ማጋባት ወዘተ ስሜቶች የአዚም መንፈስ ስሜቶች ናቸው፡፡ የአዚም መንፈስ በተማሪዎች ላይ በሦስት መልኩ ይከሰታል፡፡ አንደኛው የሰውን ብሩህ አእምሮ ለመስለብ በሚደረገው በምቀኞች ተስቦ እንዲጠናወተን ይደረጋል፡፡ ይህም አእምሮን እውቀትን ለመስለብ የሚጠቀሙበት ነው፡፡ እንደ መተት አጋንንት ስበው ያስገቡታል፡፡ ሁለተኛው በሰው ብሩህ አእምሮ በመቅናት ተማሪው ጉብዝናውን አጥቶ ፈዞ ደንዝዞ ትምህርት እንዲተው፣ እንዲያስጠላው አልያም ትምህርቱን እርግፍ አድርጎ እንዲተውና ባተሌ ሆኖ እንዲቀር የሚደረግ ነው፡፡ ሦስተኛው እራሱ የአዚም አጋንንቱ በመልካም ብሩህ አእምሮአችን በመቅናት በድንገት ወደ ሕይወታችን በመግባት የትምህርት እድላችንን ለማበላሸት የሚጠቀምበት ነው፡፡
ወዳጆቼ ከላይ ባየናቸው ሦስት ምክንያት ስንቱ ጎበዝ ለሀገር ለወገን፣ ለቤተሰብ የሚጠቅም ተማሪ በአዚም መንፈስ እድለ ቢስ ሆኖ ቀርቷል? ስንቱ ተስፋ የተጣለበት ተማሪ ክፍል ውስጥ እየደበተው፣ እያንቀላፋው ውጤቱ ተበላሽቷል? ይህ ችግር ዛሬም በኢሊመንተሪ፣ በሃይ ስኩል እና በዩኒቨርሲቲ የሚታይ ነው፡፡ 
ወዳጆቼ የአዚም መንፈስ በውስጣችን ያለውን መንፈሳዊ መቀጣጠልን በማጥፋት ወደ መሰላቸት ውስጥ ይከተናል፡፡ የአየር አጋንንት ከአዚም መንፈስ ጋር በመተባበር ቢቻል ገና ጸሎት ሳንጀምር አሰላችቶ ማስተው፣ ሰውነታችንን ማድከም እና ሕሊናችንን ማዛል ይጀምራል፡፡ ይህ ባይሆን ጸሎት ስንጀምር የጀመርነውን ጸሎት አንጨርስም፡፡ የአዚም መንፈስ ሕሊናና ልቦናን እንዲሁም ሙሉ አካልን ስለሚያደክም ተማሪ ከሆንን ያጠናነውን እንዳንይዝ፤ ሠራተኛ፣የቤት እመቤት ከሆንን የተባልነውን፣ ያስቀመጥነውን እንድንረሳ ያደርገናል፡፡
በተለይ በአሁን ሰዓት ብዙ ወጣቶች በአዚም መንፈስ ተይዘው እንዳይሠሩ፣ ባላቸው እውቀት እንዳይጠቀሙ፣ ደንዝዘው ፈዘው የእናት አባት ተጧሪ ሆነዋል፡፡ የት ይደርሳሉ የተባሉት እነሱም በማያውቁት ከጊዜ በኋላ በመጣ መፍዘዝ እና መደንዘዝ ውስጥ ገብተው ተስፋም ቆርጠው ሱሰኛ ሆነዋል፡፡ ይህ ሁሉ የአጋንንቱ ጥቃት ነው፡፡
የአዚም መንፈስ በተለይ በልጆች ላይ የተባሉትን እንዳይሰሙ፣ የተነገራቸውን እንዳያደርጉ የማፍዘዝ ሥራ ይሠራል፡፡ ቤተሰብም የገዛ ልጃቸውን ችግር ባለመረዳት ‹‹ይሄ ፈዛዛ፣ የደነዘዘ፣ የተባለውን የማይሰማ›› እያለ በመስደብ ለአዚም መንፈስ ሽፋን ይሆናል፡፡ ቤተሰብ የልጆችን ችግር ሳይረዱ በዝምታ ካለፉ የአዚም መንፈሱ በልጆች ውስጥ በመደላደል ተቀምጦ የሕይወታቸው መሰናክል ይሆናል፡፡
ተወዳጆች ሆይ የአዚም መንፈስ በጸሎት ጊዜ ድብት በሚያደርግ ከፍተኛ እንቅልፍ በማምጣት እንድናንቀላፋና በጸሎት መጽሐፍ የምናነበውን እንዳናስተውል ፍዝዝ ድንዝዝ በማድረግ ሕሊናችን ውስጥ እንዳይገባ ያደርገናል፡፡ የሚገርመው በአዚም መንፈስ በእንቅልፍ ምክንያት ጸሎታችንን ትተን ብንተኛ የመቃዠት እንጂ የእረፍት እንቅልፍ አንተኛም፡፡ የአዚም መንፈሱ ከእኛ ጋር ያለው ውጊያ ከመደበኛ እንቅልፋችን ጋር ሳይሆን እሱ እያመጣ በጸሎት ሰዓት ከሚቆልልብን እንቅልፍ ጋር ነው፡፡ ተኝተን ተኝተን እንቅልፍ የማንጠግብ እንሆናለን፡፡
አእምሮ በባሕሪው እንቅልፍ ከተጫጫነው መፍዘዝ እና መደንዘዝ እንጂ በንቃት መሥራት አይችልም፡፡ ስለዚህ ይህን የአእምሮ ጠባይ የአዚም መንፈሱ እየተጠቀመ ይጫወትብናል፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ ‹‹ራስ ሁሉ ለሕመም፣ ልብም ሁሉ ለድካም ይሆናል›› እንዳለው የአዚም መንፈስም በጸሎት ሰዓት ራስን ለሕመም፣ ልባችንንም ለድካም ይዳርግና የተለመደ መንፈሳዊ ትሩፋቶችን እንዳንሠራ ያደርገናል፡፡ /ኢሳ 1÷5/
ይህ የአዚም መንፈስ በጸሎት ሰዓት መጫጫን ሲጀምር ጸሎታችንን ለጊዜው በአቡነ ዘበሰማያት በማሰር 41፣ 64 ወይም 105 በመስገድ መንፈሱን ማራቅ ይቻላል፡፡ ግን እንዳንሰግድ የማዳከምና የማሰላቸት ሥራ ስለሚሠራ ይህ ከመሆኑ በፊት በትጋት ስግደት ልንቀድመው ይገባል፡፡ የአዚም መንፈሱ በጸሎት ሰዓት የማፍዘዝ የማደንዘዝ ሥራ ሊሠራ ሲል ወይም ከሠራ እኛም መስገድ ካስለመድን ከእኛ ባስ ወዳለው ይሄዳል እንጂ ከእኛ ጋር በመታገል ጊዜውን አያባክንም፡፡
የአየር አጋንንት ከአዚም መንፈስ ጋር በማበር ውስጣዊ መደንዘዝ ይፈጥርብናል፡፡ በዚህም አቅም እንድናጣ፣ ጉልበታችን እንዲዝል፣ የአእምሮአችንና የአካላችንን ኃይል እንድናጣ ያደርገናል፡፡ ወዳጆቼ የአፍዝዝ አደንዝዝን ክፉ መንፈስ በጸሎት በስግደት ካልተዋጋነው ነገ በመደበኛ ሕይወታችን ውስጥ ያለው አሉታዊ ተጽዕኖው ከፍተኛ ስለሚሆን ልንቋቋመው አንችልም፡፡ በውስጣችን ያለው የአፍዝዝ የአደንዝዝ ክፉ መንፈስ በዘር በተዋርዶ ወደ ትውልዳችን እንዳይተላለፍ፣ የደነዘዙ የፈዘዙ ልጆች እንዳናተርፍ ‹ሳይቃጠል በቅጠል› እንደሚባለው መዘዙ በልጆቻችን ሳይመዘዝ በመንፈሳዊ የጦር ዕቃዎች በጾም በጸሎት በስግደት፣ በጸበል በቅዱስ ቁርባን በእግዚአብሔር እርዳታ ከእኛ ልናርቀው ይገባል፡፡
‹‹ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሳ ጠፍቶአል›› ት.ሆሴ 4÷6
‹‹ከትውልዱ ማን አስተዋለ?›› ት.ኢሳ 53÷8
ክፍል ሃያ ሰባት
የአየር አጋንንት በልባችን አድሮ እግዚአብሔርን፣ እመቤታችንን እና ቅዱሳንን ይሳደባል!
/ብዙ ወንድሞቼ እና እህቶቼ የሚሰቃዩበት ፈተና/
ይቀጥላል ….
ሰኔ 3-10-12 ዓ.ም
አዲስ አበባ

1 comment:

  1. የአባታችን በረከት ከሁሉ ጋር ይሁን አሜን(3)

    ReplyDelete